ጥንተ ስቅለት

መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ለዓለም ሁሉ ድኅነት መድኃኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ መጋቢት በባተ በ፳፯ኛው ቀን በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ልጆቹም ይህን እናዘክር ዘንድ ዓይን ልቡናችንን ወደ ቀራንዮ እናንሣ!

በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጻፈው አይሁድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊይዙት ወደ ጌቴሴማኒ በመጡ ጊዜ ‹‹ማንን ትፈለጋላችሁ?›› ቢላቸው ‹‹የናዝሬቱን ኢየሱስን እንፈልጋለን›› ሲሉት ‹‹እኔ ነኝ›› ቢላቸው ከአንደበቱ የወጣውን መለኮታዊ ቃል ብቻ መቋቋም አቅቷቸው መሬት ላይ ወድቀው ተዘርረዋል፡፡ (ዮሐ.፲፰፥፩) የጌታችን ሞቱ በፍጹም ፈቃዱ እንደሆነም በዚህ እንረዳለን::

ስለዚህም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ትዕግሥት አንክሮ ይገባል! ዓለምን በመዳፉ የያዘ አምላክ በአይሁድ እጅ እንደሌባ ተያዘ፤ ሠራዊተ መላእክት ለምሥጋና በፊቱ የሚቆሙለት መድኃኔዓለም እርሱ ሊፈረድበት በፍርድ ዐደባባይ ቆመ፡፡ በእስራት ያሉትን የሚፈታ እርሱ በብረት ችንካር ተቸነከረ፡፡ ሰማይን በከዋክብት ምድርም በአበባ ያስጌጠ እርሱ ግን የእሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፋ፡፡ ዓለሙን ሁሉ በቸርነቱ የሚመግብ እርሱ ‹‹ተጠማሁ›› አለ፡፡

አይሁድ በምቀኝነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመስቀል ከያዙት በኋላ  እሾህ ያለው አክሊል ሠርተው ከፍላት አግብተው በጉጠት አንስተው ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሥ ነህ ዘውድ ይገባሃል ብለው በራሱ ላይ ደፉበት፡፡ እራሳቸው እንደ መሮ፣ ወርዳቸው እንደ ሞረድ ዐራት ማዕዘን አሠርተው ቁመታቸውን ክንድ ከስንዝር፣ ስለታቸውን እንደ ወስፌ አድርገው ችንካር ሠርተው በስቁረት አግብተው በጌታችን በራሱ ላይ ቢመቱበት ሥጋ ለሥጋ ገብቶ መሐል ልቡን ወጋው፡፡ አክሊለ ሦኩን በራሱ ላይ አድርገው ሲያበቁ ከቤት ወደ ዐደባባይ እያመላለሱ ‹‹ንጉሥ ሆይ!…›› እያሉ ምራቃቸውን እየተፉበት ተዘባበቱበት፡፡ መስቀል አሸክመው ከሊቶስጥራ እስከ ቀራኒዮ ድረስ እያዳፉ ሲወስዱት በምድር ላይ ጣሉት፡፡ ከኋላ ያሉት ‹‹ፍጠን›› እያሉ ገፍትረው ይጥሉታል፤ ከፊት ያሉት ደግሞ ‹‹ምን ያስቸኩልሃል?›› እያሉ መልሰው ገፍትረው ይጥሉታል፡፡ ከዚህ በኋላ ክፉዎች አይሁድ ቁመታቸውን ክንድ ከስንዝር ስለታቸው ደግሞ እንደ ወስፌ የሆኑ አምስት ችንካሮችን ሠርተው ሳዶር በሚባለው ችንካር ቀኝ እጁን፣ በአላዶር ግራ እጁን፣ በዳናት ሁለት እግሮቹን፣ በአዴራ መሐል ልቡንና በሮዳስ ደረቱን ቸንክረው የአዳም ራስ ቅል ባለበት ቀራኒዮ ዐደባባይ ላይ ሰቅለውታል፡፡

የኋሊትም አስረው አፍንጫውን ደጋግመው ቢመቱት ደሙ በመሬት ላይ እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ከጌቴሴማኒ እስከ ሐና ቤት ድረስ አስረው የፊተኞቹ ሲጎትቱት የኋለኞቹ እየለቀቁት የኋለኞቹም በተራቸው ሲጎትቱት የፊተኞቹ ይለቁታል፤ እንዲህ እያደረጉ ከመሬት ጋር እያጋጩ አሠቃዩት፡፡ ሳውል በእግሩ ሲረግጠው ጌታችን ‹‹መመለስህ ላይቀር ለምን ትረግጠኛለህ?›› ቢለው ስለዚህ ንግግርህ ብሎ ሳውል አስገረፈው፡፡ በሁለት ግንዶች መካከል አድርገው ከግንዱ ጋር አጋጩት፡፡  በእጃቸው ሲመቱት እጃቸውን ስላመማቸው ድንጋይ ጨብጠው ፊቱን ጸፉት፡፡

በሽመል ደብድበውታል፡፡ በጲላጦስ ዐደባባይም የጌታችንን ፂሙን ነጭተውታል፡፡ ጲላጦስ እንደ ሕጋቸው ገርፈው እንዲለቁት ቢያዝም ክፉዎች አይሁድ ግን ጌታችንን ሲገርፉት ‹‹አሠቃቂ ግርፋቱን ዓይተን ልባችን እንዳይራራ›› ብለው ሰንጠረዥ ገበጣ ሠርተው ሲጫወቱ አንዱ ተነሥቶ ይገርፍና ሲደክመው ‹‹ቆጠራችሁን?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ‹‹አልቆጠርንም›› ሲሉት ከድካሙ የተነሣ ‹‹እኔው ልግረፍ እንደገና እኔው ልቁጠር›› ብሎ ትቶት ሲቀመጥ ሌላኛው ይነሣና እንደዛኛው ሁሉ በተራው ይገርፈዋል፡፡ ሁሉም እንዲህ እያደረጉ ጌታችንን ሥጋው አልቆ አጥንቱ እንደበረዶ ነጭ ሆኖ እስኪታይ ድረስ ፮፲፻፮፻፷፮ (ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት) ጊዜ ጽኑ ግርፋትን ገረፉት፡፡ በእነዚህ ሁሉ ግርፋቱ ወቅት ሥጋው ተቆርሶ መሬት ላይ ወድቋል፡፡

የዓለም መድኃኒት የማዳኑ ምሥጢር ምንኛ ድንቅ ነው!!! ለዚህ ባሕርይው አንክሮ ይገባል!!!

አምላካችን እግዚአብሔር በአንድ ልጁ በጌታችን በመድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ መስቀል፣ ሞትና ትንሣኤ ከሞተ ነፍስ ይታደገን ዘንድ ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን!!!