የማኅበሩ 20ኛ አመት ምሥረታ ተከበረ
ግንቦት 28 ቀን 2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ አመት የምሥረታ በኣል በጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም. ተከበረ፡፡ ከረፋዱ 4፡ 00 ስኣት ጀምሮ የተካሔደው መርሐ ግብር በብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ ፤ የኢሉባቦርና ጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ መሪነት ጸሎተ ወንጌል በማድረስ ተከፍቷል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የምዕራብ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ምእዳን ‹‹ ክርስቶስ ወደዚህ አለም ሳይመጣ ፤ወንጌል ከመሰበኩ በፊት እግዚአብሔርን አምነን የተገኘን እትዮጵያውያን ነን፡፡ እግዚአብሔር ምስጢሩን ፤ጥበቡን የገለጠውና ያረጋገጠው ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንና ለኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ነው፡፡ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የሚስተካከልና የሚተካ አንድም የለም፡፡ ቤተክርስቲያን ራሷን ከቻለችበት ጊዜ አንስቶ በሊቃውንት ፤ በመምህራን ተጠብቃ አስተምህሮውንም አመስጥራ ፤ተርጉማ የተገኘች ናት በማለት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ብፁዕነታቸው ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ‹‹ ማኅበሩ ቤተክርስቲያንን በጥሩ ሁኔታ እያገለገለ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ ምእመናን ከዓላማውና ከእንቅስቃሴው ጎን ናቸው” ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡብ ትግራይ ማይጨው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው ‹‹ ወቅቱ የቤተ ክርስቲያን የፈተና ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን ማኅበሩ በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን እንዳትወድቅ ፤ፈታኝ እንዳይጥላት እግዚአብሔር ያቋቋመው ማኅበር ነው፡፡ አባቶች ያላዩትን ወጣቶች ሲሰሩት በጣም ያስደስታል፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በገዳማት ፤አድባራትና አብነት ት/ቤቶች ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ይህ ማህበር የአባቶችን አደራ እየተወጣ እንደሆነ እገነዘባለሁ፤ አምናለሁም በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ በሰጡት ቃለ ምእዳንና ቡራኬ ‹‹ ነፋስ ይነፍሳል፤ ወደ ወደደው ይነጉዳል ፤ድምጹን ትሰማላችሁ፡፡ ብዙ ወጀብ ፤ብዙ ንፋስ አለ በዘመናችን፡፡ ወጣቶችን የሚያምታታ፤ እምነት የሚያሳጣ፡፡ ያ! ሁሉ ሳይበግራችሁ በዚህ ማኅበር አንድ ሆናችሁ እምነታችሁን ይዛችሁ፤ ለሌሎችም እየመሰከራችሁና እያስመሰከራችሁ ስለምትገኙ በራሴና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስም ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ›› ብለዋል፡፡
በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ሰላማ የምዕራብ ትግራይ አክሱም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከምባታ ሃዲያ፤ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኃላፊ ፤ብፁዕ አቡነ እንባቆም የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የተገኙ ሲሆን በተጨማሪም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፤ የሰ/ት/ቤቶች አባላትና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የሕይወት ታሪክ ፤ የማኅበሩ የ20 አመት ጉዞ ፤ ያሬዳዊ ዝማሬ፤ ግጥምና ሌሎች መንፈሳዊ መርሐ ግብሮች ቀርበዋል፡፡