ዘመነ ክረምት – ክፍል አራት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በክፍል ሦስት ዝግጅታችን ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፱ ቀን ድረስ ያለው ሁለተኛው ክፍለ ክረምት መብረቅ፣ ነጐድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል እንደሚባል በማስታወስ ከወቅቱ ጋር ተያያዥነት ያለው ትምህርት አቅርበን ነበር፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ቀጣዩን ክፍል ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

፫. ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ

ከነሐሴ ፲ እስከ ፳፯ ቀን (ከማኅበር እስከ አብርሃም) ድረስ ያለው ሦስተኛው የዘመነ ክረምት ክፍለ ጊዜ (ንዑስ ክፍል) ‹ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ› ይባላል፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ ብቻ ሳይኾን የሰማይ አዕዋፍ፣ የምድር አራዊትና እንስሳት ሳይቀሩ እግዚአብሔርን አምነው በተስፋ መኖራቸው የሚዘከርበት፤ በተጨማሪም በዝናም አማካይነት በዙርያቸው ያለው የውኃ መጠን ከፍ ሲልላቸው ደሴቶች ዅሉ በልምላሜ ማሸብረቃቸው የሚነገርበት ክፍለ ክረምት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ዅሉ በእነዚህ ምሥጢራት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥለን ስለ ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያትና ዓይነ ኲሉ በቅደም ተከተል ማብራሪያ ለመስጠት እንሞክራለን፤

ዕጕለ ቋዓት

‹ዕጕል፣ ዕጓል› ማለት ‹ልጅ›፤ ‹ቋዕ› ደግሞ ‹ቍራ› ማለት ነው፡፡ ‹ቋዕ› የሚለው ቃል በብዙ ቍጥር ሲገለጽም ‹ቋዓት› ይኾናል፡፡ በዚህ መሠረት ‹ዕጕለ ቋዓት› የሚለው የግእዝ ቃላት ጥምረትም (ሐረግ) ‹የቍራ ልጆች (ግልገሎች፣ ጫጩቶች)› የሚል ትርጕም አለው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን የቍራ ጫጩቶች አስተዳደግ ከምእመናን ሕይወት ጋር ተነጻጽሮ ይነገራል፡፡ ይህም እንዲህ ነው፤ የቍራ ጫጩት ከእንቍላሉ ፍሕም መስሎ ይወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ እናትና አባቱ ባዕድ ነገር የተወለደ መስሏቸው ትተውት ይሸሻሉ፡፡ እርሱም በራበው ጊዜ ምግብ ፍለጋ አፉን ይከፍታል፡፡ በዚህ ሰዓት ርጥበት የሚፈልጉ ተሐዋስያን ወደ አፉ ይገባሉ፡፡ ከዚያም አፉን በመግጠም ይመገባቸዋል፡፡ እንደዚሁም ተሐዋስያን በአጠገቡ ሲያልፉ በእስትንፋሱ (በትንፋሹ) እየሳበ ይመገባቸዋል፡፡ የቍራ ጫጩት እስከ ፵ ቀን ድረስ እንደዚህ እያደረገ ከቆየ በኋላ ቀስ በቀስ ፀጕር ያበቅላል፤ ከዚህ በኋላ በመልክ እነርሱን እየመሰለ ስለሚመጣ እናት አባቱ ተመልሰው ይከባከቡታል፡፡ ይህ የቍራ ዕድገትና ለውጥም እግዚአብሔር ፍጡራኑን የማይረሳ አምላክ እንደ ኾነ፣ ፍጥረቱንም በጥበቡ እየመገበ እንደሚያኖራቸው ያስገነዝበናል፡፡

ቅዱስ ዳዊት ይህን የቍራ የዕድገት ደረጃና የእግዚአብሔርን መግቦት በተናገረበት መዝሙሩ ‹‹ወሐመልማለ ለቅኔ ዕጓለ እመሕያው ዘይሁቦሙ ሲሳዮሙ ለእንስሳ ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውዕዎ፤ ለሰው ልጆች ጥቅም ለምለሙን የሚያበቅል፤ ለእንስሳትና ለሚለምኑት የቍራ ጫጩቶች ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ ነው›› ሲል ይዘምራል (መዝ. ፻፵፮፥፱)፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜያቸው እንደ ገለጹት ይህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አምላክ ለእርሱ ለሚገዙ የሰው ልጆች እኽሉን፣ ተክሉን የሚያበቅልላቸው፤ ለእንስሳቱና ለአዕዋፍ ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ እንደ ኾነ ያስረዳል፡፡ ‹‹… ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውዕዎ፤ … ለሚለምኑት ለቍራ ጫጩቶች›› የሚለው ሐረግም አዕዋፍ፣ ምግብ እንዲያዘጋጅላቸው እግዚአብሔርን እንደሚለምኑትና እርሱም ልመናቸውን እንደሚቀበላቸው ያስገነዝበናል፡፡ በመዝሙረ ዳዊት አንድምታ ትርጓሜ እንደ ተጠቀሰው ‹‹ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውዕዎ›› የሚለው ሐረግ ‹‹… እለ ኢይጼውዕዎ›› ተብሎ ሊነገር ይችላል፤ ይህም የቍራ ጫጩቶች አፍ አውጥተው ባይነግሩትም እንኳን እርሱ ፍላጎታቸውን ዐውቆ የዕለት ምግባቸውን እንደሚያዘጋጅላቸው የሚያመለክት ምሥጢር አለው፡፡ ምሥጢሩን ወደ እኛ ሕይወት ስናመጣውም እግዚአብሔር አምላክ ስሙን የሚጠሩትንም የማይጠሩትንም፤ ‹‹የዕለት እንጀራችንን ስጠን›› እያሉ የሚማጸኑትንም የማይጸልዩትንም በዝናም አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ ሳያደላ ዅሉንም በቸርነቱ እንደሚመግባቸው ያስተምረናል፡፡ ‹‹… እርሱ ለክፎዎችና ለደጎች ፀሐይን ያወጣልና፤ ለጻድቃንና ለኃጥአንም ዝናምን ያዘንማልና፤›› እንዳለ ጌታችን በወንጌል (ማቴ. ፭፥፵፭)፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቍራዎችንና የሌሎችንም አዕዋፍ አኗኗር ምሳሌ በማድረግ ስለ ምድራዊ ኑሮ ሳይጨነቁ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ መኖር እንደሚገባን በቅዱስ ወንጌል አስተምሮናል፡፡ እንዲህ ሲል፤ ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፡፡ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና፡፡ ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱምም፡፡ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፡፡ እናንተ ከወፎች ትበልጡ የለምን? … አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም … ዛሬ ያለውን፣ ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የኾነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከኾነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ! እናንተንማ ይልቁን እንዴት? … የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፤ አታወላውሉም፡፡ ይህንስ ዅሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፡፡ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል፡፡ ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ፤ ይህም ዅሉ ይጨመርላችኋል፤›› (ሉቃ. ፲፪፥፳፪-፴፩)፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹… ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ …›› የሚለው ኃይለ ቃል እንደ እንስሳት ሳትሠሩ እግዚአብሔር ምግብ እንዲሰጣችሁ ለምኑት ማለት እንዳልኾነ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ኃይለ ቃሉን ለማብራራት ያህል የሰው ልጆች ከእንስሳት ከምንለይባቸው ባሕርያት አንደኛው ሠርተን መብላት መቻላችን ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም የታታሪነትንና የሠርቶ ማደርን ጥቅም እንጂ ሳይሠሩ ተቀምጦ መብላትን አላስተማሩንም፡፡ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሰው ልጅ እጁ ከሥራ መለየት እንደማይገባው ተገልጿል፡፡ ለምሳሌ አባታችን አዳም ከሳተ በኋላ በምድር ጥሮ፣ ግሮ እንዲኖር ተፈርዶበታል፡፡ ይህንም ‹‹… የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ፡፡ ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ›› ከሚለው ኃይለ ቃል ለመረዳት እንችላለን (ዘፍ. ፫፥፲፰-፲፱)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እግዚአብሔር አማላክ አዳምን ከዔደን ገነት ያስወጣው የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ መኾኑም ተጠቅሷል (ዘፍ. ፫፥፳፫)፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ ሠራቶ አዳሪ ፍጥረት መኾኑን የሚያመላክት ምሥጢር ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹አንተ ታካች! እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት ትተኛለህ፤ ጥቂት ታንቀላፋለህ፡፡ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፡፡ እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፣ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል›› በማለት የሰው ልጅ እንቅልፍን (ስንፍናን) ካበዛና ካልሠራ ክፉ ድህነት እንደሚመጣበት ተናግሯል (ምሳ. ፮፥፱-፲)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ‹‹ከእናንተ ሊሠራ የማይወድ አይብላ›› በማለት ሥራ የማይወድ ሰው ምግብ መሻት እንደሌለበት አስረድቷል (፪ኛ ተሰ. ፫፥፲)፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ስንፍናን የሚያወግዝ፣ ሥራን ደግሞ የሚያበረታታ ኾኖ ሳለ ‹‹ለምንድን ነው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ …› ሲል ያስተማረው?›› የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ያህል ቃሉ አትጨነቁ ማለቱ ‹‹ለሥጋዊ ጉዳይ ቅድሚያ አትስጡ፤ እየሠራችሁ እግዚአብሔርን በጸሎት ጠይቁ›› ሲለን ነው፡፡ የሰው ልጅ ሠራተኛ ፍጥረት ቢኾንም ዝናም አልጥልለት ሲል፤ የዘራበት መሬት ሳያበቅል ሲቀር፤ የወር ደመወዙ ሲዘገይ፤ እኽል የሚሸምትበት ገንዘብ ሲያጣ፤ ወዘተ. በመሳሰሉት ፈተናዎች ውስጥ በኾነ ጊዜ ምን ልበላ ነው? ልጠጣ ነው? ልጆቼ እንዴት ሊኾኑብኝ ነው? ዛሬን እንዴት ላልፍ ነው? በሚሉትና በመሳሰሉት የጭንቀትና የተስፋ መቍረጥ ስሜቶች ሳይያዝ የዕለት ጕርሱን፣ የዓመት ልብሱን ይሰጠው ዘንድ የጠፋውን ዝናም ማምጣት፤ የደረቀውን ዘር ማለምለም፤ ባዶ የኾነውን ቤት መሙላት የሚቻለውን እግዚአብሔርን (እርሱን) በእምነት ኾኖ በጸሎት ይጠይቀው ለማለት መድኀኒታችን ክርስቶስ ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ›› ብሎናል፡፡ ሐሳቡ ሲጠቃለል የሰው ልጅ ይርበኛል፣ ይጠማኛል ማለቱን ትቶ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩን በማሰብ ዓቅሙ በሚችለው ዅሉ እንዲሠራ፤ የጐደለውን እንዲሞላለት ደግሞ ጸሎቱን ወደ ፈጣሪው እንዲያቀርብ ሲያስረዳ ጌታችን ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት፣ ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ›› በማለት አስተምሯል፡፡

ይህም የሰው ልጅ ለሚበላው፣ ለሚጠጣው መጨነቅ እንደማይገባውና እየሠራ ሙሉ ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ እንዳለበት፤ ከዅሉም በላይ ለምድራዊው ኑሮው ድሎት ሳይኾን ሰማያዊውን መንግሥት ለመውረስ መትጋት እንደሚጠበቅበት ያስገነዝባል፡፡ ስለዚህም አምላካችን እንዳስተማረን ስለምንበላውና ስለምንጠጣው ሳይኾን ስለ በጎ ምግባርና ስለ ዘለዓለማዊው መንግሥት መጨነቅ ይገባናል ማለት ነው፡፡ ራሳችንን ለመንግሥተ እግዚአብሔር በሚያበቃ የጽድቅ ሥራ ካስገዛን ለሥጋችን የሚያስፈልገን ምድራዊ ዋጋም አብሮ ይሰጠናልና፡፡ ‹‹ወዘእንበለ ንስአሎ ይሁብ ፍትወተነ ዘእምፈቃዱ፤ ሳንለምነው ልባችን የተመኘውን በፈቃዱ የሚሰጠን እርሱ ነው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡ ‹‹ይሰጠዎ ወይሰምዖ ጸሎቶ ለኵሉ ለዘሰአሎ እግዚአ ለሰንበት አምላከ ምሕረት ያርኁ ክረምተ በበዓመት ይሰምዑ ቃሎ ደመናት፤›› በማለት ቅዱስ ያሬድ በዘመነ ክረምት መዝሙሩ ያቀረበው ምስጋናም ይህንኑ እውነት የሚያንጸባርቅ ኃይለ ቃል ነው፡፡ ትርጕሙም፡- ‹‹እግዚአብሔር አምላክ የለመነዉን ፍጥረት ዅሉ ጸሎት ተቀብሎ ምላሽ ይሰጣል፡፡ የሰንበት (የፍጥረታት) ጌታ እርሱ የምሕረት (የይቅርታ) አምላክ ነው፡፡ የምሕረት አምላክ በመኾኑም በየዓመቱ (በየጊዜው፣ በየዘመኑ) ወርኃ ክረምትን (ወቅቶችን) ያፈራርቃል፡፡ ደመናትም (ፍጥረታትም) ቃሉን ይሰማሉ (ትእዛዙን ይፈጽማሉ)፤›› ማለት ነው፡፡

ይቆየን

ዘመነ ክረምት – ክፍል ሦስት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ፳፭ ቀን ፳፻፱ .

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ዘርዕ እና ደመናን መነሻ በማድረግ ወቅቱን የሚመለከት ትምህርት ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ዛሬ ደግሞ ቀጣዩን ክፍል ይዘን ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን እንድትከታተሉ በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡

፪. መብረቅ፣ ነጐድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል

ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፱ ቀን ድረስ ያለው ሁለተኛው ክፍለ ክረምት ‹መብረቅ፣ ነጐድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል› በመባል ይታወቃል፡፡ ይኸውም የመብረቅና የነጐድጓድ ድምፅ በብዛት የሚሰማበት፤ የባሕርና የወንዞች ሙላት የሚያይልበት፤ የምድር ልምላሜ የሚጨምርበት ወቅት ነው፡፡ ዘመነ ክረምት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ልምላሜ ቢኖርም በዚህ ክፍለ ክረምት በስፋት ይነገራል፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱ፣ በቅዳሴው የሚቀርበው ትምህርትም የእግዚአብሔርን አምላካዊ ጥበብ የሚያስረዳ እና የወቅቱን ተፈጥሯዊ ሥርዓት የሚዳስስ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በስፋት የሚወሱትን የሁለተኛውን ክፍለ ክረምት ስያሜዎችም እንደሚከተለው ለማብራራት እንሞክራለን፤

መብረቅ እና ነጐድጓድ

‹‹ወገብረ መብረቀ ለጊዜ ዝናም፤ መብረቅን ለዝናም ምልክት አደረገ፤›› (መዝ. ፻፴፬፥፯) በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደ ገለጸው መብረቅ በዝናም ጊዜ የሚገኝ ፍጥረት ነው፡፡ የሚፈጠረውም ውኃ በደመና ተቋጥሮ ወደ ላይ ከተወሰደ በኋላ በነፋስ ኃይል ወደ ምድር ሲወርድ በደመና እና በደመና መካከል በሚከሠት ግጭት አማካይነት ነው፡፡ ነጐድጓድ ደግሞ መብረቅ በሚፈጠርበት ጊዜ የሚሰማው አስፈሪ ድምፅ ነው (ራእ. ፬፥፭)፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የመብረቅ አፈጣጠርን በቅቤ እና በዐረቄ አወጣጥ ይመስሉታል፡፡ ወተት ሲገፋ ቅቤ ይወጣል፤ ልዩ ልዩ የእኽል ዓይነት ከውኃ ጋር ተዋሕዶ በእሳት ሲሞቅ ዐረቄ ይገኛል፡፡ ልክ እንደዚሁ ዅሉ ደመና እና ደመና ሲጋጩም መብረቅ ይፈጠራልና፡፡ የምድር ጠቢባንም ሞቃት እና ቀዝቃዛ አየር ሲጋጩ መብረቅ እንደሚፈጠር ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ላይ ዘመናዊው ትምህርት ከመምጣቱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መብረቅ አፈጣጠር አስቀድሞ ማስተማሩን ልብ ይሏል፡፡

የእነዚህን ፍጥረታት ምሳሌነት ለማስታወስ ያህል መብረቅ እና ነጐድጓድ በእግዚአብሔር መቅሠፍት (ቍጣ) አንድም በቃለ እግዚአብሔር ይመሰላሉ፡፡ መብረቅ ብልጭታውና ድምፁ (ነጐድጓዱ) እንደሚያስደነግጥና እንደሚስፈራ ዅሉ፣ እግዚአብሔር አምላክ መቅሠፍት ሲልክ ወይም ሲቈጣ የሰው ልጅ ይጨነቃል፤ ይረበሻልና፡፡ ‹‹ቃለ ነጐድጓድከ በሠረገላት አስተርአየ መባርቅቲሁ ለዓለም ርዕደት ወአድለቅለቀት ምድር፤ የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበረ፡፡ መብረቆች ለዓለም አበሩ፡፡ ምድር ተናወጠች፤ ተንቀጠቀጠችም፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት (መዝ. ፸፮፥፲፰)፡፡ ይህ የነቢዩ ዝማሬ ግብጻውያን እስራኤላውያንን ከባርነት አንለቅም በማለታቸው የደረሰባቸውን ልዩ ልዩ መቅሠፍትና መዓት የሚመለክት ምሥጢራዊ ትርጕም አለው፡፡ እንደዚሁም እስራኤላውያን የኤርትራን ባሕር በተሻገሩ ጊዜ ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ›› እያሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረባቸውንም ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ እግዚአብሔር አብ ከሰማይ ኾኖ ‹‹የምወደውና የማፈቅረው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱንም ስሙት፤›› በማለት ስለ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት መመስከሩንና ወንጌለ መንግሥተ ሰማያት (ቃለ እግዚአብሔር) በቅዱሳን ሐዋርያት፣ በሰብዓ አርድእት፣ በአበው ሊቃውንት አማካይነት በመላው ዓለም መሰበኩን ያጠይቃል፡፡

ደመና እና ደመና ተጋጭተው መብረቅን እንደሚፈጥሩ፣ የሰው ልጅ ባሕርያተ ሥጋ እርስበርስ ሲጋጩና አልስማማ ሲሉም ልዩ ልዩ ስሜት ማለት ቍጣ፣ ብስጭት፣ ቅንዓት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ የጠባይዕ ለውጦች ይከሠቱና ኀጢአት ለመሥራት ምክንያት ይኾናሉ፡፡ የመብረቅና የነጐድጓድ ድምፅ እንደሚያስፈራው ዅሉ፣ በሥጋዊ ባሕርይ አለመስማማት የተነሣ የሚፈጠሩ የኀጢአት ዘሮችም ፍርሃትንና መታወክን በሰው አእምሮ ውስጥ እንዲመላለስ ያደርጋሉ፡፡ ከዅሉም በላይ በምድርም በሰማይም ቅጣትን ያስከትላሉ፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራል፤›› ሲል ጠቢቡ ሰሎሞን በኀጢአት ምክንያት ስለሚመጣ ፍርሃት የተናገረው (ምሳ. ፳፰፥፩)፡፡ እንግዲህ እኛ የሰው ልጆችም ራሳችንን ከክፉ ዐሳብና ምኞት በመጠበቅ አእምሯችንን ለክርስቲያናዊ ምግባር እና ለመልካም አመለካከት እናስገዛ፡፡ እንዲህ ብናደርግ በምድር በሰላም ለመኖር እንችላለን፤ በሰማይ ደግሞ ዘለዓለማዊ መንግሥቱን ለመውረስ እንበቃለን፡፡ ስለኾነም ባሕርያተ ሥጋችን ተስማምተውልን በጽድቅ ሥራ እንድንኖር ይረዳን ዘንድ እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቀው፡፡

እንደ ሌሎቹ ፍጥረታት ዅሉ መብረቅ እና ነጐድጓድም አስገኛቸውን፤ ፈጣሪያቸውን ልዑል እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፡፡ ‹‹ይሴብሕዎ ሰማያት ወምድር ባሕርኒ ወኵሉ ዘይትሐወስ ውስቴታ፤ ሰማይና ምድር ባሕርም በእርስዋም የሚንቀሳቀስ ፍጥረት ዅሉ ያመሰግኑታል፤›› እንዲል (መዝ. ፷፰፥፴፬)፡፡ ሠለስቱ ደቂቅም ሰማዩም፣ ምድሩም፣ ባሕሩም፣ ወንዙም በአጠቃላይ ፍጥረታት ዅሉ እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግን ሲያስረዱ እንዲህ በማለት ዘምረዋል፤ ‹‹ይባርክዎ ኵሉ ግብረ እግዚእ ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ ኵሉ ማያት ዘመልዕልተ ሰማያት ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ ጠል ወዝናም ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ ቍር ወአስሐትያ ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ በረድ ወጊሜ ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ በረድ ወጊሜ ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ መብረቅ ወደመና ለእግዚአብሔር ስቡሕኒ ውእቱ ወልዑልኒ ውእቱ ለዓለም፤ የጌታ ፍጥረቶች ዅሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል … ከሰማዮች በላይ ያሉ ውኃዎች ዅሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል … ጠል እና ጤዛ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል … ብርድ እና ውርጭ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል … በረድ እና ጕም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል … መብረቅ እና ደመና እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው፤›› (ዳን. ፫፥፴፭-፶፩)፡፡

ይህም እግዚአብሔር በመላእክትም፣ በሰው ልጅም፣ አንድም በትሑታኑም በልዑላኑም፤ በከተማውም በገጠሩም እንደዚሁም በባሕር ውስጥ በሚመላለሱ ፍጥረታት ዅሉ የሚመሰገን አምላክ መኾኑን ያስረዳል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በሰዓታት ድርሰቱ ‹‹… ዘበጸዐዕ ይትነከር ወእመባርቅት ይትአኰት ወይትናበብ በእሳት ድምፀ ነጐድጓዱ በሠረገላት፤ በብልጭታ የሚደነቅ፤ በመብረቆች የሚመሰገን፤ በእሳት ውስጥ የሚናገር፤ የነጐድጓዱም ድምፅ በሠረገሎች ላይ የኾነ እግዚአብሔር ንጹሕ፣ ልዩ፣ ክቡር፣ ጽኑዕ ነው፤›› ሲል ከፍጥረታቱ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የአምልኮ ሥርዓት ገልጾታል፡፡ የማይሰሙ፣ የማይናገሩ፣ የማያዩ ግዑዛን ፍጥረታት እንዲህ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ከኾነ፣ በእርሱ አርአያና አምሳል የተፈጠረው፤ ሕያዊት፣ ለባዊትና ነባቢት ነፍስ ያለችው የሰው ልጅማ ፈጣሪውን እንዴት አልቆ ማመስገን ይጠበቅበት ይኾን?

ባሕር እና አፍላግ

ባሕርና አፍላግ በቃልና በመጠን፣ ወይም በአቀማመጥ ይለያዩ እንጂ ሁለቱም የውኃ ክፍሎች ናቸው፡፡ ‹ባሕር› የግእዝ ቃል ሲኾን ይኸውም በጎድጓዳ መልክዐ ምድር ውስጥ የሚጠራቀም ጥልቅ የውኃ ክምችት ማለት ነው (ዘፍ. ፩፥፲)፡፡ ‹አፍላግ› የሚለው የግእዝ ቃልም የ‹ፈለግ› ብዙ ቍጥር ኾኖ ትርጕሙ ወንዞች ማለት ነው፡፡ ይህም ከውቅያኖስ፣ ከባሕር ወይም ከከርሠ ምድር መንጭቶ ረጅም ርቀት የሚፈስ የውኃ ጅረትን አመላካች ነው (ዘፍ. ፪፥፲፤ መዝ. ፵፭፥፬)፡፡ በዚህ ወቅት የባሕርና የወንዞች መጠን ለዋናተኞች፣ ለመርከብና ለጀልባ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ እስኪኾን ድረስ ከቀድሞው በበለጠ መልኩ በሙላትና በኃይል ይበረታል፤ ከሙላቱ የተነሣም ሰውን፣ ንብረትን እስከ ማስጠም እና እስከ መውሰድ ይደርሳል፡፡

ይህ የባሕር እና የወንዞች ሙላትም የምድራዊ ሕይወት መከራን፣ ሥቃይን፣ ፈቃደ ሥጋን (ኀጢአትን) እና ፈተናን፤ ዳግመኛም በሰው ልጅ ኀጢአት ምክንያት የሚመጣ ሰማያዊም ኾነ ምድራዊ ቅጣትን ያመለክታል፡፡ እንደዚሁም የእግዚአብሔርን የተአምራቱን ብዛት ይገልጻል፡፡ ‹‹ወዓሠርከኒ ውስተ ማይ ብዙኅ ወኢይትዐወቅ ዓሠርከ፤ መንገድህ በባሕር ውስጥ፤ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፤›› እንዳለ መዝሙረኛው (መዝ. ፸፮፥፲፱)፡፡ ይኸውም የእግዚአብሔር መንፈስ በመላው ዓለም ሰፍኖ እንደሚኖርና በሃይማኖት በምግባር ጸንተው፣ ከኀጢአት ተለይተው እርሱን የሚሹ ዅሉ ይቅርታውን እንደ ውኃ በቀላሉ እንደሚያገኙት የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡ ‹‹እስመ ማይ ለኵሉ ርኩብ›› እንዲሉ ሊቃውንት፡፡ እኛም የኀጢአት ባሕር እንዳያሰጥመን፤ የኀጢአት ወንዝም እንዳይወስደን ተግተን ነቅን ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ እንደ ውኃ ለዅሉም የሚፈሰው የእግዚአብሔር ይቅርታው ደርሶን የመንግሥቱ ወራሾች እንኾን ዘንድም ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን እናስገዛ፡፡

ጠል

‹ጠል›፣ ‹ጠለ – ለመለመ› ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲኾን ትርጕሙም ‹ልምላሜ› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ለምግብነት የሚዉሉም ኾኑ የማይዉሉ አብዛኞቹ ዕፀዋት በቅለው፣ ለምልመው የሚታዩበት ጊዜ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹በመከር ወራት የውርጭ ጠል ደስ እንደሚያሰኝ እንዲሁ የታመነ መልእክተኛ ለላኩት ነው፤›› በማለት እንደ መሰለው (ምሳ. ፳፭፥፲፫)፣ ይኼ የዕፀዋት ልምላሜ በጎ ምግባር ባላቸው ምእመናንና በመልካም አገልጋዮች ይመሰላል፡፡ በተጨማሪም ዕፀዋት በዝናም አማካይነት በቅለው መለምለማቸው በስብከተ ወንጌል (ቃለ እግዚአብሔር) ተለውጠው፣ በሃይማኖታቸው ጸንተው፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ተግተው፣ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ተወስነው የሚኖሩ ምእመናንን ሕይወት፤ እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጆች የሚያድለውን ጸጋ እና በረከት ያመለክታል፡፡ ‹‹ወይረውዩ እምጠለ ቤትከ፤ ከቤትህ ጠል ይጠጣሉ (ይረካሉ)፤›› እንዳለ ነቢዩ በመዝሙሩ (መዝ. ፴፭፥፰)፡፡ ይኸውም በቤተ መቅደሱ ዘወትር የሚፈተተውን ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን መቀበል፣ እንደዚሁም የቅዳሴ ጠበሉን መጠጣት የሚያስገኘውን መንፈሳዊ ርካታ ይገልጻል፡፡

በዘመነ ክረምት የሚለመልሙ ዕፀዋት የመብዛታቸውን ያህል በለስና ወይንን የመሰሉ ተክሎች ክረምት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ደርቀው ይቆዩና በበጋ ወቅት ይለመልማሉ፡፡ እነዚህም በመልካም ዘመን ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩና በመከራ ሰዓት ተነሥተው ወንጌልን የሚሰብኩ የሰማዕታት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በለስና ወይንን የመሰሉ ዕፀዋት በዝናም ጊዜ ደርቀው በፀሐይ ጊዜ እንዲለመልሙ፤ ቅዱሳን ሰማዕታትም በምድራዊ ሹመት፣ በሽልማት ወቅት ተሠውረው፤ ሥቃይና ፈተና በሚበረታበት ጊዜ ምድራዊውን መከራ ተቋቁመው ስለ እውነት (ወንጌል) እየመሰከሩ ራሳቸውን በሰማዕትነት አሳልፈው ይሰጣሉና፡፡ ዅላችንንም እንደ ዕፀዋቱ በወንጌል ዝናም ለምልመን መልካም ፍሬ እንድናፈራ የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ይቆየን

ዘመነ ክረምት – ክፍል ሁለት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች፤ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰላምታ እንደምን ሰነበታችሁ? በርኅራኄው እየጠበቀ፣ በቸርነቱ እየመገበ እስከ ዛሬ ድረስ ያቆየን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን! እንደምታስታዉሱት ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ባስተላለፍነው ክፍል አንድ ዝግጅታችን ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ያለው የዘመነ ክረምት ክፍል ስለ ክረምት መግባት፣ ስለ ዘርዕ እና ደመና የሚነገርበት ወቅት እንደ ኾነ በማስገንዝብ ወቅቱን (በዓተ ክረምትን) የሚመለከት አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበን ነበር፡፡ ስለ ዘር እና ደመና የሚያትተውን ቀጣይ ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል፤  

ዘርዕ

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹እለ ይዘርዑ በአንብዕ ወበሐሤት የዐርሩ ሶበሰ የሐውሩ ወፈሩ እንዘ ይበክዩ ወጾሩ ዘርዖሙ ወሶበ የአትዉ መጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ ወጾሩ ከላስስቲሆሙ፤ በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ፡፡ በሔዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው መጡ፤›› በማለት እንደ ተናገረው (መዝ. ፻፳፭፥፭-፮)፣ ይህ ወቅት አርሶ አደሩ በእርሻና ዘር በመዝራት የሚደክምበት፣ የምርት ጊዜውንም በተስፋ የሚጠባበቅበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ የአርሶ አደሩ ድካምና ተስፋም የሰውን ልጅ የሕይወት ጉዞና ውጣ ውረድ እንደዚሁም በክርስቲያናዊ ምግባር የሚወርሰውን ሰማያዊ መንግሥት ያመለክታል፡፡

ምድር ከሰማይ ዝናምን፣ ከምድርም ዘርን በምታገኝበት ወቅት ዘሩን አብቅላ ለፍሬ እንዲበቃ ታደርጋለች፡፡ በምድር የምንመሰል የሰው ልጆችም ከእግዚአብሔር ባገኘነው ጸጋ ተጠቅመን፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት እና ከመምህራነ ቤተ ክርስቲያን የምናገኘውን ቃለ እግዚአብሔር በተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባን ከምድር እንማራለን፡፡ ይህን ካደረግን ዋጋችን እጅግ የበዛ ይኾናል፤ ከዚህም አልፎ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንበቃለን፡፡ የተዘራብንን ዘር ለማብቀል ማለትም ቃሉን በተግባር ለማዋል ካልተጋን ግን በምድርም በሰማይም ይፈረድብናል፡፡ ‹‹ምድርም በእርስዋ የሚወርደውን ዝናብ ከጠጣች፣ ያን ጊዜ ስለ እርሱ ያረሱላትን መልካም ቡቃያ ታበቅላለች፡፡ እሾኽን እና ኵርንችትን ብታበቅል ግን የተጣለች ናት፡፡ ለመርገምም የቀረበች ናት ፍጻሜዋም ለመቃጠል ይኾናል፤›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ገለጸው (ዕብ. ፮፥፯-፰)፡፡

ደመና

እግዚአብሔር አምላካችን የውቅያኖስ እና የሐኖስ ድንበር ይኾን ዘንድ በውኃ መካከል ጠፈርን ፈጥሮ ከጠፈር በታች (በዚህ ዓለም) ያለው ውኃ በአንድ ቦታ እንዲወሰን አድርጎታል፡፡ ከዚያም ከምድር እስከ ብሩህ ሰማይ ድረስ የነበረውን ውኃ ከሦስት ከፍሎ ሢሶውን አርግቶ ጠፈር ብሎ ሰይሞታል፡፡ ከጠፈር በላይ ያለውን ሢሶው የውኃ ክፍል ሐኖስ ብሎታል፡፡ ሢሶውንም ይህንን ዓለም ከሰባት ከፍሎ ሰባተኛውን ዕጣ አጐድጕዶ በዚያ ወስኖ ስሙን ውቅያኖስ ብሎ ጠርቶታል፡፡ የብሱን ክፍል ደግሞ ምድር ብሎ ሰይሞታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከደረቅ ምድር ደረቅ ጢስን፤ ከርጥብ ባሕር ርጥብ ጢስን አስወጥቶ እንደ ጉበት በለመለመች ምድር ላይ ደመናን አስገኝቷል (ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት፣ መዝ. ፻፴፬፥፯)፡፡

ከላይ እንደ ተጠቀሰው ደመና፣ ዝናምን የሚሸከም የማይጨበጥ፣ የማይዳሰስ ጢስ መሰል ፍጥረት ነው፡፡ በትነት አማካይነት፣ በደመና ተሸካሚነት ከውቅያኖሶች እና ከወንዞች እየተቀዳ ወደ ሰማይ ተወስዶ እንደ ገና ተመልሶ ወደ ምድር የሚጥለው ውኃ ዝናም ይባላል፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ጥበብ በደመና ወንፊትነት ተጣርቶ ለፍጡራን በሚመችና በሚጠቅም መጠን በሥርዓት ይወርዳል፡፡ ‹‹ያጸንዖ በፍኖተ በድው ከመ ይዝንም ብሔረ ኀበ አልቦ ሰብእ ወኢይነብሮ ዕጓለ እመሕያው፤ ዝናሙን ሰው በሌለበት በምድረ በዳ ያዘንመዋል፤›› እንዳለ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በቅዳሴው፡፡ ይህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር በረዶውን በምድረ በዳ አፍስሶ የጠራውን ውኃ ሰው ወዳለበት እንዲዘንም ማድረጉን የሚያስረዳ መልእክት የያዘ ሲኾን፣ ምሥጢሩም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንበለ ዘርዐ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) በልዩ ጥበቡ ተፀንሶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱንና በለበሰው ሥጋ በምድር ተመላልሶ ወንጌልን ማስተማሩን፤ እንደዚሁም ‹‹ሑሩ ወመሀሩ፤ ሒዱና አስተምሩ›› ብሎ ቅዱሳን ሐዋርያትን በመላው ዓለም ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማሠማራቱን ያመለክታል (ትርጓሜ ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ፣ ፪፥፭-፮)፡፡

‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር ዘያበቍል ሣዕረ ውስተ አድባር ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እመሕያው፤ ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፣ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ፣ ልምላሜውንም ለሰው ልጆች አገልግሎት የሚያበቅል … እርሱ ነው፤›› (መዝ. ፻፵፮፥፰) በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደ ዘመረው እግዚአብሔር አምላክ ውኃ ከውቅያኖሶች ተቀድቶ፣ በደመና ተቋጥሮ፣ ወደ ሰማይ ሔዶ፣ እንደ ገና ተመልሶ ወደ ምድር እንዲዘንም እያደረገ ዓለምን በልዩ ጥበቡ ይመግባል፡፡ ይህን አምላካዊ ጥበብ በማድነቅ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት አምላክነ በተነ ጊሜ ረቂቅ ዘያአቍሮ ለማይ ያዐርጎ እምቀላይ ወያወርዶ እምኑኀ ሰማይ፤ ረቂቅ በኾነ የጉም ተን ውኃውን የሚቋጥረው፤ ከወንዝ ወደ ላይ የሚያወጣው፤ ከሩቅ ሰማይም የሚያወርደው እግዚአብሔር ቅዱስ፣ ልዩ፣ ምስጉን አሸናፊ አምላክ ነው፤›› በማለት ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ልዑል እግዚአብሔርን ያመሰግናል (መጽሐፈ ሰዓታት ዘሌሊት)፡፡

የደመና አገልግሎቱ ዝናምን ከውቅያኖስ በመሸከም ወደ ምድር እያጣራ ማውረድ ነው፡፡ ኾኖም በሰማይ የሚዘዋወርና በነፋስ የሚበታተን ዝናም አልባ ደመናም አለ፡፡ በመልካም ግብር፣ በትሩፋት ጸንተው የሚኖሩ ምእመናን ዝናም ባለው ደመና ሲመሰሉ፣ ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር በስመ ክርስትና ብቻ የምንኖር ምእመናን ደግሞ ዝናም በሌለው ደመና እንመሰላለን፡፡ ሐዋርያው ይሁዳ ‹‹… በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች …›› በማለት የተናገረውም የእንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን ሕይወት ይመለከታል (ይሁዳ ፩፥፲፪)፡፡ አንድም ዝናም ያለው ደመና የእመቤታችን የቅድስት ደንግል ማርያም ምሳሌ ነው፡፡ እርሷ ንጹሑን የሕይወት ውኃ (ዝናም) መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገኝታልናለችና፡፡ ‹‹አንቲ ዘበአማን ደመና እንተ አስተርአይኪ ለነ ማየ ዝናም፤ የዝናም ውኃን ያስገኘሽልን እውነተኛ ደመና አንቺ ነሽ፤›› እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም (ውዳሴ ዘረቡዕ)፡፡ እኛም ውኃ ሳይኖረው በነፋስ እንደሚበታተን ዝናም አልባ ደመና ሳይኾን፣ ዝናም እንደሚሸከም ደመና በምግባረ ሠናይ ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም የእግዚአብሔርን ቃል ሕይወታችን በማድረግ ራሳችንን ከማዳን ባሻገር ለሌሎችም አርአያና ምሳሌ ልንኾን ያስፈልጋል፡፡

ስለ ደመና ሲነገር ዝናምም አብሮ ይነሣል፡፡ ዝናም ያለ ደመና አይጥልምና፡፡ ዝናም የቃለ እግዚአብሔር ምሳሌ ነው፤ ዝናም ለዘር መብቀል፣ ማበብና ማፍራት ምክንያት እንደ ኾነ ዅሉ በቃለ እግዚአብሔርም በድንቁርና በረኃ የደረቀ ሰውነት ይለመልማል፤ መንፈሳዊ ሕይወትን የተራበችና የተጠማች ነፍስም ትጠግባለች፤ ትረካለችና፡፡ ‹‹ሲሲታ ለነፍስ ቃለ እግዚአብሔር፤ የነፍስ ምግቧ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤›› እንዲል፡፡ በሌላ በኩል በዚህ ዓለም የሚያጋጥም ልዩ ልዩ ፈተናም በዝናም ይመሰላል፡፡ ጌታችን በወንጌል እንደ ነገረን ቃሉን ሰምቶ በሥራ ላይ የሚያውል ክርስቲያን ቤቱን በዓለት ላይ የመሠረተ ልባም ሰውን ይመስላል፡፡ ቤቱ በጐርፍ ቢገፋ አይናወጥምና፡፡ ቃሉን የማይተገብር ክርስቲያን ግን ያለ መሠረት በአሸዋ ላይ ቤቱን የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል፡፡ ቤቱ በዝናብ፣ በጐርፍና በነፋስ ተገፍቶ የከፋ አወዳደቅ ይወድቃልና፡፡ ይህም ሃይማኖቱን በበጎ ልቡና የያዘ ክርስቲያን ከልዩ ልዩ አቅጣጫ በሚደርስበት መከራ ሳይፈራና በሰዎች ምክር ሳይታለል፤ በኢዮብ እንደ ደረሰው ዓይነት ከባድ ፈተና ቢመጣት እንኳን ሳያማርር በምክረ ካህን፣ በፈቃደ ካህን እየታገዘ አጋንንትን ድል እያደረገ በሃይማኖቱ ጸንቶ እንደሚኖር፤ በአንጻሩ ሃይማኖቱን በበጎ ሕሊና ያልያዘ ክርስቲያን ግን ፈተና ባጋጠመው ጊዜ በቀላሉ እንደሚክድና ለአጋንንትም እጁን እንደሚሰጥ የሚያስረዳ ምሥጢር አለው (ትርጓሜ ወንጌል፣ ማቴ. ፯፥፳፬-፳፯)፡፡

ዝናም ሲጥል የወንዞች ሙላትና ማዕበል ቤት እንዲያፈርስ፤ ንብረት እንዲያወድም በክርስቲያናዊ ሕይወት በሚያጋጥም ፈተናም በእምነት መዛል፣ በመከራ መያዝ፣ መቸገር፣ መውጣትና መውረድ ያጋጥማል፡፡ ዝናም ለጊዜው እንዲያስበርድና ልብስን እንዲያበሰብስ ፈተናም እስኪያልፍ ድረስ ያሰንፋል፤ ያስጨንቃል፤ ያዝላል፡፡ ነገር ግን ዝናም፣ ጐርፍና ማዕበል ጊዜያቸው ሲደርስ ጸጥ እንደሚሉ ዅሉ፣ ምድራዊ ፈተናም ከታገሡት የሚያልፍ የሕይወት ክሥተት ነው፡፡ ስለዚህ ዅላችንም እምነታችንን በጠንካራ መሠረት ላይ በመገንባት በውኃ ሙላትና በማዕበል ከሚመሰል ውድቀት ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ ዝናም ሲመጣ የውኆችን ሙላትና ጐርፉን ሳንፈራ ወደ ፊት የምናገኘውን ምርት ተስፋ እንደምናደርግ፣ በሃይማኖታችን ልዩ ልዩ ፈተና ሲያጋጥመንም ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘውን ሰማያዊ ዋጋ በማሰብ ዅሉንም በትዕግሥት እናሳልፍ፡፡

ይቆየን

ዘመነ ክረምት – ክፍል አንድ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ወቅቶች በአራት ይከፈላሉ፡፡ በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት፣ እንደዚሁም በመጽሐፈ ግጻዌ እንደ ተገለጸው እነዚህም፡- ዘመነ መጸው (መከር)፣ ዘመነ ሐጋይ (በጋ)፣ ዘመነ ጸደይ (በልግ) እና ዘመነ ክረምት ይባላሉ፡፡ ከአራቱ ወቅቶች መካከል ከሰኔ ፳፭ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ (አሁን የምንገኝበት ወቅት) ዘመነ ክረምት ተብሎ ይጠራል፡፡

እንደ ማስገንዘብያ፡- ክረምቱ የሚጀምረው ሰኔ ፳፮ ቀን ቢኾንም ከዋይዜማው ጀምሮ የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ዘመነ ክረምትን የሚመለከት ስለ ኾነ ከሰኔ ፳፭ ቀን ጀምረን መቍጠር እንችላለን፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስረዱን ከዋይዜማው ወይም ከመነሻው ጀምረን ቀኑን መጥቀሳችን የአስተምህሮ ለውጥ አያመጣም፡፡ ይህ አቈጣጠር ለሌሎች ወቅቶች እና ለዘመነ ክረምት ክፍሎችም ተመሳሳይ መኾኑን ከወዲሁ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! በዚህ ዝግጅት ዘመነ ክረምትን የሚመለከት ተከታታይ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም የንባብ ጊዜ!

‹ክረምት› ከረመ፣ ከረመ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፤ እንደዚሁም ዕፅዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት ነው፡፡ ይኸው ዘመነ ክረምት በሰባት ንዑሳን ክፍሎች ይመደባል፤ የክፍፍሉ መሠረት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሲኾን፣ ክፍሎቹም የሚከተሉት ናቸው፤

፩ኛ ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ያለው ጊዜ በአተ ክረምት ወይም ዘርዕ፣ ደመና፤

፪ኛ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፱ ቀን ያለው ጊዜ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል፤

፫ኛ ከነሐሴ ፲ – ፳፯ ቀን ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ፤

፬ኛ ከነሐሴ ፳፰ እስከ ጳጉሜን ፭ (፮) ቀን ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባህ፣ ብርሃን፣ መዓልት፤

፭ኛ ከመስከረም ፩ – ፯ ቀን ዮሐንስ፤

፮ኛ ከመስከረም ፰ – ፲፬ ቀን ፍሬ፤

፯ኛ ከመስከረም ፲፭ – ፳፭ ቀን ፀአተ ክረምት (የክረምት መውጫ) ወይም ዘመነ መስቀል፡፡

እያንዳንዱን ክፍለ ክረምትም በመጠኑ እንደሚከተለው ለመዳሰስ እንሞክራለን፤

፩. በአተ ክረምት (ዘርዕ፣ ደመና)

ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው የመጀመሪያው የክረምት ክፍለ ጊዜ በአተ ክረምት ወይም ዘርዕ፣ ደመና ይባላል፡፡ በዚህ ወቅት ስለ ክረምት መግባት፣ ስለ ዘርዕ፣ ስለ ደመና እና ስለ ዝናም የሚያዘክሩ መዝሙራትና ምንባባት ይዘመራሉ፤ ይነበባሉ፡፡ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፤ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ ነው፡፡

በአተ ክረምት (የክረምት መግብያ)

በዘመነ ክረምት መጀመርያ (መግብያ) ሳምንት በቤተ ክርስቲያናችን የሚቀርበው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር የሚከተለው ነው፤

‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይጸግቡ ርኁባን ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ደምፀ እገሪሁ ለዝናም››

የመዝሙሩ ቀጥተኛ ትርጕም፡-

‹‹የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ ዝናም በሚዘንም ጊዜ የተራቡ ይጠግባሉ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ ዝናም በሚዘንም ጊዜ ድሆች ይደሰታሉ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ አምላካችን ለሰው ልጅ ዕረፍት ሰንበትን ፈጠረ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡››

ይህ መዝሙር ከሰኔ ፳፮ ጀምሮ ያለው ወቅት ክረምቱ የሚገባበት እና ዝናም በብዛት የሚጥልበት ጊዜ መኾኑን የሚያበሥር ሲኾን፣ በተጨማሪም ዝናም በሚዘንብበት ጊዜ የሚበቅለውን እኽልና የምንጮችን መብዛት ተስፋ በማድረግ የተራቡ እንደሚጠግቡ፤ የተጠሙም እንደሚረኩ የሚያትት ምሥጢር ይዟል፡፡ እንደዚሁም ጊዜ ለበጋ፣ ጊዜ ለክረምት የሚሰጥ አምላክ ለሰው ልጅ ማረፊያ ትኾን ዘንድ ዕለተ ሰንበትን መፍጠሩንም ያስረዳል፡፡ በዚህ ሳምንት በዕለተ ሰንበት በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትም የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፤

፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፭፥፴፫ – ፶፩

ፍሬ ዐሳቡ፡- አዝርዕት በስብሰው እንደሚበቅሉ ዅሉ የሰው ልጅም ከሞተ በኋላ ከሞት እንደሚነሣ፤ ሲነሣም እግዚአብሔር እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን እንደሚከፍለው፤ እንደዚሁም የሰው ልጅ ሞቱንና የሚያገኘውን ሰማያዊ ዋጋ በማሰብ ከኀጢአት መለየት እንደሚገባው ያስረዳል፡፡

ያዕቆብ ፭፥፲፮ እስከ ፍጻሜው

ፍሬ ዐሳቡ፡- ነቢዩ ኤልያስ በጸሎት ዝናም እንዳይዘንምና እንደገና እንዲጥል ማድረጉን በመተረክ እኛም እምነቱ ካለን በጸሎት ኹሉን ማድረግ እንደሚቻለን ይናገራል፡፡

ግብረ ሐዋርያት ፳፯፥፲፩ – ፳፩

ፍሬ ዐሳቡ፡- ቅዱስ ጳውሎስና ተከታዮቹ መርከባቸው በማዕበል ክፉኛ መናወጧንና በእግዚአብሔር ኃይል መዳናቸውን፤ በባሕሩ ውስጥም በጨለማ ለብዙ ጊዜ መቆየታቸውን በማውሳት ይህ ወቅት (ዘመነ ክረምት) የውኃና የነፋስ ኃይል የሚያልበት ጊዜ መኾኑን ያስተምራል፡፡

ምስባክ፡- መዝሙር ፻፵፮፥፰

ኃይለ ቃሉ፡- ‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር ዘያበቍል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡››

የመዝሙሩ ቀጥተኛ ትርጕም፡- ‹‹ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፣ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ የሚያበቅል እርሱ ነው፡፡››

የመዝሙሩ ፍሬ ዐሳብ፡- እግዚአብሔር ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፤ ዝናምንም (ክረምትን) ለምድር (ለሰው ልጅ) የሚያዘጋጅ፤ እንደዚሁም በተራሮች ላይ ሣርን (ዕፀዋትን) የሚያበቅል አምላክ መኾኑን ያስገነዝባል፡፡

ወንጌል፡- ሉቃስ ፰፥፩-፳፪

ፍሬ ዐሳቡ፡- ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃለ እግዚአብሔርን በዘርዕ፣ የምእመናንን ልቡና (የመረዳት ዓቅም) ደግሞ በመንገድ፣ በዓለት፣ በእሾኽና በመልካም መሬት በመመሰል ቃሉን ሰምተው በሚለወጡትና በሚጠፉት መካከል ስላለው ልዩነት ማስተማሩን ያስረዳል፡፡

ቅዳሴው፡- ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ ሲኾን ይህ ቅዳሴ ስለ ዝናም፣ ደመና፣ መብረቅ፣ ባሕርና መሰል ፍጥረታት ዑደት፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ዓለማትን በጥበቡ ፈጥሮ የሚገዛና የሚመግብ አምላክ መኾኑን ስለሚያብራራ በዘመነ ክረምት ይቀደሳል፡፡

ጠቅለል አድርገን ስንገልጸው በዘመነ ክረምት መጀመርያ ሳምንት ከአዝርዕት፣ ከዝናም፣ ከልምላሜ፣ ከውኃ ሙላትና ከባሕር ሞገድ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ትምህርቶች ከሰው ልጅ ሕይወትና ከምግባሩ እንደዚሁም በምድር ከሚያጋጥሙት ፈተናዎች ጋር እየተነጻጸሩ ይቀርባሉ፡፡ የወቅቱን ትምህርት ከሕይወታችን ጋር አያይዘን ስንመለከተውም ዘመነ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፡፡ ገበሬ በክረምት ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሣል፡፡ ይህም ምእመናን በሰማያዊው ዓለም የምናገኘውን ተድላና ደስታ በማሰብ በምድር ቆይታችን የሚደርስብንን ልዩ ልዩ መከራ በትዕግሥት ማሳለፍ እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

ይቆየን

ቀዳም ሥዑር

ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የሰሙነ ሕማማቷ ቅዳሜ ‹ቀዳም ሥዑር› ወይም ‹ቀዳሚት ሥዑር› ትባላለች፡፡ ትርጕሙም ‹የተሻረች ቅዳሜ› ማለት ነው፡፡ የማትጾመዋ ቅዳሜ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል ‹የተሻረችው ቅዳሜ› ተብላ ተጠርታለች፡፡ ነገር ግን ቃሉ ጾምን እንጂ በዓል መሻርን አያመለክትም፡፡ በቀዳም ሥዑር  ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኅሌቱም እዝሉ እየተቃኘ፣ እየተመጠነ፣ እየተዘመመ፣ እየተመረገደ፣ እየተጸፋ ያድራል፡፡ ጠዋት አቡን፣ መዋሥዕት፣ ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ‹‹ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ›› በሚለው ሰላም ሥርዓተ ማኅሌቱ ይጠናቀቃል፡፡

ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለ ኾነ ዕለተ ቅዳሜ ‹ለምለም ቅዳሜ› ተብላም ትጠራለች፡፡ በቀዳም ሥዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል (ቃለ ዓዋዲ) እየመቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ›› የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደ ሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደ ገለጠልን በማብሠር፤ ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብሥራት ነው፡፡

ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት ድረስ በራሳቸው ላይ አሥረውት ይቆያሉ፡፡ ይህም አይሁድ በጌታችን ራስ ላይ የእሾኽ አክሊል ማሠራቸውን የሚያስታውስ ነው፡፡ የቀጤማው አመጣጥና ምሥጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በማየ አይኅ (በጥፋት ውኃ) በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ‹‹የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ፤ ታወጀ፤›› በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡

ዕለተ ቅዳሜ ‹ቅዱስ ቅዳሜ› እየተባለችም ትጠራለች፡፡ ቅዱስ መባሏም ቅዱስ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ዅሉ ስላረፈባት ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ዅሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፤ በነፍሱ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለ ኾነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየች ዕለት መኾኗን ለማመላከት ‹ቅዱስ› (ቅድስት) ተብላለች፡፡

ምእመናን ሆይ! በአጠቃላይ የጌታችንን የመከራ ሳምንት ‹ሰሙነ ሕማማት› ብለው ሰይመው፣ ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ያቆዩልንን ትውፊት ልንጠብቀውም፣ ልንጠቀምበትም ይገባል፡፡ የዕለታቱን ክብርና ስያሜ ከማወቅና ከመረዳት ጋር በዕለታቱ የታዘዙትን ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት ይኖርብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ (ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት)፣ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ከሚያዝያ ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም፣ ማኅበረ ቅዱሳን፤ አዲስ አበባ፡፡

መስቀል የድኅነት ዓርማ (ምልክት)

በዲያቆን ዘላለም ቻላቸው

ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እግዚአብሔር አምላካችን በቸርነቱ አዳምንና ሔዋንን ከፍጥረቱ ዅሉ አልቆ በራሱ አርአያና አምሳል ፈጥሮ ገነትን ያህል ቦታ አዘጋጅቶ በተድላ በደስታ እንዲኖሩ፣ ሌሎችንም ፍጥረታት ዅሉ እንዲገዙ ሥልጣንንም ጭምር ሰጣቸው (ዘፍ. ፩፥፳፭)፡፡ አዳምና ሔዋንም በገነት በነበሩባቸው ዓመታት ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገሩ በፍጥረታት ላይ ነግሠው በደስታ ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላ ግን ‹‹አትብሉ›› የተባሉትን ዕፅ በልተው የእግዚአብሔርን ሕግ በማፍረስ በደሉ፡፡

ከፈጣሪያቸው ጋር ራሳቸውን ለማስተካከል (አምላክ ለመኾን) በማሰብና በመመኘታቸው ይቅርታ የማይገባውን ዐመፅ  ፈጸሙ፡፡ በዚህ ጊዜ አዳም፡- ‹‹… ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትኹን፣ በሕይወት ዘመንህ ዅሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾኽና አሜከላ ታበቅልብሃለች …››፤ ሔዋን ደግሞ፡- ‹‹… በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛዋለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ …» ተብለው ተረገሙ (ዘፍ. ፫፥፲፭-፲፱)፡፡ «ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ» (ዘፍ. ፪፥፲፰) ተብሎ አስቀድሞ በተነገራቸው ሕግ መሠረት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣሉ፤ ከገነት ተባረሩ፤ የሞት ሞት ተፈረደባቸው፡፡

አዳምና ሔዋንም ኾኑ ልጆቻቸው ከዚህ ውድቀት ራሳቸውን ለማዳን አልቻሉም፤ ከተፈረደባው የሞት ሞት እንዲድኑ የበደሉን ካሣ በሞት የሚከፍል ሰው ያስፈልግ ነበር፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ፍርዱ እውነተኛና ትክክለኛ ነውና ካሣ ሳይከፈል ፍርዱ አይሻርምና፡፡ ከአቤል ጀምሮ የፈሰሰው የነቢያት ደምም ካሣ ሊኾን አልተቻለውም፤ እነዚህ ሰዎች ራሳቸው የአዳምና ሔዋን በደል ስለ ነበረባው ለመሥዋዕትነት አልበቁም፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ርኅሩኅ አምላክ ነውና የፍጡሩ የሰው ልጅ ሥቃይ ስላሳዘነው ከራሱ ጋር የሚታረቅበትን መንገድ አዘጋጀ፡፡ ስለዚህም ሥጋ ለብሶ (ሰው ኾኖ)፣ መከራ ተቀብሎ፣ ሙቶ እንደሚያድናቸው ቃል ኪዳን ገባላቸው፡፡

የዘመኑ ፍጻሜ (የቀጠሮው ቀን) በደረሰ ጊዜም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ቃል (ወልድ) ከነፍሷ ነፍስ፣ ከሥጋዋ ሥጋ ነሥቶ (ተዋሕዶ) ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ነቢዩ አሳይያስ «በሰዎች ዘንድ የተናቀና የተጠላ የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር፤ በእርግጥ እርሱ ደዌአችንን ወሰደ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ …፤›› እንዳለው ከልደቱ እስከ ስቅለቱ ድረስ መከራን በመቀበል የበደላችንን ዋጋ ከፈለ (ኢሳ. ፶፫፥፫-፬)፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በከፈለው የሕይወት መሥዋዕትነትም የሰው ልጆችን ከራሱ፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አስታረቃቸው፡፡ በመስቀሉም መለኮታዊ ሥልጣኑን ገልጦ፣ ዲያሎስንና ሠራዊቱን ቀጥቅጦ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን ነጻ አወጣቸው፡፡ «ወሪዶ እመስቀሉ ቀጥቀጠ ኃይሎ ለፀላኢ አርአየ ሥልጣኖ ለዕለ ሞትከመስቀሉ ወርዶ የጠላትን ኃይል ቀጠቀጠ፤ በሞትም ላይ ሥልጣኑን ገለጠ፤» እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡

መስቀል ክርስቶስ መከራ የተቀበለበት እና የማዳኑን ሥራ የገለጠበት የድኅነታችን ዓርማ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰፊ አገር በሰንደቅ ዓላማ (ባንዲራ) ይወከላል፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ጨርቅ ቢኾንም ትርጕሙ ግን አገር ማለት ነው፡፡ ባንዲራን መውደድ፣ ለባንዲራ መሞት ስንልም አገርን መውደድ፣ ለአገር መሞት ማለታችን ነው፡፡ ተቋማትና ድርጅቶችም እንዲሁ የራሳቸው መገለጫ የኾነ ዓርማ አላቸው፡፡ መስቀልም የክርስቶስ የማዳኑ ሥራ የመከራውና የሞቱ ወካይ ዓርማ (ምልክት) ነው፡፡ መስቀሉን ስናይ፣ ስናማትብ፣ ስሙን ስንጠራ (ስንሰማ) በእነዚህ ዅሉ የክርስቶስን መከራና የማዳን ሥራውን እናስታውሳለን፡፡ ‹‹በመስቀሉ አዳነን›› ስንልም ጌታችን በመስቀል ላይ በፈጸመው ቤዛነት ድነናል ማለታችን ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን በብሉይ ኪዳን የነበሩትን የመሥዋዕት ሥርዓቶች ያዘጋጀው፤ በሕዝቡ መካከል ለመገኘቱ ምልክት የኾነውን ታቦት የሰጠው ሰዎች አምልኮታቸውን ለመፈጸም የሚታይ የሚዳሰስ ነገር በመፈለጋቸው ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም በቤተ ክርስቲያን ያሉት ልዩ ልዩ ሥርዓቶች፣ ንዋያተ ቅዱሳት፣ ከዚሁ አንጻር የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው የማይታይ ጸጋ በሚታይ አገልግሎት የሚፈጸመውም ስለዚህ ነው፡፡ መስቀልም እግዚአብሔር አምላካችን ለእኛ ሲል የተቀበለውን መከራ የምናስታውስበት፤ ከሞት ሞት መዳናችንን በማሰብ አምልኮታችንን የምንገልጥበት የድኅነታችን ዓርማ ነው፡፡ የጌታችንን መከራ፣ ስቅለት እና ሞት ክርስቲያኖች ዅል ጊዜ ማሰብ አለብን፡፡ ይህንን እንድናደርግ የሚያስችለን፤ ስለ ክርስቶስ ሕማም ስናስብም ሕሊናችንን ሰብስቦ የተከፈለልንን ዋጋ እንድናስታውስ የሚያደርገን መስቀል ነውና፡፡

ጌታችን «መስቀሌን ተሸክማቸሁ ተከተሉኝ» ሲልም መከራዬን፣ ስቃዬን፣ ሞቴን ተጋሩ ማለቱ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «ጥልን በመስቀሉ ገደለ» ሲል እንደ ገለጸው (ኤፌ. ፪፥፲፮)፣ እኛም «መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንዕነ መስቀል ቤዛነ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ አይሁድ ክህዱ ንሕነሰ አመነ ወእለ አመነ በኀይለ መስቀለ ድኅነ፤ መስቀል ኃይላችን ነው፤ መስቀል የምንጸናበት ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፤ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው፡፡ አይሁድ ይክዱታል፤ እኛ ግን እናምነዋለን፡፡ ያመነውም እኛ በመስቀሉ ኃይል እንድናለን፤ ድነናልም» እያልን የክርስቶስን መከራውን፣ መስቀሉን፣ ሞቱን፣ በሞቱም እኛ መዳናችንን እንመሰክራለን፡፡

‹‹… በመስቀልህ …›› ስንልም ‹‹መከራ በመቀበልህ፣ በመሰቀልህ፣ በሞትህ፣ …›› ወዘተ ማለታችን ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም «መስቀል ብርሃን ለኵሉ ዓለም መሠረተ ቤተ ክርስቲያን፤ መስቀል የዓለሙ ዅሉ ብርሃን፤ የቤተ ክርስቲያንም መሠረት ነው፤ … » ዳግመኛም ‹‹በመስቀሉ አርኀወ ገነተ ወተሞዐ ኃይለ ሥልጣኑ ለሞት፤ በመስቀሉ ገነትን ከፈተ፤ የሞተ ኃይልም ድል ተደረገ፤›› በማለት ክርስቶስ በመስቀሉ ገነት መከፈቷን፤ ሞትም ድል መደረጉን ያብራራል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ መስቀል ያገኘችውን ጸጋና ለክርስቶስ ያላትን ክብር ራሷ መመስከሯን ሲገልጽም ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ሲል ይዘምራል፤ ‹‹ትዌድሶ መርዓት ቤተ ክርስቲያን እንዘ ትብል ‹በመስቀልከ አብራህከ ሊተ እንዘ ግድፍት ወኅድግት አነ ምራቀ ርኩሳን ተዐገሥከ በእንቲአየ ሕይወተከብኩ በትንሣኤከ ጸጋ ነሣዕኩ ወደቂቅየኒ ገብኡ ውስተ ሕጽንየ በመስቀልከ አብራህከ ሊተ በመስቀልከ አድኀንከ ኵሎ ዓለመ›፤ ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን (ጌታን) እንዲህ እያለች ታመሰግነዋለች፤ ‹የተተውሁና የተጣልሁ ኾኜ ሳለ አብርተህልኛል፤ ስለ እኔ ብለህ የርኩሳንን ምራቅ ታግሠሃል፡፡ በትንሣኤህጋን አገኘሁ፤ ልጆቼም ወደ እቅፌ ገቡ፡፡ በመስቀልህ አበራህልኝ፤ በመስቀልህም ዓለምን ዅሉ አዳንህ›፤»

መስቀል ምንን ያስታውሰናል?

መስቀልን ስናይ፣ መስቀልን ሰናስብ፣ ስሙንም ስንጠራ የሚከተሉትን ምሥጢራት እናስታውሳለን፤

ሀ. እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር

ነቢዩ ኢሳይያስ «እኛ ዅላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጎድን፤» እንዳለው (ኢሳ. ፶፫፥፮)፣ እኛ የሰው ልጆች በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይተን፣ በሞት ጥላ ሥር በመከራና በችግር እንኖር ነበር፡፡ አምላካችን እኛን ለማዳን አንድያ ልጁን ወደዚህ ምድር ልኮና የሞት መሥዋዕትነት ከፍሎ አድኖናል፡፡ «በእርሱ የሚያምን ዅሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን ወዷል፤» ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዮሐ. ፫፥፲፮)፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ስለ ወዳጆቹ ሕይወትን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውምና (ዮሐ. ፲፭፥፫፤ ሮሜ. ፭፥፰)፡፡ ስለዚህ መስቀል ስለ እኛ ሲል በመስቀል ላይ የሞትን ጽዋ የተቀበለው መድኃኒታችን ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያስታውሰን ምልክት ነው፡፡

ለ. ኃጢአታችንንና የኃጢአት ደመወዝ ሞት መኾኑን

መስቀል ኃጢአታችንን የሚያስታውሰን ምልክት ነው፡፡ ጌታችን በመስቀል የተሰቀለው ኃጢአተኞች በመኾናችን፣ እኛን ለማዳን ነውና፡፡ «በበደላችን ሙታንነን ሳለ በክርስቶስ ሕያዋንንን» እንደ ተባለው (ኤፌ. ፪፥፭)፣ ጌታችን እኛን ከሞት ለማዳን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለመሞት ያበቃው እኛ መበደላችን፤ የበደል (የኃጢአት) ደመወዝ ደግሞ ሞት መኾኑ ነው፡፡ መስቀል ይህንን ያስታውሰናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «በዋጋ ተገዝታችኋልና የራሳችሁ አይደላችሁም፤» እንዳለው (፩ኛ ቆሮ. ፮፥፳)፣ ከኃጢአት ባርነት ነጻ የወጣነው ዋጋ ተከፍሎብን እንደ ኾነ በመረዳት እግዚአብሔርን ማመስገን፤ ለእርሱም በትሕትና መገዛት ይኖርብናል፡፡

ሐ. የእግዚአብሔርን ቅን ፈራጅነት

መስቀል የእግዚአብሔር ፍቅር እና ቅን ፍርድ በአንድ ላይ የተደረጉበት አደባባይ ነው፡፡ አዳም በበደለ ጊዜ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ሞት ተፈረደበት፤ እግዚአብሔር የሰው ልጆች ወዳጅ በመኾኑ ሊያድነው ቢወድም፣ ስለ በደሉ ካሣ ሳይከፈል አላዳነውም፡፡ ስለዚህ ራሱ መጥቶ መሥዋዕት በመኾን የበደሉን ካሣ በመስቀል ላይ ከፈለ፤ በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩና ቅን ፍርዱ በአንድ ላይ ተገለጠ፡፡

መ. የጌታችንን ሕማማትና ሞት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበደላችንን ዋጋ የከፈለው ሊነገሩ የማይችሉ ሕማማትን ተቀብሎ፣ ተሰዶ፣ ተሰድቦ፣ ተዋርዶ፣ ተገርፎ፣ የኃጢአተኞች ምራቅ ተተፍቶበት፣ መስቀል ተሸክሞ ተራራ ወጥቶ፣ እጆቹና እግሮቹ ተቸንክረው፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ የሞትን ጽዋ ቀምሶ ነው፡፡ መስቀል እነዚህን ዅሉ የጌታችንን ሕማማትና ሞት የሚያስታውሰን ምልክት ነው፡፡

ሠ. ይቅር መባላችንን እና ድኅነታችንን

መስቀልን ስንመለከት እግዚአብሔር ኃጢአታችንን እንዴት ይቅር እንዳለንና በመስቀል ላይ ሳለ «አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁም ይቅር በላቸው» ማለቱን እናስታውሳለን (ሉቃ. ፲፫፥፴፬)፡፡ ዳግመኛም ጌታችን በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ በዲያብሎስ አገዛዝ ሥር የነበሩ ነፍሳትን ነጻ እንዳወጣቸው፤ እኛንም በአዳም በደል ምክንያት ከመጣብን የባሕርይ ድካም እንዳዳነን እናስባለን፡፡ አሁንም መስቀልን ስንመለከት በጌታ ቀኝ ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ ድኅነትን እንዳገኘ፤ ጌታችን በቸርነቱ በደሉን ዅሉ ይቅር ብሎ በፍቅሩ ወደ እርሱ እንደ ሳበውና ወደ ገነት እንዳስገባው እናስባለን፡፡ እኛም በተስፋ እንሞላለን፡፡

ረ. ትንሣኤንና ዳግም ምጽአትን

የጌታችንን መስቀልና ሞት ስናስታውስ አብረን ትንሣኤውንም እናስባለን፤ በእርሱ ትንሣኤ ደግሞ የእኛን ትንሣኤ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መስቀል ዳግም ምጽአትንም ያስታውሰናል፡፡ ዳግም ምጽአትን ስናስብም ለፍርድ በፊቱ እንደምንቆም እናስታውሳለን፡፡ ጌታችን ስለ ኅልፈተ ዓለምና ዳግም ምጽአት ሲያስተምር እንዲህ ብሏልና፤ «የዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት (መስቀል) በሰማይ ይታያል …. የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ኾኖ በኃይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል፤» (ማቴ. ፳፬፥፴)፡፡

ሰ. መስቀልን እንድንሸከም መታዘዛችንን

መስቀል ጌታችን «ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ … የራሱንም መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ደቀ መዝሙሬ ሊኾን አይችልም፤» በማለት ያስተማረንን ትምህርት ያስታውሰናል » (ማቴ. ፲፮፥፳፬፤ ሉቃ. ፲፬፥፳፯)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ክብረ ሰሙነ ሕማማት – ክፍል አራት (የመጨረሻ ክፍል)

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና (የሊቃውንት ጉባኤ አባል)

ሚያዝያ  ቀን ፳፻፱ .

‹‹ማን ይናገር የነበረ›› እንዲሉ ቅዱሳን ሐዋርያት እስከ ትንሣኤ ድረስ መንፈስን (ልጅነትን) ሳይቀበሉ ቆይተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ እነርሱ በመጣ ጊዜ በንፍሐት መንፈስ ቅዱስን እንዳሳደረባቸው ራሳቸው በግልጥ ተናግረዋል፡፡ በጌታችን ቀኝ ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ በክርስቶስ ደም ካሣ እንደ ተፈጸመ፣ ልጅነት እንደ ተመለሰ ሲያረጋገጥ ጌታችንን ‹‹ዳግመኛ በመጣህ ጊዜ በመንግሥትህ አስበኝ?›› ቢለው ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ‹‹እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ፤›› ብሎታል (ሉቃ. ፳፫፥፵፫)፡፡ ወገኔ ሆይ! ስለዚህ የሐዋርያት ጥምቀት የትንሣኤ ዕለት ለመኾኑ ከዚህ የበለጠ ማስረጃ ምን አለ? ማወቅ ለሚሻ ቅን ልቡና ላለው ከዚህ በላይ የቀረበው ማስረጃ በቂ ነው፡፡ ተጨማሪ ማስረጃ ካስፈለገ ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ ያስቀመጥናቸውን ጥቅሶች መመልከት ይቻላል፤

  • ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ›› (ሐዋ. ፳.፳፰)፤ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት ተቀድሰናል›› (ዕብ.፲.፲)፤
  • ‹‹ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡ …›› (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፪)፤
  • ‹‹በክቡር በክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ እናንተ ታውቃላችሁ›› (፩ኛ ጴጥ. ፲፰፥፲፰)፤
  • ‹‹… ከኃጢአታችን ላጠበን፤ በደሙ ላነጻን …›› (ራእ. ፩፥፮)፤
  • ‹‹. . . ተገድለሃልና በደምህም ከሕዝብና ከአሕዛብ ከነገድም ዅሉ፤ ከወገንም ዅሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃልና›› (ራእ. ፭፥፱)፡፡

እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች የልጅነት ክብር (ጥምቀት) ለሐዋርያት የተሰጠው የክርስቶስ ደም ከፈሰሰ በኋላ ነው እንጂ ከዚያ በፊት በሕጽበተ እግር እንዳልኾነ በግልጥ ያስረዳሉ፡፡

 ቅዱስ የኾነ ትውፊታዊ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን

በመሠረቱ የተቀደሰ ትውፊታዊ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናችን በራሱ አስተማሪ ነው፡፡ የማያስተውል ሰው ግን ብዙ ማስረጃ ቢቀርብለትም አያምንም፡፡ ስለዚህም በቅዱሳት መጻሕፍት መነሻነት ዘወትር በግልጥ ሲከናወን የኖረውን፤ አሁንም ባለ ማቋረጥ እየተከናወነ የሚገኘውን፤ ለወደፊትም የሚከናወነውን ቅዱስ የኾነውን የኦርቶዶከሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ ሥርዓት ወደ ጐድን በመተው ግምታዊ ልማድን እየተከተለ ‹‹የሐዋርያት ጥምቀት በሕጽበተ እግር ነው፤ እኛ የዳነው በሕጽበተ እግር ነው፤›› የሚሉ ሰዎች መጡ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ስታጠምቅም፣ ቅብዐ ቅዱስ ስትቀባም ከራስ ጀምራ ነው፡፡ በመጨረሻም በራስ ላይ እፍ ብላ መንፈስ ቅዱስን በማሳደር ነው እንጂ እግርን በማጠብ አጥምቃ አታውቅም፡፡

ይኸውም ከሐዋርያት የተገኘ፤ ከሐዋርያት ሲያያዝ የመጣ ትውፊታዊና ቅዱስ ሥርዓት ነው እንጂ አሁን የተፈጠረ አዲስ ባህል አይደለም፡፡ ስለዚህም የጸሎተ ሐሙስ ሕጽበተ እግር ጥምቀት ሳይኾን ፍጹም ትሕትናን ሠርቶ ለማሠራት ጌታችን የፈጸመው ተግባር ነው፡፡ ይህንም ያለ ጥርጥር ልንቀበለውና ልንተገብረው ይገባል፡፡ ከዚህ ሌላ የሐዋርያት ጥምቀት አንዳንዶቹ ተከተሉኝ ሲላቸው ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በበዓለ ኀምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ዅሉ አባባል ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት ያልተደገፈ ግምታዊ አሳብ ነው እንጂ፡፡

የሐዲስ ኪዳን ቍርባን መጀመሪያ

በዕለተ ሐሙስ ከተፈጸሙ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ መድኃኒታችን ክርስቶስ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው፤ ይህ ደሜ ነው፤›› ብሎ አማናዊ ሥጋውንና ደሙን መስጠቱ ነው (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፰)፡፡ እንደዚሁም ይህ ዕለት ሰፊ ጸሎት የተደረገበት የጸሎት ቀን ነው፡፡ ጌታችን ሐሙስ ዕለት ወዙ እንደ ውኃና እንደ ደም ወርዶ መሬቱን ጭቃ እስኪያደርገው ድረስ መላልሶ ስለጸለየ ዕለቱ ‹ጸሎተ ሐሙስ› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ጌታችን የጸለየበትን ቦታም ወንጌላውያኑ በተለያየ ስያሜ ጠርተውታል፤

ማቴዎስና ማርቆስ – ‹ዐጸደ ወይን›፣ ‹ጌቴሴማኒ›፤ ሉቃስ – ‹ደብረ ዘይት›፤ ዮሐንስ – ‹ማዕዶተ ቄድሮስ›፣ ‹ፈለገ አርዝ›፣ ‹ዐጸደ ሐምል› በማለት ሰይመውታል (ማቴ.፳፮፥፴፮፤ ማር.፲፬፥፴፪፤ ሉቃ. ፳፩፥፴፯፤ ፳፪፥፴፱፤ ዮሐ. ፲፰፥፩)፡፡ በተጨማሪም ይህ ዕለት (ሐሙስ) ያለ እርሱ ፈቃድ ሊይዙት እንደማይችሉ ለማስረዳት ጌታችን በመለኮታዊ ኃይሉ እንደ ቅጠል እንዲረግፉ ካደረጋቸው በኋላ በይቅርታው ብዛት መልሶ በማስነሣት በፈቃዱ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠበት ዕለት ነው (ዮሐ. ፲፰፥፭-፰)፡፡

ዓርብ ስቅለት (የድኅነት ቀን ዓርብ)

ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹የድኅነት ቀን› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. ፳፯፥፩-፶፯)፡፡ አይሁድ ይህን አጥፍቶአል የሚሉት ነጥብ ሳይኖራቸው ነውና ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት ጲላጦሰ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡

‹‹ክፉ የሠራ ባይኾንስ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር›› በሚል የሸፍጥ ቃል ሲያጕረመርሙ ጲላጦስ መልሶ ‹‹እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት፤›› አላቸው፡፡ አይሁድም ኦሪት ‹‹ኢትቅትል ብእሴ ጻድቀ ወኀጥአ ኢታኅዩ፤ ጻድቅን ሰው አትግደል፤ ኀጥኡንም ከፍርድ አታድን፤›› ትላለችና ‹‹እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም፤›› ብለዋል (ዮሐ. ፲፰፥፳፰-፴፩)፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ‹‹በሕጋችን ጻድቀ ባሕርይ ክርስቶስን መግደል አይገባንም ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች ነን፤›› ሲያሰኛቸው ነው፡፡ በኋላም እርሱ ሞቶ ዓለም ይድን ዘንድ ወደ ምድር መጥቷልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ስለዚህም ገርፈው ሰቀሉት፡፡ ጌታችን ሲሰቅልም የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤

፩. ፀሐይ ጨለመ፤

፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤

፫. ከዋክብት ረገፉ፤

፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤

፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤

፮. መቃብራት ተከፈቱ፤

፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤

፩. ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)››፤

፪. ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ››፤

፫. ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፤

፬. እመቤታችንን ‹‹ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ›› ደቀ መዝሙሩንም ‹‹እናትህ እነኋት›› በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤

፭. ‹‹አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ››

፮. ‹‹ተጠማሁ››

፯. ‹‹ዅሉ ተፈጸመ›› (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡

ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቈየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ኾኖአል፡፡ ‹‹ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነ ፀሐይ›› እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ቅድስት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር›› እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ክብረ ሰሙነ ሕማማት – ክፍል ሦስት

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና (የሊቃውንት ጉባኤ አባል)

ሚያዝያ  ቀን ፳፻፱ .

በዚህ አንጻር ጌታችን እስከ መስቀል ሞት ድረስ ከፊቱ ከባድ መከራ ተደግሶለት እያለ በሕጽበተ እግር ሐዋርያትን አጠመቀ፤ ልጅነትን ሰጠ ማለት አያስሔድም፡፡ ምክንያቱም አንድ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን የሚያውጀው፤ ሹመት፣ ሽልማትን መስጠት የሚጀምረው ጠላቱን ድል አድርጎ መንግሥቱን ካደላደለ በኋላ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዓለሙን ያዳነውና ልጅነትን የሰጠው ዲያብሎስን በመስቀል ድል ከነሣው በኋላ ነው እንጂ በሕጽበተ እግር አይደለም፡፡ ከሕጽበተ እግር በኋላ ሊይዙት ወደ እርሱ የመጡትን የካህናት አለቆችን፣ የቤተ መቅደስ ሹሞችንና ሽማግሌዎችን ጌታችን እንዲህ ብሏቸዋል፤ ‹‹ሌባን እንደምትይዙ በሰይፍና በጎመድ ልትይዙኝ መጣችሁን? ዘወትር ከእናንተ ጋር በቤተ መቅደስ ስኖር እጃችሁን እንኳ አልዘረጋችሁብኝም፤ ነገር ግን ጊዜያችሁ ይህ ነው፡፡ የጨለማው አበጋዝም ሥልጣኑ ይህ ነው፡፡›› (ሉቃ. ፳፪፥፶፪-፶፫)፡፡

ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበበት እና በአትክልት ቦታ ከጸለየበት ከሐሙስ ማታ እስከ ዓርብ እኩለ ቀን ድረስ ለመግለጽ እጅግ የሚከብድና የሚያሰቅቅ ሥቃይና መከራን በፈቃዱ ተቀብሏል፡፡ ከዚህ አሰቃቂ መከራና ሞት በፊት ቅዱሳን ሐዋርያት ተጠመቁ፤ ልጅነትን አገኙ ማለት ከጋብቻ በፊት ልጅ መውለድ እንደ ማለት ከመኾኑም በላይ የዓለም ቤዛ የኾነውን የጌታችንን ሞት ከንቱ ዋጋ አልባ ማድረግ ነው፡፡ እንዴት ቢባል በክርስቶስ ክርስቲያን የተባለ በሙሉ ከሐዋርያት በተገኘ ልጅነት ነው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በፊት በተከናወነ ሕጽበተ እግር ተጠመቁ ከተባለ ሞቱ ምንም ሥራ አልሠራም ማለቱ ነውና፡፡ ወገኔ ሆይ ከዚህ በላይ እንደ ተገለጠው የዳንኸውና ልጅነትን ያገኘኸው በክርስቶስ ሞትና ደም እንጂ በእግር መታጠብ እንዳልኾነ ልብ በል፡፡

የሐዋርያት አማናዊ ጥምቀት እንዴትና መቼ ተከናወነ?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት ‹‹የሙት ልጆች ትኾኑ ዘንድ አልተዋችሁም፡፡ እኔ ወደ እናንተ እመጣለሁና ገና ጥቂት ጊዜ አለ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህም ዓለም አያየኝም፡፡ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፡፡ እኔ ሕያው ነኝና እናንተም ሕያዋን ትኾናላችሁ፤›› በማለት ለአባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት የማይለወጥ አምላካዊ ጽኑ ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበረ (ዮሐ. ፲፬፥፲፰-፲፱)፡፡ ይህም ሲብራራ እንደ ሙት ልጆች እንድትኾኑ ሐሙስ ማታ እንደ ተለያኋችሁ አልቀርም፡፡ እኔ ከጥቂት ቀን ማለትም ከሁለት ቀን በኋላ በትንሣኤ ወደ እናንተ እመጣለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ዓለሙ አያየኝም፤ እኔ በማይራብ፣ በማይጠማ፣ በማይታመም፣ በማይሞት ሕያው ሥጋ እነሣለሁና እናንተም በልጅነት ሕይወት ልዩ ሕያዋን ትኾናላችሁ ሲላቸው ነው፡፡

ከዚያ በፊት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን ‹‹ዅላችሁ በዚህች ሌሊት እንደማታውቁኝ ትክዱኛላችሁ›› በማለት ደጋግሞ ነግሯቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ዅሉም ቢክዱህ እኔ ፈጽሜ አልክድህም›› ቢለው ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ›› ሲል አስረግጦ ነግሮታል፡፡ ስለኾነም የአምላክ ቃል አይታበይምና የአይሁድ ጭፍሮች ጌታችንን በያዙት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ዅሉ ትተው ሸሹ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ›› ሲሉት ‹‹የምትሉትን ፈጽሞ አላውቀውም›› ብሎ ደጋግሞ ምሎ ተገዝቷል (ማቴ. ፳፮፥፶፮፤ ማር. ፲፬፥፳፯-፶)፡፡

በተነሣ ጊዜም ቅዱሳን መላእክት ‹‹ተነሥቶአል፤ ከዚህ የለም፤›› ብለው ለቅዱሳት አንስት እንደነገሩአቸውና ራሱ ጌታችንም በመንገድ ተገልጦ እንዳነጋገራቸው ለቅዱሳን ሐዋርያቱ ሲያበሥሯቸው ሙቶ ይቀራል ብለው ተስፋ ቈርጠዋልና እንደ ተነሣ አላመኗቸውም፡፡ ከዚህ በኋላ ከእነርሱ መካከል ለሁለቱ ወደ ገጠር ሲሔዱ በሌላ መልክ ተገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ጌታችን እንደ ተገለጠላቸው ሔደው ለባልንጀሮቻቸው ነገሩ፡፡ እነርሱንም ቢኾን አላመኗቸውም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ተገለጠላቸው፡፡ አሁንም መነሣቱን ያዩ ደቀ መዛሙርትን አላመኗቸውም ነበር፡፡ ጌታችንም ስለ ሃይማኖታቸው ጉድለት ገሥፆአቸዋል፤ የልባቸውንም ጽናት ነቅፏል (ማር. ፲፮፥፲፪-፲፬)፡፡ በዚህ ኹኔታ ለቅዱሳን ሐዋርያት ካሣ ሳይፈጸም ከስቅለት በፊት በሕጽበተ እግር ተጠመቁ ቢባል እንኳ ትንሣኤውን አላመኑም ነበር፡፡ እንዳውም የክርስቶስ ትንሣኤ ተረት እንደ መሰላቸው ተጽፋል (ሉቃ. ፳፬፥፲፩)፡፡ አንድ ሰው ከካደ ደግሞ ልጅነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለኾነም የሐዋርያት ጥምቀት እግር በመታጠብ እንዳልኾነ እንረዳለን፡፡

እርግጠኛው የቅዱሳን ሐዋርያት ጥምቀት ግን ካሣ ከተፈጸመ በኋላ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከሃሊነቱ ዲያብሎስን ድል ነሥቶ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በተነሣ ጊዜ ነው፡፡ ቀድሞውንም አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ በአደባባይህ ተመላልሼ፣በመስቀል ተሰቅዬ አድንሃለሁ፤›› ብሎ ለአዳም በሰጠው ተስፋ መሠረት ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ዅሉንም በእርሱ ይቅር ብሎ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በምድርና በሰማይ ላሉ ሰላምን አደረገ (ቆላ. ፩፥፳)፡፡ ‹‹በውኂዘ ደሙ ቅዱስ አንጽሖሙ ለመሐይምናን ወለሕዝብ ንጹሐን፤ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስያሉትን አዳነ፤›› እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም (የእሑድ ውዳሴ ማርያም)፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ክርስቶስም ስለ ሰው ኃጢአት አንድ ጊዜ ሙቶአልና ጻድቅ እርሱ እኛን ወደ እግዚአብሔር ያቀርበን ዘንድ ስለ እኛ ኃጢአት በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ነው፡፡ በእርሱም በወኅኒ ወደሚኖሩ ነፍሳት ሒዶ ነጻነትን ሰበከላቸው›› በማለት ጌታችን በዕለተ ዓርብ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ መለየቱንና በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን ማውጣቱን አስረድቶናል (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፰-፲፱)፡፡

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ በዓለመ ነፍስ በሲኦል ሥቃይ ውስጥ የነበሩትን ነፍሳት ሕያው በኾነ ደሙ አንጽቶና ቀድሶ ወደ ገነት ከመለሰ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹እግዚአብሔርነቱ ግን የሞትን ማሰሪያ ፈቶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው፡፡ ሞት እርሱን ሊይዘው አይችልምና፤›› እንዳለው ጌታችን ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ሞትን ድል ነሥቶ እሑድ በመንፈቅ ሌሊት ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ እንደ ተነሣም በቀጥታ ወደ ቅዱሳን ሐዋርያት ነው የሔደው፡፡

ደቀ መዛሙርቱም አይሁድን ስለ ፈሩ ደጁን ቈልፈው ተሰብስበው የነበሩበት ቤት ሳይከፈት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እነርሱ ገብቶ በመካከላቸው ቆመና ‹‹ሰላም ለእናንተ ይኹን!›› አላቸው፡፡ እነርሱም ፈሩ፤ ደነገጡ፡፡ ጌታችንም ‹‹እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤›› አለና እጆቹንና እግሮቹን፣ ጎኑንም አሳያቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ጌታችንን ባዩት ጊዜ ደስ አላቸው፡፡ ማለትም ፍርኃቱ ተዋቸው፤ ጥርጣሬው ተወገደላቸው፡፡ ፈጣሪያቸው ሙቶ እንደ ተነሣ አመኑ፤ ተረዱ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ መልኩ ካሳመናቸው በኋላ ዳግመኛ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይኹን! አብ እኔን እንደ ላከኝ እንዲሁ እኔ እናንተን እልካችኋለሁ፤›› አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እፍ አለባቸው፤ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ (ዮሐ. ፳፥፳፩-፳፪)፡፡

‹‹እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ በፊቱም ሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፡፡ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ኾነ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዘፍ. ፪፥፯) አዳም በተፈጠረ በዐርባ ቀኑ እግዚአብሔር አምላክ በፊቱ እፍ ብሎ ያሳደረበትን ልጅነት ዕፀ በለስን በልቶ ቢያስወስዳት ዳግማይ አዳም ክርስቶስ አዳም ስላጠፋው ጥፋት ደሙን በመስቀል ላይ አፍስሶ፣ ውድ ሕይወቱን ክሦ በቅዱሳን ሐዋርያት ፊት እፍ በማለት ልጅነትን ዳግመኛ አሳደረባቸው፡፡ በዚህም ቀድሞ በዕፀ በለስ ምክንያት የሔደች ልጅነት በዕፀ መስቀል ምክንያት ተመለሰች፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት የትንሣኤ ዕለት እንደ ተጠመቁ ራሳቸው በመጽሐፈ ኪዳን እንደሚከተለው ገልጸውታል፤

‹‹… ኮነ እምድኅረ ተንሥአ አስተርአየነ ወተገሠ እምቶማስ ወማቴዎስ ወዮሐንስ ወተፈወስነ (ወአእመርነ) ከመ ተንሥአ እግዚእነወይቤለነአማን አማን እብለክሙ ኢትከውኑ ውሉደ እግዚአብሔር ዘእንበለ በመንፈስ ቅዱስ፡፡ ወተሰጠውናሁ ወንቤእግዚኦ ሀበነ መንፈሰ ቅዱሰወነፍሐ ላዕሌነ ኢየሱስ፡፡ ወእምድኅረ ነሣእነ መንፈሰ ቅዱሰ ይቤለነአንትሙ እለ መንግሥተ ሰማያት ዘእንበለ ኑፋቄ ልብእንዲህ ኾነ፤ ጌታችን ከተነሣ በኋላ ተገለጠልን፡፡ በቶማስ በማቴዎስና በዮሐንስ እጅ ተዳሰሰ፡፡ ጌታችን እንደ ተነሣም አወቅን፡፡ እርሱምእውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ቅዱስ ካልተወለዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች አትኾኑምአለን፡፡ እኛምመንፈስ ቅዱስን ስጠን?› ስንል መለስንለት፡፡ ኢየሱስም በእኛ ላይ እፍ አለ፡፡ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበልን በኋላእናንተ ጥርጥር በሌለው ልብ የመንግሥተ ሰማያት ባለቤቶች ናችሁአለን፤›› (መጽሐፈ ኪዳን አንቀጽ ፩)፡፡

ይቆየን

ክብረ ሰሙነ ሕማማት – ክፍል ሁለት

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና (የሊቃውንት ጉባኤ አባል)

ሚያዝያ ቀን ፳፻፱ .

የክርስቶስ የሕማማቱ መንሥኤ

ሰሙነ ሕማማት (የሕማማት ሰሙን መከራ) ባለቤቱ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቅዶ፣ ወስኖ እስከ መስቀል ድረስ በፈቃዱ መከራ የተቀበለበት ጊዜ ነው፡፡ አምላችን ሥራውን ያለ ምክንያት አይሠራውምና ለሕማሙና ለሞቱ መንሥኤ ከኾኑት መካከል የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው፤

አልዓዛርን ከሞት ማስነሣቱ

‹‹የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ጉባኤውን ሰብስበው እንዲህ አሏቸው፤ ‹እነሆ ይህን ሰው ብዙ ተአምራትን ያደርጋል፡፡ ምን እናድርግ? እንዲሁ ብንተወውም ዅሉ ያምንበታል፡፡ የሮም ሰዎችም መጥተው አገራችንንና ወገናችንን ይወስዱብናል›፡፡ ሊቀ ካህናት ቀያፋም ‹ሕዝቡ ዅሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል› አላቸው፤›› (ዮሐ. ፲፩፥፵፯-፶) ተብሎ እንደ ተጻፈ ለጌታችን መከራ መቀበል አንዱ ምክንያት አልዓዛርን ከሞት ማስነሣቱ ነው፡፡

በዕለተ ሆሣዕና በምስጋና ወደ ቤተ መቅደስ መግባቱና ተአምራትን ማድረጉ

በዕለተ ሆሣዕና በሕፃናት አንደበት ሳይቀር በሕዝቡ ዅሉ እየተመሰገነ ጌታችን ወደ ቤቱ መቅደስ መግባቱና በዚያ ወቅት ያደረገው ተአምራት ሌላው የመከራው ምክንያት ነው፡፡ ‹‹ያን ጊዜም የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ተአምራት፤ ልጆችንም በቤተ መቅደስ ‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ› እያሉ ሲጮኹ ባዩ ጊዜ ደስ አላላቸውም፤›› እንዲል (ማቴ. ፳፩፥፲፭)፡፡

ስለዚህም በሆሣዕና ማግስት (ሰኞ ዕለት) የአይሁድ ባለ ሥልጣናት ጌታችንን ለመግደል የአድማ ስብሰባ አድርገው ሳይስማሙ ተለያዩ፡፡ በድጋሜ ማክሰኞ ዕለት ተሰብስበው አሁንም ሳይስማሙ ተለያዩ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ረቡዕ ተሰባሰቡ፤ በዚህ ዕለት ዅሉም አንድ ኾነው ይሙት በቃ የሚል ፍርድ በጌታችን ላይ ወስነው ስበሰባቸውን ደመደሙ (የመጋቢት ፳፫ እና ፳፬ ቀን ስንክሳር)፡፡

በዚህ ጊዜ ጌታችንን አሳልፎ የሚሰጣቸው ምሥጢረኛ ቤተሰብ የኾናቸውን ይሁዳን በማግኘታቸው ደስ አላቸው፡፡ ሠላሳ ብር ሊሰጡትም ተስማሙ፡፡ እርሱም ደስ ብሎት ሰው ሳይኖር አሳልፎ ሊሰጣቸው ምቹ ቦታ ይሻ ነበር (ሉቃ. ፳፪፥፫-፮)፡፡

ጸሎት ሐሙስ

በጸሎተ ሐሙስ ጊዜ የተከናወኑ ዐበይት ተግባራት

በዕለተ ሐሙስ ከተከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል ሠራዔ ሕግ፣ ፈጻሜ ሕግ የኾነው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሕግ በታች ኾኖ ሕገ ኦሪትን እየፈጸመ አድጓልና በኦሪት ሥርዓት የሚፈጸመውን የመጨረሻውን በግዐ ፋሲካ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር መመገቡ ነው፡፡ ሁለተኛው ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ይሁዳ እንደሚያስይዘው ለሐዋርያት በምልክት ማስረዳቱ ነው (ዮሐ. ፲፫፥፳፩)፡፡ ሦስተኛው ደግሞ እንደ አገልጋይ ራሱን ዝቅ አድርጎ ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ ነው፡፡ በዚህም ኅፅበተ እግር ሐዋርያት እንደ ተጠመቁ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ኅፅበት መድኃኒታችን ክርስቶስ ወሰንና አቻ የሌለው ፍጹም ትሕትናውን የገለጠበት ምሥጢር እንጂ ጥምቀት እንዳልኾነ ብዙ መጻሕፍት ይስማማሉ፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛርቱን እግር ካጠበ በኋላ ‹‹እናንተ መምህራችን፣ ጌታችን ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፡፡ እኔ ጌታችሁ መምህራችሁ ስኾን ዝቅ ብዬ እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም ዝቅ ብላችሁ የወንድሞቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል፡፡ ምሳሌ ኾኛችኋለሁና፤›› በማለት የትሕትና ሥርዓት ሠርቶ እነርሱም በሥራ እንዲገልጡት አዝዞአቸዋል (ዮሐ. ፲፫፥፲፭)፡፡ በግእዝ የተጻፈ አንድ ትርጓሜ ወንጌል ‹‹እዘርእ ፍቅረ ወትሕትና ውስተ አልባቢክሙ፤ ፍቅርንና ትሕትናን በልባችሁ እዘራለሁ፤›› እንዳላቸው ይናገራል፡፡

ሠለስቱ ምእትም በአንቀጸ መነኮሳት ‹‹ወኢትትሐከይ ኀፂበ እግረ አኃው ሶበ መጽኡ ኀቤከ እስመ በእንተ ዛቲ ትእዛዝ ይትኀሠሥዎሙ ለእለ ያጸርዕዋ ለዛቲ ግብር ወለእመ ኮኑ ኤጲስ ቆጶሳተ እስመ እግዚአብሔር ኀፀበ እግረ አርዳኢሁ ቅድመ ወአዘዞሙ ከማሁ ይግበሩ፤ ወንድሞች ወደ አንተ በመጡ ጊዜ እግራቸውን ማጠብን ቸል አትበል፡፡ ይህችን ሥራ ቸል የሚሏትን ስለዚህች ትእዛዝ ሥላሴ በፍዳ ይመረምሯቸዋልና፡፡ ኤጲስቆጶሳትም ቢኾኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ አዝዟቸዋልና፤›› (ሃይማኖተ አበው ፳፥፳፱፤ ፩ኛ ጢሞ. ፭፥፱-፲)፡፡

‹‹የማይታዩ ረቂቃን መላእክቱ አደነቁ፤ ከልዑል ዙፋኑ ወርዶ ለደቀ መዛሙርቱ ሲያገለግል ባዩት ጊዜ አገልጋዮቹ መላእክት ደነገጡ፡፡ ትሕትና ወዳለበት ፍቅር የአሕዛብ እግረ ልቡናን ያቀና ዘንድ ግሩም እሳት በትሕትና መገለጡን ባዩ ጊዜ ብርሃናት ደነገጡ፤›› ይላል ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግ (ሃይማኖተ አበው ፹፰፥፰)፡፡ ፊልክስዩስም ‹‹ወኅፅበተ ፋሲካ ትትሜሰል በምሥጢረ ትሕትና ፍጽምት፤ የፋሲካ ኅፅበት ፍጹም በኾነ የትሕትና ሥራ ይመሰላል፤›› ብሏል (መጽሐፈ መነኮሳት)፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ‹‹… ጌታችን ወደ ስምዖን ጴጥሮስ በደረሰ ጊዜ ጴጥሮስም ‹አቤቱ እግሬን የምታጥበኝ አንተ ነህን? አለው፡፡ እርሱም መልሶ ‹እኔ እግርህን ከላጠብሁህ አንተም ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም› አለው፡፡ ይህም ማለት ‹እኔ በአገልጋይ ምሳሌ እግርህን ካላጠብሁ አንተም ከበታችህ ላሉ ራስህን ዝቅ ማድረግ አትችልም፡፡ ራስህን ዝቅ ካላደረግህም የእነርሱ አለቃ መኾን አትችልም፡፡ በሰማያት ባለው መንግሥቴስ ከእኔ ጋር እንዴት አንድ ለመኾን ትችላለህ?››› በማለት ራሱ ትሑት ኾኖ ጴጥሮስን ትሑት እንዲኾን አጥብቆ እንደ መከረው ይናገራል፡፡

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩ መጻሕፍት በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ ፍጹም ትሕትናውን ለመግለጥ እንደኾነ በማያሻማ ኹኔታ አረጋግጠዋል፡፡ ሐዋርያት በዚህ ጊዜ (በኅፅበተ እግር) ተጠመቁ የሚል ግን ማኅበረ ሐዋርያት ከባስልዮስ መጽሐፍ አገኘን ብለው ከጠቀሷት አንዲቷ ጥቅስ በስቀተር ሌላ አልተገኘም፡፡ ከዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታ አንድ ነው፤ ሃይማኖት አንዲት ናት፤ ጥምቀትም አንዲት ናት፤›› (ኤፌ. ፬፥፭) ባለው መሠረት ሠለስቱ ምእት በጉባኤ ኒቅያ በተናገሩት የሃይማኖት ጸሎት ‹‹ኀጢአት በሚሰረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን›› (ሃይማኖተ አበው ፲፯፥፲፪) ከማለታቸውም ባሻገር ጥምቀት እንዳይደገም፣ እንዳይከለስ በፍትሕ መንፈሳዊ ከልክለዋል፡፡

በየዓመቱ የሕማማት ሐሙስ በየአብያተ ክርስቲያናቱ፣ ዘወትር በየቀኑ በየገዳማቱና ትምህርት ቤቶች ለሚስተናገዱ እንግዶች ዅሉ ኅፅበተ እግር ይከናወናል፡፡ ኅፅበት ጥምቀት ነው ከተባለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሠለስቱ ምእትም ኅፅበተ እግሩ ባለማቋረጥ ዅልጊዜ ሲተገበር (ሲከናወን) ሰዎች ዅሉ በየጊዜው ይጠመቃሉ ማለት ነው፡፡ ይህም ሐዋርያትና ሠለስቱ ምእት ጥምቀት አንድ ጊዜ ብቻ እንዲፈጸም ከወሰኑ በአንድ ምላስ ሁለት ምላስ ያሰኛልና፡፡ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን የሚጣረሱ ተቃራኒ ሥርዓቶችን ማራመድ አይቻልምና፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋር ደግሞ የእግር መታጠብ ጥምቀት ከኾነ ጌታችን እግራቸውን አጥቦ እንዲህ አድርጉ ብሎ አዞናልና አዲስ ተጠማቂዎችን አብሶም ሕፃናትን መላ አካላቸውን እያጠመቅን ለምን በቅዝቃዜ እናሰቃያቸዋለን? እግራቸውን ብቻ አጥበን ‹‹ተጠምቃችኋል›› እያልን አናሰናብታቸውም? እስኪ በማስተዋል እንመርምረው፡፡

መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ያከናወናቸው አምላካውያት ተአምራት እንዳይገለጡ ‹‹ይህን ለማንም እንዳትናገሩ፤›› እያለ አጥብቆ ይከለክል ነበር (ማቴ. ፰፥፬፤ ፱፥፴፤ ፲፮፥፳፤ ፲፯፥፲፱)፡፡ ይኸውም ገደቡ ካሣ እስከሚፈጸም እስከ ትንሣኤ ድረስ ኾኖ ከዚያ በኋላ ግን ተአምራቱ መነገር እንዳለበት ‹‹ወልደ እጓለ እመ ሕያው ክርስቶስ ከሙታን እስኪነሣ›› ብሎ ግልጽ አድርጎታል (ማቴ. ፲፯፥፲፱)፡፡ ይህንም ‹‹መከራን ከፊት አስቀምጦ፣ ደስታን፣ ክብርን መናገር ስለሚገባ ነው›› ብለው ሊቃውንቱ አትተውታል፡፡

ይቆየን

ክብረ ሰሙነ ሕማማት – ክፍል አንድ

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና (የሊቃውንት ጉባኤ አባል)

ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ሰሙነ ሕማማት ሰሙነ ስቅለትም ይባላል፡፡ ይኸውም ከሆሣዕና ማግስት (ከሰኞ) ጀምሮ እስከ ዓርብ ስቅለት ያለው ክፍለ ጊዜ ሲኾን ይህም ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ‹‹እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፡፡ ስለ እኛም ታመመ፡፡ እኛም እንደ ታመመ፣ እንደ ተገረፈ ቈጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፡፡ የሰላማችንም ተግሣፅ በእርሱ ላይ ነበረ፡፡ በእርሱም ቊስል እኛ ተፈወስን፤›› በማለት ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ገለጸው (ኢሳ. ፶፫፥፬-፭)፣ ሰሙነ ሕማማት የክብርና የሥልጣን ዅሉ ባለቤት፣ ዅሉን ቻይ፣ ኃያል የኾነው አምላክ እኛን ከመውደዱ የተነሣ የእኛን ዕዳ ለመክፈል በመስቀል እስከ መሞት ድረስ እጅግ ከባድና አሰቃቂ የኾነ መከራ በፈቃዱ የተቀበለበት ሰሙን ከመኾኑም ባሻገር እኛ ፍጹም ድኅነትን ያገኘንበት ጊዜ ነው፡፡

ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ጌቴሴማኒ ይዞ ከሔደ በኋላ ከእነርሱ ፈቀቅ ብሎ ‹‹ሰውነቴ እስከ ሞት ድረስ አዘነች፤›› እያለ ወዙ እንደ ውኃና እንደ ደም እስኪወርድ ድረስ እየወደቀ እየተነሣ በስግደት በኀዘን እንደ መሠረተው ዅሉ፣ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ የኾነ ክርስቲያን በሙሉ በኀዘን፣ በለቅሶ እየሰገደ የፈጣሪውን ውለታ የሚያስብበት፤ ለፈጣሪው ያለውን ፍቅር የሚገልጥበት ወቅት ነው – ሰሙነ ሕማማት (ማቴ. ፳፮፥፴፰፤ ማር. ፲፬፥፴፬፤ ሉቃ. ፳፪፥፵፬)፡፡ ‹‹… ክርስቶስ ተሰቅለ በሥጋሁ በእንቲአነ ወአንትሙኒ ተወልተዉ በይእቲ ሕሊና እስመ ዘሐመ በሥጋሁ ድኅነ እምኃጣውኡ፤ ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋው ከተሰቀለ እናንተም ይህችን አሳብ ጋሻ አድርጋችሁ ኑሩ፡፡ በሥጋው መከራ የተቀበለ ከኃጢአት ድኖአልና፤›› በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ አጥብቆ የመከረን ስለዚህ ነው (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፩)፡፡

የሚገባ ስግደት

ስግደት የአምልኮ ስግደት እና የአክብሮት ስግደት ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ እኛ ኢያሱ ለመልአኩ እንደ ሰገደ ዮሐንስ፤ ወንጌላዊም እንደዚሁ ለመልአኩ መላልሶ እንደ ሰገደ እግዚአብሔር አምላክ ላከበራቸው ቅዱሳን መስገድ ያከበራቸው እግዚአብሔርን ማክበር መኾኑን አውቀን የአክብሮት ስግደት ስንሰግድላቸው ያልገባቸው ሰዎች ከኢያሱና ከዮሐንስ በላይ ለእግዚአብሔር አምልኮት ተቈርቋሪ በመምሰል ይዘብቱብናል፤ ባይገባቸው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎችም እንደዚሁ ‹‹በሰሙነ ሕማማት ሌሎች በዓላት ተደርበው ሲውሉ ስግደት አይገባም፤›› እያሉ ሕዝቡን በየጊዜው ያደናግራሉ፡፡ በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ‹‹በጌታችን በዓል፣ በእመቤታችን በዓል ሥጋ ወደሙ ከተቀበሉ በኋላ ሰጊድ አይገባም፤›› ይልና በጌታ በዓል አድንኖ፤ በእመቤታችን በዓል አስተብርኮ በቅዱሳን በዓል ሰጊድ ይላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሐተታ ለየትኛው ስግደት እንደ ተነገረ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

አንደኛ የሕማማት ዝርዝር ኹኔታ የተጻፈው በአንቀጸ ጾም ነው፤ ይህ ሐተታ ግን የሚገኘው በአንቀጸ ጸሎት ነው፡፡ ከሕማማት ጋር ፈጽሞ ግንኙነት የለውም፡፡ ሁለተኛ ፍትሕ መንፈሳዊ በአንቀጽ ፲፭ ሐተታውን ሲጀምር ‹‹ወዘይጼሊ ቅድመ ይስግድ ወበዘይበጽሕ ዝክረ ሰጊድ ለእግዚአብሔር ልዑል በጊዜ ጸሎት›› በማለት የሚጸልይ ሰው አስቀድሞ (በመጀመሪያ) አንድ ጊዜ ወይም ሦስት ጊዜ ሰጊድን ከሚያነሣ አንቀጽ ላይ ሲደርስ፣ ለአብነትም ‹‹ንሰግድ ለከ ኦ ዘለከ ይሰግድ ኵሉ ብርክ፤ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ፤ ንሰግድ ለከ ክርስቶስ፤ እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐተ ስግደተ፤ እሰግድ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ፤ እሰግድ ለመስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ›› የመሳሰለ ንባብ ሲያጋጥም መስገድ እንደሚገባ ያዛል፡፡

ስለዚህ በግል ጸሎት ጊዜና በንስሓ ወቅት ስለሚሰገደው ስግደት ወይም አንድ ባሕታዊ ፆር እንዳይነሣብኝ ብሎ፤ ምእመናን ክብር ለማግኘት ብለው ስለሚሰግዱት ስግደት የተወሰነውን ሥርዓት ከሕማማት በዓል አከባበር ጋር ያለ ስፍራው ማምጣት ስሕተት ነው፡፡ ምክንያቱም ሰሙነ ሕማማት ዓርብ ስቅለትን ጨምሮ ከጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ በዓሉ ደግሞ የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴ ሳይኾን ባለቤቱ በመሠረተው በኀዘን፣ በጸሎት፣ በልቅሶ፣ በስግደት ነውና፡፡ ስለኾነም ማንኛውም በዓል የዓመትም ይኹን የወር በዓል ከሕማማት ጋር ቢገጥም እንኳ አልፎ ከፋሲካ በኋላ ይከበራል እንጂ በሕማማት ውስጥ አይከበርም፡፡ ስግደትም አይከለከልም፡፡ ታዲያ በዓሉ ቦታውን ለቆ ሒዶ እያለ የሕማማትን ስግደት እንዴት ያስቀራል?

መጽሐፉ በጌታችን በዓል ‹አድንኖ›፤ በእመቤታችን በዓል ‹አስተብርኮ› ብሎ በቅዱሳን በዓል ‹ስግደት› ነው የሚለው፡፡ እንኳን በሰሙነ ሕማማት የቅዱሳን በዓላት በሚውሉባቸው ሌሎች ዕለታትም ስግድት መስገድ አይከለከልም፡፡ እነዚያ በግምት የሚነጉዱ ሰዎች ግን ‹‹የቅዱሳን በዓል በሕማማት ሲውል አይሰገድም፤›› እያሉ ችግር ሲፈጥሩና ‹‹እገሌ በበዓል ጊዜ ይሰግዳል ይላል፡፡ መናፍቅ ነው፤›› እያሉ የእውነተኞችን መምህራን ስም ሲያጠፉ ይስተዋላሉ፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው አካል ተዉ ሲላቸው ካልተመለሱ ጥብቅ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

 ጉዳት ያለው ሰላምታ

በመሠረቱ ሰላምታ በቁሙ ፍጹም ጤና፣ ዕረፍት፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ደኅንነት፣ ተድላ፣ ደስታ፣ ሰላምታ፣ ቡራኬ፣ የምርቃት ቃል፣ ሰው ሲገናኝ ወይም ሲለያይ የሚናገረው የሚፈጽመው ተግባር ነው (መጽሐፈ ሰዋስው ዘኪዳነ ወልድ)፡፡ ስለኾነም ሰላም በየትኛውም ቦታ፣ በማንኛውም ጊዜ ለዅሉ የሚበጅ፤ ከዅሉም በላይ እጅግ ጠቃሚ ተግባር ነው፡፡ ጎጂና በጣም ክፉ ወይም አደገኛ ኾኖ የተገኘው የጥፋት ልጅ የተባለው የይሁዳ ሰላምታ ነው፡፡ ‹‹ይህንንም ሲነግራቸው ሕዝቡ ደረሱ፤ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ይሁዳ ይመራቸው ነበር፡፡ ወደ ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ ሳመው፤ የሰጣቸው ምልክት ይህ ነበር፡፡ ‹የምስመው እርሱ ነውና አጽንታችሁ ያዙት፤› አላቸው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ‹ይሁዳ! የሰውን ልጅ በመሳም ታስይዘዋለህን? ልታስገድለው አይደለምን?› አለው›› (ሉቃ. ፳፪፥፵፯-፵፰፤ ማቴ. ፳፮፥፵፯-፶፮፤ ማር. ፲፬፥፫-፶፤ ዮሐ. ፲፰፥፫-፲፪)፡፡

ጌታችን በዚህ ኹኔታ ከተያዘ በኋላ ነው እስከ ሞት ድረስ ያን ዅሉ መከራ የተቀበለው፡፡ ስለኾነም ከሰሙነ ሕማማት እስከ በዓለ ትንሣኤ (ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን) እስከሚባል ድረስ መስቀል ወይም መጽሐፍ መሳለም እንዳይገባ ‹‹ወኢይትአምኁ በበይናቲሆሙ ዘእንበለ በዕለተ ፋሲካ ወኢየአምኁ መስቀለ ወወንጌለ፤ ያለ ፋሲካ ቀን እርስ በእርሳቸው አይሳሳሙ፤ መስቀልንና ወንጌልንም አይሳለሙ፤›› ተብሎ ተደንግጓል (ፍት.መን. ገጽ ፪፻፳፯)፡፡ ጸዋትወ ዜማም ‹‹ይሁዳ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ ሳመው ወይም በመሳም ስላስያዘው እርስ በርሳቸው አይሳሳሙ፤ ወንጌልንና መስቀልንም አይሳለሙ፡፡ የሞቱትንም ሰዎች አይፍቱ፤›› ይላል (ገጽ. ፺፬-፺፯)፡፡

በግብረ ሕማማት ገጽ ፵፯ እና ፭፻፺፭ ‹‹ወኢይትአምኁ በበይናቲሆሙ ወኢይአምኁ ወንጌለ ወመስቀለ በእንተ ዘአምኆ ይሁዳ ወኢይዝክሩ ሰሞሙ ለእለ ኖሙ ቅዱሳን አበው ወኢይበሉ ሐዳፌ ነፍስ›› ይላል፡፡ ይህ ትእዛዝ በእነዚህ ዅሉ መጻሕፍት እየተደጋገመ መጠቀሱ ለአጽንዖተ ነገር ነው፡፡ በሰሙነ ሕማማት እርስበርስ መሳሳም፣ መስቀል ማሳለምና መሳለም ከይሁዳ ሰላምታ ጋር የተያያዘ ስለኾነና የይሁዳ ተባባሪ ስለሚያሰኝ እስከ ትንሣኤ ድረስ መሳሳምም ኾነ ወንጌልንና መስቀልን መሳለም ተከልክሏል፡፡

ይቆየን