ዘወረደ

መምህር አብርሃም በዕውቀቱ
የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት፤ ዘመነ አዳም

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት ‹ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው፡፡ ይህም የአምላካችን ሰው መሆን ያመለክታል፡፡ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም ካለው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በመነሣት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዚህ ዕለት ምስባክ ‹‹አዳምን ለማዳን ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤ የሰማይን ሥልጣን ያለው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም አላወቁም›› ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ ይህም ድርሰት በቤተ ክርስቲያናችን የጾም መጀመሪያ የሆነው ዕለተ ሰንበት ዋዜማ፣ መግቢያ (መሐትው) ሆኖ ከዋዜማ በፊት ምንጊዜም በየዓመቱ ይቆማል፤ ይዘመራል፤ ይመሰገናል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ የሳምንቱ ስያሜ ከዚህ የተወሰደ ነው፡፡ እንዲሁም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን የጀመረው፣ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ሰው በመሆን፣ በዮርዳኖስ ተጠምቆ በማስተማር እንደሆነ ሁሉ የመጀሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡

በዚህ ሳምንት በተለይም እሑድና ሰኞ የሚነገሩት ውዳሴያት ከመጻሕፍተ ኦሪትና ነቢያት የተወሰዱ ናቸው፡፡ በዚህ ሰንበት ዕለትም በቤተ ክርስቲያናችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ከሰማይ ስለመውረዱ የሚነገርበትና የሚዘመርበት በመሆኑ ‹‹ዘወረደ›› ተብሏል፡፡ በዚህ ዕለት የሚነበበው የወንጌል ክፍል ‹‹ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ቃል የተናገረው ስለ ሰማያዊው ምሥጢር ለኒቆዲሞስ ባስተማረበት ጊዜ ነበር፡፡(ዮሐ.፫፥፲፫)

ለመሆኑ ‹‹ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም›› ማለት ምን ማለት ነው? ይህንን ጥቅስ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም ባለመረዳት ለክህደታቸው የሚመች የመሰላቸውን ቃል እየመዘዙ ክደው የሚያስክዱ፣ ተጠራጥረው የሚያጠራጥሩ መናፍቃንም በአላዋቂ አዕምሮ፣ በኢአማኒ ልቦና ያለ አውዱ በመጥቀስ በተለያዩ ቅዱሣት መጻሕፍት የተመሠከሩ፣ በታሪክ የታወቁ የቅዱሣን ሰዎችን ዕርገት እንዲሁም የቅዱሳን መላእክትን ለተልእኮ ከሰማይ ወደ ምድር፣ ከምድር ወደ ሰማይ መውረድና መውጣት ለመቃወም ይጠቀሙበታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ግን የቅዱሳን ሰዎችን ዕርገትና የቅዱሳን መላእክትን ለተልእኮ መውረድና መውጣት ያለጥርጥር ያስረዳናል፡፡ እኛ የሐዋርያትን ፈለግ የምንከተል ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ግን ከቅዱሳን መካከል ነቢዩ ኤልያስንና ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክን ጨምሮ የተወሰኑ ቅዱሳን ሞትን ሳይቀምሱ ማረጋቸውን፣ ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን ጸሎትና የእግዚአብሔርን የማዳን ብሥራት ይዘው ከሰማይ ወደ ምድር፣ ከምድር ወደ ሰማይ መመላለሳቸውን፣ ሌሎች ቅዱሳንም በሥጋ ተነጥቀው (ዐርገው) የሰማያትን ምሥጢር በተዓምራት ማየታቸውን፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግልም በልጇ ኃይልና ሥልጣን ከሞት ተነሥታ ማረጓንና በሰማያት፣ በሰማያዊ መዓርግ በልጇ ቀኝ መቆሟን እናውቃለን፤ እናምናለን፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ‹‹ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም›› የሚለው ቃል ምሥጢሩ ምንድን ነው? ሊቃውንት አባቶች እንዳስተማሩት ይህ የጌታችን ቃል የሚከተሉትን አምስት ነጥቦች ያስረዳል፡፡

ሁለተኛም ሳምንቱ ሙሴኒ በመባል ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ለማዳን ከሰማይ መውረዱንና በመስቀል መሰቀሉን ስለሚያወሳ ነው፡፡

በተጨማሪም ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ በ፯፻፲፬ ዓ.ም ሕርቃል (ኤራቅሊየስ) የቤዛንታይን ንጉሥ ነበረ፡፡ ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበት ምክንያት በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታችን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ እርሱ ወደፋርስ ዘመቶ መስቀሉን ከእነርሱ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡

ሕርቃል ከፋርሶች ጋር ከመዋጋቱ በፊት ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ነፍስ የገደለ ሰው እስከ እድሜ ልኩ ይጹም ብለው ሥርዓት ሠርተዋልና ጾሙን ፈርቶ ስለነበር በኢየሩሳሌም የነበሩ ምእመናን አሳቡን ደግፈው ‹‹አንተ ጠላታችንን አጥፋልን፣ መስቀሉን አስመልስልን እንጂ የአንድ ሰው እድሜ ቢበዛ ሰባ ሰማንያ ነው፡፡ ጾሙንአምስት አምስት ቀን ተከፋፍለን እኛ ተከፋፍለን እንጾምልሃለን›› ብለው ጾመውለታል፡፡

ይህንን መሠረት በማድረግ ያላወቁት አንድ ጊዜ ጾመው ትተውታል፡፡ ያወቁት ግን ቀድሞም ሐዋርያት ጾመውታል ብለው ሥርዓት አድርገው በዓመት በዐቢይ ጾም መጀመሪያ ላይ ጾመ ሕርቃል እያሉ የሚጾሙት ሆነዋል፡፡ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን ይህንን መሠረት በማድረግ በጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የመጀመሪያውን ሳምንት ጾመ ሕርቃል በሚል ስያሜ ሰማይ እንዲጾም አድርጋለች፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር መጋቢት ፲)

የቤተ ክርስቲያናችን ታሉቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ በዘወረደ ጾመ ድጓው ሰንበት ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወት ላለው ነገር ሁሉ ጸጥታና ሰላም የሰፈነባት የዕረፍት ቀን ስለመሆኗ ‹‹አዘዞ እግዚአብሔር ለሙሴ ወይቤሎ ሰብዕከ ወላህምከ ወኲሉ ቤትከ ያዕርፍ በሰንበት፤እግዚአብሔር ሙሴን ሕዝብህ የከብትህ መንጋህ ቤተሰብህ ሀሉ በሰንበት ቀን ከድካማቸው ይረፉ በማለት አዘዘው›› ይላል፡፡ በዚህም ዘመነ ጾም፣ ወይም ጾመ ሙሴ ይባላል፡፡ (ዘፀ.፳፥፲፣፳፫፣፲፪፣ ጾመ ድጓ)

በጾመ ድጓው ዘወረደ እየተባለ የሚታወቀው፣ በጾመ ዐርባው ወቅት በተለይም በመጀመሪያው ሳምንት የሚገኘው ያሬዳዊ ድርሰት በነግህ፣ በሠለስት፣ በቀትርና በሠርክ እንዲሁም ቅዳሜና እሑድ በሌሊት የሚዘመር ነው፡፡ በውስጡም የያዘው ፍሬ ሐሳብ፣ የጾምን፣ የጸሎትን፣ የምጽዋትንና የፍቅርን ጠቃሚነት አጉልቶ የሚያስተምር ነው፡፡

በዚህ በጾም ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት በአብዛኛው ከቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ውስጥ የሚዘመረው ምዕራፍ የተባለው ነው፡፡ ምዕራፍ የተባለበት ምክንያትም በየመዝሙራቱ መካከል ሃሌታና ድጓ እያስገባ ለመዝሙሩ ማረፊያ ስላበጀለት በዚህ ምክንያት ምዕራፍ የሚል ስያሜ ሊያገኝ ችሏል፡፡ ይህ የዜማ መጽሐፍ በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ይከፈላል፡፡ ይኸውም የዘወትር ምዕራፍና የጾም ምዕራፍ በመባል ይታወቃል፡፡ የዘወትር ምዕራፍ የሚባለው በዓመቱ ውስጥ ባሉት ቀናት ውስጥ ሳምንታትና በዓላት ሁል ጊዜ በአገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን፣ የጾም ምዕራፍ የሚባለው ደግሞ በጾመ ዐርባ ብቻ ለአገልግሎት የሚውል ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዐሥሩ ምህላት አርዕስተ ምህላ በዚሁ ክፍል ይካተታል፡፡ የምዕራፍ ቅንብር ከመዝሙረ ዳዊት፣ ከድጓና ከጾመ ድጓ ጋር የተቀናጀ ነው፡፡ የትምህርት አሰጣጡም እንደ ድጓው ወይም እንደ ዝማሬ መዋሥዕቱ መጽሐፍ ተዘርግቶ ሳይሆን በቃል የሚጠናና የሚወሰን ነው፡፡ ስለሆነም ምዕራፍን ለመማር ፻፶ መዝሙረ ዳዊትን፣ ከነቢያት ፲፭ ምዕራፎችንና አምስት መኃልያተ ሰሎሞንን በቃል ሸምድዶ መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ወይም ግድ ነው፡፡

ጾምን መጾም የፈቃድ ብቻ ሳይሆን የትእዛዝም ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ኢዩኤል ‹‹ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምህላ፤ጾምን ያዙ አጽኑ ምሕላንም ዐውጁ ሸማግሌዎቹን ከፈጣሪያችን ቤት ሰብስባችሁ በአንድነት ሁናችሁ ወደ እግዚአብሔር ጩሁ (/ለምኑ)›› ብሏል፡፡ (ኢዮ.፩፥፲፩፣ ፪፣፲፪፣፲፭-፲፮) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ወኲኑ ላዕካነ፣ ለእግዚአብሔር በጾም ወበንጽሕ፤ በጾም፣ በንጽሐና ተወስናችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ›› ብሏል (፪ኛቆሮ.፮፥፬-፮)

ጾም ከሌለ ወይም ተገቢ ካልሆነ ጌታችን በምትጾሙበት ጊዜ ‹‹እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ስለ ጽድቅ የሚራቡ የሚጠሙ ንዑዳን ክብራን ናቸው›› ለምን አለ? (ማቴ.፭፥፮፣፲፮)፡፡ ነቢዩ ዳዊትም ሰውነቴን በጾም አሳመምኳት፤ በቀጠና፣ በሰልት አደከምኳት›› ለምን አለ፤ (መዝ.፴፬፥፷፬፣ዳን. ፱፥፫-፬፣፲፬፥፭)

ነቢዩ ሚኪያስ ‹‹ሐዋርያት ሙሸራውን ከእነርሱ ለይተው የሚወስዱበት ጊዜ ይመጣል፤ ያን ጊዜ ይጾማሉ›› ያለውን የጌታችን ኢየሱስ ቃል መሠረት በማድረግ ክርስቶስ በሞት ከተለያቸው በኋላ ጾመዋል፡፡ ጾምንም ሠርተዋል (ሐዋ.፲፫፥፫)፡፡ ሠለስቱ ምዕትም ሐዋርያት የጾሙትንና እንዲጾም የወሰኑትን መጾም እንደሚገባ በማመን ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውን አጽዋማት እንዲጾሙ መወሰናቸው ይህን የጌታችንን ቃል መሠረት በማድረግ ስለሆነ የትእዛዝ መሆኑን ተገንዝበን መጾም አለብን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሠራዔ ሕግ እንደመሆኑ አርባ ቀን አርቦ ሌሊት ጾመ እንጂ እርሱ ሳይጾም ጾሙ አላለንም፡፡ (ማቴ.፬፥፪)

ጾሙን በሰላም አስጀምሮ በሰላም ያስፈጽመን፤ አሜን፡፡