የበኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የልማት ሥራ ተጎበኘ

ታኅሣሥ 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

 

eresha be 3በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማዕከል ሥራ አሥፈጻሚ አባላትን ያቀፈ የልዑካን ቡድን በበኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እየተከናወነ የሚገኘውን የልማት ሥራ ለመመልከትና ከደብሩ አስተዳደር አካላት ጋር ለመወያየት ኅዳር 23 ቀን 2005 ዓ.ም. ጉብኝት አካሄደ፡፡

 

የአዲስ አበባ ማእከል ከበኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤ ጋር ባደረገው የውል ሥምምነትeresha be 2 መሠረት በባለሙያ አስጠንቶ ዘመናዊ የግብርና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብሮች ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተያዘው እቅድ መሠረት እሰካሁን ከተከናወኑት ውስጥ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኑ ይዞታ በሆነው 3 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራው የጤፍ እርሻ የሚገኝበትን መቃኘት የመጀመሪያው የጉብኝቱ አካል ነበር፡፡

 

የጤፉ እርሻ ለዓይን ይማርካል፡፡ ከ250 አስከ 300 ካሬ ሜትር የሚሆነው ከሌላው ማሳ ለየት ባለ ሁኔታ በቁመትም፤ ሆነ በያዘው የፍሬ መጠን ከፍተኛነት ይለያል፡፡ ለአጨዳ የደረሰ በሚመስል መልኩ ወደ ቢጫነት አዘንብሏል፡፡ ቀሪውም ባማረ ሁኔታ ጎልቶ ይታያል፡፡ ከፍተኛ ክትትል እንደተደረገበትም ያመለክታል፡፡

 

የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ገብረ አማኑኤል ቦታው ጠፍ የነበረና የከብቶች መዋያ ሆኖ መቆየቱንና ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ከማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማዕከል ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት በባለሙያ ተጠንቶና ታርሶ ፍሬ ለማየት እንደበቁ የገለጹ ሲሆን ወደፊትም ተደጋግፎ የተሻለ ሥራ ለመሥራት እንደተዘጋጁ በጉብኝቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

 

“በእርሻ ሥራው ላይ የደብሩ ካህናት የንስሐ ልጆቻቸውን በማስተባበር፤ ለዘር የሚሆን ጤፍ በማቅረብ፤ በጉልጓሎና ዘር በሚዘራበት ውቅት ቤተሰቦቻቸውን ጭምር በማሰማራት፤ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ በመማር ላይ የሚገኙ ከ200 በላይ የአብነት ተማሪዎች፤ የደብሩ አስተዳደር፤ ካህናትና ዲያቆናት ተሳትፈውበታል፡፡ ምርቱም በመማር ላይ ለሚገኙት የአብነት ተማሪዎች የምግብ ፍጆታነት ይውላል” በማለት የገለጹት ደግሞ የቀድሞው የቤተ ክርስቲያኗ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ከፍያለው አየለ ናቸው፡፡

 

eresha be“የግብርና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብሮችን ለመጠቀም ጥረት አድርገናል፡፡ ለማስተማር የፈለግነው የአካባቢው አርሶ አደሮችና ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን በጎ ተሞክሮዎችን እንዲወስዱ ለማድረግ ነው፡፡ በበሬ ብቻ ሳይሆን በትራክተር እንዲታረስም አድርገናል፡፡ ከ3 ሄክታር መሬቱ ላይ ከ250 እሰከ 300 ካሬ ሜትሩ ለሙከራ ምርጥ ዘር ተጠቅመናል፡፡ የትኛው የተሻለ እንደሆነ ለሁሉም ለማሳየት የቻልንበት ነው፡፡ ገና ሳይታጨድ ልዩነቱም ጎልቶ ይታያል፡፡ በሚቀጥለው አመትም ጤፍ በመሥመር መዝራትን ተግባራዊ የምናደርግበት ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡ ይህንን የምናደርገው ምእመናን የቤተ ክርስቲያናችንን ተሞክሮ ተመልክተው እነሱም እንዲጠቀሙበት ለማስተማር ነው፡፡” በማለት ወይዘሪት መቅደስ አለሙ በአዲስ አበባ ማእከል የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍል ሰብሳቢ በጉብኝቱ ላይ ገልጸዋል፡፡

 

በቀጣይነት የተካሄደው አብነት ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት ሁኔታ ለመቃኘት የተደረገ ጉብኝት ነው፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቱ በ3 መምህራን ከ200 በላይ ተማሪዎችን በማቀፍ የአቋቋም፤ የቅኔ፤ እንዲሁም የቅዳሴ ትምህርቶች የሚሰጥበት ተቋም ነው፡፡

 

በሁለት አዳራሾች ውስጥ መኝታቸውን ያደረጉት የአብነት ተማሪዎቹ የመኝታቸው ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው፤ አልጋቸው በርብራብ እንጨትeresha be 4 የተዘጋጁ ናቸው፤ የሳር ፍራሽና ካርቱን አንጥፈውበታል፡፡ አንዱን ከአንዱ ለመለየት በማዳበሪያ ተከፋፍሏል፤ በአንዱ አዳራሽ ውስጥ አዳራቸውን የሚያደርጉት ተማሪዎች ብዛት ከአንድ መቶ ይበልጣል፡፡ አዳራሹ ውስጥ እሳት ቢነሣ ወይም በሽታ ቢገባ የሚተርፍ ያለ አይመስልም፡፡ አንድ የማብሰያ ክፍል ሲኖር ሁሉንም ማስተናገድ ስለማይችል የተወሰኑት ተማሪዎች ውጪ ሜዳው ላይ ምግባቸውን ለማብሰል ይገደዳሉ፡፡

 

የቤተ ክተርስቲያኑ አስተዳደር ጉባኤ ያለውን ችግር በመረዳት ለሰንዳፋ በኬ የማኅበረ ቅዱሳን ማእከል፤ በቅደም ተከተልም ለአዲስ አበባና ለዋናው ማእከል የችግሩ አሳሳቢነት በማሳወቅ ጥናት ተደርጓል፡፡ በጥናቱ መሠረት የአብነት ትምህርት ቤቱን ለማደራጀትና ለማጠናከር ፤ ተማሪዎቹም ተምረው የነገዎቹ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሆኑ ለማስልቻል ጥረት በመደረግ ላይ  ይገኛል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ከፍተኛ በጀት በመመደብ የአብነት ትምህርት ቤቱን ዘመናዊ ሕንፃ ለመገንባት ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ግንባታውንም በዚህ ዓመት ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ በጉብኝቱ ላይ ተገልጧል፡፡

 

በመጨረሻም በጋራ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሁሉም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አባ ገብረ አማኑኤል ጥሪያቸውን ያስተላለፉ ሲሆን በልማት ሥራው ላይ ለተሣተፉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የሰንዳፋ ወረዳ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች፤ የደብሩ አስተዳደር፤ ካህናትና ዲያቆናት፤ የደብሩ የሰበካ ጉባኤ አባላት፤ የማኅበረ ቅዱሳን የሰንዳፋ ማእከል ሓላፊዎችና አባላት፤ ጥሪ የተደረገላቸው የአጥቢያው ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

 

በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በ1860ዎቹ ውስጥ እንደ ተተከለ ይነገራል፡፡