ክረምት

ሰኔ 25 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ በዕለተ ረቡዕ የተፈጠሩት ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ቀን ለመቁጠር፣ዘመንን፣ ወራትን፣ በዓላትንና አጽዋማትን ለማወቅ ወሳኝ ፍጥረቶች ናቸው፡፡ ዘፍ.14-19፣ ዘዳ.12፡1፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አቆጣጠር አንድ ዓመት በፀሐይ አቆጣጠር 365 1/4 ቀናት፡፡ በጨረቃ አቆጣጠር 354 ቀናት፡፡ በከዋክብት አቆጣጠር ጸደይ፣በጋ፣መጸውና ክረምት የተባሉ አራት ወቅቶች አሉ፡፡

ወቅት እንዲፈራረቅ በዘመን ላይ የተሾሙ ዓመቱን በአራት ክፍለ ዘመን የሚገዙት አራት ከዋክብት ሲሆኑ በእያንዳንዱ ወር ላይ የሰለጠኑ ከአራቱ ከዋክብት ሥር እንደ ወታደር የሚያገለግሉ ሦስት ሦስት ወታደሮች በድምሩ 12 ከዋክብት አሉ፡፡ እነዚህ ከዋክብት ወቅቶቹ ሥርዐታቸውን ጠብቀው እንዲሸጋገሩ የሚያደርጉና የእግዚአብሔር ጸጋ ለፍጥረቱ እንዲደርስ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ዓመቱን ለአራት ወቅቶች የሚከፈሉትና የሚመግቡት ከዋክብት የሚከተሉት ናቸው፡-

ምልክኤል፡-

በጸደይ የሰለጠነው ኮከብ ምልክኤል ሲሆን በሥሩ ያሉት ሦስት ከዋክብት/ወታደሮች/ ሚዛን በመስከረም ወጥቶ 30 ዕለት ከ 10 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ሚዛን ነው፡፡ አቅራብ በጥቅምት ወጥቶ 29 ዕለት ከ40 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ጊንጥ ነው ፡፡ ቀውስ በኅዳር ወጥቶ 29 ዕለት ከ28 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ቀስት ነው፡፡ (ኬኪሮስ ማለት ረጅም መስመር ማለት ሲሆን የቀንና የሌሊት ሰዓቶች ክፍል ነው፡፡ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተዘርግቶ 60 ክፍሎች አሉት፡፡ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት ሁል ጊዜ እየሄዱበት በየቀኑ አንድ ጊዜ ያልፍበታል፡፡ 5 ኬክሮስ 1 ሰዓት ነው፡፡)

ናርኤል፡-

በበጋ የሰለጠነው ኮከብ ናርኤል ሲሆን በሥሩ ያሉት ሦስት ከዋክብት ወታደሮች ገዳ/ጀዲ በታኅሣሥ ወጥቶ 29 ዕለት ከ28 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ፍየል፡፡ ደላዊ በጥር ወጥቶ 29 ዕለት ከ41 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ውኃ መቅጃ ባልዲ፡፡ ሑት በየካቲት ወጥቶ 31 ዕለት ከ10 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ዓሣ ነው፡፡

ምልኤል ፡-

በመጸው የሰለጠነው ኮከብ ምልኤል ሲሆን በሥሩ ያሉት ሦስት ከዋክብት ሐመል በመጋቢት ወጥቶ 30 ዕለት ከ43 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ በሬነው፡፡ ገውዝ/ጀውዝ በግንቦት ወጥቶ 31 ዕለት ከ30 ኬክሮስ የሚታይ መልኩእንደ ባልና ሚስት ጥንድ ነው፡፡

ሕልመልመሌክ፡-

በክረምት የሰለጠነው ኮከብ ሕልመልመሌክ ሲሆን በሥሩ ያሉት ከዋክብት/ወታደሮች ሰርጣን/ ድርጣን በሰኔ ወጥቶ 31 ዕለት ከ26 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ጎርምጥ ነው፡፡ አሰድ በሐምሌ ወጥቶ 31 ዕለት ከ10 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ አንበሳ ሰንበላ በነሐሴ ወጥቶ 30 ዕለት ከ42 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ እሸት ዛላ ነው ፡፡

በዚህ መነሻነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የወቅት አቆጣጠር እንደሚከተለው ይገለጻል፡፡

  • የመጸው ወቅት ከመስከረም 26 ቀን እስከ ታኅሣሥ 25

  • የበጋ ወቅት ከታኅሣሥ 26 ቀን አስከ መጋቢት 25

  • የጸደይ ወቅት ከመጋቢት 26 ቀን እስከ ሰኔ 25

  • የክረምት ወቅት ከሰኔ 26 ቀን እስከ መስከረም 25 ቀን ሲሆኑ እነዚህን ወቅቶች በማወቅ ዘመኑን በመዋጀት ሥራው ድንቅ የሆነ አምላክ ይመሰገንበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሥርዐት ሠርታ በጸሎቱ በማኅሌቱ በቅዳሴው ወዘተ. ትጠቀምበታለች፡፡

ቤተክርስቲያን ወቅቶች ሲፈራረቁ አዲሱን ወቅት ለመቀበል ምኅላ (ጸሎት) ታደርጋለች ፡፡ ለምሳሌ ምኅላ በአተ ክረምት (የክረምት መግቢያ ምኅላ) እንደየ ዕለቶቹ እየታየ ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 23 ቀን ምኅላ ይያዛል፡፡ ይኸውም መጪው ክረምት እግዚአብሔር የሚመሰገንበትና የሚዘንበው ዝናብ ጥሩ ምርት የሚያስገኝ እንዲሆን ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ እንደጻፈው “ምድርም ብዙ ጊዜ በርስዋ የወረደውን ዝናም ከጠጣች መልካም ፍሬ ለደከሙበት ላረስዋትም ብታበቅል ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከት ትቀበላለች” ብሏል ዕብ.6፡7 ፡፡ ቅዱስ ዳዊትም ወአንተ ገበርከ አድባረ ወምድረ ኵሎ፡፡ ክረምተ ወሐጋየ ዘአንተ ፈጠርከ ወተዘከር ዘንተ ተግባረከ፡፡ አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ።ይህን ፍጥረትህን አስብ። (መዘ 74፡፡17)

“ክረምት” በደስታ ተክለ ወልድ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ በሚለው መጽሐፋቸው ሲፈታው ክረምት ከረመ ዝናም የዝናብ ወቅት በፀደይና በመጸው መካከል ያለ ክፍለ ዓመት ከሰኔ 25 እስከ መስከረም 25 ድረስ ያለው ወቅት ሲለው ቅዱስ ያሬድም በድጓው ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር ዘያበቁል ሣዕረ ውስተ አድባር ይለዋል፡፡

ጥዑመ ልሳን ካሳ ደግሞ “ክረምት” የሚለው ቃል ከርመ፣ ከረመ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ወርሃ ዝናም፣ ወርኃ ነጎድጓድ፣ ዘመነ ባሕር፣ ዘመነ ነጎድጓድ፣ ዘመነ አፍላግ፣ ዘመነ ጠል፣ ዘመነ ደመና፣ ዘመነ መብረቅ… ይሉታል፡፡ ዘመነ ክረምት/ የዝናብ ወቅት በዘጠኝ ይከፈላል አራቱ በሚጠናቀቀው ዓመት እስከ ጳጉሜ መጨረሻ ሲሆን አምስቱ ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት ውስጥ በመስከረም ናቸው፡፡ በያዝነው ዓመት ውስጥ ያለው ክፍል ፡-

  1. ዘር፣ ደመና እስከ ሐምሌ 18 ቀን

  2. መብረቅ፣ ባሕር፣ ወንዞች እስከ ነሐሴ 9 ቀን

  3. እጓለ ቁአት ፣ደሰያት ፣የሁሉም ዓይኖች እስከ ነሐሴ 27

  4. ንጋት፣ቀን፣ፍጥረት በሚል እስከ ጳጉሜን 5 ወይም 6 ናቸው፡፡ እነዚህ አራት ጊዜዎች እንደ አንድ ይቆጠራሉ፡፡

የዝናብ/የክረምት ወቅት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን በልዩ ሁኔታ የምታከብርበት ወቅት ነው፡፡

ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር የሰማይና የምድር ፈጣሪ መጋቢ መሆኑን በዝናብ ምልክትነት /አስረጅነት ታስተምራለች፡፡ በግብርና የሚተዳደሩ የሀገራችን ሰዎች በክረምት የዘሩት ዘር ፍሬ የሚያፈራው በክረምት እግዚአብሔር በሚሰጠው ዝናብ ስለሆነ ቸርነቱ መጋቢነቱ በዚህ ይመሰላል፡፡

ድሃ ስንሆን ተስፋችንን በእግዚአብሔር ላይ እናደርጋለን እርሱ ዝናቡን ይሰጠናል፡፡ ዘር እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ በአፈር ውስጥ ይቀበራል ዝናብ ሲያገኝ አድጐ ለፍሬ ይበቃል፡፡ ስለዚህ ከሰኔ 25 – ሐምሌ 18 ያለው ወቅት ዘርዕ ደመና ተብሎ መጻሕፍት ይነበባሉ፡፡ መዝሙሮች ይዘመራሉ፡፡

የሚቀርበው ምስጋና የዝናብን ወቅት እግዚአብሔር ሰጠን ምሕረትን አደረገልን ሰንበትን ለሰዎች ሠራልን ስለዚህ እርሱን ከፍ ከፍ እናድርገው እናመስግነው በማለት ነው፡፡ እንዲሁም ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል ለምድርም ዝናብን ያዘጋጃል ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም። በማለት ቤተክርስቲያን በቅዱስ ዳዊት ምስጋና ታመሰግነዋለች፡፡ መዝ 147፡8 ፡፡

በሐምሌ 2፣5፣20፣ 15 16 አሠርገዎሙ ለሐዋርያት እየተባለ ሐዋርያት በመዝሙር ይታሰባሉ፡፡ 2ጴጥ.1፡12-18 ሐዋ.23፡10-35 ከሐምሌ 19-ነሐሴ 9 መብረቅ ነጎድጓድ ባሕር አፍላግ ጠል እየተባለ ይዘመራል መጻሕፍት ይነበባሉ ፡፡ 1ጴጥ.2፡1-12፣ ሐዋ.20፡1-2፡፡

በዘመነ ክረምት ውኃ ይሰለጥናል፣ ውኃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፡፡ ሆኖም ግን በብሩህነቱ ከእሳት፤ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፤ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡ ይህ ዘመን ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት ዘመን ስለሆነ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡

ወርኃ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፤ ገበሬ በወርሃ ክረምት ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሳል፡፡ ክርስቲያንም በዚህ ምድር ላይ የሚደርስበትን መከራ ሁሉ ይታገሳል፤ ክርስቲያንም በዚህ ምድር የሚደርስበትን መከራ ሁሉ በጸጋ የሚቀበለው በዚያኛው ዓለም ስለሚያገኘው ተድላና ደስታ ነው፡፡

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- “እለ ይዘርኡ በአንብዕ ወበኃሤት የአርሩ፡፡ ሶበሰ የሐውሩ ወፈሩ እንዘ ይበክዩ፡፡ ወፆሩ ዘርኦሙ፡፡ ወሶበ የአትዉ መጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ፡፡ በሔዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ፡፡” በማለት የመንፈሳዊ ጉዞ ምሥጠርን ከግብርና ሙያ አንጻር አመልክቶአል፡፡(መዝ.125)

“ምድርን ጎበኘሃት አጠጣሃትም ብልፅግናዋንም እጅግ አበዛህ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተሞላ ነው ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል፣ በዝናም ጊዜ መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳቱንም ከመዛግብቱ ያወጣል ” (መዝ.64፥9) በማለት እግዚአብሔር በነጎድጓድና በመብረቅ በባሕርና በሐይቅ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑንና የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት ሁሉ የኃይሉ መገለጫዎች እንደሆኑ የሚያስተምሩ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡

እግዚአብሔር ክረምትን ሲያመጣና ዝናምን ሲያዘንም ብዙ ነገሮችን ልናስተውል ይገባናል፡፡ ፈጣሪያችን ፈጣሪ ዓለማት ብቻ ሳይሆን መጋቢ ዓለማት መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ መግቦቱም ከፍጥረቱ እንዳልተለየ ይህ አማናዊ መግቦቱም ፍጥረቱን እንደሚያስተምር እንረዳለን፡፡

በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፤ ብርድና ሙቀት፤ በጋና ክረምት፤ ቀንና ሌሊት አይቋረጡም፡፡” (ዘፍ.8፥22) በማለት አምላካችን እግዚአብሔር ለኖኅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት በጋና ክረምቱ ብርድና ሙቀቱ ቀንና ሌሊቱ በተወሰነላቸው ጊዜ እየተፈራረቁ ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያዊያን በአንድ ዓመት ውስጥ እየተፈራረቁ በሚመጡ አራት ወቅቶች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢርና ምሳሌ ጋር በማስማማት ለየወቅቱና ለዕለታቱ ምንባባትን በማዘጋጀት እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ ስለዚህ በክረምት ወቅት እግዚአብሔርን እያመሰገንን እንድናሳልፍ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ይቆየን

  • ምንጭ :-ባሕረ ሐሳብ የዘመን ቆጠራ ቅርሳችን