የትንሣኤ የቅዳሴ ምንባብ 4( ዮሐ.20፥1-19)

ከሳምንቱም በመጀመሪያዉ ቀን ማርያም መግደላዊት በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ ወደ መቃብር መጣች፤ ድንጋዩንም ከመቃብሩ አፍ ተነሥቶ አገኘችው፡፡ ፈጥናም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ጌታችን ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደዚያ ወደ ሌላዉ ደቀ መዝሙር መጥታ፥ “ጌታዬን ከመቃብር ወስደውታል፤ ወዴትም እንደ ወሰዱት አላውቅም” አለቻቸው፡፡ ጴጥሮስና ያ ሌላዉ ደቀ መዝሙርም ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ፡፡ ሁለቱም በአንድነት ሲሮጡ ያ ሌላዉ ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን ቀድሞት ወደ መቃብሩ ደረሰ፡፡ ጐንበስ ብሎም ሲመለከት በፍታዉን ተቀምጦ አየ፤ ነገር ግን ወደ ውስጥ አልገባም፡፡ ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ በፍታዉንም በአንድ ወገን ተቀምጦ አየ፤ በራሱ ላይ የነበረው መጠምጠሚያም ሳይቃወስ ለብቻው ተጠቅልሎ አየ፤ ከበፍታዉ ጋርም አልነበረም፡፡ ከዚህም በኋላ አስቀድሞ ወደ መቃብሩ የደረሰው ሌላዉ ደቀ መዝሙር ገባ፤ አይቶም አመነ፤ ከሙታን ተለይቶ ይነሣ ዘንድ እንደ አለው በመጻሕፍት የተጻፈውን ገና አላወቁም ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡
ማርያም ግን ከመቃብሩ በስተውጭ እያለቀሰች ቆማ ነበረ፤ እያለቀሰችም ወደ መቃብሩ ጐንበስ ብላ ተመለከተች፡፡ ሁለት መላእክትንም ነጭ ልብስ ለብሰው የጌታችን የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ አንዱ በራስጌ፥ አንዱም በግርጌ ተቀምጠው አየች፡፡ እነዚያ መላእክትም፥ “አንቺ ሴት፥ ምን ያስለቅስሻል?” አሉአት፤ እርስዋም፥ “ጌታዬን ከመቃብር ውስጥ ወስደውታል፤ ወዴትም እንደ ወሰዱት አላውቅም” አለቻቸው፡፡ ይህንም ተናግራ ወደ ኋላዋ መለስ ስትል ጌታችን ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ጌታችን ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም፡፡ ጌታችን ኢየሱስም፥ “አንቺ ሴት፥ ምን ያስለቅስሻል? ማንንስ  ትሺያለሽ?” አላት፤ እርስዋ ግን የአትክልት ቦታ ጠባቂ መስሎአት፥ “ጌታዬ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆነ ሄጄ ወደ እኔ እንዳመጣውና ሽቱ እንድቀባው ወዴት እንደ አኖርኸው ንገረኝ” አለችው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም፥ “ማርያም!” አላት፤ እርስዋም መለስ ብላ በዕብራይስጥ ቋንቋ፥ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጓሜዉም “መምህር” ማለት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም፥ “አትንኪኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጂና፡- ወደ አባቴ፥ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ፥ ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ አለ ብለሽ ንገሪአቸው” አላት፡፡ ማርያም መግደላዊትም ሄደች፤ ጌታን እንደ አየች፥ ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረቻቸው፡፡
ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩበት ቤት ደጁ ተቈልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው፡፡