‹‹እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱ ከሆነ ግን፥ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ›› (ገላ.፭፥፲፭)
ዓለም አንድ መንደር ለመገንባት የሚያደርገውን ሩጫ ባፋጠነበት በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በችግሮቻችን የተነሣ መለያየታችን እየባሰ በመሆኑ ሥቃያችን፣ ሞታችን፣ ስደታችንና መከራችን እየበዛ ነው፡፡ የመለያየቱ ጡዘት ሞትን እንጂ ሕይወትን፣ ማጣትን እንጂ ማግኘትን፣ ውርደትን እንጂ ክብርን አላመጣልንም፡፡ በመለያየት የዓለም ጅራት እንጂ ራስ አልሆንም፡፡ መለያየት ኋላ ቀርነትን እንጂ በረከትን ይዞልን አልመጣም፡፡ በመገዳደል ጠላትን ማሸነፍ ወይንም ድል ማድረግ አይቻልም፡፡ በመጻሕፍት እንደተማርነው ገድለው የወረሱ በጊዜ ሂደት ውስጥ ተገድለው ተወርሰዋል፡፡ ቆም ብለን ማስተዋል እስካልቻልን ድረስ ወደ ፊትም ይህ እውነት ይቀጥላል፤ አይቆምም፡፡