የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ 31ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጧት 3 ሰዓት ላይ በተካሄደው ጸሎት ተከፈተ፡፡

ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


ጉባኤው ከዛሬ ጥቅምት 6 ቀን ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ጥቅምት 11 ቀን ድረስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አማካኝነት አምስት አባላት ያሉበት አርቃቂ ኮሚቴ የተሰየመ ሲሆን፤ ይህንኑ ተከትሎ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቢ መንበረ ፓትርያርክ የጉባኤው መክፈቻ ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በዚሁ ቃለ ቡራኬያቸው “በዚህ ጉባኤ የታደማችሁ አባቶቼ ወንድሞቼ እንኳን ለዚህ ቀን አደረሳችሁ፡፡” ካሉ በኋላ  “ሐዋርያዊት የሆነች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በቀኖናዋ ቅዱሳን ያሰኘቻቸው ልጆቿ አያሌ ናቸው፡፡ ቅድስናናን የሚያሰጠው የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ጠብቀን በቤተ ክርስቲያናችን ሊሠራ የሚገባውን ወስነን እንሠራለን” ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በ2005 ዓ.ም. ለመፈጸም ያሰበቻቸውን የዕቅድ ሪፓርት በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊሊጶስ የቀረበ ሲሆን ብፁዕነታቸው “በልዑል እግዚአብሔር አባታዊ ፈቃድ ከሐምሌ ወር 2003 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ወጥተን ወርደን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እድገትና ልማት፣ በሕዝባችን ሰላምና አንድነት፣ ሠርተን የሥራችንን የሥራ ክንውኖችና ውጤቶች እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነን ለመገምገም ያበቃንንና የሰበሰበንን አምላክ ደግመን ደጋግመን እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡ በብፁዕ ሥራ አስኪያጅ ጋባዥነትም በአቶ ተስፋዬ ውብሸት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የ2004 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ ክንውን አጠቃላይ ሪፓርት ቀርቧል፡፡ ምክትል ሥራ አስኪያጁ በሪፓርታቸው፡- “ቅርሶችን በዓለም ዐቀፍ ምዝገባ ሰነድ ለማስያዝና የደመራ መስቀል በዓላችንን በዮኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ እንዲሁም የቅዱስ ያሬድ ዜማንና ሥርዐቱን ፊደላትና አኀዞችን የጥምቀት በዓልንም በቀጣይ ለማስመዝገብ ጥናቱ ተፈጽሟል” ብለዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አማካኝነት በ2004 ዓ.ም. የተሠራውን አስመልክቶ ሲናገሩ “በተቀናጀ የገጠር ልማት 26,864,687.00/ በመመደብ 923,254 ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዐሥር ፕሮጀክቶችን በተለያዩ ክልሎች ዘርግቶ ሠርቷል፡፡ ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ፣ በተቀናጀ የገጠር ልማት፣ በውኃ አቅርቦትና ንጽሕና አጠባበቅ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከል፣ በገዳማት ልማት፣ በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ክብካቤና ድጋፍ 26 ፕሮጀክቶን ዘርግቶ በ120,955,270.00 ብር በጀት ተግባራዊ አድርጓል” ብለዋል፡፡ ከሻይ እረፍት መልስ “ግጭት፣ የግጭት መንስኤና አፈታት” በሚል ርዕስ በልማት ኮሚሽን የስደተኞች ጉዳይ ሓላፊ አቶ ይልቃል ሽፈራው አማካኝነት ቀርቦ በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አማካኝነት ጉባኤው ተወያይቷል፡፡

 

ከምሳ ሰዓት በፊት የነበረው መርሐ ግብርም 6 ሰዓት ከሃያ ላይ በጸሎት ተዘግቷል፡፡