ቤተ መቅደስ 

መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ቤተ መቅደስ ከሁለት ጥምር ቃላት የተገኘ ትርጓሜው የተቀደሰ ቤት የሚል ሲሆን ይህም የእግዚአብሔር አምላካችን ማደሪያ ወይም ቤት ነው፤ ቤተ መቅደስን የሚወክሉ አካላትም ሦስት ናቸው፡፡

. ቤተ መቅደስ፤ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን

ቤተ መቅደስ ከእግዚአብሔር ጋር የምንናኝበት የጸሎት ቤት ማለት ነው፤ የክርስቲያን ቤት መሰብሰቢያችንም ስለሆነ የክርስቲያን መገኛ ነው፡፡ ይህም ክርስቲያኖች የሚጸልዩበት፣ የሚሰግዱበትና ሥጋ እና ደሙን የሚቀበሉበት ነው፡፡ (ኢሳ.፶፮፥፯፣ኤር.፮፥፲-፲፮፣ማቴ.፳፩፥፲፫፣ ማር.፲፩፥፲፯፣ሉቃ.፲፱፥፵፮)

የክርስቲያኖች መሰብሰቢያ የሆነው ቅድስት ሥፋራ የእግዚአብሔር አምላካችን ቤት በመሆኑ በውስጡ ያሉት መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ የተቀደሱና የተባረኩ ናቸው፡፡ በቤተ መቅደስ ታቦት አለ፤ ንዋያተ ቅዱሳት እንዲሁም የልዑል እግዚአብሔር፣ የቅድስት ድንግል ማርያምና የመላእክት፣ የቅዱሳን የጻድቃንና የሰማዕታት ስዕለ አድኅኖም በግድግዳው ተሰቅሎ ይገኛል፤ ቅዱስ ቁርባን የሚፈተተው በዚሁ በተቀደች ሥፍራ ቤተ መቅደስ ነው፡፡

፪. ቤተ መቅደስ፤ እመ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም

አስቀድሞ በነቢያት እንደተነገረ እንዲሁም በሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ተመዝግቦ እንደምናገኘው እግዚአብሔር ወልድ ዓለምን በረቂቅ ጥበቡ ሥጋን ለብሳ ለማዳን የመረጣት ቅድስት ማደሪያው ንጽሕተ ንጹሐን ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው፡፡

‹‹እግዚአብሔር በሰማይና በማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩት ሁሉ ተመለከተ፡፡ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ፡፡ ንጉሥ ውበትሽን ወደደ፡፡ ለዘለዓለም ማረፊያዬ ይህች ናት፡፡ መርጫታለሁና በእርሷ አድራለሁ አለ›› እንዲል፤ (አንቀጸ ብርሃን)

በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ጌታችንን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማኅፀኗ ለዘጠኝ ወር ተሸክማ ያለ ሕማምና ጻር ለመውለድ የበቃች ከፍጡር ሁሉ የተለየች በመሆኗ ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ ማደሪያ ቤተ መቅደስ እንላታለን፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በድርስቱ የእመቤታችንን ክብር እንዲህ በማለት ገልጾታል፤ ‹‹ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል፤የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና፡፡ መላእክት የሚፈሩትን ትጉጎች በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኅፀኗ ተሸከመችው፡፡ ይህች ከኪሩቤል ትበልጣለች፤ ከሱራፌልም ትበልጣለች፡፡ ከሦስቱ አካል ለአንዱ ማደሪያ ሆናለችና፡፡ የነቢያት ሀገራቸው ኢየሩሳሌም ይህች ናት፡፡›› (የረቡዕ ውዳሴ ማርያም)

እመቤታችን ድንግል ማርያም አምላኳን ለመውለድ የበቃች ብቻም ሳትሆን ለሰዎች ሁሉ ምሕረትንና ይቅርታን የምታሰጥ አማላጃችንና የሁላችንም ተስፋ ናት፡፡    

፫. ቤተ መቅደስ፤ ምእመናን (ክርስቲያኖች)

ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ አታውቁምን›› ብሎ እንደነገረን ቤተ መቅደስ የክርስቲያን ወገን ሁሉ የሚጠራበት ስም እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ‹‹ቤተ እስራኤል፣ ቤተ ያዕቆብ፣ ቤተ አሮን›› በማለት በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል፡፡ (፩ቆሮ. ፫፥፲፯፣መዝ. ፻፲፯፥፫፣ማቴ.፲፮፥፲፰)

ሰዎች በምድራዊ ሕይወታችው በቅድስና ሊኖሩ እንደሚገባ ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ አስተምሮናል፡፡ ፈተናና ችግር ቢበዛን እና ጠላታችን ዘወትር እኛን ተስፋ አሳጥቶ ሊጥለን ቢሞክርም የእግዚአብሔርን ሕግ ግን ተላልፈን ኃጢአት ልንሠራ አይገባም፡፡ በቅን ልቡናም ሆነን በትዕግሥት የሚመጡብንን ፈተናዎች ማላፍ ይጠበቅብናል፡፡ መከራም ቢበዛብን ጥንካሬ እንዲሰጠን አምላካችንን በመለመን ልንጸና ይገባል እንጂ በመማረር እና ያለንበትን ሁኔታ ሰበብ በማድረግ ፈጣሪያችንን ሊያስከፋና ሊያሳዝን የሚችል ሥራ እየሠራን ልንኖር አይገባም፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ዘንድ ትንሽ የሚባል ኃጢአት የለም፡፡ ትንሽም እንኳን እርሱን የሚያስከፋ ሥራ ሠርተን ቢሆን ሳንዘገይ በንስሓ መመለስ ይኖርብናል፡፡ በርካቶች በዚህ መንገድ የጠፉ አሉና በተሳሳተ መንገድ ላለመጓዝ እጅግ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡

በተለይም በዚህ ጊዜ ዓለም በኃጢአት ማዕበል በምትናወጥበት ጊዜ የክርስትና ሕይወትን ለመኖር እጅጉን ፈታኝ በመሆኑ ተጋድሏችንን ጨምረን ጠላታችንን ማሸነፍ አለብን፡፡ አሳሳች ነገሮች የበዙባት ምድር ላይ እየኖርን በመሆኑ ሁሉንም ነገር መመርመር ያሻል እንጂ ‹‹አብዛኛው ሰው የመረጠው መንገድ ስለሆነ ትክክል መሆን አለበት›› በሚል የተሳሳት አመለካካት ከጠፉት ጋር አብረን እንዳንጠፋ መጠንቀቅ አለብን፡፡ ምክንያቱም ሰው ለሠራው ኃጢአት ንስሓ ገብቶ ቶሎ መመለስ ካልቻለ የእግዚአብሔር መንፈስ ይርቀውና የሰይጣን ማደሪያ ይሆናል፡፡ ስለዚህም መልካሙንና በጎውን መለየት እስኪያቅተው ድረስ ዓይነ ልቡናው ይታወራል፡፡ ልቡም ይደነድናል፤ በትዕቢትም ይሞላል፡፡ አምላኩን መበደሉንም ረስቶ በእኩይ ተግባሩ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ያለ ንስሓ ኖሮ ለዘዓለም ቅጣት ይዳረጋል፡፡

ነገር ግን ቤተ መቅደስ የሆኑት የክርስቶያን ወገኖች ሰውነታቸው ወይም ሰብእናቸው በንጽሕናና በቅድስና የተጠበቀ የእግዚአብሔር ቤት ናቸው፡፡ ስለዚህ ‹‹እናንተ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች ናችሁ›› ያለው ቅዱስ ጳውሎስ ከማንኛውም ኃጢአት የራቁትንና የጸዱትን፣ ለሕጉ ተገዢ የሆኑትን  እንዲሁም ሥርዓቱን ጠብቀው የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ነው፡፡

ስለዚህ እኛም የእግዚአብሔር ማደሪያ ልንሆን ይገባልና ፈጣሪያችን የሚወደውን ክርስቲያናዊ ምግባር በመተግበር ከየትኛውም እኩይ ተግባር፣ ኃጢአትና በደል ተጠብቀን በቅድስና ሕይወት መኖር ይጠበቅብናል፡፡ በተለይም በዚህ የጾም ወቅት ይህን በታላቅ ትጋት ፈጽመን ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃንን ሥራ ልንሠራ ይገባል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ጾማችንን ይቀበለን፤አሜን፡፡