a tenat 2006 1

የንባብ ባህልን ለማሳደግ ቤተ ክርስቲያን የሚኖራት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

 ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም.

ይብረሁ ይጥና

a tenat 2006 1ከፍተኛ ድር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትርጉም ያለው የንባብ ባሕልን ለማሳደግ ከፍተኛውን ድርሻ መያዝ እንደሚገባት በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል ባዘጋጀው የንባብ ባሕል አስመልክቶ በቀረበ የጥናት ጉባኤ ላይ ተገለጸ፡፡

ሠኔ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ለግማሽ ቀን በማኅበሩ ሕንፃ ላይ በተካሔደው ጉባኤ ትርጉም ያለው የንባብ ባሕል በዕውቀት እና በሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋ ለማፍራት በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን፤ “የንባብ ባሕልን ለማሳደግ የተለያዩ አካላት ሚና” ፤ እንዲሁም “ትርጉም ያለው የንባብ ባሕል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በሚሉ ሁለት ርእሰ ጉዳች ላይ የተደረጉ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋ፤ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር መምህር የሆኑት መምህር ደረጀ ገብሬ “የንባብ ባህል ለማሳደግ የተለያዩ አካላት ሚና” በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት፤ የንባብ ምንነት፤ የንባብ ክሂል የእድገት ደረጃዎች፤ የማንበብ ጠቃሚነት፤ የማንበብ ባሕልን የማሳደግና የማዳበሪያ ሥልቶቹ ምን እንደሆኑ በስፋት ዳስሰዋል፡፡ በተለይም ሕፃናት የቋንቋ ችሎታቸውን በማዳበር በየጊዜው የማዳመጥና የማንበብ ፍላጎታቸውን ማሳደግ እንደሚቻል ገልጠዋል፡፡

ለንባብ ባሕል መዳበር ትምህርት ቤቶችና ወላጆች፤ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትኩረት ሠጥተው መሥራት እንደሚገባቸውም በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡ “ትርጉም ያለው የንባብ ባህል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርእስ ጥናታቸውን ያቀረቡት አቶ ጸጋዘአብ ለምለም ደግሞ ትርጉም ያለው የንባብ ባሕል ለፈጣሪነት፤ ለውጤታማነት፤ ለብቁ ተወዳደሪነትና ለሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፋዊት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የብዙ መጻሕፍትና መዛግብት እንዲሁም ቅርሶች ባለቤት እንደመሆኗ መጠን አገልግሎቷን ካለንባብ ማሰብ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አመልክተው፤ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ምሥጢራት እንዳሏት ሁሉ እነዚህን ምሥጢራት ለአገልግሎት ለማብቃት ትርጉም ያለው የንባብ ባሕል አስፈላጊነትና ንባብ የቤተ ክርስቲያኗ አንዱ አካል መሆኑን በጥናታቸው ዳስሰዋል፡፡

ንባብ ሲባል ከፊደል ቆጠራ ጀምሮ ያለው ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያን የፊደል ባለቤት ሆና ብትቀጥልም ትርጉም ያለው የንባብ ባሕል አድማሷን አለማስፋፋቷን በስፋት አቅርበዋል፡፡ የዐቅም ማጣት ሳይሆን ዐቅምን አለማወቅ፤ የአጠቃቀም ችግር፤ ተቋማዊ የሆነ አስተዳደር አለመዘርጋት፤ ቤተ ክርስቲያን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አለመተሳሰሯ፤ ንባብን እንደ አንድ የአገልግሎት አካል አለመመልከት እንደ ምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ትርጉም ያለው የንባብ ባሕል አድማስን ለማስፋፋት ንባብን እንደ ሃይማኖታዊ በዓል አከባበራችን ባሕል ማድረግ፤ ዐቅምን ማሳደግና ማበልጸግ፤ ጠንካራ ተቋማዊ አስተዳደርን መዘርጋት፤ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ማስተሳሰር፤ የጥናትና ምርምር ማእከላትን ማበራከት የመሳሰሉትን ጥናት አቅራቢው እንደ መፍትሔ አቅርበዋል፡፡

በቀረቡት ሁለቱም ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች ቀረበው በባለሙያዎቹ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡