ቅድስት

መምህር አብርሃም በዕውቀቱ

የካቲት ፳፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ቅድስት ማለት የተለየች፣ የነጻች፣ የከበረች ማለት ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የጀመረባት፣ ልዩ፣ የተቀደሰች፣ የከበረች፣ ንጹሕ፣ ክቡር በሚሆን በጌታችን የተጾመች መሆኗን ያመላክታል፡፡ ይህች ጾም በማቴዎስ ወንጌል የተገለጠች ስትሆን፣ አምላካችን በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት በጾመበት ጊዜያት ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል አድርጓል፡፡ (ማቴ.፬፥፪)

ሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ የሚባሉትም፡- ትዕቢት፣ ስስትና ፍቅረ ንዋይ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሦስት ኃጢአቶች ጌታችን በዲያሎስ በተፈተነ ጊዜ በትዕቢት ቢመጣበት በትሕትና፣ በስስት ቢመጣበት በትዕግሥት፣ በፍቅረ ንዋይ ቢመጣባት በጸሊዓ ንዋይ ጌታችን ዲያሎስን ድል አድርጎታል፡፡ ለእኛም እነዚህን ድል ለማድረግ የምንችልበትን ጥበብ ጾምን ገልጦልናል፡፡ ትዕቢት ያልተሰጠንን መሻት፣ ስስት አልጠግብ ባይነት ስግብግብ መሆን፣ ፍቅረ ንዋይ ለገንዘብ ሲሉ ፈጣሪን መካድ ነው፡፡ አንደ ክርስቲያን ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል ካደረገ ሌሎችን ኃጣውእ በቀላሉ ድል ማድረግ ይቻለዋል፡፡ ይህም ለቅድስና ያበቃዋል ማለት ነው፡፡

ቅድስት የተባለችው ሰንበትም ስያሜዋና የዕለቷ የምስጋና ሥርዓትም የቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ስያሜም ሰንበት የዕረፍታችን ቀን እንድትሆን በኦሪትም በሐዲስም እግዚአብሔር የባረካት የቀደሳት ዕለት መሆኑዋን የሚያመለክት ነው፡፡ የሰንበትን ክብር ለማስገንዘብ የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት ሰንበት ቅድስት ተብላለች፡፡  ከዋዜማው ጀምሮም የሚዘመረው ጾመ ድጓ የአምላካችንን ቅድስና እና ሰንበትን ቀድሶ በፈቃዱ እንደሰጠን የሚያነሣው ክፍል ነው፡፡ ይህም ከጾመ ድጓው ‹‹ዛቲ ዕለት ቅድስት ይዕቲ፤ ሰንበትየ ቅድስትየ እንተ አዕረፍኩ፤  ቅዱሳነ ኩኑ እስመ አነሂ ቅዱስ አነ፤ አብ ቀደሳ ለሰንበትይህች ቀን የተቀደሰች ናት፤ ያረፍኩባት ቅድስት ሰንበት ናት፤  እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፤ አብ ሰንበትን አከበራት፤ ቀደሳት›› የሚል ነው፡፡

ከዚህ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱን ስለ ቅድስና ልጆቿን  ታስተምርበታለች፡፡ በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበከው ምስባክ፣ የሚነበቡ መልእክታት፣ የሐዋርያት ሥራና ወንጌል ስለ ቅድስት የሚያስተምሩ ናቸው፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ በአምሳሉና በአርአያው እንደፈጠረን ሁሉ ቅድስናው የባሕርይ ገንዘቡ በመሆኑ እኛም ቅዱስ መሆን አለብን፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁን ተብሎ ስለተጻፈ የጠራቸው ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ›› ያለንም ይህንን ሲያስተምረን ነው፡፡ (፩ጴጥ.፲፭፥፲፮)

በሥነ ፍጥረት ትምህርት እንደምንረዳው ከመፈጠራችን አስቀድሞ እግዚአብሔር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን፣ ለውርደት ሳይሆን ለክብር፣ ለርኩሰት ሳይሆን ለቅድስና፣ ለሞት ሳይሆን ለሕይወት ነው፡፡ የመፈጠራችንም ዓላማ በፊቱ በፍጹም ምግባርና ሃይማኖት በመመላለስ ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም እንድንኖር ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኩሰት አልጠራንምና›› በማለት ያስተማረውም ለዚህ ነው፡፡ (፩.ተሰ.፬፥፯) ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ ደግሞ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳን ንጹሐንና ያለነውር በፍቅር ያደርገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን፡፡›› (ኤፌ.፩፥፫-፬)

ሆኖም ግን የመጀመሪያው አዳም ሕገ እግዚአብሔር ተላልፎ ቅድስናውና ክብሩን በማጣቱ እግዚአብሔር አብ አንዱ ልጁን ለእርሱ ሲል መሥዋዕት አድርጎ አዳነው፤ ወደ ቀደመ ክብሩም መለሰው፡፡

ስለዚህም በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን የእግዚአብሔር ልጆች በሙሉ አምላካችን ቅዱስ በመሆኑ ቅዱስ እንደሆንና በቅድስና ሕይወት እንድንኖር ቃሉ ያስተምራናል፡፡ የተከፈለልን ዋጋ እጅግ የከበረና የላቀ በመሆኑ ይህን ዘወትር በማሰብና በጽድቅ በመመላለስ ልንኖር ይገባል፡፡ በተለይም በዚህ በያዝነው የዐቢይ ጾም ወቅት ኃጢአት የሠራን ካለን በንስሓ ሥርየት ማግኝት እንድንችል፣ በጽድቅ የኖርን ካለን የበለጠ ተግተን በቅድስና ሕይወት እስከ መጨረሻው እንድንጓዝ አምላካችን ይረዳን ዘንድ ዘወትር በጸሎታችን መማጸን እንዲሁም በጾምና በጸሎት መትጋት ያስፈልጋል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ጾሙን የንስሓ እንዲሁም የበረከት ያድርግልን፤ አሜን፡፡