የትንሣኤ የማሕሌት ምንባብ 1 (ማቴ.28፥1-ፍጻሜ )

በሰንበትም ማታ ለእሑድ አጥቢያ ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ፡፡ እነሆ፥ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶአልና፤ ቀርቦም በመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋይዋን አንከባሎ በላይዋ ተቀመጠ፡፡ መልአኩም እንደ መብረቅ፥ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፡፡ እርሱንም ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁ ታወኩ፤ እንደ በድንም ሆኑ፡፡ መልአኩም መልሶ ሴቶችን እንዲህ አላቸው፤ “እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና፡፡ በዚህ የለም፤ እርሱ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል፤ ነገር ግን ኑና ተቀብሮበት የነበረውን ቦታ እዩ፡፡ ፈጥናችሁም ሂዱና፡- ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ እነሆ፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ በዚያም ታዩታላችሁ፤ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው፤ እነሆም፥ ነገርኋችሁ፡፡” በፍርሀትና በታላቅ ደስታም ከመቃብሩ ፈጥነው ሔዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ይነግሩአቸው ዘንድ ሮጡ፡፡ እነሆም፥ ጌታችን ኢየሱስ አገኛቸውና፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው፤ እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ “አትፍሩ ሒዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፤ በዚያም ያዩኛል፡፡”
እነርሱም ከሔዱ በኋላ ጠባቂዎች ወደ ከተማ ገብተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች ነገሩ፡፡ ተሰብስበውም ከሽማግሌዎች ጋር መክረው ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጡአቸው፡፡ እንዲህም አሏቸው፥ “ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ፡፡ ይህም ነገር በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደ ሆነ እኛ እናሳምነዋለን፤ እናንተንም ያለ ሥጋት እንድትኖሩ እናደርጋለን፡፡” ጭፍሮችም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ፤ ይህም ነገር እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁድ ዘንድ ሲነገር ይኖራል፡፡
ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ጌታችን ኢየሱስ ወደ አዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፡፡ ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ እኩሌቶቹ ግን ተጠራጠሩ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ፡፡ እንግዲህ ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ፡፡ ያዘዝኋችሁንም እንዲጠብቁ አስተምሩአቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ፡፡”
ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ሐዋርያ ማቴዎስ በምድረ ፍልስጥኤም በዕብራይስጥ ቋንቋ የጻፈው ወንጌል ተፈጸመ፤ መንፈስ ቅዱስ እያተጋው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በስምንተኛው ዓመት፤ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያዉ ዓመት ጻፈው፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡