St_Anthony_Icon_3.jpg

የበረሃዉ መልአክ ቅዱስ እንጦንስ

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
 
St_Anthony_Icon_3.jpgእንደተለመደው የኦሪት ዘፍጥረትን ትርጓሜ መሠረት ያደረገውን ተከታታይ ትምህርት ለመማር በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ ውስጥ ካሉት አዳራሾች በአንዱ ተሰብስበናል፡፡  ትምህርቱ ከመጀመሩ በፊት በወረቀት ለሚጠየቁት ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ሁላችንም ስለሚያጓጓን በመጠባበቅ ተቀምጠናል። ከመምህራችን የቀረበው የዕለቱ ጥያቄ ግን ሌላ ነበር። «ዛሬ ቀኑ ስንት ነው?» የሚል፡፡ ጥር 22 በማለት መለስን፡፡ «ዛሬ የዕለቱ መታሰቢያነት ለማን ነው?» ቀጥሎ ጠየቀን፡፡ መቼም ቅዱስ ዑራኤል መሆኑን አያጣውም፣ ግን ለምን ጠየቀን? በአእምሮዬ የሚመላለስ ጥያቄ ነበር፡፡ ለነገሩ ዕለቱ የተለየ ነገር ቢኖረው ነው እንጂ አይጠይቀንም ነበር፡፡ ይሄን እያሰብኩኝ ዝምታ በሰፈነበት፥ አንድ ልጅ እጁን አነሳና «የመልአኩ የቅዱስ ዑራኤል በዓል ነው» በማለት መለሰ፡፡ መምህራችንም ጥሩ ነው በማለት ተናገረና  «ሌላስ?» አለ በተረጋጋ አንደበት፡፡ ከዚህ በላይ እንኳን የማውቀው ነገር የለም አልኩኝ ለራሴ፡፡
 
ለማንኛውም በዚህ ዕለት ታላቁ አባት ርእሰ መነኮሳት ቅዱስ እንጦንስ ያረፈበት ዕለት ነው፡፡ ጽሌውም (የጽላት ነጥላ ቁጥር) በዋና ከተማችን አዲስ አበባ በምትገኘው መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ይገኛል፡፡ በርግጥ በራሱ ስም የተሰሩ ገዳማትም አሉ። ይህ የአዲስ አበባዉ ግን የእመቤታችን ጽሌ ከመምጣቱ በፊት  በቅዱስ እንጦንስ ስም ይጠራ እንደ ነበር ሁሉ ተነገረን። ይሄንን ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? የእኔ ጥያቄ ነበር። ለምን ለሌሎች አላካፍለውም? ሌላ ጥያቄ፤ እነሆ። (ሥዕል፦ቅዱስ እንጦንስ፥  ከታች በግራ በኩል ቅዱስ እንጦንስና የዋህ ጳውሊ ሲገናኙ )

ቅዱስ እንጦንስ በ25ዐ ዓ.ም ቅማን/Qimn El-Arouse/ በሚባል በማዕከላዊ ግብጽ ነው የተወለደው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በቤተክርስቲያን ሳለ ወንጌል ሲነበብ ጌታችን ለባለፀጋው ጎልማሳ የነገረውን «ፍፁም ልትሆን ብትወድ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች  ሰጥተህ ተከተለኝ» የሚለውን የእግዚአብሔርን ጥሪ ስለሰማ ወላጆቹ ከታናሽ እህቱ ጋር ትተውለት የሞቱትን ሰፊና በመስኖ የሚለማ መሬት ቶሎ ሽጦ ለድሆች ከሰጠ በኋላ እህቱን ለደናግል ማኅበር አደራ ሰጥቶ የብሕትውና ኑሮውን ጀምሯል፡፡

ቅዱስ እንጦንስ በብዙ ተጋድሎና ፈተና በመካከለኛው የግብጽ በረሃ ውስጥ ብቻውን የኖረ ከዚያም ብዙ ተከታዮችን ያፈራ፣ የምንኩስና ሕይወትም ጀማሪ የሆነ አባት ነው፡፡

ቅዱስ እንጦንስ፣ የቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ወዳጁም ነበር፡፡ ርእሰ ባህታውያን የዋህ ጳውሊንም ከፍኖ የቀበረው ቅዱስ አትናቴዎስ በሰጠው ካባ ሲሆን በመልሱም ለቅዱስ አትናቴዎስ የቅዱስ ጳውሊን ለራሱ ከዘንባባ የሠራውን እንደታታ ቅርጫት የመሰለውን ዐፅፍ ልብስ ሰጥቶታል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም በበዓለ ትንሣኤና በበዓለ ሃምሣ በውስጥ ይለብሳት ነበር፡፡

ቅዱስ እንጦንስና ዘመነ ሰማዕታት

በክርስቲያኖች ላይ መከራና ሞት በዓላውናን ነገሠታትና መኳንንት በታዘዘ ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ፍቅር እንደበግ እየተነዱ ወደሞት ይሔዱ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ ከበአቱ ወጥቶ ወደ እስክንድርያ ሔደ÷ ተጠርተንም እንደሁ በእሽቅድምድም ለመሳተፍ አለበለዚያ ተሽቀዳዳሚዎችን ለመጎብኘት እንሒድ በማለት እንጦንዮስ ሰማዕትነትን ለመቀበል ከፍተኛ ጉጉት ነበረው፡፡ ነገር ግን እርሱን የብሕትውናና የምንኩስና ሕይወት አስተማሪ ይሆን ዘንድ ስለ ብዙዎች ጥቅም ጠበቀው፡፡ ሰማዕታት ለፍርድ ሲጠሩ አጅቦ ይሸኛቸዋል÷ እስኪገደሉም ድረስ አይለያቸውም፡፡ ዳኛው ድፍረቱንና የተከታዮቹን ብዛት ጽኑ መንፈሳቸውንም ባየ ጊዜ ማንም መነኩሴ ወደ ፍርድ ቤት አካባቢና በከተማው ውስጥ እንዳይታይ አዘዘ፡፡
እንጦንስ ግን ሰማዕታትን አጅቦ ከፍርድ ቤት ፊት ለፊት ዳኛው ሊያየው በሚችል ስፍራ ተገኘ። ሁሉም በመገኘቱ ሲደነቁ ኃላፊው በትሩን ይዞ ወደ እርሱ መጣ፥ እርሱ ግን የክርስቲያኖችን ጽኑ መንፈስ ያሳይ ዘንድ ምንም ሳይፈራ ቆመ።
 
    ምንጭ፡ ያረጋል አበጋዝ (ዲ/ን) ና አሉላ ጥላሁን ፣ 1997። ነገረ ቅዱሳን 3። ማኅበረ ቅዱሳን፣ አ.አ።

የልደትን ብርሃን መናፈቅ ስብከት፣ ብርሃን ኖላዊ

            በዲ/ን ዘላለም ቻላቸው
መግቢያ

ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ «በሞቱ እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደተነሳ እየተወ እንደ እርሱ አዲስ ሕይወት እንኖራለን» /ሮሜ. 6.4/፤ እንዳለው ክርስትና በጥምቀታችን ከክርስቶስ ጋር ሞተን ከእርሱም ጋር ተነስተን በትንሳኤው ብርሃን በአዲስ ሕይወት የምንመላለስበት የእግዚአብሔርን ፍቅር እየቀመስን ያደረገልንን እያደነቅን ፀጋውን እለት እለት እየተቀበልን፣ እኛ ሞተን ክርስቶስ በእኛ ውስጥ ህያው ሁኖ የምንኖረው ኑሮ ነው፡፡

ይህንንም ዓይነት ኑሮ ለመኖር አምላካችን ያደረገልንን የማዳን ሥራ፣ ስለ ሰው ልጆች ብሎ ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ /ልደቱን፣ ጥምቀቱን ፣ጾሙን ፣ መከራውን ፣ ስቅለቱን / በተለይም ደግሞ ለትንሳኤያችን በኩር የሆነበትን ትንሳኤውን እና እርገቱን እንዲሁም ዳግም ምጽአቱን ዘወትር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

እነዚህን ድርጊቶች /ነገሮች/ እንደ ትዝታ ማሰብ ብቻ ሳይሆን ልክ በተደረጉበት ወቅት እንደተገኙ ሁኖ መካፈልና መቅመስም የግድ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ቅዳሴ ዋነኛው መንገድ ነው፡፡ ቅዳሴ ለማስቀደስ በመሰዊያውና በመስዋእቱ ዙሪያ ስንሰበሰብ ልክ ጌታ በተሰቀለበት በዕለት አርብ በቀራንዮ አደባባይ እንደተገኘን ሆነን እንቆማለን፡፡

በአጠቃላይ ሕይወታችን እነዚህን ነገሮች በማስታወስ፣ በማሰብ እና በመካፈል ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡

ዳሩ ግን በኃጢአታችን ምክንያት በጥምቀት የተቀበልነውን አዲስ ሰውነት በማቆሸሻችን እና ራሳችንን ከፀጋ በማራቃችን፣ እንዲሁም በተለያዩ አስፈላጊ እና አላስፈላጊ ጉዳዮች ተጠምደን በወከባ በመኖራችን ይህንን ማድረግ ከባድ ይሆን ብናል፡፡

ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን እነዚህን በነገረ ድኅነት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውን ታላላቅ ድርጊቶች ቢያነስ በዓመት አንድ ጊዜ እንድናስባቸው አድርጋለች፡፡ የልደትን፣ የጥምቀትን፣ የስቅለትን፣ የትንሳኤን፣ የዕርገትን … በዓላት የማክበራችን ዋናው ምክንያትም ይኸው ነው፡፡

ነገር ግን አሁንም ቢሆን እነዚህን በዓላት ስናከብር ከሚያስጨንቁንና ህሊናችንን ከሞሉት ነገሮች መልሰን በአንድ ጊዜ ወደ መንፈሳዊ ሃሳብና ተመስጦ መምጣት ስለምንቸገር ቤተ ክርስቲያን ከበዓላቱ በፊት የዝግጅትና የማንቂያ ጊዜያት እና አጽዋማት እንዲኖሩም አድርጋለች፡፡

በእነዚህ ወቅቶች ህሊናችንን ቀስ በቀስ ወደ መንፈሳዊው ሃሳብ እና ወደ በዓሉ ጉዳይ ተመልሶና በዓሉን በናፍቆት ጠብቀን በተገቢው ሁኔታ እንድናከብረው ታደርጋለች፡፡

በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ በዓላት ከመከበራቸው በፊት አጽዋማት ይኖራሉ ሥጋ ወደሙን ከመቀበላችንም በፊት እንጾማለን፡፡ ሌሎቹም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከመፈፀማቸው በፊት የጾምና የዝግጅት ወቅቶችን ማሳለፍ ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ርእስ አድርገን የምንነጋገርበት ጾመ ነቢያት ዋነኛ ዓላማም ምእመናንን የጌታችንን የልደት በዓል እንዲያከብሩ ማዘጋጀት ነው፡፡ በተለይም ከልደት በፊት ያሉት ሦስት ሳምንታት ይህ ጎልቶ እንደሚነገርባቸው ቀጥለን እንመለከታለን፡፡

ብሉይ ኪዳን እና ጾመ ነቢያት

የአዳምን በደል ካሳ ከፍሎ ከራሱ ጋር ሊያስታርቀው ወደዚህ ምድር የመጣውና በተዋህዶ ሰው የሆነው እግዚአብሔር ወልድ በዚህ ምድር ላይ በሥጋ የተገለጠው አዳም የድኅነት ቃልኪዳንን ከእግዚአብሔር ከተቀበለ ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ ነው፡፡

እነዚህ ዓመታት ለሰው ልጆች በኋላ የሚደረገውን የድኅነት ሥራ /ሥጋዌ፣ ሞት፣ ትንሳኤ/ እንዲረዱ ለማስቻል ዝግጅት የተደረገባቸው ዘመናት ናቸው፡፡ በእነዚህ ዘመናት እግዚአብሔር የራሱ የሆኑ ሕዝቦችን እና ሰዎችን በመምረጥና ከእነዚህ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት፣ ለእነዚህ ሕዝቦች ተአምራትን በማድረግና ከጠላቶቻቸው በማዳን፣ ከእነዚህም በላይ ደግሞ ነቢያትን በመላክና በእነርሱ አማካኝነት ሕዝቡን በማስተማር፣ ትንቢት በማስነገርና ተስፋ በመስጠት /በማጽናናት/፣ ሱባኤም በማስቆጠር ማንነቱን እና የሰው ልጆችን ለማዳን ያቀደውን ዕቅድ ቀስ በቀስ፣ በጥቂት በጥቂቱ ገልጧል፡፡

በየዘመኑ የተነሱ ነቢያትም ምንም እንኳን አምላክ ይህን ዓለም እንዴት እንደሚያድነው ሙሉ በሙሉ ግልጥልጥ ብሎ ባይረዱትም እግዚአብሔር ዓለሙን የሚያድንበትን ቀን እንዲያቀርበው እንዲህ እያሉ ይማፀኑ ነበር፡፡

– «አቤቱ እጅህን ከሰማያት ልከህ አድነን» /መዝ. 143.17/
– «ሰማያትን ቀደህ ብትወርድ ምነው)» /ኢሳ.64.1/
ቅዱስ ጴጥሮስ በሁለተኛው መልእክቱ እንደሚነግረንም በመንፈስ እየተነዱ ስለሚመጣው ነገር ሁሉ ትንቢት ተናግረዋል፤ ሱባዔ ቀጥረዋል፤ ህዝቡም የጌታን ማዳን በተስፋ እንዲጠብቅ አስተምረዋል፡፡ ጌታ ሰው ሁኖ የተወለደው ከዚህ ሁሉ ዝግጅት በኋላ ነው፡፡ የአዳኙ መሲህ መወለድ በተለይ ከእስራኤል ዘንድ በጉጉት ይጠበቅ ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት ከእስራኤል መካከል ቅን የነበሩትና በእግዚአብሔር መንገድ የተጓዙት፤ «መሲሁን አገኘነው»፤ «ሙሴ በህግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው» /ዮሐ. 1.41፣ ዮሐ. 1.45/ እያሉ ተከትለውታል፡፡

እንግዲህ ይህ ታሪክ ከተፈፀመ ጌታችንም ከተወለደ እነሆ ከ2000 ዓመታት በላይ አልፎታል፡፡ እኛም የተደረገውን ሁሉ በትውፊት ተቀብለን በምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት በዚህ በድኅነት ጉዞ የተሰጡትን ፀጋዎች ተካፍለን ክርስቲያኖች ሆነናል፡፡ በመግቢያችን እንዳየነው ክርስትና እነዚህን ነገሮች ሁሉ ዘወትር እያሰብንና፣ በተመስጦ እንደ አዲስ እየተካፈልን ልንኖረው የሚገባ ኑሮ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እንዲከበር ያደረገችው ከእነዚህ ዘወትር ልናስባቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱ የሆነውን ብርሃኑንና ዘወትር ልናየው የሚገባውን የጌታችንን ልደትን ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ በተመስጦ እንድናስበውና ብርሃኑን እንድናየው ነው፡፡

ይህችን በዓመት አንድ ጊዜ የምትመጣዋን በዓልም ቢሆን ከማክበራችን በፊት አርባ ሦስት ቀናትን በመጾም እንዘጋጃለን፡፡ በመጾም ብቻ ሳይሆን እነዚህ አርባ ሦስት ቀናት ተከፋፍለው የልደት በዓልን በተገቢው መንገድ እንድናከብር የሚያዘጋጁ ትምህርቶችን እንማርባቸዋለን፡፡ በተለይም ከልደት በዓል በፊት ያሉት ሦስት ሳምንታት ይህ ዓላማ አላቸው፡፡

ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን የልደቱን ብርሃን ለማየት እንዘጋጅ ዘንድ እነዚህን ሦስት ሳምንታት የጌታችንን ልደት በናፍቆት መበጠበቅ እንደ ብሉይ ኪዳን ሰዎች ሆነን እንድናሳልፍ ታደርጋለች፡፡

በእነዚህ ሳምንታት /በተለይም በእሑዶቹ/ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የአዳኙን መምጣትና የጌታን ቀን መገለጥ በመናፈቅ ስላሳለፏቸው ጊዜያት ደጋግመን በመማር እነዚያን የጨለማ ዘመናት እንድናስታውስና እኛም በእነርሱ መንፈስ ተቃኝተን ያለንበትን ሁኔታ በመመርመርና ዘወትር ልንመላለስበት ያጣነውን ነገር ግን በሃጢአታችን ያጣነውን የልደቱን ብርሃን ለማየት እንድንናፍቅ እንደረጋለን፡፡

ሦስቱን ሳምንታት በዚህ ሁኔታ ካሳለፍንና የልደቱን ብርሃን የማየት ፍላጎታችን ከተነሳሳ በኋላ የልደትን በዓል እናከብራለን፡፡ ደጋግመን እንዳልነውም የልደትን በዓል የምናከብረው እንዳለፈ ታሪክ መታሰቢያ አይደለም፡፡ ልክ በዚያች በልደቱ ቀን ከሰብአ ሰገልና ከእረኞች ጋር እንደተገኘን ሆነን እናከብራለን የልደቱን ብርሃን እናያለን እንጂ፡፡

ለዚህም ነው የልደትን በዓል ስናከብር
«ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ»
«ዛሬ በክርስቶስ ልደት ደስታ ሃሴት ሆነ፡፡» የምንለው፡፡
«ዮም፣ ዛሬ» ማለታችን በዓሉ የልደት መታሰቢያ /ትዝታ/ ብቻ ሳይሆን በዚያ በልደት ቀን እንደነበርን የምንሆንበት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡

ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ

እነዚህ ከልደተ በዓል በፊት ያሉት ሦስቱ የጾመ ነቢያት ሳምንታት ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡

እነዚህ ሳምንታት ነቢያት አምላክ ይህንን ዓለም እንዲያድን ያላቸውን ናፍቆት የገለጡባቸው እና ይህንን አስመልክተው ያስተማሩባቸው ሦስት የተለያዩ መንገዶች እና ጌታችንም ለእነዚህ መልስ የሰጠባቸው ሁኔታዎች ይታሰቡባቸዋል፡፡

1. ስብከት

ስብከት ማለት ማስተማር ማለት ነው፡፡ ይህ ሳምንት ከሙሴ ጀምሮ የነበሩ ነቢያት በሙሉ አዳኝ /መሲህ/ እንደሚመጣ ማስተማራቸው ጌታችንም እነርሱ ይመጣል ብለው ያስተማሩለት እኔ ነኝ ብሎ ራሱን መግለጡ የሚታሰብበት ነው፡፡
ሙሴ ለጊዜው የጌታችን ምሳሌ ለሆነው ለኢያሱ ፍጻሜው ግን ለጌታችን በሆነው ትንቢቱ «አምላክህ እግዚአብሔር ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳልሃል፤ እርሱንም ስሙት፡፡» ብሎ ለሕዝበ እስራኤል ነግሯቸው ነበር፡፡ /ዘዳ. 18.15/

እግዚአብሔር ወልድም በሥጋ ማርያም በተገለጠ ጊዜ ራሱን ያስተዋወቀው ያ ነቢያት የተናገሩለት አዳኝ /መሲህ/ እንደሆነ ነው፡፡ «ሙሴ እና ነቢያት ሁሉ ስለ እኔ ይናገራሉ፡፡» ይላቸው ነበር፡፡

ትንቢቱን ያውቁ የነበሩ በእግዚአብሔር መንገድ የሚሄዱ እስራኤላውያንም «መሲሁን አገኘነው»፣ «ሙሴ በህግ መጻሕፍት፣ ነበያትም ስለ እርሱ የጻፈለትን የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው» እያሉ ተከትለውታል፡፡ /ዮሐ. 1.41፣ ዮሐ. 1.45/

ሐዋርያትና ሌሎቹ ደቀመዛሙርቱም ከጌታችን ሞትና ትንሳኤ በተለይ የተነገሩትን ትንቢቶች ሁሉ ያውቁ ለነበሩት እስራኤላውያን ያስተማሩት እነዚህን የነቢያት ትምህርቶች እና ትንቢቶች እየጠቀሱ ነበር፤

ቅዱስ ጴጥሮስን በቤተ መቅደስ እንዲህ ብሎ አስተምሯል፤ «አሁንም ወንድሞቼ ሆይ አለቆቻችሁ እንዳደረጉ ይህን ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቃለሁ፡፡ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በነቢያት ሁሉ አፍ እንደተናገረ እንዲሁ ፈፀመ» /ሐዋ. 3.17-18/፡፡

በሁለተኛው መልእክቱ ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- «ወንድሞች ሆይ የቀደሙ ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃልና ለእኛ ለሐዋርያትም ያዘዘውን የመድኃኒታችንና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ ታስቡ ዘንድ… ዕወቁ» /2ኛ ጴጥ. 3.1-3/

ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ መግቢያ ላይ እንዲህ ብሏል፤ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፤ በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው፣ ሁሉን በፈጠረበት በልጁ ነገረን፡፡» /ዕብ. 1.1-2/

2. ብርሃን

ነቢያት የአምላክን ማዳን ከጠበቁባቸው እና ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የፀናበት፣ ሁሉ ነገር አስጨናቂ የሆነበት፣ ሰው ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ያሉበትን ዘመን «ጨለማ» ብለው በመግለጥ ይህንን ጨለማ የሚያስወግድና ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን እንዲመጣ እንዲህ እያሉ ይፀልዩ ነበር፡፡

«ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፣ እነርሱም ይምሩኝ፣
አቤቱ ወደ መቅደስህ ተራራና ወደ ማደራያህ ይውሰዱኝ» /መዝ. 42.3/
ጌታችንም ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ለዚህ መልስ ሰጥቷል፤
«እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» /ዮሐ. 8.12/
ደቀመዛሙርቱም ስለ ብርሃንነቱ በመመስከር ተባብረዋል፤

– ቅዱስ ዮሐንስ ስለጌታችን ሰው መሆን /ሥጋዌ/ በተናገረበት በወንጌሉ የመጀመሪያ ክፍል ጌታችንን ብርሃን ብሎታል፤ «ሕይወት በእርሱ ነበረ፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላሰነፈውም» /ዮሐ. 1.4-5/

ቅዱስ ጳውሎስም ጌታችን በሚያንፀባርቅ ብርሃን አምሳል እንደተገለጠበት ተናግሯል፡፡ «እኩል ቀን በሆነ ጊዜ በመንገድ በሄደ ከፀሐይ ይልቅ የሚበራ መብረቅ በእኔና ከእኔ ጋር ይሄዱ በነበሩት ላይ ከሰማይ ሲያንፀባርቅ አየሁ፤ … አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ አለኝ፡፡» /ሐዋ. 26.13/

3. ኖላዊ

ኖላዊ ማለት እረኛ ማለት ነው፡፡ ነቢያቱ ራሳቸውን እና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደተዋቸው እና እንደተቅበዘበዙ በጎች በመቁጠር እንዲሰበስባቸውና እንዲያሰማራቸው እንዲህ እያሉ እራሳቸውን ይማፀኑ ነበር»

«ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ የእስራኤል ጠባቂ /እረኛ/ ሆይ፣ አድምጥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ፡፡» /መዝ. 79.1/

ጌታችንም ለዚህ ጥያቄ እንዲህ ሲል መልስ ሰጥቷል፤ «ቸር ጠባቂ /እረኛ/ እኔ ነኝ፡፡ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል፡፡»  /ዮሐ10.11/

ምን እናድርግ ?

ዛሬም እኛ በኃጢአታችንና በምታዋክበን ዓለም ምክንያት ዘወትር ልናየውና ልንመላለስበት የሚገባን ብርሃነ ልደቱ ተሰውሮብናል፣ ከቸር እረኛችን የራቅን የተቅበዘበዝን በጎች ሁነናል፡፡ በምናስበው ሃሳብ፣ በምንሰራው ሥራ ውስጥም የአምላክ ሰው መሆን ቦታ የለውም፡፡ የምንኖረው ልክ ክርስቶስ እንዳልተወለደ /as if Christ was not born/ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እንደ ብሉይ ኪዳን ሰዎች ያጣነውን ይህንን ፀጋ ለማግኘት፣ ብርሃነ ልደቱን ለማየት፣ በዚያ ውስጥም ለመመላለስ የክርስትናችንን እና የመንፈሳዊነታችንን ጥልቀት ለመጨመር መሻት አለብን፡፡

ስለዚህ እስኪ እኛም በእነዚህ ሳምንታት የብሉይ ኪዳን ሰዎች የነበሩበትን ሁኔታ እየተዘከርን፣ እኛም ያለንበትን ሁኔታ እየመረመርን፣ ስላጣነው ብርሃን ለማሰብ፣ ያጣነውን መልሰን ማየትንና ማግኘትን ለመናፈቅ እንሞክር፡፡ መጻሕፍትን ለማንበብ፣ በጉዳዩ ላይ በተመስጦ ለማሰብ እና ለመወያየት ጊዜ እንውሰድ፡፡ ብርሃነ ልደቱን ለማየት እንዲያበቃን «አቤቱ ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፤ ቸሩ እረኛችን ሆይ፣ ተቅበዝብዘናልና እባክህ ሰብስበን» እያልን እንፀልይ፡፡ ሰው ከነኃጢአቱ ወደ እግዚአብሔር ብርሃን ሊቀርብ /ሊያየው/ አይችልምና ራሳችንን በንስሃ እናድን፡፡ እነዚህን ቤተ ክርስቲያን ያስቀመጠችልንን የዝግጅት ጊዜያት በሚገባ ከተጠቀምን ትርጉም ያለው፣ በሕይወታችንና በመንገዳችን ላይ ለውጥ የሚያመጣ ልዩ የልደት በዓል እናከብራለን፡፡

አምላካችን ብርሃነ ልደቱን እንድንመለከት ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሰሙነ ሕማማት

በመ/ር መንግሥተአብ አበጋዝ

በነቢዩ ኢሳይያስ «ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ፤ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ፣ ሕመማችንንም ተሸከመ፣ እኛ ግን እንደተመታ፣ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሰፈ፣ እንደተቸገረም ቆጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፣ ስለ በደላችንም ደቀቀ፣ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡» /ኢሳ. 53፣4-7/ ተብሎ የተነገረው ቃል ተፈጽሞ፣ ጌታችን ለድኅነተ ዓለም ሲል በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለው ጸዋትወ መከራ የሚዘከርበት ሳምንት ነው፡፡ ከሆሣዕና ማግስት እስከ ትንሣኤ ያለው የጾመ እግዚእነ መዝጊያ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡

በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው፣ ከሐሜት፣ ከነገርና ከኃጢአት ርቀው፤ የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ሲያዜሙ፣ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍ ሲያነቡ፣ ሲሰሙ፣ ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፡፡ ካህናትና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሠለስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት /በዘጠኝ/ ሰዓት፣ በሰርክ /በዐሥራ አንድ/ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፣ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፣ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራ ሥቃይን እና 5ሺ 5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከር ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማት የጌታችንን ሕማማት ከማሰብ ጋር በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውንም የምናስታውስበት ሳም ንት ነው፡፡ በዕለት በዕለት ከፍለን በየትኛው ቀን ምን ተደረገ እያልን እንጠይቅ?

ሰኞ፡-ጌታችን የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ በምትባል መንደር ያድራል በማግስቱም ከቢታንያ ሲወጣ ተራበ /ማር. 11፣11-14/ ቅጠል ያላትን በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፣ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ዕለት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፡፡

ትርጓሜ፤ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች፣ ሃይማኖትና ምግባር ናት፡፡ ከእስራኤል ፍቅርን፣ ሃይማኖትን፣ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፡፡ እስራኤልን ሕዝበ እግዚአብሔር መባልን እንጂ፣ ነቢይነት፣ ካህንነት፣ መሥዋዕት አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ በመርገሙ ምክንያት ትንቢት ክህነት መሥዋዕት ከቤተ እስራኤል ጠፉ፡፡

በለስ ኦሪት ናት፡- ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና ፍሬ ባንቺ አይሁን አላት፤ ድኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡ በአዲስ ኪዳን የድኅነት ዘመንም ተተካች፡፡

በለስ ኃጢአት ናት፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ደስ ያሰኛል ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፡፡ በለሷም ስትረገም ፈጥና መድረቋ፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

ከዚህ ቀጥሎ ወደ ቤተ መቅደስ ሔደ፤ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምሥያጥ /የንግድ ቤት/ ሆኖ ቢያገኘው፤ «ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች… እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት» ማቴ.21፣13 ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸዉ፣ ገርፎም አስወጣቸዉ፣ ይህም የሚያሳየዉ ማደሪያው ቤቱ የነበርን እኛ የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ አንጽሖተ ቤተ መቅደስ የተፈጸመበት ሰኞም ይባላል፡፡

 ማክሰኞ፡- ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተመቅደስ ምክንያት፣ ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን፣ ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና፤ የጥያቄ ቀን ይባላል፡፡

ጥያቄውም ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን፣ በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? የሚል ነበር፡፡ /ማቴ. 21፣23-27፣ ማር. 11፣7-35፣ ሉቃ. 21፣23-27፣ ማር. 11፣27-33፣ ሉቃ. 20፣1-8/፤ እርሱም ሲመልስ፤ «እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፣ እናንተም ብትነግሩኝ በማን ሥልጣን እነዚህን እዳደርግ እነግራችኋለሁ፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረ፣ ከሰማይን? ወይስ ከሰዉ? በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ወይስ በሰው ፈቃድ?» አላቸው፡፡ እነርሱም ከሰማይ ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም ይለናል፤ ከሰው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፣ እንደ መምህርነቱ ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን፤ ተባብለው ከወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም አላቸው» ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተዉት አልነበረም፣ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ እንጂ፡፡

በማቴ. 21፣28፣ ምዕ. 25፣46፣ ማር. 12፣2፣ ምዕ. 13፣37፣ ሉቃ. 20፣9፣ ምዕ. 21፣38 የሚገኙት ትምህርቶች ሁሉም የማክሰኞ ትምህርት ይባላሉ፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ፣ የትምህርት ቀንም ይባላል፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር ሲጠይቅ  መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡

ረቡዕ፡- ምክረ አይሁድ ይባላል፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር ያጠናቀቁበት ቀን ነውና፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ቀን የተቃረበ በመሆኑ፣ ብዙው ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ፣ ተአምራቱንም የሚያደንቁ ስለ ነበር ሁከት እንዳይፈጠር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ፣ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ /ማቴ. 26፣1-14፣ ማር. 14፣1-2፣ ቁ 10፣11፣ ሉቃ. 22፣1-6/፤ የሐዲስ ኪዳን ካህናትና ምእመናን በዚሁ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ፣ ሐዋርያት ከጌታችን መያዝ በኋላ በኀዘን በፍርሐት እንደነበሩ እያሰቡ መጻሕፍትን በማንበብ በጾም፣ በጸሎ ትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ከአሥራ ሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ፣ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት፣ /ባለሽቱዋ ማርያም/፤ «ከእንግዲህ ወዲህ በኃጢአት ተበላሽቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚህ መልካም ሽቱ የሚያጣፍጥ፣ ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ» ስትል ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ፣ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ፣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የተሞላ ሽቱ ይዛ በመሔድ በጠጉሩ /በራሱ/ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው ነው፡፡ ረቡዕ የመዓዛ ቀን የተባለው፡፡

ረቡዕ የእንባ ቀንም ይባላል፡፡ ማርያም እንተ እፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ፣ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፤ በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሳዋለችና፡፡ /ማቴ. 26፣6-13፣ ማር. 14፣.9፣ ዮሐ. 12፣8/ ኃጢአትን በማሰብ ማልቀስና ራስን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ከምታስተምረን ማርያም እንተ እፍረት እንባን ለንስሐ ሕይወት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ሐሙስ፡- በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስያሜዎች ያሏቸው በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ዕለት ነው፡፡

ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ፣ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ተባለ፡፡ /ማቴ. 26፣36-46 ዮሐ. 17/፡፡

ሕፅበተ ሐሙስ ይባላል፡፡ ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች፤ «በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ እኛም የአንተን አርአያ አንዘነጋም የሌላውን እግር እናጥባለን፤» ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙትን ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

የምስጢር ቀን ይባላል፡፡ ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፡፡ ይኸውም «ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ» ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ «ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱም ጠጡ» በማለት፤ እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምስጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀመዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ሥያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡ ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ «ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱ ጠጡ» በማለቱ ይታወቃል /ሉቃ. 22፣20/ ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ተባለ፡፡

የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡፡ ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር «ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባርያ ጌታዉ የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ» በማለት /ዮሐ. 15፣15/፤ ከባርነት የወጣንበት ልጆች የተባል በትን ቀን የምናስብበት በመሆኑ ሊቃውንቱ የነጻነት ሐሙስ አሉት፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት  ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል፡፡ ባሮች አልላችሁም ተብለናልና፡፡

የጸሎተ ሐሙስ ምስጢራት በብሉይ ኪዳን

ለፋሲካ ዝግጅት ተደርጎበታል፡፡ ዝግጅቱም በሦስቱ ወንጌላት ላይ ተመዝግቧል /ማቴ. 26.7-13/፡፡ ፋሲካ ማለት ማለፍ ማለት ነው፡፡ ይኸውም እስራኤላውያን በግብፅ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይም በመቃኑ እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፡፡ ሙሴም ለሕዝቡ ነገረ፣ ሁሉም እንደታዘዙት ፈጸሙ፡፡ መቅሰፍት ከእግዚአብሔር ታዞ መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የግብፃውያንን ቤት በሞተ በኲር ሲመታ፣ የበጉ ደም ምልክት ያለበትን የእስራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ ማለፉን ለማመልከት ነው፡፡ /ዘጸ. 12፣1-20/፡፡ በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እስራኤላውያን በመጀመሪያ ወራቸው በ14ኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ ሀገራችንም አስቀድማ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች ሀገር እንደመሆኗ ይህ ድርጊት ይፈጸምባት ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ፋሲካ ተብሎ የተጠራበት ምክንያት በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስ ሞተ በኲር የተባለ ሞተ ነፍስ ርቆልናልና፡፡ «ፋሲካችንም ክርስቶስ ነው» /1ቆሮ. 5፣7 1ጴጥ. 1፣18-19/

በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ሁሉ በዮሐ. 14፣16 የሚገኘውን ለደቀመዛሙርቱ ረጅም ትምህርት አስተምሯል፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎች ምስጢረ ሥላሴ የሦስትነት ትምህርት፣ ምስጢረ ሥጋዌ /የአምላክ ሰው መሆን/፣ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን /የዳግም ምጽአቱን ነገር/ ነው፡፡ እነዚህን ትምህርቶች በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳ፣ በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲችል በረጅም ትምህርት እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም እሱ እያስተማራቸው ሳለ ያልገባቸውንም እየጠየቁ ተረድ ተዋል፡፡ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቆ መረዳት እንደሚገባን እንማራለን፡፡ በዚሁ ዕለት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠበት ቀን ነው፡፡ ማቴ. 26፣47-58

ዓርብ-

የስቅለት ዓርብ ይባላል፡፡ የዓለም ሁሉ መድኃኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ መዋሉን ለማስታወስ ነው፡፡ /ማቴ. 27፣35/፡፡

መልካሙ ዓርብ ይባላል፡፡ ይህም የሚያስገነዝበን ከስቅለተ ክርስቶስ በፊት አንድ ሰው ሲያጠፋ ተሰቅሎ ይሞታል፡፡ በሮማውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት ነበር፡፡ በዚህ ዕለት የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምሕረት ምልክት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስለ አደረገው፣ በሞቱ መልካሙን ሕይወትን ስለአገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡

የትንሣኤን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የሚሔዱ ምእመናን ሁሉ በዕለተ ዓርብ መከራውን ለማሰብ ከቤተ ጲላጦስ እስከ ጎልጎታ መቃብረ ክርስቶስ ድረስ ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ጉዞ የሚደረግባቸውም አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል የተፈጸሙባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡

በዚህ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው መከራውን በማሰብ ሲሰግዱ የሚውሉ እንዳሉ ሁሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ በስም ክርስቲያን ተብለን ከምንጠራው መካከል፣ ተድላ ደስታ በሚፈጸምባ ቸው ሥፍራዎች ክፉ ሥራ ስንፈጽም የምንውል አንጠፋም፡፡ እንዲህ የምናደርግ ሁሉ በአለፈው ልንጸጸትና በቀሪ ዘመናችን ልንታረም ይገባል፡፡ በዓመት አንዴ የምናገኘው ይህ ዕለት ቀራንዮን የምናስብበት፤ ነገረ መስቀሉን የምናስተውልበት እንጂ ስለ ምድራዊ ኑሮአችን ስንባክን ኃጢአት ስንሠራ የምንውልበት ሊሆን አይገባም፡፡

ቅዳሜ-

ቀዳም ሥዑር ይባላል፡፡ በዚች ዕለት ከድሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምት ውል የተሻረችው ቅዳሜ ተብላለች፡፡

ለምለም ቅዳሜ ካህናቱ ለምእመ ናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ በዚህ ተሠይሟል፡፡ ቀጤ ማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡

ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡፡ ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው  ሁሉ ያረፈበት ሲሆን፤ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን  ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷ ታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘ ለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡ የዕለታ ቱን ክብርና ሥያሜ ከማወቅና ከመ ረዳት ጋር በዕለታቱ የታዘዙትን ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡

ምንጭ- መጽሐፈ ግብረ ሕማማት
-ሐመርና መለከት መጽሔቶች
ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም

ዕለታተ ሰሙነ ሕማማት ወምስጢራት

በዲ.ቸሬ አበበ

 

ከአባታችን አዳም በደል ወይንም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሰፍታት፣ ወዘተ በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የሆነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ጥሮ ግሮ ወጥቶ ወርዶ ለፍቶ ማስኖ የዕለት ጉርስ የቀን ልብስ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ ሁልጊዜ የሰው ልጅ ቢያጠፋ ቢበድል ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳ የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የሆነ አምላክ የጠፋውን ሊፈለግ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ያጣውን ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላም ሊሰጥ፣ ተስፋ የሌለውን ተስፋ ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኃጡአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም ምሳሌ ሆነን፡፡ ዲያብሎስን ድል አድርጐ ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ሆነን፡፡
 
ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው?

ሰመነ ስምንት /ሳምንት/ አደረገ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከዕለተ ሆሣዕና ሰርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ሐመ ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልእት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡
መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም እግዚአብሔር ይፍታህ አይሉም የሳምንቱ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምጽ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መሆናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜያት

ዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/
ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ /የቤተ መቅደስ መንጻት/ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ /ማር.11-11፣ ማቴ.21-18-22 ሉቃ.13-6-9/፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወመሰለ ሎሙ ወይቤሎሙ አሐዱ ብእሲ በለሰ ቦቱ ውስተ አጸደ ወይኑ ወየሐውር ይንሣእ ፍሬሃ ወኢይረክብ …»፤ ይህንም ምሳሌ አለ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፡፡ በማለት በበለስ ስለተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደጠወለገችና እንደተቆረጠች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቆረጡ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባርን ነው፡፡ ሁላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንሆን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም እንዳይጠወለግ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡
ዕለተ ሠሉስ /ማክሰኞ/
ይህ ቀን ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?» የሚል ነበር፡፡ /ማቴ.21-23-27/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ «ወይቤሎሙ ኢየሱስ አማን እብለክሙ ከመ መጸብሓውያን ወዘማውያት ይቀድሙክሙ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር»፤ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው እውነት እላችኋለሁ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል ሲል አስተምሯል፡፡ /ማቴ.21-28/
ዕለተ ረቡዕ

ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ የምክር ቀን በመባል ይጠራል፡፡

ዕለተ ሐሙስ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም «ወሶበ ኀፀቦሙ እገሪሆሙ ነሥአ አልባሲሁ ወረፈቀ ካዕበ ወይቤሎሙ አእመርክሙኑ ዘገበርኩ ለክሙ … ወሶበ አነ እንከ ሊቅክሙ ወእግዚእክሙ ኀፀብኩክሙ እገሪክሙ ከማሁኬ አንትሙኒ ይደልወክሙ ትኅፅቡ እግረ ቢጽክሙ፡፡»፤ «እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?… እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል ሲል ተናግሯል፡፡ /ዮሐ.13-12-20/፡፡
ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ በማለት ምሥጢረ ቁርባንን የመሠረተበት ወይም ራሱ ምስጢረ ቁርባንን የጀመረበት ቀን በመሆኑ የምስጢር ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው፡፡ /ማቴ.26-26-29/፡፡
አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለሆነ በዚህ ዕለት በለሆሳስ /ብዙ የድምጽ ጩኸት ሳይሰማ/ የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለሆነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ የሕጽበት፣ የምስጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሓ ታጥበው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡
ዕለተ ዐርብ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /1ቆሮ.1-18/፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.27-35-75/፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን?  አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ፡፡ /ማቴ.27-3-9/
የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡
ቀዳሜ ስዑር
ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈበት ዕለት ነች፡፡ ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት እግዚአብሔርን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ ስላረፈበት ሰንበት ዐባይ /ታላቋ ሰንበት/ ትባላለች ታላቋን ሰንበት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዘፍ.1፡3፡፡
ዕለተ ቀዳሚት /ሰንበት ዐባይ/ በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደ ተደረገባት ሁሉ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ የሆነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በመቃብር አርፎባታል፡፡ ማቴ.27፡61፡፡
በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ «ቀዳሜ ስዑር » ትሰኛለች፡፡ ስዑር ቀዳሜ የተባለችው በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ምክንያቱም እናቱ ድንግል ማርያም ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡
ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን በመጾምና በመጸለይ ዕለቷ እንዳከበሯት የተዋሕዶ ልጆች የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው የሚያከፍሉ /የሚጾሙ/ ለሁለት ቀን እህል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡
በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ «ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፡-በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» የምሥራች እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡት ምእመናን ቄጠማ ይታደላል ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡
«ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡
የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳሃን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡ 
 

ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡አሜን፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የሆሳዕና እሁድ

በዲ/ን በረከት አዝመራው
 
«አንች የጽዮን ልጅ አትፍሪ፤ እነሆ ንጉሥሽ በእህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል» ተብሎ እንደተጻፈ ኢየሱስ የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርሱ ተቀመጠ ዮሐ.12፥15፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመምጣቱ አስቀድሞ 1400 ዓመታት በፊት እግዚአብሔር በአብርሃም የእምነት ቃል ኪዳን ሕዝቡ ያደረጋቸውን እስራኤላውያንን በጽኑ  ክንድ ከባርነት ቀንበር አውጠቶ ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን አምድ እየመራ በመገናኛዋ ድንኳን ውስጥ አድሮ እርሱ ንጉሣቸው ሆኖ እነርሱ ደግሞ ህዝቡ ሆነው በምድረ በዳ መራቸው፤ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከነዓንም አገባቸው፡፡ እስራኤል ግን ምድራዊ ንጉሥ በመፈለግ ንጉሣቸው እግዚአብሔርን በመተዋቸው እግዚአብሔርን በደሉ፤ በምድር ላይ ያለች የመንግሥቱ ማሳያ ሊሆኑ የመረጣቸው ሕዝቡ ምድራዊ ንጉሥ ፈልገዋልና፡፡ መልከ መልካምና ያማረ የሆነው ሳኦል እስራኤል የመረጡት ምድራዊ ንጉሥ ውጫዊ ክብር ብቻ ያለው መሆኑን አስመስከረ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከዚህ ዓለም ያልሆነች በቁሳዊው ኅብር ያላጌጠች፣ የትህትናና የፍቅር የምሥጋና የሆነች መንግሥቱን ሊያመለክት ሲወድ ከወንድሞቹ ሁሉ ያነሰውንና በገና ደርደሪውን የእሴይን ልጅ ዳዊትን መረጠ፡፡ የዳዊት መንግሥት ብታልፍም « ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ» ያለውን ቃልኪዳን ግን አላጠፋም ፡፡ ስለዚህም በአምላክነቱ ለዘላለም የነገሥታት ንጉሥ የሆነ ወልድ ከዳዊት ዘር ሰው ሲሆን የዳዊት ተስፋ ተፈጸመ፤ በመለኮታዊ ስልጣኑ በእግዚአብሔር እሪና ያለው ወልደ እግዚአብሔር የዳዊት ልጅ ሆኗልና፡፡ ስለዚህም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበስራት «ካንቺ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፡፡ እርሱም በያዕቆብ ወገን ላይ ለዘላለም ይነግሳል» በማለት የትንቢቱን ፍፃሜ አበሰረ፡፡ /ሉቃ.1/

  ንጉሥነ ክርስቶስ

ጌታችን ሲወለድ ስብዓሰገል «የተወለደው የእስራኤል ንጉሥ ወዴት ነው» በማለት ንጉሥነቱን ገልጠዋል፡፡ /ሉቃ. 2፥2/ ነገር ግን በምድራዊ ክብር ያጌጠ ሳይሆን በከብቶች ግርግም የተኛ፣ በእረኞችና በከብቶች የተከበበ ትሁት ንጉሥ ነው፡፡ መንግሥቱ ከዚህ ዓለም ያልሆነች ሰማያዊት ነችና መላእክት በዝማሬ አመሰገኑት፡፡ ጌታ ንጉሥ ያልሆነበት አንድ ጊዜም  ባይኖርም ይህች መንግሥቱ በምድራዊ ክብር ሳይሆን በትህትና በፍቅር ያጌጠች ሰማያዊት ስለሆነች በሃሳባቸው ምድራውያን የሆኑ ሰዎች ሊያውቋት አልቻሉም፡፡ ስለዚሀ የቀጠራት ሰዓት ስትደርሰ ሰማያዊትና መንፈሳዊት መንግሥቱን በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ በትህትና ገለጣት፡፡

«ሆሳዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው፡፡» ዮሐ.12፥13   

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአልዓዛር ቤት በቢታኒያ የመጨረሻውን ራት ከበላ በኋላ ሐዋርያቱን ልኮ የአህያ ውርንጫ አስመጥቶ በርሷ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚህም  የሚከተሉት ነገሮች ተገልጠዋል፡ ፣

1.    መንግሥቱ የትህትና እና የፈቃድ መሆኗን

አህያ ከእንሰሳት ሁሉ የማታስፈራ ናት፡፡ ጌታም እንደ ነገሥታቱ ስርዓት በከበረ ሰረገላና በፈረስ ሳይሆን በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ መንግሥቱ የትህትና መሆኗንና ሁሉም ሰው ተገዶ እና ፈርቶ ሳይሆን በፈቃዱ የሚገባባት መሆኗን ለማሳየት ነው፤ በአህያ ሰውን አባሮ መያዝ እንኳ አይቻልምና፡፡ ይህም በአጋጣሚ እንደ አንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ የሆነ ሳይሆን ነቢያት በትንቢት የተናገሩትና በእግዚአብሔር የድህነት ጉዞ የታሰበ ነው፡፡ ነቢዩ ዘካርያርስ ስለዚህ ሲናገር «አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንች የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዬ፤ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም  ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንች ይመጣል» በማለት ገልጦታል፡፡ ዘካ.9፥9፡፡

2.    የመገለጡ አላማ ለድህነት እንጅ ለክብር አለመሆኑ

 
እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል ከማክበራቸው ከአምስት ቀን በፊት በዚህ ዕለት ለፋሲካ የሚሆኑት ጠቦቶችን ወደ ኢየሩሳሌም ይዘው ይገቡ ነበር፡፡ /ዘጸ.12፥1- 36/ ጌታችንም በዚህ ዕለት ወደ ኢየሩሳሌም መውጣቱ የመንግስቱን ምሥጢር በመስቀልና በመስዋዕትነት ፍቅር የሚገልጽ የእግዚአብሔር በግ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ከላይ በተጠቀሰው የዘካርያስ ትንቢት ላይ « እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው» የሚለው፡፡ ጌታችን ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ለመመስገን አስቦ ሳይሆን ይቀበሉት ዘንድ አለምን ለማዳን የመጣው ንጉሥ እርሱ መሆኑን በአደባባይ ለማወጅ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ምሥጋናን  ከህፃናት የተቀበለው፤ ሕፃናት ሁሉን ይቀበላሉና፡፡ ለዚህም ነው እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አትገቡም በማለት የተናገረው፡፡ / ሉቃ. 18፥17 / የመዳን ተስፋ የተነገረላቸው እስራኤላውያን ባልተቀበሉት ጊዜ ግን የመጣበት ዓላማ ይህ ስለነበር  ስለነርሱ አለቀሰ፡፡ ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፤ እንዲህም አለ «ለሰላምሸ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ እንኳ ብታወቂ አሁን ግን ከአይንሽ ተሰውሯል» ሉቃ. 19.41፡፡ የመምጣቱ ዓላማ ለዓለም ሰላምን የሚሰጥ /እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቅ/ አዳኝ ንጉሥ፣ የፋሲካ በግ መሆኑን ለማወጅ ነበርና ባልተቀበሉት ጊዜ አለቀሰላቸው፡፡ «ሆሳዕና» ማለት ግን «አሁን አድን» ማለት ስለሆነ አዳኝነቱ መቀበል ነበር፡፡ ንጉሥነቱን በአዳኝነቱ መግለጡም መንግሥቱ የፍቅር መሆኑንና ዙፋኑም መስቀል መሆኑን ለመግለጥ ነው፤ በጉ «የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ» ነውና፡፡ ራዕይ.19፥13- 16

  የሆሳዕና አከባበር በቅድስት ቤተክርስቲያናችን

ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሆሳዕና በታላቅ ክብር ታከብራለች፡፡ አከባበሯም እንደ አይሁድ እሁድ ሆሳዕና በእግዚአብሔር ስም የመጣች የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፣ ሆሳዕና በአርያም ካሉ በኋላ አርብ « ይሰቀል ይሰቀል» በማለት ሳይሆን እስከ መጨረሻው ድረስ ከእርሱ ጋር መሆንን በሚያሳይ አስደሳችና መንፈሳውያን ስርዓቶቿ ነው፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡

ዑደት

በቤተከርስቲያትን ሥርዓት መሰረት የሆሳዕና ጠዋት ቅዳሴ ከመገባቱ በፊት ዑደት ይደረጋል፡፡ ዑደቱም ከቤተመቅደስ ተጀምሮ በየአራት በሮች እየቆመ ምስባክ እየተሰበከ ወንጌል እየተነበበ ከተዞረ በኋላ በመጨረሻ ካህናቱና ዲያቆናቱ ወደ ቤተመቅደሱ ሲመለሱ ያልቃል፡፡ ዑደቱንም ዲያቆናት መስቀልና ስዕል /የእመቤታችን/ ይዘው፣ ካህኑ ማዕጠንት እያጠኑ ይመሩታል፡፡

 
ይህ ዑደት የቤተክርስቲያን ዘላለማዊው ጉዞዋ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ጉዞ ከእግዚአብሔር ይጀምራል፡፡ ክርስትና የእግዚአብሔር ጅማሬ እንጅ የሰው አይደለምና፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ዑደት ከመሰዊያው ይጀምራል፤ መስዊያው ሰማያዊ ነውና፡፡ የዚህ የቤተክርስቲያን ጉዞ መሪ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር መርቶ ያደረሰ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ ካህኑ ዕጣን እያጠነ ይመራል፡፡ ይህ ጉዞ መከራ ያለበት መንገዱ ጠባብ ይሁን  እንጅ በደስታ የተሞላ ነው፡፡ ስለዚህ ዲያቆኑ መስቀል ሲይዝ ሕዝቡ ደግሞ ይዘምራሉ፡፡ ደስታና መስቀልን በአንድ ላይ ለመግለጥ ነው፡፡ የዚህ ጉዞ ፍጹም አርአያ ደግሞ እመቤታችን ናት ሁለቱንም ታሳያለችና፡፡ በአንድ በኩለ «ኅዘን በልቧ ያለፈ» ሲሆን በሌላ በኩል « ተአብዮ ነፍስዬ ለእግዚአብሔር ወትተሐሰይ መንፈስየ» ብላ ዘምራለችና፡፡ ዑደቱ በምዕራብ በር በኩል /በዋናው በር/ መጀመሩ እና በእያንዳንዱ በር መቆማችን የዘላለም ደጆች መከፈታቸውንና ሰማያውያንም የጉዞአችን /የማኅብራችን/ ተካፋዮች መሆናቸውን ያጠይቃል፡፡ በመጨረሻም ዑደቱ በካህናቱ ወደቤተ መቅደሱ መግባት መጠናቀቁ የክርስትና ጉዟችን ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም በመኖር መፈጸሙን ያሳያል ፡፡ በዚህ ጉዞዋ ቤተክርስቲያናችን እስከ መጨረሻው ከክርስቶስ የሚጸና ዘላለማው ጉዞዋን ትናገራለች፡፡

  ቅዳሴ

ከዑደት በኋላ ቅዳሴ ይቀጥላል፡፡ በቅዳሴም የክርስቶስን ሥጋና ደም እንቀበላለን በዚህም እስከሞት ድረስ የሚዘልቅ አንድነታችን እንገልጣለን፡፡ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ «ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሌ ይፈጸማል፡፡ ለአህዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና ይዘብቱበትማል፣ ያንገላቱትማል፣ ይተፉበታል፤ ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል በሦስተኛውም ቀን ይነሳል፡፡» እንዳለ የኢየሩሳሌም ጉዞው ወደሞት የተደረገ ጉዞ ነበር፡፡ ስለዚህ በሥጋወደሙ ከእርሱ ጋር የሆንን ምእመናንንም ከእርሱ ጋር ወደ ሙት እንሄዳለን፡፡   

ፍትሐት

ከቅዳሴ በኋላ ፍትሃት ይደረጋል፤ ይህም ለህዝቡ ሁሉ ነው፡፡ አንዳንዶች ይህ ፍትሃት ምናልባት በዚህ ሰሞን የሚሞቱ ካሉ በሚል የሚደረግ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ፍትሃት ለሁሉም ክርስቲያን ጭምር ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የጌታን ሞትና ትንሳኤ ማሰብ ሳይሆን አብረነው ሞቱን ትንሳኤውን እንካፈላለንና፡፡ ሰውነታችን በጸሎትና በስግደት ለዓለማዊ ፈቃዳችን ሁሉ ገድለን በእርሱ ትንሳኤ ትንሳኤ ልቦናን እንነሳለንና፡፡ ይህም ለመነኮሳት እንደሚደረግ ፍትሃት ያለ ነው፡፡ መነኮሳት ሲመነኩሱ ለዚህ ዓለም የሞቱ መሆናቸውንና የክርስቶስን መስቀል መሸከማቸውን ለማጠየቅ የሙታን ጸሎት እንደሚደረግላቸው ምእመናንንም የጌታን መስቀል በመሸከምና መከራውን በመካፈል ለዓለም ለመሞት በመወሰን ቤተክርስቲያን የሙታን ጸሎት ታደርግላቸዋለች፡፡ በዚህም ጌታችንን አብረን ወደ ሞቱ እንከተለዋለን፡፡

  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዐቢይ ጾም፤ ወደ ትንሣኤ የሚደረግ ጉዞ

ዲ/ን ዘላለም ቻላቸው

አንድ ሰው ለጉዞ ሲነሣ ወዴት እንደሚሄድ ማወቅ አለበት፡፡ በዐቢይ ጾምም እንዲሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ዐቢይ ጾም መንፈሳዊ ጉዞ ነው፤ መድረሻውም ትንሣኤ ነው፡፡ ለእውነተኛው መገለጥ ለፋሲካ መሟላት የሚደረግ ዝግጅት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈላጊ የሆነና ስለ ክርስትና እምነታችንና ሕይወታችን በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር ስለሚገልጥልን ይህን በዐቢይ ጾም እና በትንሣኤ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመረዳት በመሞከር መጀመር አለብን፡፡

የትንሣኤ በዓል ከበዓላት አንዱ ከመሆን እና የአንድ ያለፈ ክስተት መታሰቢያ ከመሆን በላይ ሊታሰብ ያስፈልገዋል፡፡ አንድ ጊዜም ብቻ እንኳን ቢሆን የትንሣኤን በዓል በሚገባው መልኩ አክብሮ በዚያም ከቀን ይልቅ በሚያበራው ሌሊት የተሳተፈና ያንን ልዩ ደስታ የቀመሰ ማንም ሰው ያውቀዋል፡፡ ያ ደስታ ግን ስለ ምንድን ነው? በትንሣኤ በዓል ዕለት እንደምናደርገው «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሀጺባ በደመ ክርስቶስ»፤ «ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ»፣ «ዛሬ ሁሉም ነገር፣ ሰማይም፣ ምድርም፣ ከምድር በታች ያሉ ነገሮችም በብርሃን ተሞሉ» እያልን መዘመር የምንችለው ለምንድነው? «የሞት መሞት፤ የሲኦል መበዝበዝ፣ የአዲስና የዘለዓለማዊ ሕይወት መጀመሪያ…» እያልን ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?

ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሱ ይህ ነው፡፡ ከሁለት ሺሕ ዓመታት በፊት ከመቃብር ወጥቶ ያበራው አዲስ ሕይወት በክርስቶስ ለምናምን ለሁላችንም ተሰጥቶናል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ «በሞቱም እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን፤ እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን» /ሮሜ.6-4/ እንዳለው ይህ አዲስ ሕይወት እና ብርሃን ለእኛ የተሰጠን በጥምቀታችን ዕለት ነው፡፡

ስለዚህ የትንሣኤን በዓል ስናከብር፣ የክርስቶስን ትንሣኤ በእኛ ላይ እንደተደረገ እና አሁንም እንደሚደረግ አድርገን እናከብራለን፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዳችን የዚያን የአዲስ ሕይወት ስጦታ እና ያንን የምንቀበልበት እና በእርሱም የምንኖርበትን ኃይል ተቀብለናል፡፡ ይህ ስጦታ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር ሁሉ ስለ ሞትም ጭምር ያለንን አመለካከት የሚቀይር ነው፡፡ በደስታ «ሞት የለም» ብለን በእር ግጠኝነትም መናገር እንድንችል የሚያደርገን ነው፡፡

ኦ! ሞት ግን አሁንም አለ፤ በእርግጠኝነት አንጋፈጠዋለን፤ አንድ ቀንም መጥቶ ይወስደናል፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ በራሱ ሞት፣ የሞትን ባሕርይ /ምንነት/ እንደቀየረው ይህ ሙሉ እምነታችን ነው፤ ሞትን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት መሸጋገሪያ፣ ማለፊያ፣ ፋሲካ አድርጎታል፤ ከአሳዛኝ ነገሮች ሁሉ የበለጠ አሳዛኝ የነበረውን ሞት ወደ ፍጹም ድልነት ቀይሮታል፡፡ «ሞትን በሞቱ ደምስሶ» የትን ሣኤው ተካፋዮች አድርጎናል፡፡ ለዚህም ነው «ክርስቶስ ተነሥቷል፣ ሕይወትም ሆኗል፤ ማንም በመቃብር አይቀርም» የምንለው፡፡

ቁጥር በሌላቸው በቅዱሳኖቿ የተረጋገጠውና ግልጽ የተደረገው የቤተክርስቲያን እምነት ይህ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እምነት በእኛ ውስጥ ሁልጊዜ አለመኖሩ [ይህንን ሁል ጊዜ አለማሰባችን]፤ እንዲሁም እንደ ስጦታ የተቀበልነውን አዲስ ሕይወት ሁልጊዜ መጣላችንና መካዳችን እንዲሁም ክርስቶስ ከሞት እንዳልተነሣ ሆነን የመኖራችን ነገር እና ያ ልዩ ክስተት ለእኛ ምንም ዓይነት ትርጉም የሌለው መሆኑ የዕለት ተዕለት ተሞክሮአችን አይደለምን?

ይህ ሁሉ የሆነው በድካማችን ምክንያት ነው፡፡ ማለትም ጌታ «አስቀድማችሁ መንግሥቱንና ጽድቁን ፈልጉ» ባለን ጊዜ በወሰነልን ደረጃ «በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር» መኖር ለእኛ የማይቻለን በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ በቀላሉ እንረሳዋለን፤ ምክንያቱም ሁልጊዜም በተለያዩ ሥራዎች የተጠመድን እና በዕለት ተዕለት ተግባሮቻችን የተዋጥን ነን፤ ስለ ምንረሳም እንወድቃለን፤ በጥምቀት የተቀበልነውን አዲስ ሕይወት እና ብርሃንም እንጥላለን፡፡

በዚህ በመርሳት፣ በመውደቅ እና ኃጢአት በመሥራት በኩልም ሕይወታችን በድጋሚ «አሮጌ» ይሆናል፤ ጥቅም /ረብ/ የሌለው፤ ጨለማ እና ትርጉም አልባ፤ ትርጉም የሌለው ጉዞ፤ ትርጉም ወደሌለው ፍጻሜ ይሆናል፡፡ሞትን እንኳን ሳይቀር ረስተነው ከቆየን በኋላ በድንገት «ደስታ በሞላበት ሕይወታችን» መሐል አስፈሪ፣ ሊያመልጡት የማይችሉት እና አስጨናቂ ሆኖ ወደ እኛ ይመጣል፡፡

በየጊዜው ኃጢአታችንን ልንናዘዝ እንችላለን፤ ነገር ግን ሕይወታችንን ከዚያ ክርስቶስ ለእኛ ከገለጠውና ከሰጠው ከአዲሱ ሕይወት ጋር ማዛመድና ሕይወታችንን በዚያ ላይ መመሥረት እናቆማለን፡፡ ትልቁና እውነተኛው ኃጢአት፣ የኃጢአቶች ሁሉ ኃጢአት፣ የስም ብቻ የሆነው ክርስትናችን በጣም አሳዛኝ ገጽታ ይህ ነው፡፡ የሕይወታችንን ትርጉም በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ አለመመሥረት፡፡

ይህንን ልብ ካልን፣ የትንሣኤ በዓል ምን እንደሆነና ዐቢይ ጾም ለምን ከእርሱ በፊት እንዲኖር እንዳስፈለገ እንረዳለን፡፡

በዐቢይ ጾም በቤተክርስቲያን የሚደረገው ሥርዓተ አምልኮ ዓላማም በቀላሉ የምንጥለውንና የምንወስደውን የዚያን የአዲስ ሕይወት ርእይ እና ጣዕም በውስጣችን እንድናድሰው ለመርዳት እና ተጸጽተን ወደ እርሱ እንድንመለስ ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም የማናውቀውን ነገር እንዴት ልንወድና ልንፈልግ እንችላለን? አይተነው እና አጣጥመነው የማናውቀውን ነገር እንዴት በሕይወታችን ካሉ ነገሮች ሁሉ በላይ ልናደርገው እንችላለን? በአጭሩ ስለ እርሱ ምንም አሳብ የሌለንን መንግሥት እንዴት ልንፈልግ እንችላለን? አንችልም፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያን በእነዚህ ሥርዓተ አምልኮዎች ይህን እንድናደርግ ትረዳናለች፡፡

በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ወዳለው ሕይወት መግቢያችን፤ ከዚያም ጋር ያለን ኅብረት መሠረት በቤተክርስቲያን ያለው አምልኮ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን «ጆሮ ያልሰማውን፣ ዓይንም ያላየውን በሰው ልብም ያልታሰበውን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እርሱን ለሚወዱት ያዘጋጀውን» ከዚያ ነገር ጥቂቱን ለእኛ የምትገልጥልን በአምልኮ ሕይወቷ አማካኝነት /through her liturgical life/ ነው፡፡ በዚያ በአምልኮ ሕይወት መሐል ላይ ደግሞ፣ እንደ ጠቅላላው የአምልኮ ሥርዓት ልብ እና ከፍታ፣ እንዲሁም ጨረሮቿ ሁሉም ቦታ እንደሚደርሰው ፀሐይ ሆኖ የትንሣኤ በዓል ይቆማል፡፡

የትንሣኤ በዓል በየዓመቱ ወደ ክርስቶስ መንግሥት ግርማ እና ውበት ለማሳየት የሚከፈት በር ነው፡፡ የሚጠብቀን ዘለዓለማዊ ደስታ ቅምሻ ነው፡፡ ምንም እንኳን በስውር ቢሆንም ፍጥረትን ሁሉ የሞላው፣ «ሞት የለም!» የሚለው የዚያ ድል ክብር መገለጫ ነው፡፡

አጠቃላይ የቤተክርስቲያን የአምልኮ ሕይወት ዓመታዊው የአምልኮ መርኀ ግብር / liturgical year/ የተደራጀው በትንሣኤ ዙሪያ ነው፤ ማለትም በዓመቱ በተከታታይ የሚመጡት ወቅቶች እና በዓላት ወደ ፋሲካ፣ ወደ ፍጻሜው የሚደረጉ ጉዞዎች ይሆናሉ፡፡ ፋሲካ ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን ጅማሬም ነው፤ «አሮጌ» የሆነው ነገር ሁሉ ፍጻሜ እና የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ፤ ከዚህ ዓለም በክርስቶስ ወደ ተገለጠው መንግሥት መሸጋገሪያ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የኃጢአት እና የማይረቡ ነገሮች መንገድ የሆነው «አሮጌው» ሕይወት ግን በቀላሉ የሚሸነፍ እና የሚቀየር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ አሁን ባለበት ሁኔታ ሊፈጽመው የማይችለውን ነገር የወንጌል ሕግ ትጠብቅበታለች፡፡ ከአቅማችን እና ከምንችለው እጅግ በጣም በሚበልጥ ርእይ፣ ግብ እና የሕይወት መንገድ እንፈተናለን ምክንያቱም ሐዋርያት እንኳን ሳይቀሩ የጌታን ትምህርት ሲሰሙ ተስፋ በመቁረጥ «ይህ እንዴት ይቻላል?» ብለው ጠይቀውታል፡፡ በእርግጥም በየዕለቱ በሚያስፈልጉን ነገሮች በመጨነቅ፣ ቀላል ነገሮችን፣ ዋስትናን እና ደስታን በመፈለግ የተሞላን የማይረባ የሕይወት እሳቤ ትቶ «ሰማያዊ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ» የተባለለትንና ከፍጽምና በቀር ሌላ ምንም ግቡ ያልሆነውን የሕይወት እሳቤ መያዝ ቀላል አይደለም፡፡

ዓለም በመገናኛ ብዙኃኖቿ በሙሉ «ተደሰቱ፣ ቀለል አድርጋችሁ እዩት / take it easy/፣ ሰፊውን መንገድ ተከተሉ» ትለናለች፡፡ ክርስቶስ ደግሞ በወንጌል «ጠባቡን መንገድ ምረጡ፣ ተዋጉና መከራን ተቀበሉ፤ ይህ ወደ እውነተኛው ደስታ የሚያደርስ ብቸኛው መንገድ ነውና» ይለናል፡፡ ቤተክርስቲያን ካልረዳችን ካልደገፈችን እንዴት ያንን አስጨናቂ ምርጫ መምረጥ እንችላልን? እንዴትስ መጸጸት /ንስሐ መግባት/ እና በየዓመቱ በትንሣኤ በዓል ዕለት ወደሚሰጠው የከበረ ቃል ኪዳን መመለስ እንችላለን? የዐቢይ ጾም አስፈላጊነቱ እዚህ ላይ ነው ይህ በቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀልን ዕርዳታ፣ የትንሣኤ በዓልን የመብላት የመጠጣት እና የመዝናናት ፈቃድ የሚገኝበት ዕለት ነው ብለን ሳይሆን፣ በውስጣችን ያለው የአሮጌው መጨረሻ እና የእኛ ወደ አዲሱ መግቢያ አድርገን እንድንቀበለው የሚያስችለን የንስሐ ትምህርት ቤት ነው፡፡

በጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን የዐቢይ ጾም ዋና ዓላማ ንኡሰ ክርስቲያንን ማለትም አዳዲስ አማንያንን በዚያን ጊዜ በትንሣኤ ዕለት ለሚፈጸመው ጥምቀት ማዘጋጀት ነበር፡፡ ነገር ግን /ክርስትና ከተስፋፋና/ የሚጠመቁ ሰዎች ቁጥር ከቀነሰ በኋላም ግን ቢሆን የዐቢይ ጾም መሠረታዊ ትርጉም በዚያው ጸንቷል፡፡ ስለዚህም ትንሣኤ በየዓመቱ ወደ ጥምቀታችን መመለሻ ሲሆን ዐቢይ ጾም ደግሞ ለመመለስ መዘጋጃችን ነው፤ በክርስቶስ ወደሆነው አዲስ ሕይወት ለመተላለፍ የምናደርገው ትጋትና ጥረታችን ነው፡፡

ዐቢይ ጾም ጉዞ ነው፤ መንፈሳዊ ጉዞ ነው፡፡ ገና ስንጀምረው፣ በዐቢይ ጾም ብሩህ ሐዘን /bright sadness/ ውስጥ የመጀመሪያውን እርምጃ ስንራመድ ከር. . . ቀት ፍጻሜውን /መጨረሻውን/ እናያለን፡፡ ይህም የትንሣኤ በዓል ደስታ ነው፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ክብር መግባት ነው፡፡ የዐቢይ ጾምን ሐዘን ብሩህ የሚያደርገውና በወቅቱ የምናደርገውን ጥረት «መንፈሳዊ ምንጭ» የሚያደርገውም ይህ የትንሣኤ በዓል ቅምሻ የሆነው ብሩህ ርእይ ነው፡፡

ሌሊቱ ጨለማ እና ረጅም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በመንገዱ ሁሉ ምስጢራዊ የሆነ ብሩህ ወገግታ በአድማሱ ላይ ያንፀባርቃል፡፡
«ሰውን ወዳጅ /መፍቀሬ ሰብእ/ ሆይ! አቤቱ ተስፋ ያደረግነውን ነገር አታስቀርብን» አሜን፡፡

ምንጭ፡- [The Lent, Father Alexander Schemaman, St. vladmir’s Seminary Press,].

የክርስቲያን ፊደል- ኒቆዲሞስ

ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ የምስራቹን ቃል ሲያውጅ እስራኤላውያን የተቀበሉት በተደበላለቀ ስሜት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ሕዝቡ ለብዙ ዘመናት በባርነት ሲገዛ ስለነበር ከሮማውያን ቅኝ ግዛት ነጻ የሚያወጣቸው መሲህ ይፈልጋሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ለብዙ ዘመናት በባርነት ቀንበር ስለደከመ ተስፋ በመቁረጥ ተዳክሞ ነበር፡፡ መሲህ ቢመጣ እንኳ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ጦር ይዞ ሰራዊት አስከትሎ ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው ክርስቶስን መሲህ ነኝ ብሎ ሲመጣ ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጦር ሳይዝ ሰራዊት ሳያስከትል እንዲሁ ባዶ እጁን አርነት ላወጣችሁ መጥቻለሁ እያለ ደጋግሞ ተናግሯልና ነው፡፡ ምንም እንኳ አብዛኛው እስራኤላዊ የክርስቶስን መሲህነት ቢጠራጠርና ባይቀበለውም፣ በፍጹም እምነት እስከ መጨረሻው  የተከተሉትም  ነበሩ፡፡ ለዚህም  ትልቅ ማሳያ የሚሆነን ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አይሁዳዊ ነው፡፡ቅድስት ቤተክርስቲያንም ይህን  ታላቅ ሰው ለማዘከር የዐቢይን ጾም ሰባተኛ እሁድ በእርሱ ስም ሰይማ ታከብረዋለች ፡፡ ተከታዮቿ ምዕመናንም የእርሱን አሰረ ፍኖት እንዲከተሉ ትመክራለች ታስተምራለችም፡፡ 
ኒቆዲሞስ ማነው?

፩. ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ነው  ዮሐ 3-1

የእስራኤላዊያን ለብዙ ዘመን በባርነት መኖር የሕዝቡን የአኗኗር ሁኔታ ቀይሮታል፡፡በግዞት ጊዜ ከአሕዛብ የቀሰሟቸው አጉል ትምህርቶች በእምነትም በአስተሳሰብም እጅግ እንዲለያዩና እንዲራራቁ ምክንያት ሆኗል፡፡ አይሁዳዊ ሳምራዊ፤ ከአይሁድም ሰዱቃዊ ፣ ፈሪሳዊ ፣ ጸሐፍት ፣ ኤሴያዊ ብለው እንዲከፋፈሉ ከዚህም እጅግ ወርደው ገሊላዊ ናዝራዊ እንዲባባሉ ያበቃቸው ከአህዛብ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ፈር ባለማስያዛቸው ነበር፡፡ ፈሪሳዊያን ደግሞ ሕግን በማጥበቅ ሕዝቡን የሚያስመርሩ ቀሚሳቸውን በማስረዘም እነሱ የማይፈጽሙትን ሕግ በሕዝብ ላይ የሚጭኑ ራሳቸውን ከሌሎች በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርጉ አባታችን አብርሐም እያሉ የሚመጻደቁ የአባታቸው የአብርሐምን ስራ ግን የማይሰሩ ክፍሎች ናቸው ዮሐ 8-39፡፡ ታዲያ ኒቆዲሞስ ምንም እንኳ ከፈሪሳዊያን ወገን ቢሆንም ራሱን ከዚህ ሕዝብ ለይቶ ክርስቶስን ፍለጋ  በፍጹም ልቡ የመጣ ፈሪሳዊ ነው፡፡ ቀድሞ አባታችን አብርሀምን ከቤተሰብህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ ያለው አምላክ ኒቆዲሞስን ከፈሪሳዊያን ለይቶ ጠራው፡፡ ዘፍ 12

፪. ኒቆዲሞስ  የአይሁድ አለቃ ነው  ዮሐ 3-1

ሮማውያን ሕዝቡን የሚያሥተዳድሩት ከላይ ያለውን ዋና ሥልጣን ተቆናጠው ታች ያለውን ሕዝብ ደግሞ ባህላቸውን በሚያውቅ ቋንቋቸውን በሚጠነቅቅ አይሁዳዊ ምስለኔ ነው፡፡ አውሮፓውያንም አፍሪካን ለመቀራመት የተጠቀሙበት ስልት ይህን ዓይነት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስም ምንም እንኳ ፈሪሳዊ ቢሆን አለቃ እንዲሆን በሮማውያን የተሾመ ባለሥልጣን ነው፡፡

፫. ኒቆዲሞስ መምህረ እስራኤል ነው ዮሐ 3-10

ጌታ ምስጢረ ጥምቀትን በገለጸለት ጊዜ ሲደናገር አይቶ «አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን? » ብሎታል፡፡ ይህ የሚጠቁመን ኒቆዲሞስ አለቅነትን ከመምህርነት የያዘ በአይሁዳውያን የታፈረና የተከበረ ሰው እንደነበረ ነው፡፡ መምህር ቢሆንም የሚቀረኝ ያላወቅሁት ያልጠነቀቅሁት ብዙ ነገር አለ በማለት የመምህርነቱን ካባ አውልቆ የተማሪነትን ዳባ ለብሶ ከክርስቶስ ሊማር መጣ፡፡

፬. ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት ነው ዮሐ 7-51

አንዳንዴ ሳያውቁ አወቅን ሳይማሩ እናስተምር የሚሉ ደፋር መምህራን አይጠፉም፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ከዚህ በተለየ አለቅነትን ከመምህርነት መምህርነትን ከምሁርነት አስተባብሮ የያዘ ዕውቀትን ከትህትና ምሁርነትን ከደፋርነት አንድ አድርጎ የያዘ ሰው ነበር፡፡ የኦሪት ምሁር መሆኑን የሚጠቁመን ደግሞ ከካህናት አለቆች ጋር ያደረገውን ክርክር ባስታወስን ጊዜ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ ምን አደረገ?

ለምስጢረ ጥምቀት መገለጥ ምክንያት ሆነ ዮሐ 3 1-21

የአይሁድ የፋሲካ በዓል እየቀረበ ሲመጣ ክርስቶስ ቀኑ እንደደረሰ ለሐዋርያቱ ተናግሮ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡ እንደ ሰውነቱ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል ሕዝቡን ቀንና ሌሊት በትምህርትና በተዐምራት ያገለግል ነበር፡፡ በዚህ ሰዐት ነው ኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው፡፡ በፊቱ ቀርቦም «መምህር ሆይ » ብሎ የእርሱን አላዋቂነት የክርስቶስን ማእምረ ኅቡዐትነት (የተሰወረን አዋቂነት) መሰከረ፡፡ ጌታችንም አመጣጡ ከልብ መሆኑን አውቆ ምሥጢረ ጥምቀትን (ዳግም ውልደትን) ገለጸለት፡፡ ምስጢሩ የኦሪት ምሁር ለነበረው ኒቆዲሞስ ለጆሮ የከበደ ለመቀበል የሚቸግር ሆነበት፡፡ የከበደውን የሚያቀል የጠበበውን የሚያሰፋ አምላክ ምሥጢሩ ለኒቆዲሞስ  እንደከበደው ስለተረዳ ቀለል አደረገለት፡፡ ዳግም ውልደት ከእናት ማኅፀን ሳይሆን ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ አብራራለት ፡፡

አዋቂ ነን የሚሉትን አሳፈራቸው ዮሐ 7-51

ወቅቱ የአይሁድ የፋሲካ በዓል የቀረበበት ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ እንደሙሴም ህግ ሊያስፈርዱበት የቋመጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን መቸ አወቁና? የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ በሚመካከሩ ጊዜ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው እሱ ነበር፡፡በዚህም የተነሳ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የሆነ ታላቅ ሰው ነው፡፡

ጌታን ለመገነዝ በቃ ዮሐ 19-38

ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ እስከ ሞት ከአንተ አንለይህም ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ሲበታተኑ ፣ከዮሐንስ በቀር ፣በዘጠኝ ሰዐት ቀራንዮ የነበረ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ሆኖ የክርስቶስን  ስጋ ከአለቆች ለምኖ፣ የገነዘ፣የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ከርቤና የእሬት ቅልቅል ያርከፈከፈለት ወደ ሐዲስ መቃብር ያወረደውም ኒቆዲሞስ ነበር፡፡

ከኒቆዲሞስ ምን እንማር?

አትኅቶ ርእስ

በቅዱስ ወንጌል ላይ በተደጋጋሚ የምናገኘው የፈሪሳውያንን ግብዝነትና የጌታችንን ተግሳጽ ነው፡፡ ማቴ 9 10፣ ማቴ 23፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነን የፈሪሳዊውና የቀራጩ ጸሎት ምን ይመስል እንደነበር መመልከት ነው ሉቃ 18 9፡፡ ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፣ የአይሁድ አለቃ ፣መምህረ እስራኤል ፣ምሁረ ኦሪት ቢሆንም ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታ እግር ስር ቁጭ አለ፡፡ ሕዝብን ከመምራትና ከማስተማር ይልቅ ቁጭ ብሎ መማር ምንኛ መታደል ነው! ጌታስ በትምህርቱ «ማርያምም  መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርሷም አይወሰድባትም » ያለ ለዚህ አይደል ሉቃ 10 42፡፡ ብዙዎቻችን ባለን የኑሮ ደረጃ የዕውቀት ደረጃ የስልጣን ደረጃ ራሳችን ሰቅለን የመማር አቅም አጥተናል፡፡ ቁጭ ብሎ መማር ደረጃችንን የማይመጥን የሚመስለንስ ስንቶች እንሆን? አንድ ወቅት አባ መቃርስ ከህጻናት እንቆቅልሽ ለመማር ቁጭ እንዳሉ በእንቆቅልሹም ልባቸው ተነክቶ እያነቡ ወደ በዐታቸው መመለሳቸውን እያወቅን የመማር አቅም ያጣን ስንቶች እንሆን? ማን ያውቃል ከአንድ ሰአት ስብከት ውስጥ እግዚአብሔር ሊያስተመረን የፈለገ አንዲት ዐረፍተ ነገር ቢሆንስ? ትሑት የሚያሰኘው ሳያውቁ አላውቅም ማለት ሳይሆን እያወቁ አላውቅም ማለት ነው፡፡ ሳይማሩ ተምሬያለሁ ማለት ሳይሆን ተምረውም ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ለመማር ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡

ጎደሎን ማወቅ

መምህርም ምሁርም ሆኖ ቁጭ ብሎ መማር ምን ረብ አለው? ይባል ይሆናል፡፡ ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት እንጅ ምሁረ ሐዲስ አይደለም ኒቆዲሞስ መምህረ እስራኤል ዘስጋ እንጅ መምህረ እስራኤል ዘነፍስ አይደለም፡ ክርስትና አለቃና ባሪያን አንድ እንደምታደርግ አያውቅምና የጎደለውን ፍለጋ መጣ ገላ 3 26፡፡ ያለውን ሳይሆን ያጣውን የሞላለትን ሳይሆን የጎደለውን ፍለጋ መጣ፡፡ዕውቀት ብቻውን ምሉእ አያደርግም፡፡ አለቅነትም ቢሆን ገደብ አለው፡፡የሕይወቱን ክፍተት ሊሞላ የሚችል አንድ ክርስቶስ ብቻ ነውና ጎደሎነቱን አምኖ መጣ፡፡ የሚጎድለኝ ምንድን ነው? ብሎ እንደጠየቀው እንደዚያ  ሰው ጎደሎን ማመን ምንኛ ታላቅ ነገር ነው ማቴ 18 21፡፡ በአብዛኞቻችን የሚታየውና ክርስትናችንን አገልግሎታችንን ቤተክርስትያናችንን እየተፈታተነ ያለ ችግር ጎደሎዎቻችንን አለማወቅና ምሉእ ነኝ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ምንም  እንዳልሆኑ አውቆ ራስን ለክርስቶስ፣ ራስን ለመርዐተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አሳልፎ መስጠት ምንኛ መታደል ነው!

አልዕሎ ልቡና (ልቡናንን ከፍ ማድረግ)

ኒቆዲሞስ ይዞ የመጣው ስጋዊ ህዋሳቱን ነበር፡፡ጌታችን ግን አመጣጡ ለመልካም እንደሆነ አውቆ ለስጋዊ ዕውቀት እጅግ የሚከብደውን ምስጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ መጀመሪያ ይህን ምስጢር ለመቀበል አልተቻለውም ነበር፡፡ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ምስጢሩን ፍንትው አድርጎ ሲያብራራለት ግን ልቡናው ይህን ምስጢር ለመቀበል ከፍ ከፍ አለ፡፡ ምስጢራትን ለመቀበል ልቦናን ከፍ ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡የእምነታች መሰረት በስጋ ዓይን ማየት በስጋ ጆሮ መስማት በስጋ እጅ መዳሰስ ብቻ ከሆነ ልክ እንደ እንቦይ ካብ ሆነ ማለት ነው፡፡ ትንሽ ነፋስ ትንሽ ተፅዕኖ ሲያርፍበት መፈራረስ መናድ ይጀምራል፡፡ ኒቆዲሞስም ምስጢሩ መጀመሪያ ቢከብደውም ቅሉ በኋላ ላይ  ልቦናውን ወደ ሰማያዊው ምስጢር ከፍ ስላደረገ ምስጢሩ ተገለጸለት፡፡ ቤተክርስቲያንን ሲፈታተኗትና እየተፈታተኗት ያሉ አካላት በሙሉ የስህተታቸው ምንጭ እንደ ግያዝ ከአካባቢያቸውና ከምናየው አካል (ቁሳዊ ዓለም) ውጭ መመልከት አለመቻል ነው 2ነገ 6- 17፡፡ ለዚህም ነው ካህኑ በስርዓተ ቅዳሴ ጊዜ የቁርባኑ ምስጢር እንዲገለጽልን «አልዕሉ አልባቢክሙ (ልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ)» የሚሉን፡፡

የእውነት ምስክር (ስምዐ ጽድቅ) መሆን

ኒቆዲሞስ ያለፍርሐትና ያለ ሃፍረት በካህናቱ ፊት እውነትን መስክሯል፡፡እውነትንና ፀሐይን ፈርቶ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ካህናቱን መጽሐፍ ጠቅሶ እውነትን ተናግሮ አሳፍሯቸዋል፡፡ በመሪዎች ፊት በታላላቅ ሰዎች ፊት እውነትን መመስከር ክርስትናችን የሚያስገድደን ቁም ነገር ነው ሉቃ 12 8፡፡ ቤተክርስቲያን ሰማዕታት እያለች የምትዘክራቸው በሙሉ ለእውነት ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አሳልፈው የሰጡ ቅዱሳንን ነው፡፡በፍርሐትና በሀፍረት በይሉኝታና በሀዘኔታ እውነትን አለመመስከር በክርስቶስ ፊት ያስጠይቃል እንጅ አያስመሰግንም ማቴ 10 32፡፡ «ለእውነት እንጅ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልም» እንዳለ 2ቆር 13 8፡፡

ትግሃ ሌሊት

እንደ ሌሊት ለመንፈሳዊ ህሊና ለተመስጦ የሚመች ጊዜ የለም ፡፡ ቀን ለስጋ ሲራወጥ የነበረ አካልና መንፈስ ሌሊቱን ለነፍስ በምገዛት ስጋውን መጎሰም አለበት፡፡ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተክርስቲያን ቀኑን በቅዳሴ ሌሊቱን ደግሞ በማኅሌት በሰዓታት በኪዳን እግዚአብሔርን ስታምሰግን  የምታድረው፡፡ ቅዱስ ማር ይስሐቅ ሌሊትስ ጌታን ለማመስገን የተፈጠረ ድንቅ ጊዜ ነው ያለው፡፡ ጌታችንም ሐዋርያቱን ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ ብሏቸዋል ማቴ 26፡፡ አሁንም ቤተክርስቲያን እንደ ኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ለኪዳን ለማኅሌት ለጸሎት የሚመጣን ምዕመን ትፈልጋለች፡፡

እስከ መጨረሻ መጽናት

ጌታችንን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ሺህ ሕዝብ ቢከተለውም እስከመስቀሉ አብረውት የነበሩ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የተወሰነው ሕዝብ ቀድሞም የተከተለው ለምግበ ስጋ ነበርና ቀራንዮ ላይ አልተገኘም፡፡ ቀራንዮ ላይ ምግበ ነፍስ እንጅ ምግበ ስጋ የለም፡፡ ሌሎችም በቤተሰብ በሀብት በፍርሀት ምክንያትነት መስቀሉ ስር አልተገኙም፡፡ ምንም እንኳ ኒቆዲሞስ በስድስት ሰዐት ባይገኝም  የክርስቶስ ስጋ ከነፍሱ በምትለይበት ሰዐት ክርስቶስን ከመስቀል አውርዶ ለሐዲስ መቃብር ያበቃው እሱ ነበር፡፡ በዚህ የመከራ ሰዐት ከዮሐንስና ከእናቱ ከድንግል ማርያም ውጭ ማንም እንዳልነበረ መጻሕፍት ከገለጹልን በኋላ የምናገኛቸው የቁርጥ ቀን ልጆች ዮሴፍንና ኒቆዲሞስን ነው፡፡ ይህም ፈተናውን ሁሉ ተቋቁሞ እስከ መጨረሻው ለመጽናቱ ምስክር ነው፡፡ በክርስትና ሕይወታችንም የምናያቸው ነገሮች ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡፡በምቹ ጊዜ የምናገለግል ፈተና ሲመጣ ጨርቃችን(አገልግሎታችንን) ጥለን የምንሮጥ ማር 14-51 ሰበብ አስባብ ፈልገን የምናፈገፍግ ብዙዎች ነን፡፡ ዕውቀት ጣዖት ሆኖበት መሀል መንገድ የቀረው ሀብት ጣዖት ሆኖበት ሩጫ ያቋረጠውን ጊዜ ጣዖት ሆኖበት ቅዳሴ የሚቀረውን ቆጥረን እንጨርሰው ይሆን? ጌታ በትምህርቱ «ለዘአዝለፈ ትዕግስቶ ውእቱ ይድኅን -እስከ መጨረሻው የሚፀና እርሱ ይድናል » እንዳለ ማቴ 2413፡፡ ክርስትና ለጀመሩት ሳይሆን ለጨረሱት ለወጠኑት ሳይሆን ለፈጸሙት የድል አክሊል የምትሰጥ መንገድ እንጅ የመሮጫ መሙን ጠበበን ሩጫው ረዘመብን ለሚሉ ዴማሶች ቦታ የላትም፡፡2ጢሞ 4-9

በአጠቃላይ ከኒቆዲሞስ ህይወት ብዙ ቁምነገሮችን እንማራለን፡፡ የኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ መምጣት ለምስጢረ ጥምቀት ትምህርት መገለጥ ምክንያት እንደሆነ ሁሉ በቅዳሴው በኪዳኑ በሰዓታቱ በማኅሌቱ መገኘትና መሳተፍ ረቂቅ የሆነው ሰማያዊ ምሥጢር ፍንትው ብሎ አንዲገለጥልን ምክንያት ነውና በምሥጢራት በመሳተፍ ራስን ዝቅ በማድረግ ለታላቅ ክብር እንድንበቃ የእርሱ መልካም ፈቃድ ይሁንልን፡፡    

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ገብርሔር

በዲ/ን አባተ አስፋ
ዛሬ ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተክርስቲያን «ገብርሔር» የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ገብርሔር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ.25-14-30 ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መሀከል አንዱ የሆነው ይህ የዛሬው ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ሓላፊነት የእገሌና የእገሊት ተበሎ ባይወሰንም ቅሉ ቤተክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የሓላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ አሳቦችን በአትኩሮት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡

በምሳሌያዊው ታሪክ መጀመሪያ ላይ የምናገኘው አንድ መንገድ ሊጀምር ያሰበ ሰው ከመሔዱ በፊት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደሰጣቸው ነው፡፡

ገና ከታሪኩ መጀመሪያ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ምንም እንኳን እርሱ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ በዚህም አገልጋዮቹን ጠርቶ ገንዘቡን በአደራ ተቀብለው «እንዲያተርፉበት» ማዘዙን እንደማስረጃ ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ማትረፍ በመፈለጉ ብቻ ገንዘቡን ያለአግባብ አልበተነም፡፡ ነገር ግን ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ ያውም እንደየችሎታቸው መጠን ሓላፊነቱ ሳይከብዳቸው እንዲሠሩበት ገንዘቡን አከፋፈላቸው፡፡

ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደሆነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ሓላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት ይችላል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ሓላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት ሁለት አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡

ምናልባት ስስት ባልተላቀቀው ስሜት ለሚያስብ ሰው የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለው ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የሚያሳየን የባለ መክሊቱን ባለቤት ቅንነት ነው፡፡ ቀጥለን እንደምናነበው ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ አትርፉበት ብሎ መክሊቱን ሰጥቷቸው በሔደበት ሀገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው እንደመጣ እናነባለን፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መክሊትን በመስጠት ምን ሠርተው የተሰጣቸውን መክሊት ያህል ማትረፍ እንደሚችሉ በማሰብ እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናየው ያለምንም ጭንቀት ከአእምሯቸው በላይ ሳይሆን ባላቸው ኃይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደሰጣቸው ነው፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት እንዲሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፎ ጌታቸው ፊት እንደቆሙ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታው እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው ምድርን ቆፍሮ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት እንደቀበረ ከዚህም አልፎ ምን አደረክባት ተብሎ ሲጠየቅ የአመጽ ንግግር እንደተናገረ በዚህ ከፊቱ ያዘነው ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው አናነባለን፡፡

በዚህኛው ክፍል ከተጠቀሰው ታሪክ ሦስቱን አካላት ማለት የመክሊቱን ሰጪ ጌታ፣ በጎ የተባሉ አገልጋዮችና ክፉ እና ሰነፍ የተባለውን አገልጋይ በተናጥል እንመልከታቸው፡፡

1. የአገልጋዮቹ ጌታ፡-

ይህ ሰው ለገንዘቡ ጠንቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በአገልጋዮቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው እናያለን፡፡ በክፉው አገልጋይ ላይ ባለመታዘዙ ምክንያት የፈረደበትን ፍርድ /ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት በውጪ ወዳለ ጨለማ አውጡት/ ስንመለከት የሚያሳየን የአገልጋዮቹን ጌታ ታላቅ ሥልጣን ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥልጣኑ ጽኑ ቢሆንም ይህ ጌታ ፍርዱ ግን በእውነት ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ደግሞ በድካማቸው ታግዘው በተሰጣቸው መክሊት ላተረፉት በጎ አገልጋዮች የሰጣቸውን ፍጹም ደስታ መጥቀስ ይቻላል፡፡

2. በጎ አገልጋዮች:-

በአገልጋዮቹ ጌታ በጎ አገልጋዮች የተባሉት አምስት መክሊት የተቀበለውና ሁለት መክሊት የተቀበለው ናቸው፡፡ እዚህ ጋር ማስተዋል የሚገባው እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች በጎ አገልጋዮች ለመባል ያበቃቸው አስቀድመው ብዙ ወይንም የተሻለ ቁጥር ያለው መክሊት ለመቀበል መብቃታቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የመክሊቱ ቁጥር ሳይሆን በተሰጣቸው መክሊት መጠን የሚገባቸውን ያህል ደክመው ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡ ወይንም ያ ባለ አንድ መክሊት አገልጋይ ከሁለቱ ያሳነሰው ከአንድ በላይ መክሊት መቀበል የማይችል መሆኑ ሳይሆን በዚያችው በአንዷ መክሊት እንኳን መሥራት አለመቻሉ ነው፡፡

3. ክፉና ሰነፍ አገልጋይ:-

ይህ ሰው የተጠቀሱ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡

ሀ. የአገልጋዮቹ ጌታ ወደ መንገድ ሊሔድ በተዘጋጀበት ወቅት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደችሎታቸው ገንዘቡን ሲሰጣቸው አትርፈው እንዲቆዩት ነው፡፡ ከላይ እንደተነገጋገርነው እንደ አቅማቸው መስጠቱም አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ ደረጃ እንዲሰማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰነፍ አገልጋይ ግን ያደረገው ከታዘዘበት ዓላማ በተቃራኒው መልኩ ነው፡፡ ሊሠራበት የሚገባውን መክሊት ቀበረው፡፡ ይህም ለጌታው ትዕዛዝ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል፡፡

ለ. ጌታው በመጣ ጊዜ አመጽ የተመላበት የሐሰት ንግግር ተናግሯል፡- ከሔደበት ቦታ ተመልሶ ጌታው በተሰጠው መክሊት ምን እንዳደረገ ሲጠይቀው «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ ስለፈራሁም ሔድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፡፡» ሲል መለሰለት፡፡ ይህ ንግግር ከአመጽ ንግግርነቱ በተጨማሪ ውሸት አለበት፡፡ ምክንያቱም እርሱ እንዳለው ጌታው ካልዘራበት የሚያጭድ ካልበተነበት የሚሰበሰብ ጨካኝ ሰው ቢሆን ኖሮ ያደርግ የነበረው ምንም መክሊት ሳይሰጠው ከነትርፉ ሁለት መክሊቶችን ይጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጽፎ የምናነበው ትርፉን ከመጠየቅ በፊት አንድ መክሊት ሰጥቶት እንደበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስቀድሞ ገንዘቡን ዘርቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጌታ ዘርቷልና ማጨድ ይገባዋል፤ በትኗልና መሰብሰብም መብቱ ነው፡፡

ሐ. እርሱ መሥራት ሲሳነው እንኳን ዕድሉን ለሌሎች አልሰጠም፡- ይህ ሰው የተሰጠው መክሊት በትርፍ ሊመለስ እንደሚገባው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ገና ሲቀበል ከጌታው የተቀበለው ትዕዛዝ ነውና፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን መውጣት መውረዱ ቢከብደውም ወጥተው ወርደው ማትረፍ ለሚችሉ ሰዎች አለመስጠቱ ተጨማሪ ጥፋቱ ነው፡፡ ይህን እንዳያደርግ ያሰረው ደግሞ ውስጡ የተቀረጸው የአመጽ መንፈስ ነው፡፡ ጌታው መጥቶ ስለ ትርፉ ሲጠይቀው የሚመልስለትን ረብ የለሽ ምክንያት እንደ መከላከያ አድርጎ ማሰቡ አእምሮው ሌላ አማራጭ እንዳያስብ የዘጋበት ይመስላል፡፡

የመጽሐፈ ቅዱስ መተርጉማን አባቶች የዚህን ምሳሌያዊ ታሪክ ምስጢር ሲያስተምሩ የአገልጋዮቹ ጌታ የፍጡራን ጌታ የሆነ የእግዚአብሔር ምሳሌ እንደሆነ እንዲሁም ሦስቱ አገልጋዮች በተለያየ ደረጃ ያሉ ምዕመናንን እንደሚወክሉ ያስተምራሉ፡፡

ከዚህ የወንጌል ክፍል ምን እንማራለን?

ከተጠቀሰው ታሪክ የምንማራቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም አበይት የሆኑትን ሁለቱን እንመልከታቸው፡፡

1. ለእያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ እንዳለ እንረዳበታለን

እግዚአብሔር እያንዳንዳችን በሃይማኖት ሆነን የምናፈራውን ፍሬ ይፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ከእኛ ፍሬን ቢፈልግም ያን ፍሬ ማፍራት የምንችልበትን ኃይል ግን የእግዚአብሔርን ልጅነት ካገኘንበት ከዕለተ ጥምቀት ጀምሮ እንደሚያስፈልገን መጠን እየሰጠን ነው፡፡

ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበልናቸው ስጦታዎች በቁጥር እጅግ ብዙ ቢሆኑም በአይነታቸው ግን ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው እያንዳንዱ ክርስቲያን ዳግመኛ በመወለድ ምስጢር ያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት ጸጋና ከልጅነት ጋር በተያያዘ የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው ፡፡ዮሐ.3-3 ሁለተኛው አይነት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደ ሰውየው አቅም ለተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ማስፈፀሚያ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ትንቢት መናገር ፣ በተለያዩ ልሳናት መናገር ፣ አጋንንትን ማስወጣት … የመሳሰሉት ከዚህኛው አይነት ስጦታ የሚመደቡ ናቸው፡፡ 1ኛ ቆሮ.12-4፡፡

በመጀመሪያውም ይሁን በሁለተኛው አይነት ስጦታ ተቀባዮች ዘንድ ግን ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች አሉ፡፡ በዳግመኛ መወለድ ምሥጢር (በ40 ና 80 ቀን ጥምቀት) ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ ጊዜ ሰጥቶ የሚያስብ ክርስቲያን ማግኘት በዚህ ዘመን በጣም አዳጋች ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ክርስቲያንነቱ ለጥምቀት በዓልና ለመስቀል ደመራ ካልሆነ ትዝ የማይለው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከቤተ ዘመድ አንድ ሰው ምናልባትም ራሱም ሊሆን ይችላል ነፍሱ ከሥጋው ካልተለየች ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ብቅ አይልም፡፡

እግዚአብሔር ለእኛ የልጅነትን ጸጋ በመስጠቱ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅሩን አሳይቶናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችን ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ እንዲሁ በቀላሉ አይደለም ልጆች የተባልነው፡፡ እኛ ልጅነትን እንድንቀበል አምላክ መከራን ተቀብሏል፡፡ የጥምቀታችን ውሃ የፈሰሰው በጦር ከተወጋው ከጌታ ጎን ነው ፡፡ ዮሐ.19-24፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይሄንን ሁሉ ሲያመለክት ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፡፡›› 1ኛ ዮሐ.3-1 ያለው፡፡

እኛ ልጆቹ እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር ካሳየን የአባትነት ፍቅር በተጨማሪ ልጆቹ ስለመሆናችን የገባልንም ተስፋ ከአዕምሮ በላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምዕመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፡፡ ልጆች ከሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፡፡›› ገላ.4-7 ስለሚጠብቀን ተስፋ ነግሮናል፡፡

ትልቁ ችግር ግን ተጠማቂው ሰው ይህን የልጅነት ክብር አለመረዳቱ ነው፡፡ የልጅነቴን ክብር ተረድቻለሁ እያለ የሚያወራውም ቢሆን የልጅነቱን መክሊት በልቡናው ውስጥ ቀብሮ አንድም ፍሬ ሳያፈራ ስለማንነቱ ለማውራት ቃላት ሲመርጥ ጊዜውን ያባክናል፡፡ አብዛኛው ግን የክርስትና እምነት ደጋፊ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነት ሊገለጥ የሚገባው እንደ ሀገር ልጅነታችን በምናሳየው የደጋፊነት /የቲፎዞነት/ ስሜት አይደለም፡፡ ደጋፊነት በጊዜ ና በቦታ ለተወሰነ ያውም ኃላፊ ለሆነ ድርጊት ነው፡፡ ክርስትና ግን በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜ የሚኖርበት የህይወት መስመር እንጂ የሚደገፍ ጊዜያዊ ድርጊት አይደለም፡፡

ስለዚህ በጣም ልንጠነቀቅበት የሚገባን የመጀመሪያው መክሊታችን ልጅነታችን መሆኑን መረዳት ያስፈልገናል፡፡በዚህም መክሊት እንድንሰራ የታዘዝናቸውን ምግባራት እንድናፈራ የሚጠበቅብንን ፍሬዎች ማፍራት አለብን፡፡ ያለበለዚያ መክሊቱን እንደቀበረው ሰው መሆናችን ነው፡፡

2. እያንዳንዱ ስጦታ እንደሚያስጠይቅ እንረዳለን

እግዚአብሔር ያለ አንድ አላማ ለሰዎች ኃላፊነትን የሚያሰከትል ስጦታ አልሰጠም አይሰጥምም፡፡ ማንም ከእግዚአብሔር የተቀበለ ሰው የተሰጠው ስጦታ ለሆነ አላማ ነውና ጥያቄ አለበት፡፡ ጠያቂው ደግሞ የስጦታው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

መንጋውን እንዲጠብቁለት ሥልጣንና የተለያዩ የአገልግሎት ሰጦታዎችን እግዚአብሔር የሰጣቸው አሉ፡፡ዮሐ. 21-15 ፤ ገላ.1-15-16፡፡ ሆኖም ግን የተሰጣቸው ኃላፊነት የሚያስጨንቃቸው፣ ከልባቸው በእውነተኛ ትህትና የሚተጉ ያሉትን ያህል የሚያገለግሉበትን ስጦታ ከእግዚአብሔር መቀበላቸውን እንዲሁም የሚያስጠይቃቸው መሆኑን እስኪዘነጉ ድረስ መንገዳቸውን የሳቱ አሉ፡፡ በእግዚአብሔርና በሰዎች መሀከል እንደ ድልድይ ሆነው ያገለግሉበት ዘንድ በተሰጣቸው ሥልጣን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር የሚፈፅሙ ሰዎች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

እንዲሁም ደግሞ ተሰባኪውን ወደ እግዚአብሔር ከመምራት ይልቅ የነሱ ደጋፊ፣ ስለክብራቸው ተሟጋች እንዲሆን በህዝቡ መሀከል ጎራ እንዲፈጥርና የጳውሎስ ነኝ የአጵሎስ ነኝ እንዲል የሚያደርጉት ሰባኪዎችም ሌሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ማንም ይሁን ማን ግን ስለተሰጠው መክሊት ባለቤቱ ከፊቱ አቁሞ እንደሚጠይቀው መዘንጋት የለበትም፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

«ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ ( የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች ናት)»፡፡

የንግግርና ሥነ ጽሕፈት ሙያን የተካኑ ምሁራን በትምህርት ጌጣቸው እንደሚሉት «ውሃን ከጥሩው ሲቀዱት፣ ነገርን ከሥሩ ሲያመጡት» ውሃው ጠጭውን፣ ነገሩም ሰሚውን ያረካዋል፡፡ በዚህ እውነተኛ ሃይማኖትን ከጊዜው ስመ መሳይ ኑፋቄና የለየለት ክሕደት ለይቶ በሚያሳይ ትምህርታችን «አበዊነ = አባቶቻችን» ያልናቸው እነማን እንደሆኑ በጥቅል ማመልከት እንወዳለን፡፡ የቃሉን ዐይነ ምስጢር ቁልጭ አድርጎ ለመግለጽ ያህል አባትነት መልክና ይዘቱ፣ ግብርና ዐይነቱ በጣሙን ብዙ ነው፡፡ ይሁንና እዚህ ላይ «የቀናች፣ የጸናች ሃይማኖት» ባለቤቶች ብለን በትምህርታችን ርእስ በመሪነት ያነሣናቸው፡፡

– ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኅ በደብር ቅዱስ የነበሩ አርእስተ አበውን፣
– ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የነበሩትን የእግዚአብሔር ሰዎች፣
– አዕይንተ አርጋብ ዐበይት ደቂቅ ነቢያትን፣

ይልቁንም «አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው = አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ» ከማለታቸው አስከትለው «እግዚኦ ኀበ መኑ ነሐውር እንዘ ቃለ ሕይወት ዘለዓለም ብከ፣ ወንሕነሰ አመነ፣ ወአእመርነ፣ ከመ አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልዱ ለእግዚአብሔር ሕያው = አቤቱ! የዘለዓለም ደኅንነት የሚገኝበት ትምህርት ከአንተ ዘንድ እያለ ወደማን እንሔዳለን? እኛስ የሕያው እግዚአብሔር ልጁ ክርስቶስ እንደሆንህ ዐውቀን አምነናል» ማቴ.16-16፣ ዮሐ. 6-68-70 ብለው መስክረው ሲያበቁ ሃይማኖትን አብርተው ያረጋገጡ፣ ሁለንተናቸው በደመ እግዚእነ ኢየሱስ ክርሰቶስ ተኮልቶ የበራ፣ የጠራ ጽሩያነ አዕንይት የትምህርት፣ የሃይማኖት፣ የክህነት አባቶቻችን የሆኑ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው የተሟሟቁ ቅዱሳን ሐዋርያትን ነው፡፡

ደግሞም የእነርሱን ዓላማና ግብር የተከተሉ ሰብአ አርድዕትና ምሉአነ አእምሮ ሠለስቱ ምእት ሊቃውንትን፣ ተጋዳልያን ሰማዕታትና ጻድቃን፣ ቅዱሳን ማለታችን ነው፣ እንጂ የመጀመሪያው የወንድሙ ነፍሰ ገዳይ የቃኤል ልጆችን ሁሉ አደባልቀን፣ ነገርን ከነገር አጣልፈን፤ ምስጢሩንም ደብቀን፣ ከሐድያን፣ ጣዖት አምላኪዎች መስሕታንን ቀደምት አበው ከሆኑ ብለን ሳናስተውል በጅምላው አይደልም፡፡ ስለይህ የእነዚህን ቅዱሳን = የተለዩ አበው የቀናች፣ የጸናች ሃይማኖት የሆነችው «ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ = የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች የጸናች ናት፡፡» በዚች መሠረትነት ለሁለት ሺኽ ዘመናት እምነቷ፣ ሥርዐቷ፣ ባህሏ ተጠብቆ ለሕዝበ ክርስቲያን የሚገባውን መንፈሳዊና ሐዋርያዊ፣ ማኅበራዊም አገልግሎት ስታቀርብ የኖረች ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ብሔራዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የገጠሙአትን ችግሮች፣ ፈተናዎች በታላቅ ትዕግሥት፣ በጾምና በጸሎት፤ በመንፈሳዊ ጥበብ የማለፍ ልምድና ዕውቀቷ በዓለም የተመሰከረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአለንበት ጊዜ እምነቷን፣ ሕጓንና ሥርዐቷን ለማፋለስ በግልና በቡድን የተነሣሡ የእምነት ተቀናቃኞች በየአቅጣጫው በመዝመት ላይ መሆናቸው ለሕዝበ ክርስቲያን ግልጽ እየሆነ መጥቷል፤ አሁንም የበለጠ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የመናፍቃንና የሃይማኖት ለዋጮች እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያልተለመደና እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ቀድሞ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ ምክንያቱም አዝማቹ ጠላት በሞተ ሥጋ የማያርፍ ዲያብሎስ እንደሆነ በብሩህ ልቡና ይታወቃል፡፡ በመልካም እርሻ /ማሳ/ የተዘራው ንጹሕ ስንዴና ጠላት ጨለማ ለብሶ በስንዴው ማሳ ላይ የበተነው እንክርዳድ እስከ መኸር ጊዜ ዐብረው እንደሚኖሩ ጌታችን ራሱ ባለቤቱ በቅዱስ ወንጌል አስተምሮናል ማቴ. 13-24 – 31 ይህ የማይሻር ቃል ስለሆነ ሌላ ምን ይባላል? ዐይነ ኅሊናችንን ወደ ቀደመው ታሪክ ስናቀና በአበው ሐዋርያት ዘመንም በመልካም እርሻ ላይ በብርሃን የተዘራውን ጥሩ ዘር፣ ለማበላሸት የጥፋት ዘር በጨለማ የሚበትኑ ቢጽ ሐሳውያንና መናፍቃን ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩና ሲያምሱ ኖረዋል፡፡

በቀና ሃይማኖት ስምና ጥላ ተሸፍነው ትክክለኛውን እምነትና መሠረት ለማፋለስ ከማሴርም ዐልፈው ራሳቸውን በአማልክት ደረጃ በማስቀመጥ ሰዎችን ወደ ጥፋት በሚያደርስ መንገድ ለመምራት የቃጣቸው ብዙዎች ነበሩ፡፡ ዳሩ ግን ሁሉም እንደገለባ እሳት ብልጭ እያሉ ጠፍተዋል፡፡ በዓለም ላይ የበተኑት የጥፋት ዘር ግን ክሕደት የሚያብብበት ካፊያ ባካፋ ቁጥር በምንጭ ላይ እንደወደቀ ዘር በፍጥነት ይበቅላል፡፡ የእውነት ፀሐይ ስትወጣ ደግሞ መልሶ ይጠወልጋል፡፡ እንደነ ይሁዳ ዘገሊላ፣ እንደነ ቴዎዳስ ዘግብጽ የመሳሰሉት ከብዙዎች በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ «ቴዎዳስ ዘግብጽ» አምላክ ነኝ ብሎ ተነሥቶ እሰከ አራት መቶ የሚደርሱ ተከታዮች አፍርቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ አልተጓዙም እርሱም፣ ተከታዮችም ፀሐየ ጽድቅ ሲወጣ እንደሚጠወልገው ሣር ፈጥነው ጠፍተዋል፡፡ ይሁዳ ዘገሊላም እንደዚሁ ነው፡፡ አልቆየም፤ ጠፍቷል፡፡ /ግ.ሐ. 5-37/

ጥንታዊት ሐዋርያዊት ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያናችንን ለመበታተን የሚጥሩት ሁሉ መሠረቷ በክርስቶስ ደም የጸናውንና በቅዱሳን አባቶቻችን ዐፅም የታጠረችውን ቤተ ክርስቲያን ሲገፏትና ሲነቀንቋት ፈተናውን በትዕግሥት በማስተዋልና በትምህርት በመከላከል ትቋቋመዋለች፡፡ ይህ የብዙ ዘመን ልማዷ ነው፡፡ መቼውንም ቢሆን ግራ አያጋባትም፡፡

አባቶቻችን ያቆዩን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ጥንታዊት የቀናች፣ የጠራች፣ ስለሆነች ተካታዮቿን የምታኮራ እንጂ የምታሳፍር አይደለችም፡፡… በሰዎች የግል ድካም እንጻርም አትመዘንም፡፡ ለመከራም አትበገርም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ዛሬ ድረስ በእምነቷ፣ በጾሟና በጸሎቷ የማያቋርጥ የገቢረ ተአምራት ወመንክራት፣ ኀይላትም ሥራ ስትሠራ የምትገኝ ለተከታዮቿ ተስፋ ሆና የምትኖር እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ርግጥ ነው፤ በቅን ልቡናና በትሑት ሰብእና ለተቀበለው ሸክሟ ቀላል ቀንበሯ ልዝብ ነው፡፡ ዳሩ ግን በገድል የተቀመመ ሕጓ፣ ባህሏና ሥርዐቷ ጥብቅ ስለሆነ የሕግና የሥርዐት ቀንበር ላለመደ ስስ ጫንቃ አይመችም፡፡ መንገዱ ቀጭን፣ በሯ ጠባብ ነው፡፡ የእግዚአብሔርም መንግሥት የምትወርሰው በመከራ መስቀልና ብዙ ትዕግሥት፣ በዚሁ ቀጭን መንገድ ተጉዞና በጠባቡ በር ዐልፎ ስለሆነ በቀና ሃይማኖት ጸንቶ፣ በጾም በጸሎት ተወስኖ ሕይወቱን = አኗኗሩን በሥነ ምግባር፣ ገዝቶ በአበው፣ መንፈሳዊ መንገድ መጓዝ ለክርስቲያን አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ ማቴ. 7-13-05 የሐዋ.14-22 ይህ ጠባብ በርና ቀጭን መንገድ የሃሪካችን መዛባት የለበትም፡፡ ተቆርቋሪዎች እንሁን፡፡ የወይራ ዛፍ ተቀጥላው ብሳና ቢሆን እጅግ ያሳፍራልና፡፡ በነገረ ጠቢባን «ሳይረቱ አይበረቱ» ተብሏልና፡፡

ለመሆኑስ አባቶቻችን ታቦት ተሸክመው እየዘመቱ ከጾም ጸሎታቸው ጋር በተጋድሎ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው በአቆዩአት ኢትዮጵያ ሀገራችን ነጻነታችንን ማን ይነካብናል ብለን እንሰጋለን? ሕግ አክባሪነትና ወሰን የሌለው ትዕግሥታችን ካልሆነ በስተቀር ለመሥዋትነቱ ከቶ የእነማን ልጆች እንደሆን ሊዘነጋ አይገባምና በአካልም በመንፈስም ስለ ሃይማኖታችን እንበርታ፡፡ የእውነተኛ ሃይማኖት ዐላማው፣ ውጤቱ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ትንሽም አለመፍራት መሆኑን ማስታወስ አለብን፡፡ ት.ዳ.3-13-ፍጻ፡፡ አሁንም እንደ ቀድሞው መንፈሰ ኀይልን ታጥቀን እንነሣ፤ አምላካችን እንደ አባቶቻችን የኀይልና የጥበብ መንፈስን እንጂ የፍርሀትና የመደንገጥ ሀብትን አልሰጠንምና በሃይማኖታችን ማንንም አንፍራ፤ አንሸበር፡፡ የዜግነት ግዴታችንን እየተወጣን መብታችንን ጠብቀን ለማስጠበቅ እንታገል፡፡ 2ጢሞ.1-7፡፡

በሰፊዋ ሀገራችን እንኳን ተወልደው ያሉ ዜጎቿ ቀርቶ ከተለያዩ ሀገሮች የሚመጡ ባዕዳን ሁሉ በተለያየ እምነታቸው ተከራይተውና ተጎራብተው እንዲኖሩ ቤተ ክርስቲያናችን አልተቃወመችም፡፡ ከማንኛውም የእምነት መሳይ ተቋም ደልላ የእንጀራ ልጆች ለማፍራትም አትፈልግም፡፡ ከጅሏትም አያውቅ፡፡ ይህን የሚያደርጉ ግን ሌሎች ናቸው፤ እዚህ ላይ ስማቸው ባይጠራም በዚሁ የሃይማኖት መሳይ ኑፋቄ የደላላነት ግብራቸው ይታወቃሉ፡፡ ማቴ. 7-15

«የሁሉ ሰው መብትና ነጻነት ሰብአዊ ፍላጎትም ተጠብቆ በእኩልነት እንኑር» የሚለውን የአስተዳደር መርሕ እንቀበላለን፡፡ አምላካዊ ሕግም ነው፡፡ በሃይማኖት ከማይመስሉን ጋር ግን በእምነት ጉዳይ መቼም ቢሆን አንድነት የለንም አይስማማንም፡፡ ከይዞታችንና መብታችን ሌሎች እንዲገቡብንም አንፈልግም፡፡ እኛም ከነሱ የምንሻው ምንም ነገር የለም፡፡ አይጠቅመንምና፡፡ ይህ ምርጫችን ነው፡፡ ግድ የሚለን የለም፡፡ «ሲኖሩ ልጥቅ፣ ሲሔዱ ምንጥቅ» የሚለው የአበው ምሳሌያዊ ቃለ ኀይል ሥጋችንን ዐልፎ ዐጥንታችንን በማስተዋል አለምልሞታልና፡፡ ይልቁንም «ብርሃንን ከጨለማ ጋር የሚቀላቅለው ማነው?» የሚለው ቃለ ቅዱስ መጽሐፍ ጠፈር፣ ደፈር ሆኖ ይከለክለናል፡፡ክርስትናችንን ይበርዝብናል ክልክል ነው፡፡ 2ኛቆሮ.6-14-ፍጻ፡፡ ይህን በጥሞና እንገንዘበው፡፡ እኛ ሃይማኖት መጽደቂያ፣ ምግባረ ሃይማኖት ማጽደቂያ እንጂ የሥጋ መተዳደሪያ እንዳልሆነ በውል ስለምናውቅ የሃይማኖትን ጉዳይ ከማናቸውም ሥጋዊና ጊዜያዊ ደስታ ጥቅም ጋር አናያይዘውም፡፡. . . ለዚህም ብለን ሃይማኖትና ሥርዐታችንን አንሸጥም፤ አንለዋውጥም፡፡ ይህ የቅዱሳን አበው ትውፊታችን ነው፡፡ ከደማችን የተዋሐደ ክርስቲያናዊ ጠባያችንም ይኸው ነው፡፡ ሮሜ12-18 ነገር ግን ይህ አቋምና ጠባያችን ከሞኝነት ተቆጥሮ ያላችሁን ሁሉ እንቀማችሁ እንቀስጣችሁ የሚሉንን አምረን እንቃወማለን፡፡ ይገባናልም፡፡ ብዙዎች የእምነት ተቋሞች ሳይሆኑ ነን ባዮች የታሪክና የሃይማኖት መሠረታቸውን እየለቀቁ፣ የነበራቸውን ትውፊት በቁሳቁስና በኃላፊ ጥቅም እየለወጡ ባዶ እጃቸውን ስለቀሩ እኛ ከቅዱሳን አበው ወርሰን ጠብቀንና አጥብቀን የያዝነውን ነፍስ እንዳላወቀ ሕፃን «ካክሽ» እያሉ በማስጣል እኛነታችንን ሊአስረሱን ይፈልጋሉ፤ አልፈው ተርፈውም ወቅትንና አጋጣሚን ዐይነተኛ ተገን /መሣሪያ/ በማድረግ፣ ነገሮችንም ከፖለቲካና ከግዚያዊ ችግር ጋር በማስተሳሰር የሕዝብን አስተያየት ለማዘናጋትና የመብታችን ተካፋዮች ለመሆን መስለው ይቀርባሉ፡፡ ከሃይማኖት መሳይ ቤተሰባቸው ለጊዜያዊ ችግር የሚገኘውን ጥቂት ርዳታ የሃይማኖት፣ የታሪክና የቅርስ መለወጫ ሊአደርጉትም በእጅጉ ይሻሉ፡፡

እውነተኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን «ኩራት እራቱ» ስለሆነ እንደኤሳው ብኩርናውን በጊዜያዊ ጥቅም /ነገር/ አይለውጥም፡፡ «ነብር ዥንጉርጉርነቱን» እንደማይለውጥ የኢትዮጵያ ሕዝብም፣ ለሃይማኖቱ፣ ለክብሩ፣ ለታሪኩና፣ ለነጻነቱ መሞት እንኳ የተለየ መታወቂያው፣ የማይለወጥ ጠባዩ ነው፡፡ ኤር. 13-23፡፡

በዐያሌው ከልብ የተወደዳችሁ፣ እውነቱ ያልተሰወራችሁ የቤተ ክርስቲያን አባላት ሆይ!

የእምነታችሁና ሥርዐታችሁ ጠባቂዎች፣ የቤተ ክርስቲያናችን ሕይወቷ ደስታዋና ክብሯ ተከታዮቿ እናንት ምእመናን ስለሆናችሁ ልጆቻችሁና ወዳጆቻችሁ በዐዲስ የሃይማኖት ትምህርት መሰል ክሕደት እንዳይወስዱ ጊዜና ቦታ በማይገድባቸው ወደ ጥፋት በሚወስዱ ሰፋፊ መንገዶች ከሚመሩ አዘናጊዎች መናፍቃንና ቢጽ ሐሳውያን መምህራን እንድትጠበቁ፣ «ዐደራ»! ትላችኋለች እናታችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፡፡ ደግሞም በቅዱሳን አበው ሃይማኖታችሁ እንድትጸኑ ታሪካችሁን፣ ሀገራችሁን ባህላቸሁን፣ ፍቅራችሁን፣ አንድነታችሁን ጠብቃችሁ በጥንቃቄና በሥርዐት እንድትኖሩ፣ እኛም እጅግ ጥብቅ የሆነ መንፈሳዊ ፍቅር የተመላ መልእክታችንን በእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕያው ስም ከቅን ልቡና በመነጨ ሐሳብ አናስተላልፋልን፡፡ 1ቆሮ.14-15

መድኀኒታችን እንዳስጠነቀቀው ከሐሰተኞች መምህራን ተጠበቁ፤ የዘመኑን ምትሐታዊ ሒደትና ይዘት ዕወቁ፤ በመንፈሳዊ ሕይወት ጽኑ፡፡ በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ከዓለም ኅብረተሰብ የምናገኘው ጊዜያዊ ርዳታ በሰብአዊና ማኅበራዊ ግዴታ ላይ የተመሠረተ እንጂ የሃይማኖትና የታሪክ ለውጥ መዋዋያ አይደለም፡፡ የመልካም ጠባይና ማንነት መለወጫም አይደለም፡፡ ድኽነትን ከየቤታችን ለማጥፋት ሥራን እንውደድ፡፡ እርስ በርስ እንረዳዳ፡፡ ችግረኛውን ተባብረን ነፃ እናውጣው፡፡ እንደቀሞው ባህላችን ያለንን ተካፍለን ዐብረን እንብላ እንጂ መነፋፈግን አንልመድ፡፡ በዚህ ጊዜ የበረከት አምላክ ረድኤት በረከቱን ይሰጠናል፡፡ ወገንና መጠናችንንም ለይተን ዕንወቅ እንጂ የቅዱሳን አበው ልጆች እዚህ ላይ አትኩረን ልብ እንበል፡፡ በምንም ሰበብ እንደ ገደል ውሃ ክንብል አንበል፡፡ ይህን ከመሰለው ደካማ ሐሳብም ልጆቻችሁን በብዙ ዘዴ ጠብቁ፡፡ የሃይማኖት ፍቅር ቁም ነገሩም ከቤተሰብ በላይ ስለሆነም ይህን አትርሱ፡፡ ምንም ቢሆን ክፉን ማስወጣት ያቃተው ስንኳ ቢኖር መውጣት አያቅተውም፡፡ ማቴ. 10-36-40

በቤተሰብ አባላት በወዳጅ ዘመድና በጎረቤት መስለው የሚመጡ የበግ ለምድ ለባሾችን ዕወቁባቸው፡፡ ፊልጵ. 3-2 ዋናው ዘዴ ከእነርሱ ጋር ዐብሮ አለመራመድ፣ ዐብሮ አለመገኘት ነው፡፡ ከደጃቸውም አለመቆም ነው፡፡ የእነርሱ የሆነንም ሁሉ አለመከጀል፣ ፈጽሞ አለመንካት ነው፡፡ የጠላት ገንዘብ ምግብ፣ ልብስና ቁሳቁስ በሙሉ የተወገዘ፣ እርኩስ ነው፡፡ ሕርም ነው፣ መርዝ ነው፡፡ ደዌ ክሕደትን ያመጣል እንጂ ጤና ሕይወት አይሆንም፡፡ እንወቅ፡፡ በሌላ በኩል በእውነቱ ከሆነ አንድ ልጅ እናቱ መልካም ፍትፍት ምግብ አዘገጅታ ባትሰጠው እንኳ ከጎረቤት ሔዶ በመርዝ የተቀመመ ምግብ መብላትና መታመም፣ ዐልፎም መሞት የለበትም፡፡ እንደዚሁም ታዲያ በሥራዋና በመልካም አቋሟ ሁሉ እንደ መማር፣ ባይሆንም እንደ መጠየቅ «እናቴ ቤተ ክርስቲያን ጮኻ ባታስተምረኝ ነው» እያሉ ከክሕደትና ኑፋቄ ማኅበር እንደ እሳት ራት ዘሎ መግባት አግባብ አይደለም፤ የሰውነት መመዘኛም አይሆንም፡፡ እንግዲያውስ ተጠበቁ፡፡ ተጠንቀቁ፤ ሌላ የሚያዋጣ ነገር ፊጽሞ አይገኝም፤ ዐጉል መዋተት ብቻ ይሆናል፡፡ በዚህ ዐዲስ ዘመን ዐዳዲስ የሃይማኖት መሳይ ድርጅት የቀናች አንዲት እውነተኛ የአበው ሃይማኖትን ሊተካት ቀርቶ ሊመስላት አይችልም፡፡ ይህን የመሰለው ሐሳብ የዘባቾች ከንቱ ዘበት ነው፡፡

ሰው ሆኖ በተዋሕዶ ተገልጾ በባሕርይ ክብሩ ያለ መድኀኒታችን የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከባለቤቱ እንደባዘነ የቤት እንስሳ በዚህ ዘመን በየሜዳውና በየግል አጋጣሚ «አገኘሁት» አይባልም፡፡ ድፍን ያለ ሐሰት ነው፡፡ እናስተውል፡፡ ወይም እራሳቸውን እንኳ በማያውቁ ልሙጥ ማይማን ዘባቾች «ተቀበሉት» የሚባልለት ቁስ አካል፣ አልያም ማደሪያ የሌለው ባይተዋር አይደለም፡፡ ዓለምን በእጁ የያዘ እርሱ በእኛ የሚወሰን ይመስል የተለያየ ችግር ባለባቸው፣ ተግባር ሥጋዊን በጠሉ፣ የዕለት ምግብ ፈላጊዎች ልንጎተትና በእነርሱ ዐቅም ተታለን በየዛኒጋባው ልንመሰግ የሚገባን ሰብአዊ ግብር አይደለንም፡፡ አሁንም በሃይማኖት ቁሙ፣ ጠንክሩ፣ ንቁም በተማራችሁትና በያዛችሁት እውነተኛ ሃይማኖታችሁ ጽኑ፡፡ ባይረዳችሁ እንኳ ከእናታችሁ ቅድስት ቤተክርስቲያን ተግታችሁ ተማሩ፤ ጠይቁ፡፡ «ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ = የቅዱሳን አባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች፣ የጸናች እውነተኛም ናት» አማራጭ ተለዋጭ ፈጽሞ የላትም፤ ዘለዓለማዊት ናት፡፡ በባዕድ ዘመን አመጣሽ ትምህርት እንዳትወሰዱ አሁንም፣ ምን ጊዜም ተጠበቁ፤ ዕወቁ፤ ተጠንቀቁ፡፡ በቃለ አበው ሐዋርያት ተገዝታችኋል፡፡ ስለእውነተኛዋ ሃይማኖታችሁ በየትና በማን እንደምትማሩ ለይታችሁ አስተውሉ፡፡ ተረዱም፡፡ በቀናች ሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ በሰላም በብርታት እንድትኖሩም፣ ለጸሎትና ምህላ ትጉ በሥራችሁ ሁሉ እንዳትሰናከሉም፣ እንቅፋታችሁን «ወአምላከ ሰላም ለይቀጥቅጦ ለሰይጣን በታሕተ እገሪክሙ ፍጡነ = የሰላም አምላክ ፈጥሮ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ይቀጥቅጠው!!!» ኀያሉ አምላክ ኀይል፣ ከለላ፣ ይሁነን፡፡ የእመቤታችን ቅድስት፣ ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎት ግርማ ሞገስ ይሁነን፡፡ ሮሜ 16-20፣ 1ኛቆሮ.16-13፣ ገላ.1-8፣ ቆላ.2-6-11

ምንጊዜም «ክፉ አይልከፋችሁ፣ ደግ አይለፋችሁ»

 

ከሊቀ ትጉሃን ኀ/ጊዮርጊስ ዳኘ
በጠ/ቤተ ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ም/ሓላፊ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አምላከ ሰማያት ወምድር