የትንሣኤ የማሕሌት ምንባብ 1 (ማቴ.28፥1-ፍጻሜ )

በሰንበትም ማታ ለእሑድ አጥቢያ ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ፡፡ እነሆ፥ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶአልና፤ ቀርቦም በመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋይዋን አንከባሎ በላይዋ ተቀመጠ፡፡ መልአኩም እንደ መብረቅ፥ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፡፡ እርሱንም ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁ ታወኩ፤ እንደ በድንም ሆኑ፡፡ መልአኩም መልሶ ሴቶችን እንዲህ አላቸው፤ “እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና፡፡ በዚህ የለም፤ እርሱ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል፤ ነገር ግን ኑና ተቀብሮበት የነበረውን ቦታ እዩ፡፡ ፈጥናችሁም ሂዱና፡- ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ እነሆ፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ በዚያም ታዩታላችሁ፤ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው፤ እነሆም፥ ነገርኋችሁ፡፡” በፍርሀትና በታላቅ ደስታም ከመቃብሩ ፈጥነው ሔዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ይነግሩአቸው ዘንድ ሮጡ፡፡ እነሆም፥ ጌታችን ኢየሱስ አገኛቸውና፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው፤ እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ “አትፍሩ ሒዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፤ በዚያም ያዩኛል፡፡”
እነርሱም ከሔዱ በኋላ ጠባቂዎች ወደ ከተማ ገብተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች ነገሩ፡፡ ተሰብስበውም ከሽማግሌዎች ጋር መክረው ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጡአቸው፡፡ እንዲህም አሏቸው፥ “ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ፡፡ ይህም ነገር በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደ ሆነ እኛ እናሳምነዋለን፤ እናንተንም ያለ ሥጋት እንድትኖሩ እናደርጋለን፡፡” ጭፍሮችም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ፤ ይህም ነገር እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁድ ዘንድ ሲነገር ይኖራል፡፡
ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ጌታችን ኢየሱስ ወደ አዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፡፡ ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ እኩሌቶቹ ግን ተጠራጠሩ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ፡፡ እንግዲህ ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ፡፡ ያዘዝኋችሁንም እንዲጠብቁ አስተምሩአቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ፡፡”
ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ሐዋርያ ማቴዎስ በምድረ ፍልስጥኤም በዕብራይስጥ ቋንቋ የጻፈው ወንጌል ተፈጸመ፤ መንፈስ ቅዱስ እያተጋው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በስምንተኛው ዓመት፤ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያዉ ዓመት ጻፈው፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡

የሆሣዕና ምንባብ17(ዮሐ.5÷11-31)

እርሱም መልሶ÷ “ያዳነኝ እርሱ፡- አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው፡፡ አይሁድም÷ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና÷ “እነሆ÷ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ደግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” አለው፡፡ ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡  ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና፡፡ ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ “ሰንበትን የሚሽር ነው” በማለት ብቻ አይደለም ደግሞም እግዚአብሔርን “አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል” በማለት ነው እንጂ፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል፡፡ አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል፡፡ አብ ሙታንን እንደሚያስነሣቸው÷ ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል፡፡ አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ፡፡ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይሄድም፡፡

“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአበሔርን ልጅ ቃል የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም ይድናሉ፡፡ ለአብ በራሱ ሕይወት እንዳለው÷ እንዲሁም ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጠው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ነውና ይፈርድ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠው፡፡

“በመቃብር ያሉ ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚህ አታድንቁ፡፡ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ÷ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ፡፡ እኔ ከራሴ አንዳች አደርግ ዘንድ አልችልም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ እንጂ፤ ፍርዴም እውነት ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የእኔን ፈቃድ አልሻምና፡፡

 

የሆሣዕና ምንባብ16(ሐዋ.28÷11-ፍጻ.)

 ከሦስት ወር በኋላም በዚያች ደሴት ወደ ከረመችው ወደ እስክንድርያ መርከብ ወጣን፤ በዚያች መርብ ላይም የዲዮስቆሮስ ምልክት ነበረባት፤ ይኸውም “የመርከበኞች አምላክ” የሚሉት ነው፡፡ ከዚያም ሄደን ወደ ሰራኩስ ደረስን፤ በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥን፡፡ ከዚያም ሄደን ሬቅዩን ወደምትባል ሀገር ደረስን፤ በማግሥቱም ወጣን፤ ከአንድ ቀንም በኋላ ከጐንዋ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ ደረስን፡፡ በዚያምም ወንድሞችን አግኝተን ተቀበሉን፤ በእነርሱ ዘንድም ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚያም በኋላ ሄደን ወደ ሮሜ ደረስን፡፡ በዚያም ያሉት ወንድሞች ስለ እኛ በስሙ ጊዜ፤ አፍዩስ ፋሩስ እስከሚባለው ገበያና እስከ ሦስተኛው ማረፊያ ድረስ ወጥተው ተቀበሉን፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ልቡም ተጽናና፡፡  ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ የመቶ አለቃው እስረኞችን ለሠራዊቱ አለቃ አስረከበ፤ ጳውሎስ ግን ከሚጠብቀው አንድ ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ፈቀደለት፡፡

ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቅ ሰዎች ሰበሰባቸው፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው÷ “ወንድሞቻችን ሆይ÷ እኔ በሕዝቡም ላይ ቢሆን÷ በአባቶቻችንም ሕግ ላይ ቢሆን ያደረግሁት ክፉ ነገር የለም፤ ነገር ግን በኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ ለሮም ሰዎች አሳልፈው ሰጡኝ፡፡ እነርሱም መርምረው ለሞት የሚያበቃ በደል ስለአላገኙብኝ በተነሡ ጊዜ ወደ ቈሣር ይግባኝ ለማለት ግድ ሆነብኝ፤ ነገር ግን ወገኖቼን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም፡፡ ስለዚህም ላያችሁ÷ ልነግራችሁና ላስረዳሁ ወደ እኔ እንድትመጡ ማለድኋችሁ፤ ስለ እሰራኤል ተስፋ በዚህ ሰንሰለት ታስሬአለሁና፡፡” የአይሁድ ታላላቅ ሰዎችም እንዲህ አሉት÷ “ለእኛስ ከይሁዳ ሀገር ስለ አንተ መልእክት አልደረሰንም፤ ከኢየሩሳሌም ከመጡት ወንድሞችም ቢሆን አንድ ስንኳ ከዚህ አስቀድሞ ስለ አንተ ክፉ ነገር ያወራን÷ የነገረንም የለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ነገር በየስፍራው ሁሉ እንዲጣሉ በእኛ ዘንድ ታውቋልና የአንተን ዐሳብ ደግሞ ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንወድዳለን፡፡” ከዚህም በኋላ ወደ እርሱ የሚመጣበትን ቀን ቀጠሩትና ብዙዎች ወዳረፈበት ወደ እርሱ መጡ፤ ከጥዋትም ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየመሰከረ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ኦሪትና ከነቢያት እየጠቀሰ ነገራቸው፡፡ ከእነርሱም እኩሌቶቹ የተናገረውን አመኑ፤ እኩሌቶቹ ግን አልተቀበሉትም፡፡ እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ከእርሱ ተመለሱ፤ እንዲህም አላቸው÷ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አንደበት ለአባቶቻችን በእውነት እንዲህ ብሎ መልካም ነገር ተናግሮአ፡፡ ‹ወደዚህ ሕዝብ ሂድና እንዲህ በላቸው፡- መስማትን ትሰማላችሁ፤ ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ግን አትመለከቱም፡፡ በዐይናቸው እንዳያዩ÷ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ÷ በልባቸውም እንዳያስተውሉ÷ ወደ እኔም እንዳይመለሱና ይቅር እንዳልላቸው የዚህ ሕዝብ ልባቸው ደንድኖአልና÷ ጆሮአቸውም ደንቁሮአልና÷ ዐይናቸውንም ጨፍነዋልና›፡፡ እንግዲህ ከእግዚአብሔር የተገኘች ይህቺ ድኅነት ለአሕዛብ እንደምትሆን ዕወቁ፤ እነርሱም ይሰሙታል፡፡” ይህንም በተናገራቸው ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ወጥተው ሄዱ፡፡ ጳውሎስም በገንዘቡ በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ተቀመጠ፤ ወደ እርሱ የሚመጣውንም ሁሉ ይቀበል ነበር፡፡ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት ይሰብክ ነበር፤ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር፡፡ ጳውሎስም በመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኔሮን ቄሣር ገብቶ ነበርና ረትቶ በሰላም ሄደ፤ ከዚህም በኋላ ሁለት ዓመት ኖሮ ከሮም ወጣ፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ሮም ተመልሶ የኔሮን ቄሣር ዘመዶችን አጠመቀ፤ በኔሮን ትእዛዝም በሰይፍ ተመትቶ መከራውንም ታግሦ ሰማዕት ሆነ፡፡

 

የሆሣዕና ምንባብ15(1ኛጴጥ.4÷1-12)

 ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋው ከተሰለቀ÷ እናንተም ይህቺን ዐሳብ ጋሻ አድርጋችሁ ኑሩ፤ በሥጋዉ መከራ የተቀበለ ከኀጢአት ድኖአልና፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋው ከሕይወቱ ዘመን የቀረውን÷ በሰው ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲፈጽም ነው እንጂ፡፡ የአሕዛብን ፈቃድ፡- ዝሙትንና ምኞትን÷ ስካርንና ወድቆ ማደርን÷ ያለ ልክ መጠጣትንና ጣዖት ማምለክን ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋልና፡፡ እንግዲህ ወደዚህ ሥራ እንዳትሮጡ ዕወቁ፤ ከዚች ጎዳናና መጠን ከሌለው ከዚያ ሥራም ተለዩ፤ እነሆ÷ ከእነርሱም መካከል ሰዎች ስለ እናንተ ያደንቃሉ፤ በዚያም በቀድሞው ሥራ ሳትተባበሩአቸው ሲያዩአችሁ ይሰድቡአችኋል፡፡ እነርሱም በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ተዘጋጅቶ ላለው መልስ ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህም በሥጋቸው በሰው ሕግ አንዲቀጡ÷ በነፍሳቸውም በእግዚአብሔር ሕግ እንዲድኑ ለሙታን ወንጌልን ሰበኩላቸው፡፡

የሁሉ ፍጻሜው ቀርቦአልና ልባችሁን አንጹ፤ ለጸሎትም ትጉ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ በፍጹም ልቡናችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ፍቅር ኀጢአትን ሁሉ ይሸፍናልና፡፡ ሳታንጐራጒሩ እርስ በርሳችሁ እንግዳ መቀበልን ውደዱ፡፡ ሁላችሁም በየራሳችሁ ከእግዚአበሔር የተሰጣችሁን ዕድል እንደ ተቀበላችሁ መጠን እንደ ደግ መጋቢ አገልግሉ፤ ለአያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ስጦታው እየራሱ ነውና፡፡ የሚያስተምርም÷ እንደ እግዚአብሔር ቃል ያስተምር÷ የሚያገለግልም እግዚአብሔር በሚሰጠው ኀይል ያገልግል፤ ክብርና ኀይል እስከ ዘለዓለም ድረስ ገንዘቡ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በሁሉ ነገር ይመሰገን ዘንድ፡፡

ወዳጆች ሆይ÷ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ÷ ድንቅ ነገር እንደመጣባችሁ አትደነቁ፡፡

 

የሆሣዕና ምንባብ14(ዕብ. 9÷11-ፍጻ.)

 ክርስቶስ ግን ለምትመጣይቱ መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ÷ የሰው እጅ ወደ አልሠራት÷ በዚህ ዓለም ወደ አልሆነችው÷ ከፍተኛዪቱ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው ድንኳን÷ የዘለዓለም መድኀኒትን ገንዘብ አድርጎ÷ በገዛ ደሙ አንድ ጊዜ ወደ መቅደስ ገባ እንጂ በላምና በፍየል ደም አይደለም፡፡ የላምና የፍየል ደም÷ በረከሱትም ላይ የሚረጭ የጊደር አመድ÷ የሚያነጻና የረከሱትንም ሥጋቸውን የሚቀድሳቸው ከሆነ÷ ነውር የሌለው ሆኖ÷ በዘለዓለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርም እናመልከው ዘንድ ሕሊናችንን ከሞት ሥራ እንዴት ይልቅ ያነጻ ይሆን?

ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ተቀብሎ÷ በቀደመው ሥርዐት ስተው የነበሩትን ያድናቸው ዘንድ ወደ ዘለዓለም ርስቱም የጠራቸው ተስፋውን ያገኙ ዘንድ÷ ለአዲሲቱ ኪዳን መካከለኛ ሆነ፡፡ ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡ ሰሙ ሞት ይመጣ ዘንድ ግድ ነው፡፡ የሙአች ሰው ኑዛዜ የጸናች ናት፤ ተናዛዡ በሕይወት ባለበት ጊዜ አትጠቅምምና፡፡ ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለ ደም አልከበረም፡፡ ሙሴ የኦሪትን ትእዛዝ ሁሉ ለመላው ሕዝብ ከነገረ በኋላ÷ የላምና የፍየል ደም ከውኃ ጋር ቀላቅሎ÷ ቀይ የበግ ጠጒርና የስሚዛ ቅጠል ነክሮ መጽሐፈ ኦሪቱንና ሕዝቡን ሁሉ ይረጭ ነበር፡፡ “እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው” ይላቸው ነበር፡፡ ድንኳኑንና የመገልገያው ዕቃ ሁሉ በደሙ ይረጭ ነበር፡፡ ደግሞም በቀረበው ሁሉ እንዲህ ያደርግ ነበር÷ በኦሪት ሕግ ሁሉ በደም ይነጻ ነበር፤ ደም ሳይረጭ ግን አይሰረይም ነበር፡፡

በሰማይ ባለው አምሳል የተሠራው ይህ ሥራ÷ በዚህ ደም የሚነጻ ከሆነ÷ ይህ ሰማያዊ መሥዋዕትስ ከዚህ ይበልጣል፡፡ ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና÷ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ÷ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ፡፡ ሊቀ ካህናቱ ያደረገው እንደ ነበረ÷ በያመቱም ደም ይዞ ወደ ቅድስት ይገባ እንደ ነበረ ዘወትር ራሱን የሚሠዋ አይደለም፡፡ ይህስ ባይሆን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ በሞተ ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ÷ ራሱን በመሠዋት ኀጢአትን ይሽራት ዘንድ አንድ ጊዜ ተገለጠ፡፡ ለሰው አንድ ጊዜ ሞት÷ ከዚያም በኋላ ፍርድ እንደ ሚጠብቀው÷ እንዲሁ ክርስቶስም የብዙዎችን ኀጢአት ያስተሰርይ ዘንድ ራሱን አንድ ጊዜ ሠዋ፤ በኋላ ግን ያድናቸው ዘንድ ተስፋ ለሚያደርጉት ያለ ኀጢአት ይገለጥላቸዋል፡፡

 

የሆሣዕና ምንባብ13(ዮሐ.12÷12-20)

በማግሥቱም ለበዓል መጥተው የነበሩ ብዙ ሰዎች ጌታትን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመጣ በሰሙ ጊዜ÷ የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው “ሆሣዕና በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ÷ የእስራኤልም ንጉሥ ቡሩክ ነው” እያሉ ወጥተው ተቀበሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርስዋ ላይ ተቀመጠ፡፡ “የጽዮን ልጅ ሆይ÷ አትፍሪ፤ እነሆ÷ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ይመጣል” ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም አስቀድመው ይህን ነገር አላወቁም፤ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያ ጊዜ ይህ ነገር ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ÷ ይህንም እንደ አደረጉለት ትዝ አላቸው፡፡ ከዚያም አብረውት የነበሩት ሕዝብ አልዓዛርን ከመቃብር እንደ ጠራው÷ ከሙታንም እንደ አስነሣው መሰከሩለት፡፡ ስለዚህም ነገር ሕዝቡ ሁሉ ሊቀበሉት ወጡ፤ ይህን ተአምራት እንደ አደረገ ሰምተዋልና፡፡ ፈሪሳውያንም እርስ በርሳቸው÷ “የምታገኙት ምንም ጥቅም እንደሌለ ታያላችሁን? እነሆ÷ ዓለም ሁሉ ተከትሎታል” ተባባሉ፡፡

የሆሣዕና ምንባብ12(ሉቃ.19÷28-ፍጻ.)

 ይህንም ተናግሮ ወደ ፊት ሄደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ወጣ፡፡ ደብረ ዘይት ወደ ሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ÷ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፡፡ እንዲህም አላቸው÷ “በፊታችሁ ወደ አለችው መንደር ሂዱ፤ገብታችሁም ሰው ያልተቀመጠበት የታሰረ ውርንጫ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም አምጡልኝ፡፡ ለምን ትፈቱታላችሁ? የሚላችሁ ቢኖር ጌታው ይሻዋል በሉ፡፡” የተላኩትም ሄደው እንደ አላቸው አገኙ፡፡ ውርንጫውንም ሲፈቱ ባለቤቶቹ “ውርንጫውን ለምን ትፈቱታላችሁ?” አሉአቸው፡፡ እነርሱም “ጌታው ይሻዋል” አሉ፡፡ ይዘውም ወደ ጌታችን ኢየሱስ ወሰዱት፤ በውርንጫው ላይም ልብሳቸውን ጭነው ጌታችን ኢየሱስን በዚያ ላይ አስቀመጡት፡፡ ሲሄዱም በመንገድ ልብሳቸውን አነጠፉ፡፡ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት መውረጃም በደረሱ ጊዜ÷ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ ስለ አዩት ኀይል ሁሉ ደስ ይላቸውና እግዚአበሔርን በታላቅ ቃል ያመሰግኑት ዘንድ ጀመሩ፡፡ እንዲህ እያሉ÷ “በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ የእስራኤል ንጉሥ ቡሩክ ነው፤ ሰላም በምድር÷ በአርያምም ክብር ይሁን፡፡” ከፈሪሳውያንም በሕዝቡ መካከል÷ “መምህር ሆይ÷ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” ያሉት ነበሩ፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “እነዚህ ዝም ቢሉ እኒህ ድንጋዮች ይጮሀሉ፡፡”

በደረሰ ጊዜም ከተማዪቱን አይቶ አለቀሰላት፡፡ እንዲህም አላት÷ “አንቺስ ብታውቂ ሰላምሽ ዛሬ ነበረ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ከዐይኖችሽ ተሰወረ፡፡ ጠላቶችሽ አንቺን የሚከቡበት ቀን ይመጣል፤ ይከትሙብሻል፤ ያስጨንቁሻልም፤ በአራቱ ማዕዘንም ከብበው ይይዙሻል፡፡ አንቺን ይጥሉሻል፤ ልጆችሽንም ከአንቺ ጋር ይጠሉአቸዋል፤ ድንጋይንም በደንጋይ ላይ አይተዉልሽም፤ የይቅረታሽን ዘመን አላወቅሽምና፡፡”

ወደ ቤተ መቅደስም ገብቶ በዚያ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የለዋጮችንም መደርደሪያ÷ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ፡፡ “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል የሚል ጽሑፍ አለ፤ እናንተ ግን የሌቦችና የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው፡፡ ዘወትርም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ የካህናት አለቆች÷ ጻፎችና የሕዝብ ታላላቆችም ሊገድሉት ይሹ ነበር፡፡ ነገር ግን የሚያደርጉትን አጡ ሕዝቡ ሁሉ ትምህርቱን በመስማት ይመሰጡ ነበርና፡፡

 

የሆሣዕና ምንባብ11(ማር.11÷1-12.)

ኢየሩሳሌም ለመግባት በደብረ ዘይት አጠገብ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በደረሱ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፡፡ እንዲህም አላቸው÷ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደ መንደርም በገባችሁ ጊዜ÷ ሰው በላዩ ያልተቀመጠበት የአህያ ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ፡፡ ‹ምን ታደርጋላችሁ?› የሚላችሁ ሰው ቢኖርም ‹ጌታው ይሻዋል› በሉ፤ ወዲያውኑም ወደዚህ ይሰድደዋል፡፡” ሄደውም በበሩ አጠገብ ባለው ሜዳ በመንገድ ዳር የታሰረ ውርንጫ አገኙ፤ ፈቱትም፡፡ ከዚያ ቆመው የነበሩትም÷ “ምን ልታደርጉት ነው ውርንጫዉን የምትፈቱት?” አሉአቸው፡፡ ጌታችን ኢየስስ እንደ አዘዛቸውም ነገሩአቸው፤ እነርሱም ተዉአቸው፡፡ ውርንጫዉንም ወደ ጌታችን ኢየሱስ ወሰዱና ልብሳቸውን በላዩ ደልድለው አስቀመጡት፡፡ ብዙዎችም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር፡፡ በፊት የሚሄዱ÷ በኋላም የሚከተሉ እንዲህ እያሉ ይጮኹ ነበር÷ “ሆሣዕና÷ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ስም የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሣዕና በአርያም፡፡” ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ ሁሉንም ተመልክቶ በመሸ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ ወደ ቢታንያ ሄደ፡፡

የሆሣዕና ምንባብ9(ማቴ. 9፥26-ፍጻ.)

የተአምራቱም ዝና በሀገሩ ሁሉ ተሰማ፡፡ ጌታችን ኢየስስም ከዚያ በአለፈ ጊዜ ሁለት ዕውራን÷ “የዳዊት ልጅ ሆይ÷ ራራልን” ብለው እየጮኹ ተከተሉት፡፡ ወደ ቤትም በገባ ጊዜ እነዚያ ዕውራን ወደ እርሱ መጡ፤ ጌታችን ኢየሱስም “ይህን ማድረግ እንዲቻለኝ ታምናላችሁን?” አላቸው፤ እነርሱም÷ “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉት፡፡ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” ብሎ ዐይኖቻቸውን ዳሰሳቸው፡፡ ያንጊዜም ዐይኖቻቸው ተገለጡ፤ ጌታችን ኢየሱስም÷ “ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ” ብሎ አዘዛቸው፡፡ እነርሱ ግን÷ ወጥተው በዚያ ሀገር ሁሉ ስለእርሱ ተናገሩ፡፡

እነዚያም ከወጡ በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ወደ እርሱ አመጡ፡፡ ያደረበትም ጋኔን በወጣ ጊዜ ዲዳ የነበረው ተናገረ፤ ሰዎችም “በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ያለ ከቶ አልተየም” እያሉ አደነቁ፡፡ ፈሪሳውያን ግን “በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” አሉ፡፡

ጌታችን ኢየሱስም በምኲራቦቻቸው እያስተማረ÷ የመንግሥት ወንጌልንም እየሰበከ÷ በሕዝቡም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በየከተማውና በየመንደሩ ሁሉ ተመላለሰ፡፡ ብዙ ሰዎችንም አይቶ አዘነላቸው፤ ደክመው ነበርና÷ እረኛ እንደሌላቸው በጎችም ተበትነው ነበርና፡፡ ያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “መከሩሰ ብዙ ነው፤ ሠራተኛው ግን ጥቂት ነው፡፡ እንግዲህ ለመከሩ ሠራተኛን ይጨምር ዘንድ የመከሩን ባለቤት ለምኑት፡፡”

 

የሆሣዕና ምንባብ10(ማቴ.21÷1-18)

ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦ÷ ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፡፡ እንዲህም አላቸው፤ “በፊታችሁ ወደ አለችው መንደር ሂዱ፤ ያንጊዜም የታሰረች አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ፡፡ ምን ታደርጋላችሁ? የሚላችሁ ቢኖርም ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ÷ ያንጊዜ ይሰዱአችኋል፡፡” ይህም ሁሉ የሆነው በነቢይ እንዲህተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ “ለጽዮን ልጅ፡- እነሆ÷ የዋህ ንጉሥሽ በአህያይቱና በአህያይቱ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት”፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ጌታችን ኢየሱስ እንደ አዘዛቸው አደረጉ፡፡ አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፤ ልብሳቸውንም በላያቸው ጫኑ፤ ጌታችን ኢየሱስም በእነርሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ ብዙ ሕዝብም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎችም ከዛፎች ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፡፡ በፊቱ የሚሄዱትና የሚከተሉት ሕዝብም÷ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ይጮሁ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ÷ “ከተማዪቱ ይህ ማነው?” እያለች ታወከች፡፡ ሕዝቡም÷ “ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ፡፡

ጌታችን ኢየሱስም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አባረረ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም መደርደሪያ÷ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ፡፡ “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላይ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው፡፡ በቤተ መቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡ፤ አዳናቸውም፡፡ ያን ጊዜም የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ተአምራት÷ ልጆችንም በቤተ መቅደስ÷ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ” እያሉ ሲጮሁ ባዩ ጊዜ ደስ አላላቸውም፡፡ እነርሱም÷ “እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን?” አሉት፤ ጌታችን ኢየሱስም÷ “አዎን÷ እሰማለሁ÷ ከልጆችና ከሕፃናት አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ ያነበባችሁበት ጊዜ የለምን?” አላቸው፡፡ ትቶአቸውም ከከተማው ወደ ቢታንያ ሄደ፤ በዚያም አደረ፡፡