ደብረ ዘይት

መምህር አብርሃም በዕውቀቱ

መጋቢት ፲፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ደብረ ዘይት የወራ መብቀያ፣ በወይራ ደን የተሸፈነ ተራራ ማለት ነው። «ደብር» ማለት «ተራራ» ማለት ሲሆን «ዘይት» ማለት ደግሞ «ወይራ» ማለት ነው። በዚህም «ደብረ ዘይት» ማለት የወይራ ዛፍ የሞላበት፣ የበዛበት፣ የይወራ ተራራ ማለት ይሆናል።

ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የሚገኝ ቦታ የሚገኘው ተራራ በደብረ ዘይት በመካከል የቄድሮን ሸለቆ ብቻ አለ። ከግርጌው ጌቴ ሴማኒ የተባለው የአትክልት ስፍራ ይገኛል። የጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተያዘበትና በኋላም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋዋ ያረፈበት ወይም የድንግል መካነ መቃብር በዚህ ተራራ ግርጌ ይገኛል። ቤተ ፋጌ እና ቢታንያ በኮረብታው ጫፍ እና በምሥራቅ ዳገት ላይ ይገኛሉ። ይህ ተራራ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸ ብዙ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ቦታ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ፣ ስለ ዓለም ፍጻሜና ስለ ዳግም ምጽአት በዚህ ተራራ ላይ ተናገሯል። (ማቴ.፳፬፥፫) በዚሁ ተራራ ላይ ወደ ሰማይ ዐርጓል። በዚሁ ተራራ ላይ ቀን በከተማና በገጠር ሲያስተምር ውሎ ሌሊት የሚያድርበት የኤሌዎን ዋሻ ይገኛል። በኋለኛው ምጽአቱ በዚሁ ቦታ እንደሚገለጥ ትንቢት ተነግሯል። (ሉቃ.፳፬፥፶፣ዘካ.፲፬፥፫-፭)

የዓቢይ ጾም እኩሌታ ላይ ያለው ሰንበት በዚህ ተራራ ተጠርቷል። ይህንን ዕለት የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የዳግም ምጽአት አድርጎ መዝሙሩን ጽፏል። በዚህ ተራራ ላይ «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት»  ተብሎ እንደተጻፈው ለደቀ መዛሙርቱ የዳግም ምጽአቱን፣ የዓለምን ፍጻሜና የትንሣኤ ሙታንን፣ ትምህርት በሰፊው ስላስተማረ በዓሉ በተራራው ስም ተሰይሟል።(ማቴ.፳፬፥፫)

ከዕለታት አንድ ቀን ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሥነ ሕንፃ በትኩረት እያንዳንዱን ነገር በመመልከት አደነቁ። ጧት በጸሎት ጊዜ ጸሎታቸውን አድረሰው ሲጨርሱ የጧት ፀሐይ አርፎበት ያሸበረቀውን ቤተ መቅደስ ውበቱን አስተውለው የትኛው ጥበበኛ እንዳሠራው እየተነጋገሩ ጌታችንንም አብሮ እንዲያደንቅ ሲጠብቁ እርሱ ግን ያልጠበቁትን ነገር ተናጋረ። ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ፣ አያይዞም ከሞት በኋላ ተነሥቶ እንደሚያርግና ነገር ግን ዓለምን ለማሳለፍ ዳግም እንደሚመጣ ወደፊት የሚሆኑ ምሥጢራትን እንዲሁም በቤተ መቅደሱና በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ትንቢት ነገራቸው። ይህም ነገር ዕረፍት ስለነሣቸው ወደ ደብረ ዘይት ከተሻገሩ በኋላ በሰፊው እንዲገልጽላቸው ጠየቁት። በዚህ ክፍል እንደምናየው ጥያቄያቸው ዕለትና ምልክት ነው፤ ወይም «መቼ» እና «ምን» የሚል ነው። የቤተ መቅደሱ መፍረስ መቼ ይሆናል? የዓለም መጨረሻና የመምጣትህስ ምልክቱ ምንድን ነው? ጌታችንም በጥያቄያቸው ላይ ብቻ አተኩሮ ሰፊ መልስ ሰጥቷቸዋል።

መቼ ይሆናል ላሉት የመጀመሪያው ጥያቄ «ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም (ሰውም) ቢሆን የሚያውቅ የለም» ሲል አጭር መልስ ሲሰጥ፣ ስለ ሁለተኛው ጥያቄም መቀበል ቢከብዳቸውም በማስጠንቀቂያዎች፣ በምክሮች፣ በማጽናኛዎችና በምሳሌዎች አስተምሯቸዋል። (ማቴ.፳፬፥፴፮)

የዳግም ምጽአት ምልክቶቹ፦

፩.ሐሰተኞች ክርስቶሶች

ጌታችን ኢየሱስ በአንደኛ ደረጃ የተናገረው ምልክት በተለያዩ ወቅቶችና ሀገራት ብዙ ሐሰተኛ ክርስቶሶች እንደሚነሡ ነው። የጌታችን ቃል አይቀርምና ከዚህ ቀደም ብዙ ሰዎች «እኔ ክርስቶስ ነኝ» በማለት ተነሥተው ነበር።  በዮሐንስ ራእይ ላይ ዋናው አውሬ ተብሎ የተጠቀሰውና በቅዱስ ጳውሎስ «የዐመፅ ሰው እርሱም የየጥፋት ልጅ» የተባለው ብዙ ጥፋትና መከራ የሚያደርሰው ባለ ፮፷፮ (ስድስት ስድሳ ስድስት) መለያ ምልክቱ ሐሳተኛ ክርስቶስ እስኪገለጥ ደረስ መንገድ ብዙ ሐሰተኞች ክርስቶሶች ተነሥተዋል። በእውነተኛው ንጉሥ ክርስቶስ ዳግም መምጣት የሚደመሰሰው ሐሳዊ መሲሕ የመጨረሻውና ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚወጋ የታላቁ መከራ ፈጻሚና አስፈጻሚ ይሆናል። ጌታችን እስኪመጣ ድረስ እንዳንሰናከል አስቀድሞ «ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ … በዚያን ጊዜ ማንም እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ»  ሲል ያስጠነቀቀን ለዚህ ነው።(ራእ. ፲፫፥ ፭፣፳፫)

በሀገራችንም ኢትዮጵያ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንገሥት «እኔ ክርስቶስ ነኝ»  የሚል ሐሳዊ (ሐሰተኛ) ክርስቶስ ተነሥቶ እንደነበር በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቧል። ይህ ሐሳዊ ልክ እንደ እውነተኛው ክርስቶስ ፲፪ ሐዋርያት፣ ፸፪ አርድእትና ፴፮ ቅዱሳት አንስትን ክርስቶስ እንደሆነ በመናገር በየሥፍራው ሲንቀሳቀስ ንጉሡ አስቀርበው «አንተ ማን ነህ?» ቢሉት በድፍረት «እኔ ክርስቶስ ነኝ» አላቸው። ንጉሡም «ክርስቶስማ ከድንግል ማርያም ተወልዶ አስተምሮ፣ ተሰቅሎ፣ ዓለምን አድኖ ከሞት ተንሥቶ ዐርጓል፤ ዳግም ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል፤ አንተ ግን ማነህ?» አሉት፤ እርሱ ግን «አዎ ትክክል ነው። ከዚህ ቀደም ከቤተ እሥራኤል ከምትሆን ከድንግል ማርያም ተወልጄ፣ አስተምሬ፣ ተሰቅየ፣ ሙቼ፣ ተነሥቼ ዐርጌ ነበር፤ አሁን ድግሞ ጥቁሮች አፍሪካውያን ባይታወር አደረገን እንዳይሉኝ ከእናቴ ከድንግል መርዐተ ወንጌል ለጥቁሮቹ ዳግም ተወልጄ ነው» አላቸው። ንጉሡም «ሰይጣን በሰው እያደረ እንዴት ይጫወታል» ብለው በሰይፍ አስቀጡት፤ ተካታዮቹም ተበተኑ ይባላል።

፪.ጦርነት

ጦርነት ቀደምት የነበረ፣ በአሁኑ ጊዜ ዘመን በብዛት የተከሰተ ነገር ግን  በተለይ በዚህ ጊዜ በብዙ ሀገራት የተካሄድ ነው፡፡ ጦርነት በቀደምት ዘመናት ሴቶችን፣ አቅመ ደካማ ሺማግሌዎችንና ሕፃናትን ለእልቂት የማያጋልጥ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ጦርነት ማንንም የማይለይ፣ ለማንም የማይራራ፣ የሁሉን ደም የሚያፈስና እጅግ አስከፊ ሆኗል። ይህንንምም ጌታችን የዳግም ምጽአቱን ምልክት ለጠየቁት ለደቀ መዛሙርቱ ሁለተኛ ምልክት አድርጎ «ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና»  ሲል ተናግሯል። (ማቴ.፳፬፥፮)

፫.ረኃብ

ረኃብ ሰዎችን በአስከፊና በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ የሚከት አሳዛኝ ክስተት ነው፤ ስለ ረኃብ ወሬ በሀገራችንም ኢትዮጵያ ጭምር የሰማነውና ያየነው በመሆኑ የገንዘብ አቅም ያለው ረኃብተኞችን ለማብላት እና ለማጠጣት የሌለው ደግሞ በጸሎት ለመርዳት ጥሯል፡፡ ነገር ግን ይህ ሰው ሰራሽ ችግር ለጠላቶቻችን መሳለቂያ አድርጎን ይኖራል። በተለይ የተፈጥሮ ችግር ሳያጋጥመን ሰዎች ባመጣነው ችግር በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ለአስቸኳይ ምግብ ርዳታ የተጋለጠበት ሁኔታ ያሳዝናል። ይህም ዓይነት በጥል፣ በተንኮልና በጭካኔ ሰዎች የሚፈጥሩት ችግር የምጽአት ሦስተኛ ምልክት ሆኖ በጌታችን ለደቀ መዛሙርት ተነግሯል፤ «ረሀብም ቸነፈርም በልዩ ልዩ ሥፍራ ይሆናል» እንዲል። (ማቴ.፳፬፥፯)

፬. የመሬት መንቀጥቀጥ

የመሬት መንቀጥቀጥ ባለፉት ዓመታት በርካታ ጉዳት በተለያዩ ሀገሮች እንዳደረሰ የሚዘንጋ አይደለም። በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ በዘመናት በተለያዩ ሀገሮች የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈና በርካቶችን ቤት ንብረት አልባ ያደረገ የመሬት መንቀጥቀጥ በሄይቲ፣ በታይዋን፣ በቱርክ፣ በፊልፕንስ፣ አንዲሁም በሌሎች ሀገራት ተከሥቷል። ይህም ለደቀ መዛሙርቱ የዓለም ፍጻሜ ምልክት የማግኘት ጥያቄ የተሰጠው «የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል» ተብሎ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ፍጻሜ ምልክት ተደርጎ የተነገረው ቃል አይቀርምና እየሆነ ነው። (ማቴ.፳፬፥፯)

፭. የክርስቲያኖች መከራ

የክርስቲያኖች መከራ እየጀመረ ይመስላል። ሰይጣን ኢቴስቶችን፣ እስላሞችንና አይሁድን በመጠቀም በክርስቲያኖች ላይ ከምንጊዜውም በላይ ችግር መፍጠር የጀመረበት ጊዜ ነው። በአውሮፓ የክርስቲያኖች ጥያቄ ቶሎ የማይመልስበት ጊዜ ሆኗል፤ የቤተ ክርስቲያንን ጥያቄ ለማስተናገድም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ፈቃደኛነታችውን እያጡና ይህንን ወንጀላቸውን ለመሸፈንም በሕግ አንቀጽ እየፈጠሩለት ይታያሉ። «በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችሁማል፤ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ» ተብሎ እንደተጻፈው በሃይማኖት ጸንቶ መኖር እንደኋላ ቀርነት፣ ከሐዲነት እንደተራማጂነትና ሥልጡንነት የሚታይበት ዘመን ላይ እንዳለን ግልጽ ነው። ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተስፋፋ አመለካከት ክርስቲያኖችን ወደ ማግለልና ወደ መወንጀል የሚያድግ መሆኑ ከሚታዩት እኩይ ተግባራት መካከልም ይቆጠራል፡፡ (ማቴ.፳፬፥፱)

፮. ሐሰተኞች ነቢያት

በዲያብሎስ መንፈስ ምትሐታዊ አሠራርን እያሳዩ፣ አይቻላቸው እንጂ ቢቻላቸው የተመረጡትን ሳይቀር የሚያስቱ «ነቢያት ነን» የሚሉ ብዙዎች ደፋሮች እንዲመነሡ ጌታችን ስድስተኛ የዳግም ምጽአቱ ምልክት አድርጎ ጠቅሷቸዋል። በአሁኑ ዘመን በሀገራችንም «ነቢያት ነን» የሚሉ አጭበርባሪዎች እንደ አሸን ፈልተዋል።

እነዚህም በነቢይ ኤልያስ እንዲሁም በነቢዩ ኤልሣዕ ስም እያጭበረበሩና እየዋሹ በምትሐታዊ አሠርራር የሚያስቱ ሐሰተኞች እንደሚነሡ ሌላው የዳግም ምጽአቱ ምልክት ሆኖ ተነግሯል፤ «ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ …ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ … እንግዲህ፦ እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ»  እንዲል። (ማቴ.፳፬፥፲፩፣፳፮) እንግዲህ በዘመናችን በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም በነቢይነትና በሰባኪነት ስም የሚደረገውን የንግድና የርኩሰት እንቅስቃሴ በማስተዋል መከታተልና መጠበቅ ያስፈልጋል።

፯. የፍቅር መጥፋት

ሌላውና አሳዛኙ ጉዳይ የፍቅር መቀዝቀዝ ነው፤ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነውና የሰው ልጅ ፍቅርን ማጣት የለበትም። አሁንም «ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች»  የሚለው ትንቢት እንዳይፈጸምብን ፍቅርን መንከባከብ፣ ማልማትና ማስፈት ይገባል። (ማቴ.፳፬፥፲፪) ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው፤ ፍቅር የመልካምና በጎ ንገር ሁሉ መገኛና ምንጭ ነው። ስለዚህ ሰዎች በፍቅር መኖር አለብን፡፡

፰. የወንጌል መዳረስ

የወንጌል ለዓለም መዳረስ ለደቀ መዛሙርቱ የዳግም ምጽአቱ ምልክቶች ሁነው ከተሰጡት አንዱ ነው። በፍርድ ቀን በክርስቶስ አምኖ እና እምነቱን በሥራ ገልጾ ስለመኖር ሲጠየቅ «አልሰማሁም፤ አላየሁም፤ አላወኩም» የሚል ከኃጥአን ጋር ይፈረድበታል፤ «ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል» ተብሎ እንደተነገረው በሁሉም ቤት ወንጌል ይሰበካል፡፡ (ማቴ.፳፬፥፲፬)

በመሆኑም በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዕለት «እናንተ የአባቴ ቡሩካን ኑ፥ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ» እንድንባል ቅዱስ ቃሉን ሰምተን፣ አምነንና ታምነን እስከ መጨረሻው በሕገ እግዚአብሔር መመራትና በበጎ ምግባር በቅድስና ሕይወት ልንኖር ይገባል፡፡  (ማቴ.፳፭፥፴፬)

በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን ርስተ መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ የአምላችን እግዚአብሔር ርዳታ አይለየን፤ አሜን፡፡