«ጾምን ቀድሱ» /ኢዮ.2-15/

ጾም


የሰውን ልጆች የሚወደውና ስለ እነርሱም ብሎ በገነት ያሉትን ዛፎች ሁሉ የፈጠረው እግዚአብሔር በገነት ካሉት ዛፎች መካከል አንዲቱን እንዳይበላ አዳምን አዘዘው፡፡ ይኽ አዳምን ለመጫን፣ ኃይሉን በእርሱ ላይ ለማሳየት ሳይሆን ሰው በመጾም /ባለመብላት/ እና በመታዘዝ ለሚወደው አምላኩ ፍቅሩን ይገልጽ ዘንድ ነው፡፡

 

ከአዳም ድቀት በኋላም በየዘመናቱ የተነሡ መንፈሳውያን ሰዎች እና ሕዝቦች በየግላቸው እንዲሁም በአንድነት /በጋራ/ ሲጾሙ፣ በጾማቸውም ሲጠቀሙ ኖረዋል /ሕዝበ እስራኤል ሙሴ፣ ኤልያስ፣ የነነዌ ሰዎች. . ./፡፡

 

ጌታችንም፣ በእደ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ፤ የማስተማር አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት ጾሟል፡፡ ከዚህ ክርስቲያናዊ ትውፊት በመነሣትም ሐዋርያትና ደቀመዛሙርቱም እንዲሁ አገልግሎታቸውን ከመጀመራቸው በፊትና በአገልግሎታቸው ወቅት ይጾሙ ነበር፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርቲያናችን በትውፊት ያገኘነውን፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተማሩንን ጠቃሚ ሥርዓቶችን አውርሳናለች፡፡ ከነዚህ የከበሩ ሀብታት መካከል ሥርዓተ ጾም አንዱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የአዋጅ እና የግል /የፈቃድ/ አጽዋማት አሉን፡፡ ቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊት ዓለም እንደመሆኗም የጾም አስተምህሮዋ «ለጾም አድሉ» የሚል ነው፡፡ ምእመናንም የዓመቱ ብዙውን ቀናት በዚህ በተቀደሰ መንፈሳዊ ምግባር ያሳልፋሉ፡፡

የጾም ጽንሰ ሐሳብ

1. መጾም ማለት በፈቃድ ለተወሰነ ጊዜ ከምግብ መከልከልና መራብ ማለት ነው፡፡ ጌታችን በጾመ ጊዜ ተርቧል /ማቴ.4-2/፡፡ ሐዋርያትም በጾማቸው ጊዜ ተርበዋል /ሐዋ.10-1/፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተወሰነ ጊዜ /ሰዓታትን፣ ቀናትን. . . / ካሳለፍን በኋላም ቢሆን ሥጋን የሚያለመልሙ ምግቦች አንመገብም፡፡ ከአባቶቻችን እንደተማርነው ከእንስሳትና ከእንሰሳት ውጤቶች፣ እንዲሁም ከሌሎች ለሥጋ እጅግ ከሚመቹ ምግቦች እንርቃለን እንጂ፤

ዳንኤል:-«በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሳዝን ነበርሁ፡፡ ማለፊያ እንጀራ አልበላሁም፣ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፡፡ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም»/ዳን.10-3/፡፡

ዳዊት:- «ሥጋዬ ቅባት በማጣት ከሳ፣ ጉልበቶቼም በጾም ደከሙ»/መዝ.108-24/፡፡

ይኽ እንዳለ ሆኖ ጾም ማለት ከምግብ፣ ከመጠጥና ከምቾት መታቀብ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ የግዴታ አንድያ ልጁን ለእኛ እንዲሞት ለሰጠው ለእምላካችን ያለንን ፍቅር የምንገልጥበት መንገድ መሆንም አለበት፡፡ ስለዚህ የጾም ወቅት የበለጠ ስለ እግዚአብሔር የሚያስቡበትና በፍቅሩ የሚመሩበት፤ ወደ እርሱ የሚቀርቡበት ወቅት መሆን አለበት፡፡ የምንጾመው «ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኔ ሞቶልኛል፤ እኔም ቀኑን ሙሉ ፈቃዴን ለእርሱ እገድላለሁ» በሚል አሳብ ነው፡፡

ከዚህም በላይ ጾም ከኃጢአት መራቅን ስለ ቀደሙ በደሎች ንስሓ መግባትን እና በመንፈሳዊነት ማደግን ያካተተ መሆን አለበት፡፡

2. እግዚአብሔር እኛን የፈጠረን ሥጋችንና ነፍሳችን መንፈሳዊ ሆነው በአንድነት ለእርሱ እንዲገዙና ፈቃዱን እንዲፈጽሙ ነው፡፡ መንፈሳዊ መሆን ማለት በመንፈስ ቅዱስ መመራት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የሥጋችንን ፈቃድ በናረ ጊዜ ነፍሳችን ለመንፈስ ቅዱስ /ለእግዚአብሔር/ ፈቃድ ሳይሆን ለሥጋ ፈቃድ ትገዛለች፡፡ እንደ ሥጋውያን መመላለስ ኃጢአት መሥራት እንጀምራለን፡፡ ጾም ይህንን ለማስቀረት ሥጋችንን የምናደክምበትና ፈቃድ እንዳያይል የምናደርግበት መንገድ ነው፡፡

3. የጾም ወቅት የንስሓ እና የሐዘን ወቅት ብቻ ሳይሆን የደስታ ወቅትም ነው፡፡ ምክንያቱም የጾም ወቅት ነፍስን ከሚያስጨንቅ የሥጋ ፈቃድ የምንላቀቅበትና መንፈሳዊ ድል የምናገኝበት እንዲሁም የእግዚአብሔርን ፍቅር የምናጣጥምበት ወቅት ነው፡፡

በነቢዩ ኢዩኤል «የተቀደሰ ጾም» ተብሎ የተገለጠው እንዲህ ያለው ጾም ነው፡፡ /ኢዩ.2.15/፡፡

ሥርዓተ ጾም

ይኽንን በመረዳት ሁላችንም አዘውትረን መጾም አለብን፡፡ በእርግጥም ብዙ ክርስቲያኖች የዓመቱን አብዛኛውን ጊዜ በጾም ያሳልፋሉ፡፡ እናት ቤተክርስቲያንም በመንፈሳዊ ዝለት ይኽንን በሚገባ ሳናደርገው እንዳንቀር በዓመቱ ውስጥ በዐዋጅ የሚጾሙ አጽዋማትን አዘጋጅታለች፡፡ እነዚህም ጾመ ነቢያት፣ ጾመ ጋድ፣ ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ድኀነት /ረቡዕና አርብ/፣ጾመ ሐዋርያት፣ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡

በእነዚህ የአዋጅ አጽዋማት ወቅት በብሉይ ኪዳን እና በሐዲስ ኪዳን የተደረጉ የተለያዩ ነገሮች ስለሚታሰቡባቸው ይኽም ለመንፈሳዊ ተመስጦ ስለሚጠቅም ጥቅማቸው እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡

ጾመ ነቢያት

ከላይ በተናገርነው መሠረት ከምንጾማቸው የአዋጅ አጽዋማት አንዱ በየዓመቱ ከኅዳር 15 እስከ ታኅሣሥ 28 /በዘመነ ዮሐንስ እስከ ታኅሣሥ 27/ ድረስ የምንጾመው ጾመ ነቢያት ነው፡፡ ይኽን ጾም የምንጾመው ነቢያት በየዘመናቸው ስለ መሲህ መመጣት በናፍቆት ይጾሙ ይጸልዩ ስለነበር የእነርሱን አርአያ ተከትለን ነው፡፡ የክርስቶስን ልደት ከማክበራችን ቀደም ብለን ይኽን ጾም እንድንጾምም ቅድስት ቤተክርስቲያን ወስናለች፡፡ የተቀደሰ ጾም ለመጾም፣ ጾመንም ልደተ እግዚእን ለማክበር እንትጋ፡፡

አምላከ ነቢያት አይለየን፡