mkmesfin1

የማዕረግ ተመራቂው የወርቅ ሜዳልያውን ለማኅበሩ አበረከተ

29/03/2005ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

ደብረ ዘይት በሚገኘው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንስሳት ህክምናና ግብርና ኮሌጅ በ2004 ዓ.ም. የተመረቀው ዶክተር መስፍን ማሞ በአጠቃላይ ውጤት (GPA) 3.98  እጅግ በጣም ከፍተኛ ማዕረግ በማምጣት ተመርቋል፡፡ ኮሌጁም ላስመዘገበው ውጤት Outstanding Student Of The Year 2012 College Of Veternary & Agriculture በማለት ኮሌጁ በበላይነት ላጠናቀቁ ተማሪዎች የሚሰጠውን የወርቅ ሜዳልያ ሽልማት አበርክቶለታል፡፡

mkmesfin1

ዶክተር መስፍን ማሞ ይህንን ሽልማት በመያዝ ወደ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል በመምጣት “በትምህርቴ ባስመዘገብኩት ውጤት ያገኘሁት ሽልማት ነው፡፡ ለኔ አይገባኝም፡፡” በማለት ለማኅበሩ እንደሚሰጥ አሳወቀ፡፡

 

በርክክቡ ላይ ከኮሌጁ የተሸለመውን  የወርቅ ሜዳልያ ለማኅበረ ቅዱሳን  ለምን መሥጠት እንደፈለገ ዶክተር መስፍን ማሞ ሲገልጽ “ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም ከፍተኛ አገልግሎት እያበረከተ ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በማስተዋወቅና ምዕመናንን በማስተማር እያበረከተ ላለው ጥረት ከፍተኛ አክብሮት አለኝ፡፡ በግቢ ጉባኤ አማካይነት በሥነ ምግባር የታነጸና የዓላማ ሠው እንድሆን ማኅበሩ ከፍተኛ እገዛ አድርጎልኛልና ያለኝን ታላቅ አክብሮት ለመግለጽ ስል ይህንን ከኮሌጁ የተሸለምኩትን የወርቅ ሜዳልያ ሰጥቻለሁ” ብሏል፡፡

mkmesfin2የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ዲያቆን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም የወርቅ ሜዳልያውን በተረከቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት  “የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በግቢ ጉባኤያት ቆይታቸው በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የተሸለሙትን ሜዳልያ ለማኅበሩ ሲያበረክቱ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡

 

ተማሪዎች የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከመደበኛው ትምህርታቸው ውጪ ጊዜያቸውን በፕሮግራምና  በአግባቡ መጠቀም ከቻሉ ለውጤት መብቃት እንደሚችሉ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው፡፡ ሽልማቱ ለማኅበራችን እንዲሁም ለቤተ ክርስቲናችን ታላቅ ኩራት ነው፡፡” በማለት የገለጹ ሲሆን ዶክተር መስፍን ማሞ ላደረጉት አርአያነት ያለው ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 

ከዚህ ቀደም ከጅማ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁት ዲያቆን ዶክተር እንግዳ አበበ የተሸለሙትን የወርቅ ሜዳልያ ለማኅበረ ቅዱሳን በሥጦታ እንዳበረከቱ ይታወቃል፡፡