መስቀል የድኅነት ዓርማ (ምልክት)

በዲያቆን ዘላለም ቻላቸው

ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እግዚአብሔር አምላካችን በቸርነቱ አዳምንና ሔዋንን ከፍጥረቱ ዅሉ አልቆ በራሱ አርአያና አምሳል ፈጥሮ ገነትን ያህል ቦታ አዘጋጅቶ በተድላ በደስታ እንዲኖሩ፣ ሌሎችንም ፍጥረታት ዅሉ እንዲገዙ ሥልጣንንም ጭምር ሰጣቸው (ዘፍ. ፩፥፳፭)፡፡ አዳምና ሔዋንም በገነት በነበሩባቸው ዓመታት ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገሩ በፍጥረታት ላይ ነግሠው በደስታ ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላ ግን ‹‹አትብሉ›› የተባሉትን ዕፅ በልተው የእግዚአብሔርን ሕግ በማፍረስ በደሉ፡፡

ከፈጣሪያቸው ጋር ራሳቸውን ለማስተካከል (አምላክ ለመኾን) በማሰብና በመመኘታቸው ይቅርታ የማይገባውን ዐመፅ  ፈጸሙ፡፡ በዚህ ጊዜ አዳም፡- ‹‹… ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትኹን፣ በሕይወት ዘመንህ ዅሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾኽና አሜከላ ታበቅልብሃለች …››፤ ሔዋን ደግሞ፡- ‹‹… በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛዋለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ …» ተብለው ተረገሙ (ዘፍ. ፫፥፲፭-፲፱)፡፡ «ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ» (ዘፍ. ፪፥፲፰) ተብሎ አስቀድሞ በተነገራቸው ሕግ መሠረት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣሉ፤ ከገነት ተባረሩ፤ የሞት ሞት ተፈረደባቸው፡፡

አዳምና ሔዋንም ኾኑ ልጆቻቸው ከዚህ ውድቀት ራሳቸውን ለማዳን አልቻሉም፤ ከተፈረደባው የሞት ሞት እንዲድኑ የበደሉን ካሣ በሞት የሚከፍል ሰው ያስፈልግ ነበር፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ፍርዱ እውነተኛና ትክክለኛ ነውና ካሣ ሳይከፈል ፍርዱ አይሻርምና፡፡ ከአቤል ጀምሮ የፈሰሰው የነቢያት ደምም ካሣ ሊኾን አልተቻለውም፤ እነዚህ ሰዎች ራሳቸው የአዳምና ሔዋን በደል ስለ ነበረባው ለመሥዋዕትነት አልበቁም፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ርኅሩኅ አምላክ ነውና የፍጡሩ የሰው ልጅ ሥቃይ ስላሳዘነው ከራሱ ጋር የሚታረቅበትን መንገድ አዘጋጀ፡፡ ስለዚህም ሥጋ ለብሶ (ሰው ኾኖ)፣ መከራ ተቀብሎ፣ ሙቶ እንደሚያድናቸው ቃል ኪዳን ገባላቸው፡፡

የዘመኑ ፍጻሜ (የቀጠሮው ቀን) በደረሰ ጊዜም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ቃል (ወልድ) ከነፍሷ ነፍስ፣ ከሥጋዋ ሥጋ ነሥቶ (ተዋሕዶ) ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ነቢዩ አሳይያስ «በሰዎች ዘንድ የተናቀና የተጠላ የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር፤ በእርግጥ እርሱ ደዌአችንን ወሰደ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ …፤›› እንዳለው ከልደቱ እስከ ስቅለቱ ድረስ መከራን በመቀበል የበደላችንን ዋጋ ከፈለ (ኢሳ. ፶፫፥፫-፬)፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በከፈለው የሕይወት መሥዋዕትነትም የሰው ልጆችን ከራሱ፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አስታረቃቸው፡፡ በመስቀሉም መለኮታዊ ሥልጣኑን ገልጦ፣ ዲያሎስንና ሠራዊቱን ቀጥቅጦ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን ነጻ አወጣቸው፡፡ «ወሪዶ እመስቀሉ ቀጥቀጠ ኃይሎ ለፀላኢ አርአየ ሥልጣኖ ለዕለ ሞትከመስቀሉ ወርዶ የጠላትን ኃይል ቀጠቀጠ፤ በሞትም ላይ ሥልጣኑን ገለጠ፤» እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡

መስቀል ክርስቶስ መከራ የተቀበለበት እና የማዳኑን ሥራ የገለጠበት የድኅነታችን ዓርማ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰፊ አገር በሰንደቅ ዓላማ (ባንዲራ) ይወከላል፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ጨርቅ ቢኾንም ትርጕሙ ግን አገር ማለት ነው፡፡ ባንዲራን መውደድ፣ ለባንዲራ መሞት ስንልም አገርን መውደድ፣ ለአገር መሞት ማለታችን ነው፡፡ ተቋማትና ድርጅቶችም እንዲሁ የራሳቸው መገለጫ የኾነ ዓርማ አላቸው፡፡ መስቀልም የክርስቶስ የማዳኑ ሥራ የመከራውና የሞቱ ወካይ ዓርማ (ምልክት) ነው፡፡ መስቀሉን ስናይ፣ ስናማትብ፣ ስሙን ስንጠራ (ስንሰማ) በእነዚህ ዅሉ የክርስቶስን መከራና የማዳን ሥራውን እናስታውሳለን፡፡ ‹‹በመስቀሉ አዳነን›› ስንልም ጌታችን በመስቀል ላይ በፈጸመው ቤዛነት ድነናል ማለታችን ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን በብሉይ ኪዳን የነበሩትን የመሥዋዕት ሥርዓቶች ያዘጋጀው፤ በሕዝቡ መካከል ለመገኘቱ ምልክት የኾነውን ታቦት የሰጠው ሰዎች አምልኮታቸውን ለመፈጸም የሚታይ የሚዳሰስ ነገር በመፈለጋቸው ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም በቤተ ክርስቲያን ያሉት ልዩ ልዩ ሥርዓቶች፣ ንዋያተ ቅዱሳት፣ ከዚሁ አንጻር የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው የማይታይ ጸጋ በሚታይ አገልግሎት የሚፈጸመውም ስለዚህ ነው፡፡ መስቀልም እግዚአብሔር አምላካችን ለእኛ ሲል የተቀበለውን መከራ የምናስታውስበት፤ ከሞት ሞት መዳናችንን በማሰብ አምልኮታችንን የምንገልጥበት የድኅነታችን ዓርማ ነው፡፡ የጌታችንን መከራ፣ ስቅለት እና ሞት ክርስቲያኖች ዅል ጊዜ ማሰብ አለብን፡፡ ይህንን እንድናደርግ የሚያስችለን፤ ስለ ክርስቶስ ሕማም ስናስብም ሕሊናችንን ሰብስቦ የተከፈለልንን ዋጋ እንድናስታውስ የሚያደርገን መስቀል ነውና፡፡

ጌታችን «መስቀሌን ተሸክማቸሁ ተከተሉኝ» ሲልም መከራዬን፣ ስቃዬን፣ ሞቴን ተጋሩ ማለቱ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «ጥልን በመስቀሉ ገደለ» ሲል እንደ ገለጸው (ኤፌ. ፪፥፲፮)፣ እኛም «መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንዕነ መስቀል ቤዛነ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ አይሁድ ክህዱ ንሕነሰ አመነ ወእለ አመነ በኀይለ መስቀለ ድኅነ፤ መስቀል ኃይላችን ነው፤ መስቀል የምንጸናበት ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፤ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው፡፡ አይሁድ ይክዱታል፤ እኛ ግን እናምነዋለን፡፡ ያመነውም እኛ በመስቀሉ ኃይል እንድናለን፤ ድነናልም» እያልን የክርስቶስን መከራውን፣ መስቀሉን፣ ሞቱን፣ በሞቱም እኛ መዳናችንን እንመሰክራለን፡፡

‹‹… በመስቀልህ …›› ስንልም ‹‹መከራ በመቀበልህ፣ በመሰቀልህ፣ በሞትህ፣ …›› ወዘተ ማለታችን ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም «መስቀል ብርሃን ለኵሉ ዓለም መሠረተ ቤተ ክርስቲያን፤ መስቀል የዓለሙ ዅሉ ብርሃን፤ የቤተ ክርስቲያንም መሠረት ነው፤ … » ዳግመኛም ‹‹በመስቀሉ አርኀወ ገነተ ወተሞዐ ኃይለ ሥልጣኑ ለሞት፤ በመስቀሉ ገነትን ከፈተ፤ የሞተ ኃይልም ድል ተደረገ፤›› በማለት ክርስቶስ በመስቀሉ ገነት መከፈቷን፤ ሞትም ድል መደረጉን ያብራራል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ መስቀል ያገኘችውን ጸጋና ለክርስቶስ ያላትን ክብር ራሷ መመስከሯን ሲገልጽም ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ሲል ይዘምራል፤ ‹‹ትዌድሶ መርዓት ቤተ ክርስቲያን እንዘ ትብል ‹በመስቀልከ አብራህከ ሊተ እንዘ ግድፍት ወኅድግት አነ ምራቀ ርኩሳን ተዐገሥከ በእንቲአየ ሕይወተከብኩ በትንሣኤከ ጸጋ ነሣዕኩ ወደቂቅየኒ ገብኡ ውስተ ሕጽንየ በመስቀልከ አብራህከ ሊተ በመስቀልከ አድኀንከ ኵሎ ዓለመ›፤ ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን (ጌታን) እንዲህ እያለች ታመሰግነዋለች፤ ‹የተተውሁና የተጣልሁ ኾኜ ሳለ አብርተህልኛል፤ ስለ እኔ ብለህ የርኩሳንን ምራቅ ታግሠሃል፡፡ በትንሣኤህጋን አገኘሁ፤ ልጆቼም ወደ እቅፌ ገቡ፡፡ በመስቀልህ አበራህልኝ፤ በመስቀልህም ዓለምን ዅሉ አዳንህ›፤»

መስቀል ምንን ያስታውሰናል?

መስቀልን ስናይ፣ መስቀልን ሰናስብ፣ ስሙንም ስንጠራ የሚከተሉትን ምሥጢራት እናስታውሳለን፤

ሀ. እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር

ነቢዩ ኢሳይያስ «እኛ ዅላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጎድን፤» እንዳለው (ኢሳ. ፶፫፥፮)፣ እኛ የሰው ልጆች በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይተን፣ በሞት ጥላ ሥር በመከራና በችግር እንኖር ነበር፡፡ አምላካችን እኛን ለማዳን አንድያ ልጁን ወደዚህ ምድር ልኮና የሞት መሥዋዕትነት ከፍሎ አድኖናል፡፡ «በእርሱ የሚያምን ዅሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን ወዷል፤» ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዮሐ. ፫፥፲፮)፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ስለ ወዳጆቹ ሕይወትን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውምና (ዮሐ. ፲፭፥፫፤ ሮሜ. ፭፥፰)፡፡ ስለዚህ መስቀል ስለ እኛ ሲል በመስቀል ላይ የሞትን ጽዋ የተቀበለው መድኃኒታችን ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያስታውሰን ምልክት ነው፡፡

ለ. ኃጢአታችንንና የኃጢአት ደመወዝ ሞት መኾኑን

መስቀል ኃጢአታችንን የሚያስታውሰን ምልክት ነው፡፡ ጌታችን በመስቀል የተሰቀለው ኃጢአተኞች በመኾናችን፣ እኛን ለማዳን ነውና፡፡ «በበደላችን ሙታንነን ሳለ በክርስቶስ ሕያዋንንን» እንደ ተባለው (ኤፌ. ፪፥፭)፣ ጌታችን እኛን ከሞት ለማዳን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለመሞት ያበቃው እኛ መበደላችን፤ የበደል (የኃጢአት) ደመወዝ ደግሞ ሞት መኾኑ ነው፡፡ መስቀል ይህንን ያስታውሰናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «በዋጋ ተገዝታችኋልና የራሳችሁ አይደላችሁም፤» እንዳለው (፩ኛ ቆሮ. ፮፥፳)፣ ከኃጢአት ባርነት ነጻ የወጣነው ዋጋ ተከፍሎብን እንደ ኾነ በመረዳት እግዚአብሔርን ማመስገን፤ ለእርሱም በትሕትና መገዛት ይኖርብናል፡፡

ሐ. የእግዚአብሔርን ቅን ፈራጅነት

መስቀል የእግዚአብሔር ፍቅር እና ቅን ፍርድ በአንድ ላይ የተደረጉበት አደባባይ ነው፡፡ አዳም በበደለ ጊዜ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ሞት ተፈረደበት፤ እግዚአብሔር የሰው ልጆች ወዳጅ በመኾኑ ሊያድነው ቢወድም፣ ስለ በደሉ ካሣ ሳይከፈል አላዳነውም፡፡ ስለዚህ ራሱ መጥቶ መሥዋዕት በመኾን የበደሉን ካሣ በመስቀል ላይ ከፈለ፤ በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩና ቅን ፍርዱ በአንድ ላይ ተገለጠ፡፡

መ. የጌታችንን ሕማማትና ሞት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበደላችንን ዋጋ የከፈለው ሊነገሩ የማይችሉ ሕማማትን ተቀብሎ፣ ተሰዶ፣ ተሰድቦ፣ ተዋርዶ፣ ተገርፎ፣ የኃጢአተኞች ምራቅ ተተፍቶበት፣ መስቀል ተሸክሞ ተራራ ወጥቶ፣ እጆቹና እግሮቹ ተቸንክረው፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ የሞትን ጽዋ ቀምሶ ነው፡፡ መስቀል እነዚህን ዅሉ የጌታችንን ሕማማትና ሞት የሚያስታውሰን ምልክት ነው፡፡

ሠ. ይቅር መባላችንን እና ድኅነታችንን

መስቀልን ስንመለከት እግዚአብሔር ኃጢአታችንን እንዴት ይቅር እንዳለንና በመስቀል ላይ ሳለ «አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁም ይቅር በላቸው» ማለቱን እናስታውሳለን (ሉቃ. ፲፫፥፴፬)፡፡ ዳግመኛም ጌታችን በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ በዲያብሎስ አገዛዝ ሥር የነበሩ ነፍሳትን ነጻ እንዳወጣቸው፤ እኛንም በአዳም በደል ምክንያት ከመጣብን የባሕርይ ድካም እንዳዳነን እናስባለን፡፡ አሁንም መስቀልን ስንመለከት በጌታ ቀኝ ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ ድኅነትን እንዳገኘ፤ ጌታችን በቸርነቱ በደሉን ዅሉ ይቅር ብሎ በፍቅሩ ወደ እርሱ እንደ ሳበውና ወደ ገነት እንዳስገባው እናስባለን፡፡ እኛም በተስፋ እንሞላለን፡፡

ረ. ትንሣኤንና ዳግም ምጽአትን

የጌታችንን መስቀልና ሞት ስናስታውስ አብረን ትንሣኤውንም እናስባለን፤ በእርሱ ትንሣኤ ደግሞ የእኛን ትንሣኤ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መስቀል ዳግም ምጽአትንም ያስታውሰናል፡፡ ዳግም ምጽአትን ስናስብም ለፍርድ በፊቱ እንደምንቆም እናስታውሳለን፡፡ ጌታችን ስለ ኅልፈተ ዓለምና ዳግም ምጽአት ሲያስተምር እንዲህ ብሏልና፤ «የዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት (መስቀል) በሰማይ ይታያል …. የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ኾኖ በኃይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል፤» (ማቴ. ፳፬፥፴)፡፡

ሰ. መስቀልን እንድንሸከም መታዘዛችንን

መስቀል ጌታችን «ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ … የራሱንም መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ደቀ መዝሙሬ ሊኾን አይችልም፤» በማለት ያስተማረንን ትምህርት ያስታውሰናል » (ማቴ. ፲፮፥፳፬፤ ሉቃ. ፲፬፥፳፯)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡