ቀዳም ሥዑር

ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የሰሙነ ሕማማቷ ቅዳሜ ‹ቀዳም ሥዑር› ወይም ‹ቀዳሚት ሥዑር› ትባላለች፡፡ ትርጕሙም ‹የተሻረች ቅዳሜ› ማለት ነው፡፡ የማትጾመዋ ቅዳሜ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል ‹የተሻረችው ቅዳሜ› ተብላ ተጠርታለች፡፡ ነገር ግን ቃሉ ጾምን እንጂ በዓል መሻርን አያመለክትም፡፡ በቀዳም ሥዑር  ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኅሌቱም እዝሉ እየተቃኘ፣ እየተመጠነ፣ እየተዘመመ፣ እየተመረገደ፣ እየተጸፋ ያድራል፡፡ ጠዋት አቡን፣ መዋሥዕት፣ ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ‹‹ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ›› በሚለው ሰላም ሥርዓተ ማኅሌቱ ይጠናቀቃል፡፡

ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለ ኾነ ዕለተ ቅዳሜ ‹ለምለም ቅዳሜ› ተብላም ትጠራለች፡፡ በቀዳም ሥዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል (ቃለ ዓዋዲ) እየመቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ›› የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደ ሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደ ገለጠልን በማብሠር፤ ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብሥራት ነው፡፡

ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት ድረስ በራሳቸው ላይ አሥረውት ይቆያሉ፡፡ ይህም አይሁድ በጌታችን ራስ ላይ የእሾኽ አክሊል ማሠራቸውን የሚያስታውስ ነው፡፡ የቀጤማው አመጣጥና ምሥጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በማየ አይኅ (በጥፋት ውኃ) በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ‹‹የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ፤ ታወጀ፤›› በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡

ዕለተ ቅዳሜ ‹ቅዱስ ቅዳሜ› እየተባለችም ትጠራለች፡፡ ቅዱስ መባሏም ቅዱስ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ዅሉ ስላረፈባት ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ዅሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፤ በነፍሱ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለ ኾነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየች ዕለት መኾኗን ለማመላከት ‹ቅዱስ› (ቅድስት) ተብላለች፡፡

ምእመናን ሆይ! በአጠቃላይ የጌታችንን የመከራ ሳምንት ‹ሰሙነ ሕማማት› ብለው ሰይመው፣ ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ያቆዩልንን ትውፊት ልንጠብቀውም፣ ልንጠቀምበትም ይገባል፡፡ የዕለታቱን ክብርና ስያሜ ከማወቅና ከመረዳት ጋር በዕለታቱ የታዘዙትን ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት ይኖርብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ (ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት)፣ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ከሚያዝያ ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም፣ ማኅበረ ቅዱሳን፤ አዲስ አበባ፡፡