በዳዊት አብርሃም
የካቲት ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ስለ በዓላት አሉታዊ አስተሳሰቦች
፩. በዓላት ድህነትን ያስፋፋሉ
በዓላት ድህነትን ያስፋፋሉ የሚሉ ወገኖች እንደ ምክንያት የሚያነሡት በበዓላት ሰዎች ከተግባረ ሥጋ ታቅበው ረፍት ስለሚያደርጉ የሥራ ሰዓት ይባክናል የሚል ነው፡፡ በተጨማሪም ለበዓላት የሚወጡ ወጪዎች ቍጠባ እንዳይኖር ያደርጋሉ በሚል መነሻ በዓላት ድህነትን ያባብሳሉ ብለው ይደመድማሉ፡፡ አስቀድመን እንደ ተመለከትነው በበዓላት ተግባረ ሥጋ ቢከለከልም መንፈሳዊ ሥራና በጎ አድራጎት አልተከለከለም፡፡ ተግባረ ሥጋም ቢኾን በዅሉም በዓላት በእኩል ደረጃ የተከለከለ አይደለም፡፡ መከልከሉም ደግሞ የሰው ልጅ ዕረፍት ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ የሰው ልጅ ክቡር ፍጡር እንደ መኾኑ ዅልጊዜ እንደማሽን ሊሠራ ይገባዋል ማለት ሰብአዊ ክብርን የሚያንኳስስ አቋም ነው፡፡
ሠራተኛ ዕረፍት ማድረጉ ለበለጠ ሥራ ያነሳሣዋል እንጂ አያሰንፈውም፡፡ ዕረፍት ካደረጉ በኋላ የሠሩት ሥራ ደግሞ የበለጠ ጥራት ይኖረዋል፡፡ ሰው ዅልጊዜ ያለ ዕረፍት ሊሠራ ይገባዋል የሚሉ ወገኖች ሰዎችን እንደ ሰው ከመቍጠርና ከማክበር ይልቅ እንደ ቍስ የሚቈጥሩና ርኅራኄ የሌላቸው ናቸው፡፡ ሥራዎች የሚሠሩት በሰዎች ብቻ ሳይኾን ለሰዎችም ተብለው መኾኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ከባሪያ ፍንገላ ዘመን ጀምሮ በዘመናችን እስከሚገኘው ጭፍን የሀብት ማጋበስ ዘመን ድረስ ሰው ለጥቂት ባለ ሀብቶች የማይጠግብ ምኞት ቁቍስ አምራችና ገንዘብ ፈጣሪ እንዲኾን የሚያስገድደው ዓለማዊው ሥርዓት የሰውን ክብር የሚያሳውቀውን የክርስትና እምነት መቃወሙ አይገርምም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሰው መሥራት እንዳለበት ታስተምራለች፤ በዚያውም መጠን ዕረፍት እንደሚያስፈልገው ታምናለች፡፡
፪. መንፈሳውያን በዓላት ‹‹ካርኒቫል›› ናቸው
መንፈሳውያን በዓላት የሥጋዊ ደስታ መፍጠሪያ መንገዶች እንዲኾኑና ዓለማዊነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲገባ የሚፈልጉ ወገኖች እንደ ጥምቀት ያሉ ክርስቲያንናዊ በዓላት በምዕራቡ ዓለም እንደሚታዩት ዓይነት በአብዛኛው ከባዕድ አምልኮ ጋር የተያያዘ የጀርባ ታሪክ እንዳላቸው በዓላት በስካርና ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ እንዲከበሩ ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የበዓላቱን መንፈሳዊነት አጥፍተው በዓላቱን ፍጹም ዓለማዊ በማድረግ በዓሉ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር ብቻ ሲመለከቱት ልብ ያላሉት ሌላ ነገር በዚህ መልኩ በዓላት መከበራቸው ሥርዓት አልባነትን እንደሚያነግሡና የሥነ ምግባር ውድቀት እንደሚፈጥሩ ነው፡፡ በዚህ መልክ የሚከበሩ በዓላት በምዕራቡ ዓለም ማኅበራዊ ቀውስን ሲፈጥሩ ይታያል፡፡ ከዅሉም በላይ ደግሞ በዓላቱ እውነተኛ ማንነታቸውን ካጡ የቱሪስት መስሕብ መኾናቸውም እንደሚቀር መታሰብ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ጥንታውያን በዓላት ‹‹ካርኒቫል›› ከኾኑማ አንድ ቱሪስት በዚያው በገዛ አገሩ እያለለት ለምን እኛ ዘንድ ይመጣል? ብሎ መጠየቅ ጉዳዩን በጥሞና ለማየት ይጠቅማል፡፡ (‹‹ካርኒቫል›› በዘፈን፣ በጭፈራ፣ ወዘተ በመሳሰሉ ዓለማዊ ባህሎች የሚከበር የአረማውያን በዓል ነው፡፡)
፫. በዓላት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘታቸው መንፈሳዊነታቸውን ይቀንሰዋል
ዛሬ ላይ ያለችው ዘመናዊቷ ዓለም በምዕራባውያን ተጽዕኖ ሥር ያለች በመኾኗ ሳቢያ ምዕራባውያኑ የጐሰቈለ የሥነ ምግባር አቋማቸውን በዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል እንዲሠራጭ ያደርጋሉ የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖች ልክ የመስቀል በዓል እንደ ኾነው ዅሉ በዓላቱ ዩኔስኮን በመሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና ማግኘታቸውን በበጎ አያዩትም፡፡ የእኛም ቤተ ክርስቲያን እንደ ሌሎች ቤተ እምነቶች ወደ ዓለማዊነት ትንሸራተታለች ብለው ይፈራሉ፡፡ በእርግጥ ለቤተ ክርስቲያን ማሰብና ዓለማዊ ዝንባሌዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ መጠንቀቅ ተገቢና አስፈላጊ ነገር ነው፡፡
ኾኖም ጠቃሚ ነገሮችን በይኾናል ስጋት ተሸብረን እንዳናስቀራቸው መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢ ክርስቲያናዊ ሐሳቦችን መያዛቸው፣ እነዚህን ሐሳቦች እንደ ሕግ መቀበላቸውና ሀገራት እነዚህን እኩይ ሐሳቦቻቸውን ተቀብለው እንዲሠሩባቸው ጫና መፍጠራቸው ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለ መንቀሳቀሷ የተፈጠረ ክፍተት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖዋን ለማሳረፍ ብትሠራ ዓለም እንደማያሸንፋት ጌታችን ቃል ገብቶላታል፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ በዓሎቻችን በዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና ማግኘታቸው በጎ እንጂ ክፉ አይደለም፡፡ ሥጋቶችን ወደ በጎ ዕድሎች የመቀየር አንዱ ዘዴ በመኾኑ ይህ ጥረት በሌሎች ዘርፎችም ሊቀጥል ይገባል፡፡
፬. በበዓላት የምእመናንን ሱታፌ የሚገድቡ አመለካከቶች
በቤተ ክርስቲያን ዅሉም አካላት ልዩ ልዩ ድርሻ አላቸው፡፡ ካህናቱና ሊቃውንቱ ብቻ አገልግለው ሌላው ምእመን ተመልካች አይኾንም፡፡ በበዓላትም ምእመናን በልዩ ልዩ መንገድ ያገለግላሉ፤ በዓሉን ያደምቃል፡፡ ለምሳሌ በበዓለ ጥምቀት ምእመናን ለየት ባሉ ግጥሞችና ዜማዎች እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ እንሰማለን፡፡ አንዳንድ ዘመን አመጣሽና ጥሩ ያልኾኑ ነገሮች በመጠኑ ቢታዩም በአብዛኛው የሕዝቡ ባህል ክርስቲያናዊ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ታዳጊ ወንዶችና ልጃገረዶች በቡሄና ዘመን መለወጫ በዓላት የሚያዜሙት ዜማ ጠፍቶባቸው፣ ግራ ተጋብተው የምናየው ባህሉ በወጉ ለትውልድ መተላለፍ ባለመቻሉ ነው፡፡ ቀስ በቀስም ‹‹ነይ ነይ እምዬ ማርያም›› የሚለው የእናቶች ዜማ እየተዘነጋ እንዳይመጣ ያሰጋል፡፡ ስለኾነም ከዓለማዊ ዘፈን እና ከባዕድ ባህል ነጻ የኾኑ የሕዝብ የምስጋና ወይም የአገልግሎት ተሳትፎዎች ሊበረታቱ እንጂ ሊነቀፉ አይገባም፡፡
፭. በዓላትን በዓለማዊነት ፈለግ የማክበር ዝንባሌ
መንፈሳውያን በዓላት ከቤተ ክርስቲያን ያገኘናቸው፣ ታላላቅ መንፈሳዊ ትርጕሞችን ያዘሉ፣ ሰማያዊ ምሥጢራትን የያዙ፣ እኛን ከመለኮታዊ መገለጥ ጋር ድልድልይ ኾነው የሚያገናኙን ዕለታት ናቸው፡፡ እነዚህን በዓላት ከዓለም እንደ ተገኙ ዅሉ በዓለማዊ መርሐ ግብሮች ማክበር ከክርስቲያኖች አይጠበቅም፡፡ ከዚያም አልፎ አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት፣ በመስከር ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ ማሳለፍ የበዓሉን ትርጕም ማዛባት ነው፡፡ በዓላት በሥርዓተ አምልኮ፣ በማኅሌት በቅዳሴ፣ በዝማሬ፣ በቃለ እግዚአብሔር፣ በክርስቲያናዊ ፍቅርና አንድነት፣ አብሮ በመብላት፣ ችግረኞችን በማስታወስ ሊከበሩ እንደሚገባው የቤተ ክርስቲያን የዘወትር ትምህርቷና ትእዛዟ ነው፡፡
፮. ክርስቲያናዊ በዓላትን ከባዕድ አምልኮ ጋር ማሻረክ
ክርስትና ጣዖትን ያጠፋ ሃይማኖት ነው፡፡ በጥንት ጊዜ በምዕራቡ ዓለም የጌታ ልደት በሚከበርበት ሰሞን ‹‹የፀሐይ ልደት›› እየተባለ የሚታሰብ የጦኦት አምልኮ ነበር፡፡ ሊቃውንቱ አማናዊው ፀሐይ ክርስቶስ ነውና በዚህ ዕለት የጌታችን ልደት እንዲከበር በማድረግ የሕዝቡን ልብ ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮ እግዚአብሔር መልሰውታል፡፡ በአገራችንም የመስቀል በዓል በሚከበርበት ሰሞን በደቡብ አካባቢ ይታሰብ የነበረውን ጣዖት አምልኮ ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ካስወገዱ በኋላ በምትኩ የጌታችን መስቀል መገኘት መከበር መጀመሩ የሕዝቡን ልብ ከጣዖት አምልኮ እንዲርቅ አድርጎታል፡፡ የሰው መንፈስ ሲዝል ግን የጠፋው ባዕድ አምልኮ ያንሰራራል፡፡ ሰይጣንም ይህን ለማድረግ አይተኛም፡፡ የተሻሩ ጣዖታት አንዳንድ ጊዜ መንፈሳዊ በዓላት ላይ ጥላቸውን ያጠላሉ፡፡ በእመቤታችን ልደት ባዕድ አምልኮን የሚደብሉ፣ በሊቃነ መላእክት በዓላት ላይ በጠንቋይ ታዘው ዝክር የሚዘክሩ ሰዎች አሉ፡፡ እንደዚሁም በመስቀልና በጥምቀት በዓላት ላይ ለሰይጣን የሚሰዉ ዅሉ ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን ክርስቲያናዊ በዓላት አርክሰዋልና በንስሐ ሊመለሱ፤ ለወደፊቱም ሊጠበቁ ይገባል፡፡
፯. የባዕድ በዓላትን ሳይመረምሩ መቀበል
በየጊዜው ከውጪ ሀገራት በተለይም ከምዕራባዊው ዓለም የሚገቡ በዓላት በዘመናችን ቍጥራቸው እየበዛ ነው፡፡ የእነዚህ ምዕራባዊ ባህሎች ተጽዕኖ ወደ ኢትዮጵያም በመዝለቅ ላይ ነው፡፡ ለአብነትም ‹‹ሀሎዊን›› በመባል የሚያታወቅ ከባዕድ አምልኮ ጋር የተቆራኘ፣ ክርስቲያኖች ሊያከብሩት የማይገባ የአሕዛብ በዓል በውጪ አገር በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ከመከበር አልፎ በአገራችንም በአንዳንድ ቦታዎች መከበር መጀመሩ አሳሳቢ ነው፡፡ እንደዚሁም የጌታችንን ልደት በአገራችን የቀን አቈጣጠር ማክበር በቂ ኾኖ ሳለ ‹‹የፈረንጆች ገና›› እያሉ ማክበር ትክክል አይደለም፡፡
፰. የበዓል አከባበርን በባዕዳን ተጽዕኖ መቀየጥ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዓላት በዋዜማ ይጀምራሉ፡፡ ማኅሌት ተቁሞ ስብሐተ እግዚአብሔር ይደርሳል፡፡ ካህናትና ምእመናን በሥርዓት ለብሰው በቤተ መቅደሱ በመገኘት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ያድራሉ፡፡ በበዓሉ ቀንም በየቤታቸው እየተገባበዙ ደስ ብሏቸው ይውላሉ፡፡ አሁን አሁን ግን የበዓሉን ዋዜማ በመሸታ ቤት፣ በዳንኪራና በስካር ማክበር እየተለመደ ስለመጣ ዋዜማን እኛጋ አክብሩ የሚሉ ጥሪዎች ከተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች ይጎርፋሉ፡፡ ከዚህም ውጪ ‹‹የገና ዛፍ›› እንደሚባለው ያለ በእኛ ባህል ትርጕምም፣ ጥቅምም የሌለው እንዲያውም ባዕድ ከመኾኑም በላይ የተፈጥሮ ሀብትን የሚያወድምና አካባቢን የሚያራቁት ተግባር በመፈጸም ፈርጀ ብዙ ቀውስ ማድረሳችንን ማቆም አልቻልንም፡፡
፱. በዓላትን የሚያጥላሉ የመናፍቃን አስተሳሰቦች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት ማጥላላትና ማጠልሸት እንደ ዋና ሥራና ግብ አድርገው የሚሠሩ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያን አጽዋማት ላይ ተቃውሞ እንደሚያነሡት ዅሉ በበዓላቶቿም ላይ የመረረ ተቃውሞን ይሰነዝራሉ፡፡ የመናፍቃኑ ተቃውሞ መጽሐፍ ቅዱስን በጭንብልነት የተጠቀመ ቢመስልም ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃና መነሻ የሌለው ከመኾኑም በላይ እንዲያውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጣረስና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የምናውቀውን የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት ያፋለሰ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በመናፍቃኑ ሐሳብ እንዳይወሰዱ ወደ ቤተክርስቲያን ቀርበው ሊማሩ፤ ጥያቄዎችን ለመምህራን አቅርበው መልስ ሊያገኙ፤ ስለ በዓላት የተጻፉ መጻሕፍትንም ሊያነቡ ይገባል፡፡ ያ ካልኾነ ግን በዕውቀት ማጣት ምክንያት በመናፍቃን ወጥመድ መያዝና መሳት ይመጣል፡፡
፲. በዓላትን ለወቅታዊ ኹኔታዎች ማስገዛት
አንዳንድ ጊዜ በዓላት በሌሎች ውጫዊ አጀንዳዎች ሲጠመዱ ይታያል፡፡ ለወቅታዊ የአረማውያን ጥቃት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ጽሑፎች የለጠፉ ልብሶችን (ቲ ሸርቶችን) በመልበስ፣ የዛቻና የማስፈራሪያ ይዘት ያላቸው ‹‹የካሴት›› መዝሙሮችን በማሰማት በዓላትን ማክበር አንዱ ችግር ነው፡፡ ሌላው ችግር መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት፣ የፖለቲካ ቡድኖች፣ ወዘተ. የሚፈጥሩትን አጀንዳ ተሸክሞ በማሰብም ይኹን ባለማሰብ በመንፈሳዊ በዓላት ላይ ማቀንቀን፣ ‹‹ለመቻቻል›› እየተባለ ክርስቲያናዊ ያልኾኑ በዓላትን ማክበር ብዙ ጠንቅ አለው፡፡ ከኹሉም በላይ ደግሞ ሸቀጣቸው እንዲነሣላቸው የሚፈልጉ ነጋዴዎች የሚፈጥሯቸው በዓላትና የበዓላት አከባበሮች ክርስቲያኖችን የሸቀጥ ሰለባ እንዳያደርገን መጠንቀቅ አለብን፡፡ በአጠቃላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዓላትን ስታከብር ሕግን ጠብቃና ሥርዓትን ሠርታ ስለኾነ ምእመናን በዓላትን በምናከብርበት ጊዜ ከኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ እንዳንወጣና ሥርዓቱንም እንዳናፋልስ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች!
ይህ ጽሑፍ በጥር ወር ፳፻፱ ዓ.ም በወጣው ፳፬ኛ ዓመት ቍጥር ፱ የሐመር መጽሔት ዕትም፣ ገጽ ፲፬ – ፲፯፤ ‹‹ቤተ ክርስቲያን የሰጠችንን በዓላት እንዴት እናክብራቸው?›› በሚል ርእስ ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡