ክብረ ሰሙነ ሕማማት – ክፍል አራት (የመጨረሻ ክፍል)

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና (የሊቃውንት ጉባኤ አባል)

ሚያዝያ  ቀን ፳፻፱ .

‹‹ማን ይናገር የነበረ›› እንዲሉ ቅዱሳን ሐዋርያት እስከ ትንሣኤ ድረስ መንፈስን (ልጅነትን) ሳይቀበሉ ቆይተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ እነርሱ በመጣ ጊዜ በንፍሐት መንፈስ ቅዱስን እንዳሳደረባቸው ራሳቸው በግልጥ ተናግረዋል፡፡ በጌታችን ቀኝ ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ በክርስቶስ ደም ካሣ እንደ ተፈጸመ፣ ልጅነት እንደ ተመለሰ ሲያረጋገጥ ጌታችንን ‹‹ዳግመኛ በመጣህ ጊዜ በመንግሥትህ አስበኝ?›› ቢለው ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ‹‹እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ፤›› ብሎታል (ሉቃ. ፳፫፥፵፫)፡፡ ወገኔ ሆይ! ስለዚህ የሐዋርያት ጥምቀት የትንሣኤ ዕለት ለመኾኑ ከዚህ የበለጠ ማስረጃ ምን አለ? ማወቅ ለሚሻ ቅን ልቡና ላለው ከዚህ በላይ የቀረበው ማስረጃ በቂ ነው፡፡ ተጨማሪ ማስረጃ ካስፈለገ ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ ያስቀመጥናቸውን ጥቅሶች መመልከት ይቻላል፤

  • ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ›› (ሐዋ. ፳.፳፰)፤ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት ተቀድሰናል›› (ዕብ.፲.፲)፤
  • ‹‹ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡ …›› (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፪)፤
  • ‹‹በክቡር በክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ እናንተ ታውቃላችሁ›› (፩ኛ ጴጥ. ፲፰፥፲፰)፤
  • ‹‹… ከኃጢአታችን ላጠበን፤ በደሙ ላነጻን …›› (ራእ. ፩፥፮)፤
  • ‹‹. . . ተገድለሃልና በደምህም ከሕዝብና ከአሕዛብ ከነገድም ዅሉ፤ ከወገንም ዅሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃልና›› (ራእ. ፭፥፱)፡፡

እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች የልጅነት ክብር (ጥምቀት) ለሐዋርያት የተሰጠው የክርስቶስ ደም ከፈሰሰ በኋላ ነው እንጂ ከዚያ በፊት በሕጽበተ እግር እንዳልኾነ በግልጥ ያስረዳሉ፡፡

 ቅዱስ የኾነ ትውፊታዊ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን

በመሠረቱ የተቀደሰ ትውፊታዊ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናችን በራሱ አስተማሪ ነው፡፡ የማያስተውል ሰው ግን ብዙ ማስረጃ ቢቀርብለትም አያምንም፡፡ ስለዚህም በቅዱሳት መጻሕፍት መነሻነት ዘወትር በግልጥ ሲከናወን የኖረውን፤ አሁንም ባለ ማቋረጥ እየተከናወነ የሚገኘውን፤ ለወደፊትም የሚከናወነውን ቅዱስ የኾነውን የኦርቶዶከሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ ሥርዓት ወደ ጐድን በመተው ግምታዊ ልማድን እየተከተለ ‹‹የሐዋርያት ጥምቀት በሕጽበተ እግር ነው፤ እኛ የዳነው በሕጽበተ እግር ነው፤›› የሚሉ ሰዎች መጡ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ስታጠምቅም፣ ቅብዐ ቅዱስ ስትቀባም ከራስ ጀምራ ነው፡፡ በመጨረሻም በራስ ላይ እፍ ብላ መንፈስ ቅዱስን በማሳደር ነው እንጂ እግርን በማጠብ አጥምቃ አታውቅም፡፡

ይኸውም ከሐዋርያት የተገኘ፤ ከሐዋርያት ሲያያዝ የመጣ ትውፊታዊና ቅዱስ ሥርዓት ነው እንጂ አሁን የተፈጠረ አዲስ ባህል አይደለም፡፡ ስለዚህም የጸሎተ ሐሙስ ሕጽበተ እግር ጥምቀት ሳይኾን ፍጹም ትሕትናን ሠርቶ ለማሠራት ጌታችን የፈጸመው ተግባር ነው፡፡ ይህንም ያለ ጥርጥር ልንቀበለውና ልንተገብረው ይገባል፡፡ ከዚህ ሌላ የሐዋርያት ጥምቀት አንዳንዶቹ ተከተሉኝ ሲላቸው ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በበዓለ ኀምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ዅሉ አባባል ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት ያልተደገፈ ግምታዊ አሳብ ነው እንጂ፡፡

የሐዲስ ኪዳን ቍርባን መጀመሪያ

በዕለተ ሐሙስ ከተፈጸሙ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ መድኃኒታችን ክርስቶስ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው፤ ይህ ደሜ ነው፤›› ብሎ አማናዊ ሥጋውንና ደሙን መስጠቱ ነው (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፰)፡፡ እንደዚሁም ይህ ዕለት ሰፊ ጸሎት የተደረገበት የጸሎት ቀን ነው፡፡ ጌታችን ሐሙስ ዕለት ወዙ እንደ ውኃና እንደ ደም ወርዶ መሬቱን ጭቃ እስኪያደርገው ድረስ መላልሶ ስለጸለየ ዕለቱ ‹ጸሎተ ሐሙስ› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ጌታችን የጸለየበትን ቦታም ወንጌላውያኑ በተለያየ ስያሜ ጠርተውታል፤

ማቴዎስና ማርቆስ – ‹ዐጸደ ወይን›፣ ‹ጌቴሴማኒ›፤ ሉቃስ – ‹ደብረ ዘይት›፤ ዮሐንስ – ‹ማዕዶተ ቄድሮስ›፣ ‹ፈለገ አርዝ›፣ ‹ዐጸደ ሐምል› በማለት ሰይመውታል (ማቴ.፳፮፥፴፮፤ ማር.፲፬፥፴፪፤ ሉቃ. ፳፩፥፴፯፤ ፳፪፥፴፱፤ ዮሐ. ፲፰፥፩)፡፡ በተጨማሪም ይህ ዕለት (ሐሙስ) ያለ እርሱ ፈቃድ ሊይዙት እንደማይችሉ ለማስረዳት ጌታችን በመለኮታዊ ኃይሉ እንደ ቅጠል እንዲረግፉ ካደረጋቸው በኋላ በይቅርታው ብዛት መልሶ በማስነሣት በፈቃዱ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠበት ዕለት ነው (ዮሐ. ፲፰፥፭-፰)፡፡

ዓርብ ስቅለት (የድኅነት ቀን ዓርብ)

ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹የድኅነት ቀን› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. ፳፯፥፩-፶፯)፡፡ አይሁድ ይህን አጥፍቶአል የሚሉት ነጥብ ሳይኖራቸው ነውና ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት ጲላጦሰ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡

‹‹ክፉ የሠራ ባይኾንስ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር›› በሚል የሸፍጥ ቃል ሲያጕረመርሙ ጲላጦስ መልሶ ‹‹እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት፤›› አላቸው፡፡ አይሁድም ኦሪት ‹‹ኢትቅትል ብእሴ ጻድቀ ወኀጥአ ኢታኅዩ፤ ጻድቅን ሰው አትግደል፤ ኀጥኡንም ከፍርድ አታድን፤›› ትላለችና ‹‹እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም፤›› ብለዋል (ዮሐ. ፲፰፥፳፰-፴፩)፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ‹‹በሕጋችን ጻድቀ ባሕርይ ክርስቶስን መግደል አይገባንም ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች ነን፤›› ሲያሰኛቸው ነው፡፡ በኋላም እርሱ ሞቶ ዓለም ይድን ዘንድ ወደ ምድር መጥቷልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ስለዚህም ገርፈው ሰቀሉት፡፡ ጌታችን ሲሰቅልም የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤

፩. ፀሐይ ጨለመ፤

፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤

፫. ከዋክብት ረገፉ፤

፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤

፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤

፮. መቃብራት ተከፈቱ፤

፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤

፩. ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)››፤

፪. ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ››፤

፫. ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፤

፬. እመቤታችንን ‹‹ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ›› ደቀ መዝሙሩንም ‹‹እናትህ እነኋት›› በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤

፭. ‹‹አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ››

፮. ‹‹ተጠማሁ››

፯. ‹‹ዅሉ ተፈጸመ›› (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡

ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቈየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ኾኖአል፡፡ ‹‹ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነ ፀሐይ›› እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ቅድስት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር›› እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡