የሆሣዕና ምንባብ17(ዮሐ.5÷11-31)

እርሱም መልሶ÷ “ያዳነኝ እርሱ፡- አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው፡፡ አይሁድም÷ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና÷ “እነሆ÷ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ደግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” አለው፡፡ ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡  ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና፡፡ ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ “ሰንበትን የሚሽር ነው” በማለት ብቻ አይደለም ደግሞም እግዚአብሔርን “አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል” በማለት ነው እንጂ፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል፡፡ አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል፡፡ አብ ሙታንን እንደሚያስነሣቸው÷ ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል፡፡ አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ፡፡ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይሄድም፡፡

“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአበሔርን ልጅ ቃል የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም ይድናሉ፡፡ ለአብ በራሱ ሕይወት እንዳለው÷ እንዲሁም ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጠው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ነውና ይፈርድ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠው፡፡

“በመቃብር ያሉ ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚህ አታድንቁ፡፡ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ÷ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ፡፡ እኔ ከራሴ አንዳች አደርግ ዘንድ አልችልም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ እንጂ፤ ፍርዴም እውነት ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የእኔን ፈቃድ አልሻምና፡፡