01

የሕገወጥ ሕግ አስከባሪዎችን ሴራ ያከሸፈ ደብዳቤ

ሚያዚያ 26/2004 ዓ.ም.

ሚያዚያ 24 ቀን 2004 ዓ.ም. ሕገወጥ ሕግ አስከባሪዎች በሚል ርዕስ ሰሞኑን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስለተፈጸመ ድርጊት ማኅበረ ቅዱሳን መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

 

የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ የሆኑት ቆሞስ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ሳያምኑበትና ሕጋዊ መስመሩን ሳይጠብቅ በጆቢራዎቹ አቀነባባሪነት የተዘጋጀውን ደብዳቤ ወጪ እንዳይሆን የሚገልጥ ትእዛዝ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ መዝገብ ቤት ሹም ለሆኑት ለወ/ት ዓለምፀሐይ ጌታቸው የላኩትን ደብዳቤ ከዚህ በታች አቅርበናል፡፡

 

01

የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በደማቅ መርሐ ግብር መከበር ይጀምራል፡፡

ሚያዚያ 20/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ዓለም አቀፋዊ ማኅበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎት የጀመረበትን 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ማክበር ይጀምራል፡፡

የማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ አክሊሉ ለገሠ እንደገለጹት ማኅበሩ 20ኛ ዓመት  የበዓል ዝግጅቱን ሚያዝያ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚያከብር ሲሆን በዓሉንም በሁሉም ማእከላትና ወረዳ ማእከላት በልዩ ልዩ መርሐ ግብራት ይካሄዳል፡፡

 

በዓሉን የተመለከተ ዘጋቢ ፊልም እና ትራክት የመጽሔተ ተልዕኮ ልዩ እትም መጽሔት መዘጋጅቱን የገለጹት ሓላፊው በዓሉ በአንድ ቀን የሚጠናቀቅ ሳይሆን በቀጣይ ተከታታይ መንፈሳዊ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን “ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት በጋራ እንሥራ” በሚል መሪ ቃል በሚያከበረው በዓል ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮች ማኅበራትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚገኙ መሆኑን ታውቋል፡፡

Gedamate 3

የጎንደር ደብረ ኀይል ወደብረ ጥበባት በዓታ ለማርያም የአቋቋም ምስክር ትምህርት ቤት ግንባታ ውል ተፈረመ፡፡

ሚያዝያ 18/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

Gedamate 3ማኅበረ ቅዱሳን በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት የሚገኘውን የደብረ ኀይል ወደብረ ጥበባት በዓታ ለማርያም የአቋቋም ምስክር ትምህርት ቤትን በ4.6 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ሚያዚያ 12 ቀን 2004 ዓ.ም. የግንባታ ውል ስምምነት ከአስማማው አያሌው ሕንጻ ሥራ ተቋራጭ ጋር ተፈራረመ፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪነት የሚከናወነው ይኸው ፕሮጀክት ማኅበረ ቅዱሳንን በመወከል የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኀ/ማርያምና የሕንፃ ሥራ ተቋራጩ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስማማው አያሌው አማካይነት የፊርማ መርሐ ግብሩ ተፈጽሟል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጽ/ቤት በተከናወነው የፊርማ መርሐ ግብር ላይ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኀ/ማርያም ባደረጉት ንግግር ‹‹ 4.6 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ፕሮጀክት ቀርጾ የአቋቋም ምስክር ትምህርት ቤት ለመገንባት ከዚህ በፊት አድርገነው አናውቅም፡፡ ይህ ትልቅ እድገት ነው፡፡ ምእመናንም ማኅበረ ቅዱሳንን ማመን የቻሉበት ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥቶ ማኅበረ ቅዱሳን ይሥራው ለማለት መቻል ሙሉ ለሙሉ በማኅበሩ ላይ እምነት እንዳሳደሩ ነው የሚያሳየው፡፡ እኛም በታማኝነት ትኩረት ሰጥተን እንድንሠራ የሚያደርገን ነው፡፡ ጨረታውን ከብዙዎቹ የሕንጻ ሥራ ተቋራጮች ጋር ተወዳድሮ ያሸነፈው ድርጅት በማኅበሩ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገና አብሮ የኖረ ነው፡፡ ሥራውንም በጥራትና ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ በማጠናቀቅ ያስረክባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን በኩልም ሥራውን ለማፋጠን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጣለሁ›› በማለት ገልጸዋል፡፡

 

የሕንፃ ሥራ ተቋራጩ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስማማው አያሌው ድርጅታቸውን በመወከል እንደተናገሩት ጨረታውን ስጋበዝ አሸንፋለሁ ብዬ አላሰብኩም፡፡ የገንዘቡ መጠን ከፍ ሲል ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳን ጓዳውን ስለማውቀው ከየት አምጥቶ ነው ብዬ ስጋት ነበረኝ፡፡ ለዚህ ደረጃ በመብቃቱ ተደስቻለሁ፡፡ ጨረታውን ለማሸነፍ ካለኝ ጉጉት የተነሣ ማግኘት ከነበረብኝ ትርፍ 7 ፐርሰንት ቀንሼ ነው የተወዳደርኩት፡፡ ለማኅበረ ቅዱሳን ገንዘብ ከመስጠት ገንዘብ መውሰድ መጀመር የጥሩ እድገት ምልክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱን ሰርቶ ለማስረከብ ከሚጠበቀው ጊዜ በፊት እንዲሁም ከሚጠበቀው ጥራት በላይ እንደባለቤት ሰርቼ አስረክባለሁ ብለዋል፡፡

 

ሕንፃ ተቋራጩ በ1998 ዓ.ም. እንደተቋቋመና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታዎችን፣ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ግንባታዎችን፣ ጤና ጣቢያዎችንና በአሁኑ ወቅት የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክትን በ6 ሚሊዮን ብር ውል በመገንባትና በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ፕሮጀክቱን አስመልክቶ እንደገለጹት የአቋቋምGedamate 2 ምስክር ትምህርት ቤቱ ባለሁለት ፎቅ ሕንፃ ሲሆን በምስክር ትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ተማሪ ድጋፍና ወርሃዊ ቀለብ እንዲያገኝ ማድረግ የማኅበራዊ ልማት ዋና ክፍሉ ዓላማ ነው፡፡ በተጨማሪም የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና፣ የስብከተ ወንጌል፣ የሐይማኖት ትምህርትና የሥራ ፈጠራ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ የተማሪዎቹ ማደሪያ ቤት የምግብ ማብሰያ ቤት፣ መጸዳጃ ቤትና የገላ መታጠቢያ እንዲሁም ጉባኤ ቤት የሚኖረው ሲሆን ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪውን 3.5 ሚሊዮን ብር የሸፈኑት በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ 3 የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆችና በጎ አድራጊዎች ሲሆኑ ፤ በአሁኑ ወቅት 1.7 ሚሊዮን ብር ለማኅበራዊ ልማት ክፍል ገቢ አድርገዋል፡፡ ቀሪውን ደግሞ ወደፊት የሚሸፍኑት ይሆናል፡፡ ተጨማሪውን ወጪ ለመሸፈን ዋና ክፍሉ የራሱን እቅድ በመቀየስ በጎ አድራጊ ምእመናንን  በማስተባበርና እንዲሳተፉ በማድረግ በጋራ ለመሥራት ነው የምናስበው ብለዋል፡፡

 

የምስክር ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ከ70 እስከ 80 ተማሪዎችን ብቻ የሚያስተናግድ ሲሆን፣  የአቋቋም ምስክር ት/ቤቱ ሲጠናቀቅ እስከ 170 ተማሪዎችን መቀበል የሚችል ነው፡፡  ተማሪዎቹ በከፍተኛ ሁኔታ የማደሪያ ቤት ችግር ስለሚያጋጥማቸው በሁለት ዓመት መጨረስ የሚገባቸው ወረፋ በመጠበቅ አራት ዓመታት ይፈጅባቸዋል፡፡ የጎጆ ወረፋ በመጠበቅ ረጅም ጊዜ ይቃጠላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ዓላማ ያደረገው ይህንን ችግር መቅረፍ ነው፡፡ ይህ ግንባታ ዛሬ ላሉት ተማሪዎች ብቻ ትኩረት ያደረገ ሳይሆን ወደፊት ማማር ለሚፈለጉ ሁሉ ደረጃውን የጠበቀ ጉባኤ ቤቶችን መገንባት ነው በማለት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

 

የማኅበሩ መሐንዲስ የሆኑት ኢንጂነር ያሬድ ደመቀ ፕሮጀክቱን በሚመለከት እንደገለጹት የአቋቋም ምስክር ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎቹ አገልግሎት የሚሰጡ ቁሳቁሶችን የሚያሟላ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በየማደሪያ ክፍሎቹ ጠረጴዛና ወንበሮች ፤ ልብስ ማስቀመጫ ቁም ሳጥኖችና አልጋን ያካትታል፡፡ ግንባታው 1 ዓመት ከ6 ወራት እንደሚፈጅ፣ ከሕንፃ ተቋራጩ ጋር ከፊርማው በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ የሳይት ርክክብ እንደሚካሄድና በ14 ቀናት ውስጥ ደግሞ ግንባታውን እንደሚጀምር በውሉ ላይ መካተቱን ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

 

በፊርማ መርሐ ግብሩ ላይ ከተገኙ ወንድሞችና እኅቶች በተሰጡ አስተያየቶችም ዛሬ በማኅበረ ቅዱሳን ታሪክ ታላቅ ነገር የታየበት ነው ብለዋል፡፡ ከ12 ዓመት በፊት ይህ ክፍል ሙያ አገልግሎትና ተራድኦ ክፍል እያለ ለገዳማት ጧፍ በመላክ ነው የጀመረው፡፡ ዛሬ ታላላቅ ቅዱሳት ቦታዎች ላይ በሚሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ወጥቶ ሥራዎችን እንድንሠራ እግዚአብሔር ስለፈቀደልን ወደ ኋላ መመለስ አንችልም፡፡ ወደፊት ከዚህ በላይ የሆኑ ፕሮጀክቶች ይጠብቁናልና ሁላችንም በእግዚአብሔር ፈቃድ ታጥቀን መነሣትና መተባበር ይገባናል፡፡  ገጽታችን ገዘፍ እያለ ሲመጣ ጠላት ይደነግጣል፡፡ ክፉ ለሚያስቡልን ደግ እንዲያስቡ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡ በጎ ተጽእኖ መፍጠር ያስችላል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

ይህ ፕሮጀክት 2ኛው ዙር የአብነት ት/ቤቶች በተለይም የምስክር ት/ቤቶችን ትኩረት ያደረገ መርሐ ግብር ሲሆን በመጀመሪያው ዙር የቅድስት ቤተልሔም የመጻሕፍትና የጉባኤ ቤት ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ይታወሳል፡፡

begana

ማእከሉ የበገና ደርዳሪዎችን አስመረቀ

ማእከሉ የበገና ደርዳሪዎችን አስመረቀ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር የአቡነ ጎርጎርዮስ የአብነትና የዜማ መሣሪያዎች ትምህርትና ሥልጠና ማእከል ለስድስት ወራት በበገና ድርደራ ያሰለጠናቸውን ከ175 በላይ የሚሆኑ የበገና ደርዳሪዎች መጋቢት 29 ቀን 2004 ዓ.ም. በቤተ ክህነት አዳራሽ አስመረቀ፡፡
የትምህርት ማእከሉ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አብዮት እሸቱ ባደረጉት ንግግር ማእከሉ ሲቋቋም በ1996 ዓ.ም. በ12 ተማሪዎች ትምህርቱን እንደጀመረና በአሁኑ ወቅት በርካታ ተማሪዎችን አቅፎ እያስተማረ እንደሚገኝ፣ በአሳሳቢ ሁኔታ እየቀነሰ የመጣውን የበገና ደርዳሪዎች ቁጥር በመጨመር ረገድ የአባቶቻችንን አሻራ ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ ማእከሉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንና በቀጣይነትም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋት እቅድ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የበገና ድርደራ ሥልጠናውን ወስዶ በእለቱ ከተመረቁት ወጣቶት መካከል ወጣት ሔኖክ መንግሥቱ ለስድስት ወራት ትምህርቱን እንደተከታተለና “በመማሬ ብዙ ተጠቅሜያለሁ፤ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ መዝሙር እንዳውቅ አድርጎኛል፡፡ ከዚህም ባለፈ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምባቸው የዜማ መሣሪያዎች የትኞቹ እንደሆኑ፤ በግል ሕይወቴም ትሕትናንና ትእግስትን በመላበስ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖረኝ አድርጎኛል” በማለት ገልጿል፡፡
በዕለቱም ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የተመራቂ ቤተሰቦች ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶችና የቅዱስ ዳዊት የበገና ቤተሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡
ሚያዝያ 13 ቀን 2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ

 

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር የአቡነ ጎርጎርዮስ የአብነትና የዜማ መሣሪያዎች ትምህርትና ሥልጠና ማእከል ለስድስት ወራት በበገና ድርደራ ያሰለጠናቸውን ከ175 በላይ የሚሆኑ የበገና ደርዳሪዎች መጋቢት 29 ቀን 2004 ዓ.ም. በቤተ ክህነት አዳራሽ አስመረቀ፡፡
begana
የበገና ድርደራ ሥልጠናውን ወስዶ በእለቱ ከተመረቁት ወጣቶት መካከል ወጣት ሔኖክ መንግሥቱ ለስድስት ወራት ትምህርቱን እንደተከታተለና “በመማሬ ብዙ ተጠቅሜያለሁ፤ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ መዝሙር እንዳውቅ አድርጎኛል፡፡ ከዚህም ባለፈ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምባቸው የዜማ መሣሪያዎች የትኞቹ እንደሆኑ፤ በግል ሕይወቴም ትሕትናንና ትእግስትን በመላበስ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖረኝ አድርጎኛል” በማለት ገልጿል፡፡

 

የትምህርት ማእከሉ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አብዮት እሸቱ ባደረጉት ንግግር ማእከሉ ሲቋቋም በ1996 ዓ.ም. በ12 ተማሪዎች ትምህርቱን እንደጀመረና በአሁኑ ወቅት በርካታ ተማሪዎችን አቅፎ እያስተማረ እንደሚገኝ፣ በአሳሳቢ ሁኔታ እየቀነሰ የመጣውን የበገና ደርዳሪዎች ቁጥር በመጨመር ረገድ የአባቶቻችንን አሻራ ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ ማእከሉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንና በቀጣይነትም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋት እቅድ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

begena graduate

በዕለቱም ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የተመራቂ ቤተሰቦች ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶችና የቅዱስ ዳዊት የበገና ቤተሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡

 

የቅዱስ ያሬድ ድርሰት በሆነው ምዕራፍ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀረበ

ሚያዝያ 13 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

‹‹በቅዱስ ያሬድ የዜማ አስተምህሮ የምዕራፍ ሚናና አጠቃቀም›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀረበ፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ትምህርትና የመምህራን ሙያ ልማት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰርና የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር  በሆኑት ዶክተር ውቤ ካሣዬ አማካይነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ትልቁ አዳራሽ ቅዳሜ መጋቢት 29/2004 ዓ.ም. ቀርቧል፡፡ የጥናቱ አላማ ስለ ምዕራፍ ጠቀሜታና ክፍሎች መጠነኛ ትንታኔ መስጠት፤ ቅኝት ማድረግ፤ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልቶችን ታዳሚው ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግና ወደፊት ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ማቅረብ እንደሆነ ገልጸው፤ ነገር ግን ጥናቱ ብዙ የሚቀረው ነገር እንዳለው ጨምረው ተናግረዋል፡፡

 

ምዕራፍ የዘወትርና የጾም ተብሎ በሁለት እንደሚከፈል የገለጹት ዶክተር ውቤ ካሣዬ፤ የዘወትር የሚባለው አመቱን ሳይጠብቅ በየአመቱ ባሉት ሳምንታትና በዓላት በአገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን፤ የጾም ምዕራፍ ደግሞ በጾመ አርባና በአንዳድ የምህላ ቀናት እንደሚዜም፤ የሁለቱም መሠረታቸው የዳዊት መዝሙርና ድጓ ወይም ጾመ ድጓ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

 

በአገልግሎት ላይ ምዕራፍ ሦስት አካላት ማለትም መሪና ተመሪ እንዲሁም አንሺ ያስፈልጉታል፡፡በግራና በቀኝ በመከፋፈልና በመቀባበል ይቀርባል፡፡ ምዕራፍ በዋናነት የሚያካትታቸው ሰባት ክፍሎች አሉት፡፡ እነሱም ውዳሴ ማርያም፤ መስተጋብእ፤ አርባዕት፤ አርያም፤ ሠለስት፤ ክስተትና መወድስ በመባል ይታወቃሉ፡፡ የየራሳቸው ባህርያትና መጠን እንዳላቸውም በጥናቱ ላይ የቀረበ ሲሆን እያንዳንዱ ክፍል ከሰኞ እስከ እሁድ በመከፋፈል አቅርበውታል፡፡የድጓ መምህር በሆኑት በመምህር መንግሰቱ መላኩ/ የጥናቱ አቅራቢ የአብነት መምህር / አማካኝነት ከእያንዳንዱ ክፍል በዜማ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡

 

ምዕራፍ ማለት ማረፊያ ማለት ሲሆን በዜማ ቤት ሲሆን ደግሞ ከሰላም ለኪ ጀምሮ የጾም ምዕራፍ እስኪፈጸም ድረስ ያለው ትምህርት ሁሉ ምዕራፍ ይባላል፡፡ የሚጠናው በቃል ነው፡፡ በቃል ትምህርት ጊዜ የተለየ አቀማመጥ ሲኖረው በመጽሐፉ ደግሞ የተለየ ተራ እንዳለው በጥናታቸው አቅርበዋል፡፡

 

የቅዱስ ያሬድ ዜማ እጅግ የመጠቀና ሰማያዊ ምስጋና መሆኑን፤  እግዚአብሔርም ለቅዱስ ያሬድ የሰጠው የተለየ ሰማያዊ ምስጢር እንደሆነ፤  ቅዱስ ያሬድ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም አባቶች አስተዋጽኦ እንዳደረጉ፤ ከእነዚህም  መካከከል አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫና ሌሎችም እንደሚጠቀሱ  በጥናቱ ላይ ተብራርቷል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከሌላው አለም የዜማ አቀራረብ ጋር ሲነጻጸር ቀደምት የሚያደርገው ሲሆን የኖታ አጠቃቀምን በተመለከተ በአለም ላይ እየተሰራበት ካለው የሙዚቃ ኖታ ፍጹም የተለየ ያደርገዋል፡፡ የቅዱስ ያሬድን የኖታ አጠቃቀም አውሮፓውያን በራሳቸው የኖታ ሥርዓት ለመቀየር ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸው በጥናቱ ላይ ተገልጸል፡፡

 

የቅዱስ ያሬድን መንፈሳዊ ድርሰቶች እጅግ እንደሚመስጣቸውና ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት እንዳደረጋቸው የገለጹት ዶክተር ካሣዬ የቅድስት ቤተክርስቲያንን የአብነት ትምህርት ለመማር ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የቅዱስ ያሬድን ዜማ በመማር ላይ እንደሚገኙና አራት አመታትን እንዳስቆጠሩ፤ ለጥናቱም እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የውጭ ሃገር ጸሐፍት የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ሥራዎች ላይ ጥናቶች የተደረጉ ቢሆንም ስራዎቻቸው በአብዛኛው የተዛቡ አቀራረቦች እንዳሏቸውና ለአንዳንዶቹም ማስተካከያ እንዲያደርጉ ጭምር እንደጻፉላቸውና ይህ ጉዳይ እጅግ ያስጨንቃቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከውጭ ጸሐፍት በተጨማሪ በጣት የሚቆጠሩ የቤተክርስቲያን አባቶችና ምሁራን በቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ላይ ጥናቶችን ያደረጉ ሲሆን፤ በአንዳንድ አባቶች ጥናት መሠረት ያሬዳዊ ዜማ በአጠቃላይ እስከ አሥራ አራት ሺህ የሚደርሱ ዜማዎች እንዳሉት ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን በእለቱ በመድረክ ላይ ከተጋበዙት ሊቃውንት መካከል የድጓ ሊቅ የሆኑት ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመሥራት ላይ የሚገኙ ሲሆን ያሬዳዊ ዜማን አስመልክቶ ባጠኑት ጥናት መሰረት ዜማዎቹ እስከ ሃያ ሺህ እንደሚደርሱ መስክረዋል፡፡

 

በዶክተር ውቤ ካሣዬ ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል ተብለው ከቀረቡ ሃሳቦች መካከል፤ የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ሥራዎች ለአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት ቢደረግ፤ ትውልዱን በመንፈሳዊ እውቀት ለመቅረጽ እንዲቻል በየሰ/ት/ቤቶች ትምህርቱ ቢሰጥ፤ ጥናትና ምርምር መደረግ ስለሚገባው ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የእውቀት ክምችት ያላትና የበለጸገች ስለሆነች ይህንንም በጥናትና ምርምር በመደገፍ ማኅበረ ቅዱሳን አጠናክሮ እንዲገፋበት አሳስበዋል፡፡

 

እስከአሁንም በቤተ ክርስቲያናችን በቅዱስ ያሬድ ላይ ከጻፉ ሊቃውንት መካከል “የኢትዮጵያ ጥንታዊ ትምህርት” በሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ፣ “ያሬድና ዜማው” በሊቀ ካህናት/ርዕሰ ደብር ጥዑመ ልሳን ካሳ፣ “ጥንታዊ ሥርዐተ ማኅሌተ ዘአቡነ ያሬድ ሊቅ” በመሪጌታ ልሣነ ወርቅ ገ/ጊዮርጊስ ይጠቀሳሉ፡፡

 

መርሃ ግብሩን በመምራት ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትየጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች ት/ክፍል ረዳት ፕሮፌሰርና የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ሰብሳቢ የተሳተፉ ሲሆን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሰሙነ ሕማመትን አስመልክቶ ከቅዱስ ያሬድ ዝማሬዎች በመርሐ ግብሩ መጀመሪያና መዝጊያ ላይ አቅርበዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ መምህራን፤ ከተለያዩ ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች ጥሪ የተደረገላቸው ኃላፊዎችና ምዕመናን የተገኙ ሲሆን በቀረበው ጥናት ላይ  ከታዳሚዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች በጥናቱ አቅራቢ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

የትንሣኤ ሰላምታ

yetnsaeselamta2in1


ቀዳም ሥዑር

ሚያዝያ 6፣2004 ዓ.ም.

ቅዳሜ፡

ቀዳም ሥዑር ይባላል፡፡ በዚች ዕለች ከድሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች፡፡

የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾም ስዑር /የተሻረች/ ተብላለች በዓል መሻርን አይመለከትም በቀዳም ሥዑር  ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኀልየ ሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኀሌቱም እዝሉ እየተቃኘ እየተመጠነ፣ እየተዘመመ እየተመረገደ እየተጸፋ ያድራል፡፡ ጥዋት አቡን መዋሥዕት ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ በሚለው ሰላም ይጠናቀቃል፡፡በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

 

ለምለም ቅዳሜ፡- ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ በዚህ ተሰይሟል፡፡ ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡

በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለዓዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡  

የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በማየ አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡

ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ ታወጀ በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡

ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡፡ ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡

ምእመናን ሆይ፣ በአጠቃላይ ሥርዓተ ሕማሙን፤ ሰሙነ ሕማማት ብለው የተለየ ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ተግተው ያቆዩልንን ሥርዓተ መላእክት ልንጠብቀውም ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ የዕለታቱን ክብርና ስያሜ ከማወቅና ከመረዳት ጋር በዕለታቱ የታዘዙትን ሃየማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ የስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ሚያዝያ 2004፣ አዲስ አበባ፡፡

ejig yetekeberu_yealemloriet

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ አረፉ

ሚያዝያ 04፣ 2004ዓ.ም

እንዳል ደምስ

ejig yetekeberu_yealemlorietእጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ሚያዚያ 2/2004 ዓ.ም. ምሽት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ከአባታቸው ከአቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፈለቀች የማታወርቅ በጥቅምት ወር 1924 ዓ.ም. በአንኮበር ከተማ ተወልደዋል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርታቸውን በእንግሊዝ አገር በሚገኘው የሥነ ጥበብ አካዳሚ በሥነ ስዕል በቅርፃ ቅርጽና በሥነ ሕንፃ ዲዛይን ተከታትለዋል፡፡

በነበራቸው የሥነ ስዕል ዝንባሌ ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ ሲሆን በወጣትነት ዘመናቸው በ1957 ዓ.ም. ከክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ጋር በኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ እጅ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ተሸላሚ ለመሆን ችለዋል፡፡ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የአራት ዓለም አቀፍ አካዳሚዎች አባል ሲሆኑ በተሰማሩበት የሥነ ሥዕል ጥበብ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ታላላቅ ሰዎች የሚሰጠውን የዓለም ሎሬት የተሰኘውን ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ እስካሁን ድረስም ከዘጠና ሰባት በላይ የዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ከተለያዩ ተቋማት አግኝተዋል፡፡

ጊዜ የማይሽራቸው ታላላቅ የሥዕል ሥራዎች ለዓለም ያበረከቱ ሲሆን በስዕሎቻቸውም ሥርዓተ አምልኮን፣ ማኅበራዊ አኗኗር የማኅበረሰቡን ደስታና ሃዘንና ጀግንነቱን ሥልጣኔውና ሀገር ወዳድነትን የሚያንጸባርቁ ሥራዎችን አበርክተዋል፡፡ በተለይም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካላቸው ጥልቅ ፍቅርና እምነት በመነጨ ለተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም በስቱዲዮአቸውና በጸሎት ቤታቸው የሚገኙ መንፈሳዊ ስዕላትን አበርክተዋል፡፡ ከሠሯቸው መካከልም በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ በግድግዳ ላይ የተሠሩ መንፈሳዊ ስዕላትን በቀለም ቅብ፣ በባለቀለም ጠጠሮች፣ በክርክም መስታወቶችና በሞዛይክ ከታወቁትና ስመ ጥር ከሆኑት ሰዓሊ ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይ ጋር ሠርተዋል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሙዚየሞች ውስጥም ስዕሎታቸው በክብር ተቀምጠውላቸው በጎብኚዎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድም በስዕሎታቸውና በቅርፃቅርጾቻቸው አማካይነት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሲሆን “ቪላ አልፋ” የተሰኘው ባለ 22 ክፍሎች መኖሪያ ቤታቸውና የግል ስቱዲዮአቸው ውስጥ ይህንኑ ለማንጸባረቅ ጥረት አድርገዋል፡፡

በቪላ አልፋ ስቱዲዮ ውስጥ የአክሱም ሐውልት፣ የጎንደር ፋሲለደስ፣ የሐረር ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ቅዱሳት ስዕላት፣ የተወለዱበት አንኮበር የሚገኘው ቤተ መንግሥት የሚያስደንቁ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ እሴቶችን አካቶ የያዘ ነው፡፡

በንግግራቸው ስመ እግዚአብሔርን መጥራት የሚያዘወትሩት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በዋናው መግቢያ በራቸው ላይ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚል ጥቅስ በትልቁ ጽፈዋል፡፡ “እንደማንኛውም ዓይነት የጥበብ ሥራ በሠራሁ ጊዜ እኔ በጥበቤ ታላቅ ነኝ የሚል ትምክህት እንዳይቀርበኝ ዘወትር እንዳነበው ነው የጻፍሁት” በማለት ከዚህ በፊት በማኅበረ ቅዱሳን ለሚታተመው ሐመር መጽሔት ጋዜጠኞች መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በዓለማችን ላይ ከሚገኙ ስመጥርና ታላላቅ ከተሰኙ 200 ሰዎች ጋር የሕይወት ታሪካቸውንና የኢትዮጵያ ባንዲራ በጨረቃ ላይ እንዲያርፍ የተደረገ ሲሆን በደረሰባቸው የጨጓራ አልሰር ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ማክሰኞ ምሽት ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸው ሚያዚያ 6/2004 ዓ.ም. ቅዳሜ በቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል፡፡

ዝግጅት ክፍላችን ለመላው ቤተሰቦቻቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡

ከጲላጦስ አደባባይ እስከ ሊቶስጥራ

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}Sekelete2{/gallery}

ማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አመራር ጠቅላላ ስብሰባውን አካሔደ፡፡

02/08/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የ2004 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ጉባኤ መጋቢት 22 እና 23 ቀን 2004 ዓ.ም. አካሒዷል፡፡sera amerare meeting 2004

ጉባኤው የሥራ አመራሩ ባለፉት 6 ወራት ያከናወናቸውን የስብሰባና የውሳኔ ቃለ ጉባኤ ማጽደቅ፣ የሥራ አስፈጻሚ 6 ወር ክንውን ሪፖርት፤ በሀገር ውስጥ 42 እና ከሀገር ውጪ የሚገኙ 3 ማእከላትና 4 ግንኙነት ጣቢያዎች፣ የቅዱሳን መካናትና ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ቦርድ፣ የልማት ተቋማት አስተዳደር ቦርድ የ6 ወር ክንውን ሪፖርት ገምግሞአል፡፡

ጉባኤው አክሎም የሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት ያከናወናቸው ተግባራት፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ ሪፖርት ያደመጠ ሲሆን የማኅበሩ ኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት አጠቃላይ የማኅበሩን አገልግሎት የተመለከተም የኦዲትና የኢንስፔክሽን ሪፖርት አቅርቧል፤ በቀረበው ሪፖርት ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

የ2004 ዓ.ም. የመጀመሪያው የ6 ወር ጉባኤ ላይ በአጀንዳነት በቀረቡት የኤዲቶሪያል ቦርድ ፖሊሲ፣ የጽ/ቤት ግንባታ ሒደት፣ የሒሳብና ገቢ አሰባሳቢ፣ የቀጣይ 4 ዓመት ስልታዊ እቅድ መነሻና የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም እና የማኅበሩ 20ኛ ዓመት የበዓል አከባበር በተመለከተ ውይይት አድርጓል፡፡
በሁለተኛው ቀን ጉባኤ ላይ ለተወሰነ ሰዓት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል፡፡ ሓላፊው ቆሞስቆሞስ መላከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው መላከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድ ይፍራው በቀረቡት ሪፖርቶችና አጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ማኅበሩ እያደረገ ያለውን አገልግሎት የቤተ ክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት የማኅበሩም ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መሥራትና አጠናክሮ እንዲቀጥል አባታዊ ምክር አስተላልፈዋል፡፡ በተጨማሪም “ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያውን ችግር እንደችግር አያነጋግርም፡፡ መፍትሔው ሕጉን በመጠበቅ በመምሪያው እየተሰጠ ነው የሚሔደው፡፡ ሌላው ጥቃቅን የቤተ ክርስቲያን ችግር ቢፈጠር እንኳን በውይይት ይፈታል በወረቀት የሚፈታ አይደለም ይህንን እኔ አምናለሁ…”
ለሁለት ቀናት በታየው በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ከሀገር ውስጥ የ39 ማእከላት ተወካዮችና ከሀገር ውጪ የካናዳ ማእከል እና የማኅበሩ ሥራ አመራርና ሥራ አስፈጻሚን ጨምሮ የኦዲትና ኢንስፔክሽንና የኤዲቶሪያል ቦርድ ሓላፊዎች ተገኝተዋል፡፡