የትንሣኤ የማሕሌት ምንባብ 2 (ማር.16፥1-ፍጻሜ )

ሰንበትም ባለፈች ጊዜ ማርያም መግደላዊት፥ የያዕቆብ እናት ማርያም፥ ሰሎሜም መጥተው ሥጋዉን ሊቀቡ ሽቱ ገዙ፡፡ በእሑድ ሰንበትም እጅግ ማልደው ፀሐይ በወጣ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዱ፡፡ እርስ በርሳቸውም፥ “ድንጋዪቱን ከመቃብሩ አፍ ላይ ማን ያነሣልናል?” አሉ፤ ድንጋዪቱ እጅግ ታላቅ ነበረችና፡፡ አሻቅበውም በተመለከቱ ጊዜ ደንጋዪቱ ተንከባልላ አዩ፡፡ ወደ መቃብሩም በገቡ ጊዜ አንድ ጎልማሳ ነጭ ልብስ ለብሶ በስተቀኝ ተቀምጦ አገኙና ደነገጡ፡፡ እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትሻላችሁን? ተነሥቶአል፤ በዚህስ የለም፤ የተቀበረበትም ቦታ እነሆ፡፡ ነገር ግን፥ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስም ወደ ገሊላ እንደሚቀድማቸው ንገሩቸው፤ እንደ ነገራቸውም በዚያ ያዩታል፡፡” ከመቃብርም ወጥተው ሸሹ፤ ፍርሀትና ድንጋጤ ይዞአቸዋልና፤ ስለፈሩም ለማንም አልተናገሩም፤ ያዘዛቸውንም ሁሉ ለጴጥሮስና ለወንድሞቹ ተናገሩ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ተገለጠላቸውና፥ ለዘለዓለም ሕይወት የሚሆን የማይለወጥ ቅዱስ ወንጌልን ለፍጥረቱ ሁሉ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ይሰብኩ ዘንድ ላካቸው፡፡
በእሑድ ሰንበትም ማለዳ ተነሥቶ ሰባት አጋንንትን ላወጣላት ለማርያም መግደላዊት አስቀድሞ ታያት፡፡
እርስዋም ሄዳ ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሲያዝኑና ሲያለቅሱ ሳሉ ነገረቻቸው፡፡ እነርሱ ግን ሕያው እንደ ሆነ፥ ለእርስዋም እንደ ተገለጠላት በሰሙ ጊዜ አላመንዋትም፡፡ ከዚህም በኋላ፥ ከእነርሱ ለሁለቱ ወደ ገጠር ሲሄዱ በሌላ መልክ ተገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ደግሞ ሄደው ለባልንጀሮቻቸው ነገሩ፤ እነርሱንም ቢሆን አላመኑአቸውም፡፡ ከዚህም በኋላ፥ ደግሞ ዐሥራ አንዱ በማዕድ ተቀምጠው ሳለ ተገለጠላቸው፤ እንደ ተነሣ ያዩትን አላመኑአቸውምና ስለ ሃይማኖታቸው ጒድለት ገሠጻቸው፤ የልባቸውንም ጽናት ነቀፈ፡፡ እንዲህም አላቸው፥ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ለፍጥረትም ሁሉ ወንጌልን ሰበኩ፡፡ ያመነ የተጠመቀም ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል፡፡ ይህችም ምልክት በስሜ የሚያምኑትን ትከተላቸዋለች፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋም ይናገራሉ፡፡ እባቦችንም በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚጐዳቸውም ነገር የለም፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡም የሚጐዳቸው የለም፤ በድውያን ላይም እጃቸውን ይጭናሉ፤ ድውያኑም ይፈወሳሉ፡፡”
ጌታችን ኢየሱስም ከተነጋገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡ እነርሱም ወጥተው ጌታ እየረዳቸው፥ ቃሉንም በማያቋርጥ ተአምር እያጸናላቸው በስፍራው ሁሉ አስተማሩ፡፡
ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዲ ወንጌላዊው ማርቆስ የጻፈው ወንጌል ተፈጸመ፤ የጻፈውም በሮም ሀገር በሮማይስጥ ቋንቋ፤ ጌታችን በሥጋ ወደ ሰማይ ባረገ በዐሥራ አንድ ዓመት፥ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በአራት ዓመት ነው፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡