hosaena

ሆሣዕና(ለሕፃናት)

ሚያዚያ 17 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቤካ ፋንታ

hosaenaበኢየሩሳሌም ሀገር ውስጥ በምትገኝ በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ ነው የምኖረው፡፡ ከተወለድኩ ዛሬ 5 ዓመት ሞልቶኛል፡፡ ቀኑ ሰንበት ነው እቤት ውስጥ እየተጫወትኩ እናቴም በጓዳ ሥራ እየሠራች ድንገት የብዙ ሰዎች የእልልታ ድምጽ ሰፈሩ ውስጥ ተሰማ፡፡ እናቴም በፍጥነት ከጓዳ ሮጣ ወጥታ “ልጄ ልጄ ነይ እንሂድ ብላ በጀርባዋ ላይ አዝላኝ ሮጣ ከቤት ወጣች፡፡ እኔም በሁኔታው ተገርሜያለሁ፡፡

በሰፈር ውስጥ ያሉ ጓደኞቼ ሁሉ በእናታቸው ጀርባና በአባታቸው ትከሻ ላይ ሆነው ደስ ብሏቸው እንደ ወላጆቻቸው እልል ይላሉ፡፡ ወላጆቻችን ሁሉ ተሰብስበው ከሰፈራችን መውጫ ጋር ወዳለ ትልቅ የዘንባባ ዛፍ ተያይዘው አመሩ፡፡ ከዚያም የዘንባባ ዝንጣፊውን እየቆረጡ ሁሉም ያዙ ለእኛም ሰጡን፡፡ ከዚያ እልል እያልን በደስታ ወደ ቤተ መቅደስ እሮጥን፡፡
በመንገድ ላይ በጣም ብዙ ሕዝብ አየሁኝ ሁሉም ደስ ብሏቸው እነርሱም እንደኛ ወደ ቤተ መቅደስ ይሮጣሉ፡፡ የሕፃናቶቹን ብዛት ሳይ ውስጤ በጣም ደስ አለው፡፡ የገረመኝ ደግሞ የሚያለቅስ ልጅ አንድ እንኳን የለም፡፡ “ዛሬ የኛ የደስታና የዝማሬ ቀን ነው” ማለት ነው ብሎ ልቤ በደስታ ፈነደቀ፡፡

ወደ ቤተ መቅደስ ለመድረስ ጥቂት መንገድ ሲቀረን በርቀት ወደ ቤተ መቅደሱ የሚጓዙ በጣም በጣም ብዙ ሕዝብ ተመለከትኩኝ፡፡ እንደኛ እነርሱም ዘንባባ ይዘዋል፡፡ በመካከላቸው አንድ ትልቅ አህያ አየሁኝ፣ ከአህያይቱም ጋር ልጇ ውርንጫዋ አለች፡፡ የሚያማምር ልብስ በአህያዎቹ ጀርባ ላይ ተነጥፏል፡፡ በውርንጫዋም ላይ የሁላችን ፈጣሪ፣ ንጉሣችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀምጦ ስመለከት በደስታ ዘለልኩኝ፡፡ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሆን በጣም ያስደስታል፡፡

ምክንያቱም እኛ ሕፃናትን ሲያይ ደስ ይለዋል፡፡ እቅፍ አድርጎ ስሞን በጉልበቱ ላይ ቁጭ አድርጎን ያስተምረናል፣ ይመክረናል፡፡ በዙሪያውም ላሉት ሰዎች እንደነዚህ ሕፃናት ንጹሃን ሁኑ፣ ኀጢአት አትሥሩ፣ እነርሱ አይዋሹም፣ እያለ ይመክራቸዋል፡፡

ከዚያ ምን ሆነ መሰላችሁ፤ እልል እያለ የሚያመሰግነው ሕዝብና በእናትና በአባቶቻችን እቅፍ ውስጥ ያለነው ሕፃናት በአንድነት ሆነን ጮክ ብለን የዘንባባውን ቅጠል ወደ ቀኝ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ ወደ ግራ እያውለበለብን መዝሙር መዘመር ጀመርን፡፡ መዝሙሩም እንዲህ የሚል ነው፡፡ “ሆሣዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም፣ ሆሣዕና በአርያም፣ ሆሣዕና በአርያም” የመዝሙሩ ድምጽ በኢየሩሳሌም ከተማ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተሰማ፡፡ በጣም ደስ ያለኝ ደግሞ የእኛ የሕፃናቱ ድምጽ ከትልልቆቹ በልጦ መስማቱ ነው፡፡ ጌታችንን በአህያዋ ላይ ተቀምጦ ባየሁት ጊዜ ትዝ ያለኝ አባዬ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ ያስተማረኝን ታሪክ ልንገራችሁ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” ት.ዘካ.9፥9፡፡

የዝማሬውን ድምጽ ሲሰሙ አባታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወዱት እና የሚያሳድዱት በከተማው ውስጥ ያሉ ጨካኝ ሰዎች እኛ ተሰብስበን እየዘመርን ወደአለንበት መጡ፡፡ ሲመለከቱ ሕዝቡ ሁሉ ደስ ብሏቸው እየዘመሩ እልል እያሉ የዘንባባውን ቅጠል እያውለበለቡ ኢየሱስ ክርስቶስን በአህያዋ ውርንጫ ላይ አስቀምጠው እያመሰገኑት ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄዱ ተመልክተው ጨካኞቹ ሰዎች በጣም ተናደው ሕዝቡን “ዝም በሉ” ብለው ተቆጧቸው፡፡ ትልልቆቹ ሁሉ ፈርትው ዝም አሉ፡፡

እኔና ጓደኞቼ ግን በእናታችን ጀርባ ላይ ካሉት ሕፃናት ጋር አብረን ሆነን ጮክ ብለን “ሆሣዕና በአርያም” የሚለውን መዝሙር መዘመር አላቆምንም ነበር፡፡ የገረመኝ ደግሞ ከእኔ የሚያንሱት ገና የተወለዱትም ሕፃናት መዝሙሩን ጮክ ብለው ሲዘምሩት በመስማቴ ነው፡፡ “እግዚአብሔር ሆይ መናገር የማንችለውን እኛን እንድንዘምርልህ ስለፈቀድክልን ተመስገን፡፡” ብዬ አመስግኜ መዝሙሩን መዘመር ቀጠልኩኝ “ሆሣዕና፣ ሆሣዕና፣ ሆሣዕና በአርያም….”

እነዚህ ጨካኞቹ ሰዎች ግን እናትና አባቶቻችንን ዝም አስብሏቸው ብለው ሲያስፈራሩዋቸው ወላጆቻችን ፈርተው የሁላችንንም አፋችንን ይዘው ዝም አስባሉን፡፡ አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያዋ ውርንጫ (በትንሿ አህያ) ላይ ቁጭ ብሎ ለጨካኞቹ ሰዎች እንዲህ አላቸው “ከሕፃናት ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራሴ አዘጋጅቻለሁ፡፡ የእነርሱንም አፍ ይዛችሁ ዝም ብታስብሏቸው በዙሪያዬ ያሉት ድንጋዮች ያመሰግኑኛል፡፡ የፈጠርኳችሁ ድንጋዮች ሆይ ሕፃናት እንደዘመሩ እናንተም በመዝሙር አመስግኑኝ፡፡” በማለት በታላቅ ድምጽ ሲናገር፤ ትልልቁም ድንጋይ፣ ትንንሹም ድንጋይ ከመሬት ወደ ላይ እየተነሡ “ሆሣዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ እናቀርባለን ምስጋና…” እያሉ በጣም ደስ በሚል ድምጽ መዘመር ጀመሩ፡፡ በዚህን ጊዜ ጨካኞቹ ሰዎች አፍረውና ፈርትው ሄዱ፡፡

እኛም ወላጆቻችንም በዙሪያችንም ያሉትም ድንጋዮች አምላካችንን ከበን በእልልታ እየዘመርን ለአህያዎቹ መርገጫ ልብሳችንንና የዘንባባውን ዝንጣፊ እያነጠፍን ወደ ቤተ መቅደስ ገባን፡፡ በዚያም ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደስ የሚል ትምህርት አስተማረን፡፡

በመጨረሻም ሆሣዕና ብለን ምስጋና ላቀረብነውና በቤተ መቅደስ ተገኝተን ቃሉን ለምንሰማው ሕፃናት እንዲህ ብሎ መከረን “ልጆቼ በመዝሙራችሁ ተደስቻለሁ፣ ሁል ጊዜ ወደ ቤቴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ኑና ዘምሩልኝ፡፡ አፋችሁ በመዝሙር ይዘምር እንጂ ዘፈን እንዳይዘፍን አደራችሁን፡፡ ዘፈን መዝፈን ኀጢአት ነው፡፡”

ትምህርቱን ጨርሰን ከእናቴ ጋር ደስ እያለን ወደ ቤት ተመለስን፡፡ ታዲያ ሁል ጊዜ ይህችን የሆሣዕናን በዓል በውስጤ አስባታለሁ፣ መዝሙሩን መዘመር በጣም ያስደስተኛል፡፡ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻ የመከረኝንም ምክር ጠብቄ ዘፈን የሚባል በአፌ ሳልዘፍን መዝሙር እየዘመርኩኝ እግዚአብሔርን እያመሰገንኩኝ አደኩኝ፡፡

ልጆችዬ ዛሬ የምታነቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚሆነው ማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 21 እስከ ቁጥር 16 እና ማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 11 ከቁጥር 1 እስከ 17 ያለውን ይሆናል፡፡ ሆሣዕና በአርያም ብለን እንድናመሰግነው ኀይሉን የሰጠን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን አሜን፡፡፡

ዳግመኛ መወለድ(ለሕፃናት)

ሚያዚያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቤካ ፋንታ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች፡፡ ዛሬ የምንማረው የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚወለዱ ነው፡፡

አንድ መምህር በኢየሩሳሌም ነበረ፣ ስሙም ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ ቀን ቀን ተማሪዎቹን ሲያስተምር ይውልና ማታ ፀሐይዋ ስትጠልቅ በጨለማ ወደ አምላካችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይመጣል፡፡ ከዚያ እግሩ ሥር ቁጭ ብሎ ይማራል፡፡ ያልገባውን እየጠየቀ በደንብ ስለሚከታተል ጌታችንም እስኪገባው ድረስ ግልጽ አድርጎ ያስረዳውና የጠየቀውን ይመልስለታል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ኒቆዲሞስ የእግዚአብሔርን ቃል ለመማር ከቤቱ ተነሥቶ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ መጣ፡፡ አምላካችንም በዚያ ሌሊት ለኒቆዲሞስ ያስተማረው ትምህርት እንዲህ የሚል ነበር፡፡ “ኒቆዲሞስ ሆይ፥ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፡፡”

ኒቆዲሞስም በጣም ደንግጦ “ዳግመኛ? መወለድ እንዴት ይቻላል? ሰው ደግሞ የሚወለደው አንዴ አይደለም እንዴ? ደግሞስ አንድ ሰው ካደገ ትልቅ ከሆነ በኋላ እንደገና ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ሊወለድ እንዴት ይችላል?” እያለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጠየቀው፡፡ ጌታችንም የጠየቀውን ጥያቄ በደንብ አድርጎ መለሰለት፡፡

ልጆች አሁን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መለሰለት መልስ ከመሄዳችን በፊት ኒቆዲሞስ የጠየቀውን ጥያቄ ደግሜ ልጠይቃችሁ፡-

  1. የሰው ልጆች የምንወለደው ስንት ጊዜ ነው?

  2. ሁለተኛ ጊዜ የምንወለደው እንዴት ነው?

  3. ዳግመኛ የምንወለደው የት ነው?   

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግሩ ሥር ቁጭ ብለው ከሚማሩት ተማሪዎች መካከል ይህንን ጥያቄ ለጠየቀው ለኒቆዲሞስ “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልኩ እታድንቅ፡፡ የእኔ ልጆች እንድትሆኑ ዳግመኛ የምትወለዱት እንዴት፣ መቼ እና የት እንደሆነ አስረዳሃለሁ” ብሎ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያስተማራቸው ትምህርት እንዲህ የሚል ነው፡-

ተማሪዎቼ ሆይ የሰው ልጆች በእናታቸው ማኅፀን ዘጠኝ ወር ከ5 ቀን ከቆዩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይወለዳሉ፡፡ ዳግመኛ የሚወለዱት ደግሞ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በመጠመቅ ነው፡፡ ሕፃናት ወንዶች እና ሴቶች ከተወለዱ በኋላ ወንድ ከሆነ በ40 ቀን ሴት ከሆነች 80 ቀን ሲሞላት እናትና አባታቸው አቅፈዋቸው ቅድስትና ንጽሕት ወደ ሆነች ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል፡፡ ከዚያ ሲደርሱ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ቀሳውስትና ዲያቆናቱ ደስ ብሏቸው ሕፃናቱን ተቀብለው ወደ መጠመቂያው ቤት ይዘዋቸው ይገባሉ፡፡

በመጠመቂያው ቤት ቄሶቹ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ ትልቅ መስቀል ይዘው፣ ወንጌሉን ዘርግተው ቅዱሱን ወንጌል ካነበቡ በኋላ ቄሱ በትልቁ መስቀል ሕፃናቱ የሚጠመቁበትን በገንዳ ውስጥ ያለውን ውኃ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተባረከ ይሁን” እያሉ ሲያማትቡበት ውኃው ተለውጦ ጸበል ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ ሕፃናቱን በገንዳው ጸበል ውስጥ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ፣ ብቅ ጥልቅ፣ ብቅ ጥልቅ እያደረጉ “በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠምቅሃለሁ” እያሉ ካህኑ ሲያጠምቋቸው ሕፃናቱ ለሁለተኛ ጊዜ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ይወለዳሉ፡፡

ከጸበሉ ሲወጡ ዲያቆኑ ሕፃናቱን ከፍ አድርጎ ሲይዝ ቄሱ በነጭ፣ በጥቁርና በቀይ ክሮች የተገመደውን ማኅተብ በመስቀል ከባረኩት በኋላ በሕፃኑ አንገት ላይ ያስሩለታል፡፡ መላ ሰውነቱንም ቅባ ሜሬን በተባለው ቅዱስ ቅባት እየቀቡት የልጁን ሰውነት ይባርኩታል፡፡ በመጨረሻም በእናት እና በአባታቸው እቅፍ ሆነው ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡

ይህንንም የተቀደሰ ሥርዓት በመፈጸም ዳግመኛ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባል፡፡ በማለት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያስተምራቸውና ጥያቄውን ለጠየቀው ለኒቆዲሞስ አስተማራቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ እንዳስተማረን ትምህርት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁል ጊዜ ይህን ታላቅና ቅዱስ ሥርዓት ለልጆችዋ እየፈጸመች ዳግመኛ ተወልደን የሥላሴ ልጆች እንድንሆን ታደርገናለች፡፡ ይህም ድንቅ ሥርዓት ለአንድ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም ነው፡፡ ሥርዓቱም ምሥጢረ ጥምቀት በመባል ይጠራል፡፡

ልጆቹ እንድንሆን ዳግመኛ በጥምቀት የወለደን እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን አሜን፡፡

ዳግም ምጽአት(ለሕፃናት)

መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም.

ቤካ ፋንታ

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ፡፡ በእኩለ ጾም /በጾሙ አጋማሽ/ ለምናከብረው ለደብረ ዘይት በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ልጆች ዛሬ የምንማረው ስለ ደብረ ዘይት በዓል ሲሆን ትምህርቱ በዋናነት ስለ ዳግም ምጽዓት ያስረዳል፡፡

 

ዳግም ምጽአት ማለት ለሁለተኛ ጊዜ መምጣት ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት አምላካችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገና ወደ እኛ የሚመጣበትን ቀን ያመለክታል፡፡ ልጆችዬ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማያት ሰማያት ወርዶ ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ለፍጥረታት ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ ታይቷል፡፡ በዳግም ምጽአት ጊዜ ደግሞ ሁሉም ሰዎች እያዩት እንደገና ስለሚመጣ ያቺ ቀን ዳግም ወደ እኛ የሚመጣበት ስለሆነች ዳግም ምጽአት ተባለች፡፡

ከታላቁ የመለከት ድምጽ በኋላ ቅዱሳን መላእክት በሙሉ ከቅዱሳን ሰዎች ጋራ ከእነ ቅዱስ አባታችን አብርሃም፣ ቅዱስ ዳዊት፣ ከቅዱሳን ሐዋርያት፣ ከእነ ቅዱስ ያሬድ፣ ከአባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋራ ሁሉም ቅዱሳን ሆነው እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በመካከል ሆና ፈጣሪያችንን እግዚአብሔርን በመዝሙር እያመሰገኑት ከበሮን እየመቱ፣ መለኮቱን እየነፉ፣ እልል እያሉ ከሰማይ ውስጥ ይመጣሉ፡፡ ያን ጊዜ ሁላችንም አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፊት ለፊት በዓይናችን እንመለከተዋለን፡፡

 

ከዚያ በኋላ አንድ ታላቅ ቅዱስ መልአክ ከምድር ጫፍ እስከ ምድር ጫፍ ድረስ የሚሰማውን የመጨረሻውን የመለከት ድምፅ ሲያሰማ የሞቱት ሰዎች ሁሉ ከተቀበሩበት ይነሣሉ፡፡ ተነሥተውም በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ፡፡ መልካም የሠሩትና እግዚአብሔርን የሚወዱት ሰዎች ነጭ ለብሰው በቀኙ ይቆማሉ፡፡ በምድር ላይ ሲኖሩ ጨካኞችና ክፉ ሥራን በመሥራት የኖሩት ደግሞ ጥቁር ለብሰው በግራ በኩል ይቆማሉ፡፡

 

እግዚአብሔር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በስተቀኝ በኩል ለቆሙት “በምድር ላይ ስትኖሩ እኔን አምናችኋል፡፡ ኀጢአት አልሠራችሁም ልጆቼ ሆይ እኔ እንዳዘዝኳችሁ እናት አባቶቻችሁን አክብራችኋል፣ ለተቸገሩ ሰዎችም የሚበሉትን ምግብ፣ የሚጠጡትን መጠጥ፣ የሚለብሱትንም ልብስ ሰጥታችኋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማረቻችሁ አሥርቱ ትእዛዛትን፣ ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን በመጠበቅ መልካምና ደግ ልጆቼ ስለሆናችሁ ታላቅ ሽልማት እሸልማችኋለሁ፡፡ ሽልማታችሁም መንግሥተ ሰማያት ነች፡፡” በማለት በቀኙ የሚቆሙትን ቅዱሳኑን እና ደጋጋ ክርስቲያኖችን ደስ ያሰኛቸዋል፡፡

 

እግዚአብሔር ለደጋግ ሰዎች ያዘጋጃት መኖሪያ መንግሥተ ሰማያት እጅግ የተዋበች በውስጧም በጣም ባማረና በከበረ እንቁ የተጌጠች ነች፡፡ በዚያች ሰማይ ሁል ጊዜ ብርሃን ያለማቋረጥ ይበራባታል፤ ጨለማም ከቶ የለም፣ የሚያስፈራ ነገር የለም፣ ድካም የለም፣ ራብ የለም በመንግሥተ ሰማያት ዘወትር ደስታ፣ ዝማሬ እልልታ ይሆናል፡፡ መንግሥተ ሰማያት በታላቅ ረጅም ቅጥር የታጠረች ናት፡፡ አሥራ ሁለት በሮች አሏት፡፡ በውስጧ የሚገቡ ሰዎች ክፉ ነገርን የማያደርጉ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የጠበቁ እና ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን ለማመስገን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ በዚያ ሲኖሩ ሁል ጊዜ ደስ እያላቸው እግዚአብሔርን ፊት ለፊት እያዩት ከእርሱ ጋር ይኖራሉ፡፡ በዚያ እጅግ የምንወዳት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሁሉም ቅዱሳን ጋር አለች፡፡

 

በመጨረሻም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግራ በኩል ለቆሙት ሰዎች “በምድር ላይ ስትኖሩ ያዘዝኳችሁን ትእዛዝ አልጠበቃችሁም፣ እናት አባታችሁን አላከበራችሁም፣ የኀጢአትን ሥራ ሠርታችችኋልና ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም፡፡ የእናንተ መኖሪያ ገሃነመ እሳት ነው ከፊቴ ሂዱ፡፡” በማለት ይናገራቸዋል፡፡ እነርሱም ወደ ዘለዓለማዊ እሳት ይጣላሉ፡፡

 

ልጆች ዳግም ምጽአት ምን ማለት እንደሆነ አሁን በደንብ ተረዳችሁ አይደል፡፡ እንግዲህ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ በሚመጣበት ጊዜ በቀኙ እንድንቆምና መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ሁላችንም እግዚአበሔር እንዳዘዘን መልካምና፣ ደግ ሰዎች ልንሆን እና በቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል እየተማርን ልናድግ ይገባል፡፡

 

እግዚአብሔር አምላካችን ዳግም በሚመጣበት ጊዜ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋራ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሰን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

የጸሎት ቤት/ለሕፃናት/

መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

ቤካ ፋንታ

ልጆችዬ እንኳን ለዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ይህ ሦስተኛው ሳምንት ምኲራብ ተብሎ ይጠራል፡፡ ዛሬ የምንማረውም ትምህርት በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ከቁጥር 12 እስከ 17 ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ቤት ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች በአንድነት ተሰብስበው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገሩበት ቤት ስለሆነች የጸሎት ቤት ወይም የእግዚአብሔር ቤት እየተባለች ትጠራለች፡፡

በአንድ ወቅት ምን ሆነ መሰላችሁ፥ ጌታችን መድኀኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ቅዱሳን ሐዋርያትን ይዞ ወደ ምኲራብ መጣ፡፡ በድሮ ጊዜ ምኲራብ ትባል ነበር፤ አሁን ግን ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትጠራለች፡፡ ጌታችንም ወደ ምኲራብ ሲገባ በቤቱ ዙሪያ ብዙ ነጋዴዎች፣ ሻጮች እና ለዋጮች ግቢውን ሞልተው ሲሸጡ ሲነግዱ አያቸው፡፡ አንዳንዱ በሬ ይሸጣል፣ ሌላው በግ፣ ሌላው ዶሮ፣ ሌላው ደግሞ እርግብ…. እየሸጡ የጸሎት ቤት የነበረውን የእግዚአብሔርን ቤት የገበያ ቦታ አደረጉት፡፡ የሰዎቹ ድምጽ፣ የእንስሳቱ ጩኸት ብቻ ምን ልበላችሁ ግቢው በጣም ተረብሿል፡፡ በዛ ላይ አንዳንዶቹ ይጣላሉ፣ ይሰዳደባሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ሆነው ክፉ ነገርን ይነጋገራሉ፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቤት ንቀው የጸሎት ቤት የሆነችውን መቅደስ የገበያ ቦታ እንዳደረጉት ሲመለከት ወዲያው ረጅም ጅራፍ ሠራ፡፡ በጅራፉም እየገረፈ በሬዎቹን በጎቹን ሁሉንም ከግቢ አስወጣቸው፡፡ በታላቅ ቃልም ጮኸ “ቤቴ የጸሎት ቤት ናት፥ እናንተ ግን የንግድ ቤት፣ የወንበዴዎች መደበቂያ አደረጋችሁት” ብሎ በአለንጋ እየገረፈ አባረራቸው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስም ሁሉንም አስወጣ ጸጥታ ሆነ ለተሰበሰቡት ሕዝብ ካሁን በኋላ እንዲህ አታድርጉ፡፡ በእግዚአብሔር ቤት መጸለይ፣ መስገድ፣ መዘመር፣ መማር እንጂ መሸጥ፣ መግዛት፣ መረበሽ፣ መሳደብ፣ መጣላት፣ ክፉ ነገር ማድረግ መጮኸ አይፈቀድም ብሎ አስተማራቸው፡፡ ሕዝቡም አጥፍተናል ይቅርታ አድርግልን ሁለተኛ ይህን ጥፋት አናጠፋም ብለው ቃል ገቡ፡፡

ከዚያም ለተሰበሰቡት የእግዚአብሔር ልጆች ያስተምራቸው ጀመረ፡፡ የሚማሩትም ሰዎች በጣም ደስ ብሎዋቸው ከእግሩ ሥር ቁጭ ብለው ተማሩ፡፡ ዐይናቸው የማያይላቸው ሰዎችም ወደ እርሱ ቀርበው አምላካችን ሆይ እባክህ አድነን ሲሉት፣ እጁን ዘርግቶ ዐይናቸውን ሲነካው ሁሉም ማየት ጀመሩ፡፡ የታመሙ ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፣  ሁሉንም አዳናቸው፡፡

ልጆችዬ በእግዚአብሔር ቤት በቤተ ክርስቲያን ስንገባና ስንወጣ ተጠንቅቀን መሆን እንዳለብን አስተዋላችሁ አይደል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቤት የተቀደሰና፣ ሁሌም መላእክት እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት የተባረከች ንጽህት ሥፍራ ስለሆነች ነው፡፡  ልጆችዬ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባም ሆነ ስንወጣ ተጠንቅቀን ሌሎችን ሳንረብሽ፣ ሳንሮጥ፣ ሳንጮኸ መሆን አለበት፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤትም ከወንድሞቻችንና ከእኅቶቻችን ጋራ ስለ እግዚአብሔር እየተነጋገርን፣ እየተማማርን ልናሳልፍ ይገባናል፡፡

እግዚብሔር አምላካችን በቅድስናና በንጽሕና በቤተ ክርስቲያን እንድንኖር ይርዳን አሜን፡፡

ታላቁ ጾም(ለሕፃናት)

መጋቢት 11 ቀን 2005 ዓ.ም.


ቤካ ፋንታ

ልጆች እንኳን ለጌታችን ጾመ ሁዳዴ በሰላም አደረሳችሁ? ልጆች ዛሬ ስለ ጾም እንማራለን፡፡

ልጆችዬ በዚህ ወቅት የምንጾመው ጾም ብዙ ስሞች አሉት፡፡ እነርሱም፡- ዐቢይ ጾም ሁዳዴ የጌታ ጾምም ይባላል፡፡ የምንጾመውም ለሃምሳ አምስት ቀናት ያህል ነው፡፡

ይህንን ጾም እንድንጾም ያስተማረን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቆሮንቶስ ወደ ሚባል ትልቅ ገዳም ደረሰና ምግብ ሳይበላ፣ ውኃ ሳይጠጣ፣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ፡፡ ልጆችዬ ጾም ማለት ውኃ ሳንጠጣ፣ ምግብ ሳንበላ እስከ ዘጠኝ ሰዓት መቆየት ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ሥጋ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ እንቁላል…. የመሳሰሉ ምግቦችን የጾሙ ቀናት እስኪያልቅ ድረስ አይበላም፡፡

ጌታችን በገዳም ውስጥ ሆኖ ለአርባ ቀናት ሲጾም ከእርሱ ጋር ማንም አልነበረም፡፡ ረሀቡን ችሎ፣ ውኃ ጥሙን ችሎ ከጾመ በኋላ ጠላታችን ሰይጣን ሊፈትነው ወደ አምላካችን መጣ፡፡

 

ወደ አምላካችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦ በምግብ ሲፈትነው ፈጣሪያችን ክርስቶስ ድል አደረገው፡፡ ከዚያ ለሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ለምን ፈተነው? ሲፈትነው ትእቢተኛነት ጥሩ እንዳልሆነ ነግሮት እንደገና አሸነፈው፡፡ በመጨረሻም ሰይጣን በዓለም ውስጥ ያለውን ገንዘብ፣ ወርቅ፣ ጌጣጌጥ ሁሉ እያሳየው “እኔን ብታመልከኝ ለእኔም ብትሰግድልኝ የምታየውን ሁሉ ወርቁን፣ አልማዙን፣ ብሩን… እሰጥሃለሁ” አለው፡፡ ጌታችንም ሰይጣንን እንዲህ አለው “ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለእግዚአብሔር ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል” ብሎ ሦስት ጊዜ አሸነፈው፡፡ ከዚያ ሰይጣን ተሸንፎ ሄደ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሞ ሰይጣንን ስላሸነፈ እኛም በየዓመቱ ሰይጣን እንዳያሸንፈን እንጾማለን፡፡

ልጆችዬ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ምን ተማራችሁ? እኔ የተማርኩትን ልንገራችሁና እናንተ ደግሞ የተማራችሁትን ትነግሩኛላችሁ፡፡

  1. ጾምን በአግባቡ መጾም እንዳለብኝ ተምሬአለሁ፡፡

  2. ወደ ቅዱሳት ገዳማት በመሄድ በዚያ መጸለይ፣ መጾም፣ እግዚአብሔርን ማመስገን እንደሚገባኝ ተምሬአለሁ፡፡

  3. ከጾምኩኝና ክፉ ነገር ካላደረኩኝ ሰይጣንን ማሸነፍ እንደምችል እግዚአብሔር አስተምሮኛል፡፡

ልጆችዬ መልካም የጾም ጊዜ ይሁንላችሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ከጾሙ በረከትን ያድለን አሜን፡፡

ነቢዩ ዮናስ (ክፍል ሁለት) /ለሕፃናት/

የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም.

በወልደ ኢየሱስ /ቤካ ፋንታ/


እግዚአብሔር በጣም የሚወዳችሁ እናንተም እግዚአብሔርን በጣም የምትወዱት ሕፃናት እንደምን ሰነበታችሁልን?

 

ልጆችዬ ባለፈው በክፍል አንድ ጽሑፍ ስለ ደጉ ልጅ ስለ ዮናስ የተማርነውን ታስታውሳላችሁ? ዮናስ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ምክንያት በባሕር ላይ የሚሄድባት መርከብ ከባድ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ዮናስን ወደ ባሕር ውስጥ ሲጥሉት ንፋሱ ቆመ፡፡ መርከቧም በሰላም መሄድ ቻለች፡፡ ዮናስ ግን ወደ ስምጡ ባሕር እንደገባ አይተን ነበረ ያቆምነው፡፡ ዛሬ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡

 

በመጀመሪያ ግን አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፡-

  • ትልቁ በጣም ትልቁ በባሕር ውስጥ ከሚኖሩት ዓሣዎች ሁሉ የሚበልጠው ትልቁ ዓሣ ስሙ ምን ይባላል?

 

ደጉ ዮናስ የመርከቧ ሠራተኞች ከመርከቧ ላይ ወርውረው ወደ ሰፊው ባሕር ሲጥሉት ውኃው ውስጥ ሰመጠ፡፡ ከዚያ ወደ ስምጡ ባሕር ሲገባ በውኃ ስለተከበበ ዮናስ መተንፈስ አቃተው እግዚአብሔርም ለዮናስ አዘነለት እንዳይሞትም አስቦለት በባሕር ውስጥ ካሉት ዓሣዎች ሁሉ በጣም ትልቁን ዓሣ ላከለት፡፡ ትልቁ ዓሣ ስሙ ዓሣ አንበሪ ይባላል፡፡ እግዚአብሔርም ዓሣውን እንዲህ ብሎ አዘዘው “የምወደው ደጉ ዮናስ ውኃው እንዳያፍነውና እንዳይሞት ሂድና ዋጠው፡፡ በሆድህ ውስጥም ለሦስት ቀን እና ለሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡” ሲለው ዓሣ አንብሪው ካለበት ቦታ ፈጥኖ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወዶ ዮናስ ደረሰና ዋጠው፡፡ ከዚያ ወደ ስምጡ ባሕር ውስጥ እየዋኘ ሄደ፡፡

 

ልጆችዬ የሚገርማችሁ ነገር ትልቁ ዓሣ ዮናስን ሲውጠው ዮናስ አልሞተም፡፡ በዓሣው አፍ ገብቶ፣ በጉሮሮው አልፎ መጨረሻ ላይ ሆዱ ውስጥ ሲደርስ ዮናስ ደነገጠ፡፡ ወዲያውም ቆሞ ሲመለከት ያለው ትልቁ ዓሣ ሆድ ውስጥ ነው፡፡ በሆድ ውስጥ ሆኖ መተንፈስ ይችላል፣ ማየት ይችላል፣ መቆም ይችላል፣ መናገርም ይችላል፡፡

 

ዮናስ እግዚአብሔር ዓሣ አንበሪውን ልኮት ከሞት እንዳዳነው ሲያውቅ በዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ሆኖ በጉልበቱ ተንበረከከና አንገቱን ቀና አድርጎ ወደ ላይ ወደ ሰማይ እያየ “እግዚአብሔር ሆይ ስለምንህ ጸሎቴን ሰምተህ ከሞት ስላዳንከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ በዚህ በዓሣ ውስጥም የዓሣው ጨጓራ እንዳይፈጨኝ ስለጠበቅኸኝ አመሰግንሃለሁ….” እያለ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ሙሉ ሳያቋርጥ ደስ ብሎት እግዚአብሔርን ሲያመሰግነው፣ እያጨበጨበ መዝሙር ሲዘምር እግዚአብሔር የዮናስን ጸሎት ሰማ፡፡ እግዚአብሔርም ዓሣውን “ልጄ ዮናስን ወደ ደረቅ መሬት ሄደህ ትፋው” ብሎ አዘዘው፡፡ ዓሣውም ዮናስን በባሕርl ዳር አጠገብ ወዳለች ነነዌ ወደምትባል ሀገር ተፋው፡፡

 

ዮናስ ከዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ሲወጣ ቶሎ ብሎ የሄደው እግዚአብሔር ወደ ላከው ሀገር ወደ ነነዌ ነው፡፡ ዮናስ ከባሕሩ ሲወጣ አንድ ነገርን ተምሮዋል፤ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ብዚ ችግር እንደሚያመጣ አውቆዋል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ወደ ላከው ነነዌ ወደምትባል ሀገር ሄደ፡፡ የነነዌ ሕዝብ ሆይ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎዋችኋል፡- ክፉ ሥራ መሥራት ትታችሁ ጥሩ ሥራ እኔ እግዚአብሔር የምወደውን መልካም ሥራ ካልሠራችሁ እቆጣችኋለሁ፡፡ ክፉ ሥራ መሥራት ካልተዋችሁ የምትኖሩበትን ከተማ እሳት ከሰማይ አውርጄ አቃጥላታለሁ፡፡” እያለ እየዞረ ለሕዝቡ ሁሉ ነገራቸው፡፡

 

የነነዌ ሕዝቦች የነቢዩ ዮናስን ቃል ሲሰሙ በጣም ደነገጡ፡፡ እግዚአብሔርም ከተማቸውን እንዳያጠፋባቸው እነርሱንም ይቅር እንዲላቸው ሁሉም ተሰበሰቡና ተማከሩ “እግዚአብሔር በክፉ ሥራችን ምክንያት ተቆጥቶ ሀገራችንን እንዳያጠፋ እንጹም፤ እግዚአብሔር እኮ እየጾምን ከለመንነው ይቅር ይለናል፡፡ ስለዚህ ከአሁን ሰዓት ጀምረን ሁላችንም ምግብ ሳንበላ ውኃ ሳንጠጣ ክፉ ሥራ መሥራት ትተን በጾም ለሦስት ቀን እግዚአብሔርን እንለምነው፡፡” ተባባሉና ሕፃናትም፣ ወጣቶችም፣ እናቶችም፣ አባቶችም፣ እንስሳቶችም ሁሉም “እግዚአብሔር ሆይ ይቅር በለን፣ ከአሁን በኋላ ክፉ ሥራ አንሠራም፣ ጥሩ ሥራ እየሠራን አንተ ያዘዝከንን እንፈጽማለን፡፡” እያሉ ለሦስት ቀን ውኃ ሳይጠጡ፣ ምግብ ሳይበሉ በጾም እግዚአብሔርን ለመኑት፡፡

 

እግዚአብሔርም ወደ ነነዌ ሕዝብ ሲመለከት ሁሉም እየጾሙ አየ፡፡ ሁሉም “ይቅር በለን” ይላሉ፡ የነነዌ ሕዝቦች ክፉ ሥራ መሥራት ትተው እየጾሙ እየጸለዩ ሲለምኑት እግዚአብሔር ከሰማይ ከተማዋን ሊያጠፋ እየፈጠነ የሚወርደውን እሳት እሳት እንዳይወርድባቸው ከለከለው እየወረደ የነበረውም እሳት ጠፋ፡፡

 

ልጆችዬ እግዚአብሔር የሚጾም ልጅን በጣም ነው የሚወደው፡፡ እግዚአብሔርን እየጾምን እየጸለይን ከለመነው በእኛ ላይ ክፉ ነገር አይመጣብንም፣ ቤተሰቦቻችንንም እግዚአብሔር ይጠብቅልናል፡፡ ጾመ ነነዌ የሚባለውን ለሦስት ቀን የሚጾመውን ጾም በሚመጣው ሰኞ ጀምረን እስከ ዕረቡ ለሦስት ቀን እንጾመዋለን፡፡ ታዲያ ልጆች ስንጾም ሳንዋሽ፣ ሳንሳደብ ክፉ ሥራ ሳንሠራ፣ ለእግዚአብሔርም ለቤተሰቦቻችንም እየታዘዝን መጾም ይኖርብናል፡፡ መልካም የጾም ቀናት ይሁንላችሁ፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ከነቢዩ ዮናስ በረከትን ያድለን፡፡ አሜን፡፡

ነቢዩ ዮናስ (ክፍል አንድ) /ለሕፃናት/

የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቤካ ፋንታ /ወልደ ኢየሱስ/

 

ልጆችዬ እንደምን ሰነበታችሁልኝ? እግዚአብሔር ይመስገን አላችሁኝ? ጎበዞች፡፡ ዛሬ ይዤላችሁ የመጣሁት በጣም ደስ የሚል ታሪክ ነው፡፡ ስለዚህ በደንብ ተከታተሉኝ እሺ፡፡

 

በድሮ ጊዜ ነው፣ በጣም በጣም በድሮ ጊዜ አንድ እግዚአብሔርን በጣም የሚወድ ልጅ ነበረ፡፡ ስሙ ዮናስ ይባላል፡፡ ታዲያ ዮናስ ደግ፣ የዋህ፣ ለሰዎች ሁሉ ታዛዥ እና ክፉ ነገርን የማያደርግ ነው፡፡ በዚህ ጥሩ ጸባዩ የተነሣ እግዚአብሔር ዮናስን በጣም ይወደዋል፣ ስሙንም ጠርቶ ያናግረዋል፡፡

 

አንድ ቀን እግዚአብሔር ዮናስን እንዲህ ብሎ አዘዘው፡- “ወዳጄ ዮናስ ሆይ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ተነሥና ሂድ፡፡ ለነነዌ ሕዝብም እንዲህ በላቸው፡- ክፉ ሥራ መሥራት ትታችሁ ጥሩ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካም ሥራ ካልሠራችሁ እግዚአብሔር ይቆጣችኋል፣ ከክፉ ሥራችሁ ካልተመሳችሁ ከተማችሁን ያጠፋባችኋል፡፡” ብለህ ተናገር ብሎ አዘዘው፡፡ ዮናስ ግን እግዚአብሔር ወደ ላከው ወደ ነነዌ መሄድ ትቶ ወደ ሌላ ሀገር ተርሴስ ወደምትባል ሀገር ሊሄድ ወደ ባሕር ዳርቻ ሄደና በመርከብ ላይ ተሳፈረ /ወጣ/፡፡ ከዚያም መርከብ ውስጥ ሆኖ በባሕሩ ላይ መጓዝ ጀመረ፡፡ ግን የሚሄደው እግዚአብሔር ወደ ላከው ሀገር ሳይሆን ወደ ሌላ ሀገር ነበረ፡፡

 

እግዚአብሔርም ዮናስ እንዳልታዘዘው ባየ ጊዜ ነፋሱን አዘዘው፡፡ ነፋሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ባሕሩን በጣም ያነቃንቀው ያወዛውዘው ጀመረ ከዚያ ከባድ ማዕበል ሆነ፡፡ የባሕሩም ውኃ መርከቧን ሊያሰጥማት አወዛወዛት፡፡ አንዴ ወደ ቀኝ አንዴ ወደ ግራ ልትወድቅ፣ ልትገለበጥ መርከቧ ተወዛወዘች፡፡ ያን ጊዜ በውስጧ ያሉ የመርከቧ ሠራተኞች መርከቧ እንዳትገለበጥና እንዳይሞቱ በጣም ቢደክሙም ነፋሱ ግን ውኃውን እያነሳ መርከቧ ላይ ይጥልባቸዋል፡፡

 

ልጆችዬ በጣም የሚገርማችሁ ነገር ግን ይህ ሁሉ ነፋስ ሲነፍስ መርከቧም ወዲህና ወዲያ ስትወዛወዝ ዮናስ በመርከቧ ውስጥ ሆኖ አልሰማም ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ? በመርከቧ ውስጠኛ ክፍል ገብቶ ኀይለኛ እንቅልፍ ተኝቶ ስለነበረ ነው፡፡ የመርከቧ ሠራተኞ ወደ ዮናስ መጣና ኧረ መርከባችን በባሕር ውስጥ ልትሰጥምብን ነው፣ ኧረ ልንገለበጥ ነው፤ ከተኛህበት ንቃ ብሎ ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው፡፡ ዮናስ ተነሥቶ ሲያይ ነፋሱ በጣም ይጮኻል፣ የባሕሩም ውኃ መርከቧን ሊገለብጣት ወደ ላይ እየተነሣ መርከቧን ይመታታል፡፡ የመርከቡ ሠራተኞችም ሁሉም በጣም ተደናግጠውና ፈርተዋል፡፡ ነፋሱን እንዲያቆምላቸውና በሰላም እንዲሄዱ ሁሉም እግዚአብሔርን “አድነን፣ ነፋሱን አቁምልን፣ በሰላም አገራችን አድርሰን፡፡” እያሉ መጸለይ ጀመሩ፡፡

 

ዮናስም ይሄ ሁሉ ችግር የመጣው እርሱ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙና ሂድ ወደ ተባለበት አገር ባለመሄዱ ምክንያት የመጣ እንደሆነ አወቀ፡፡ እግዚአብሔርም በዮናስ ተቆጥቶ እንዲህ ማድረጉን በተረዳ ጊዜ የመርከቧን ሠራተኞች “ይሄ ሁሉ ችግር የደረሰባችሁ በእኔ ጥፋት ስለሆነ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣሉኝ፡፡ ከዚያ ነፋሱ ይቆምላችሁና በባሕር ውስጥ ከመገልበጥ እና ከመሞት ትድናላችሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ባሕሩ ውስጥ እኔን ጣሉኝ፡፡” አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የመርከቧ ሠራተኞች ዮናስን ወደ ባሕር ውስጥ ወረወሩት፡፡ ወዲያውኑ የሚነፍሰው ኀይለኛ ነፋስ ቆመ፡፡ መርከቧም በሰላም ተጓዘች፡፡

 

ደጉና የዋሁ ዮናስ ወደ ሰፊው ባሕር ውስጥ ተጣለ፡፡ ወደ ባሕሩ ጥልቅ ውስጥም ገባ፡፡ በዙሪያውም በውኃ ተከበበ፡፡ ልጆችዬ ውኃ ውስጥ ደግሞ የሰው ልጆች መተንፈስ አንችልም፣ ማንም ሰው ደግሞ መተንፈስ ካልቻለ ይሞታል፡፡ ዮናስ ግን ጥልቁ ባሕር ውስጥ ተጥሎም አልሞተም፡፡ ዮናስ ለምን እንዳልሞተ፣ በባሕር ውስጥ ሲገባ ምን እንዳገኘው በሚቀጥለው ክፍል ይዤላችሁ እመጣለሁ፡፡

 

አሁን ከመሰናበቴ በፊት ሦስት ጥያቄ እጠይቃችኂለሁ፡-

  1. እግዚአብሔር ዮናስን በጣም የሚወደውና የሚያነጋግረው ዮናስ ምን ዓይነት ጸባይ ስላለው ነው?

  2. ዮናስ የተሳፈረባት መርከብ በነፋስ ብዙ ችግር የደረሰባት በማን ስህተት ነው?

  3. እግዚአብሔር ዮናስን የላከው ምን ወደ ተባለ ሀገር ነው?

ይቀጥላል

የጥምቀት በዓል በዮርዳኖስ ወንዝ /ለሕፃናት/

ጥር 9 ቀን 2005 ዓ.ም.
ከወልደ ኢየሱስ /ቤካ ፋንታ/

 

ልጆችዬ እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ! ዛሬ ስለ ታላቁ በዓል ስለ ጥምቀት ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፡፡ በደንብ ተከታተሉኝ እሺ፡፡

 

በገዳም ውስጥ ለሠላሳ ዓመት ለብቻው ሆኖ እግዚአብሔርን እያመሰገነ የሚኖር የእግዚአብሔር አገልጋይ ነበር፡፡ ስሙም ቅዱስ ዮሐንስ ይባላል፡፡ ልጆችዬ የቅዱስ ዮሐንስ ልብስ ምንድር መሰላችሁ የግመል ቆዳ ነበረ፣ የሚበላው ደግሞ በበረሃ የሚገኝ ማር ነው፡፡ በገዳም ሲኖር ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን በደስታ እየዘመረ ያመሰግነው ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ከሚኖርበት ገዳም ተነሥቶ ዮርዳኖስ ወደሚባል ወንዝ እያስተማረ መጣ፡፡ ትምህርቱም “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ፡፡” የሚል ነው፡፡ ያን ጊዜ ይህንን ትምህርት የሰሙ በጣም ብዙ ሕፃናት፣ ወጣቶች እና ትልልቅ ሰዎች ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ተሰብስበው መጡና ያጠፉትን ጥፋት፣ የበደሉትን በደል፣ የሠሩትን ኃጢአት ሁሉ እየነገሩት /እየተናዘዙ/ በጸበል አጥምቀን አሉት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የዮርዳኖስን ወንዝ በእግዚአብሔር ስም ሲባርከው ጸበል ሆነ፡፡ ከዚያም የተሰበሰቡትን ሁሉ ወንዶችን ሴቶችን እና ሕፃናትን በጸበሉ አጠመቃቸው፡፡

 

ልጆችዬ ከዚያም ምን ሆነ መሰላችሁ? ፈጣሪያችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሊጠመቅ መጣ፡፡ አጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስም ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያየው ፈጣሪዬ ሆይ አጥምቀኝ አለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አይሆንም አንተ አጥምቀኝ ብሎት በጥር 11 በቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ ስለዚህም አምላካችን በዚህች ቀን ስለተጠመቀ ዛሬ የምናከብረው የጥምቀት በዓላችን የተባረከ ሆነ፡፡

 

ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከውኃ ሲወጣ  በጣም የሚያስደንቅ ተአምር ታየ፡፡ ሰማያት ተከፈቱ፤ ከሰማዩ ውስጥም መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ ተመስሎ መጣና በጌታችንነ በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በራሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ ከዚያም አንድ ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ውስጥ ተሰማ፡፡ እንዲህ የሚል “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡”

 

ልጆችዬ ዛሬም እኛ ክርስቲያኖች ከጥር ዐሥር ጀምረን ነጭ የሀገር ልብስ ለብሰን ቅዱሱን ታቦት አጅበን እየዘመርን፣ እልል እያልን የምንዘምረውና በጸበል የምንጠመቀው በመስቀልም በአባቶቻችን ካህናት የምንባረከው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡

 

አገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ በሁሉም ቤተ ክርስቲያን ያሉት ታቦታት ጥር አሥር ቀን ከየቤተ ክርስቲያኑ ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር /ጸበሉ ቦታ/ ሄደው እየተዘመረ፣ እየተጸለየ በምስጋና ይታደራል፡፡ በነጋታው ጥር 11 በጠዋት ውኃው ተባርኮ ጸበል ይሆናል፡፡ በሥፍራው የተሰበሰቡትን ክርስቲያኖች ሁሉንም በጸበሉ እየረጩ ያጠምቋቸዋል፡፡ በመጨረሻም የእግዚአብሔር ማደሪያ ቅዱስ ታቦቱ በካህናቱ ዝማሬ በምእመናን እልልታ ታጅቦ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመለሳል፡፡

አሁን ደግሞ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡-

  1. ቅዱስ ዮሐንስ የሚኖረው በየት ነበር?

  2. ጌታችን መድኃኒጻችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው የት ነው?

  3. ኢየሱስ ክርስቶስን ያጠመቀው ማን ነው?

  4. ቅዱስ ዮሐንስ ያጠመቃቸው  ወገኖች እነማን ናቸው?

ልጆችዬ ከመሰናበቴ በፊት ለዛሬ የምታነቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ልንገራችሁ፡፡ ይኸውም የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት ነው፡፡ ስለተከታተላችሁኝ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ታሳድግልኝ፡፡ መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንላችሁ፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
christmas 1

የሕፃኑ የኢየሱስ ልደት /ለሕፃናት/

ታኅሣሥ 26 ቀን 2005 ዓ.ም.

ከወልደ ኢየሱስ /ቤካ ፋንታ/

  • “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች” ማቴ.1፥23

 

ልጆችዬ እንደምን ሰነበታችሁ? ዛሬ ስለ ታላቁ ሕፃን ልደት የምነግራችሁ ነገር አለና በማስተዋል ተከታተሉኝ እሺ፡፡ ጎበዞች!

christmas 1

የዛሬ ሁለት ሺ ዓመት ገደማ ነው፡፡ በኢየሩሳሌም ሀገር ንጉሡ ሄሮድስ ሕዝቡን ሁሉ ቤተልሄም ወደምትባል ከተማ ጠራቸው፡፡ እመቤታችንም በዚያ ጊዜ የአሥራ አምስት/15/ ዓመት ልጅ ሆኖ በሚጠብቃት በአረጋዊው /በሽማግሌው/ ዮሴፍ ቤት ትኖር ነበር፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ፀንሳ ልትወልድ ደርሳ ሳለ ወደ ቤተልሄም ከተማ ከአረጋዊው ጠባቂዋ ዮሴፍና ከቅድስት ሰሎሜ ጋር ሄደች፡፡

 

በዚያ ሲደርሱ ምን ሆነ መሰላችሁ? እናታችን ማርያም ቅድስት ሰሎሜና አረጋዊው ዮሴፍ ማደሪያ ፈልገው በየቤቱ እየሄዱ “የእግዚአብሔር እንግዶች ነን ማደሪያ ስጡን፣ እባካችሁ አሳድሩን…” ብለው ቢጠይቋቸው ሁሉም “ቦታ የለንም፣ አናሳድርም፣ አናስገባም ሂዱ፡፡” እያሉ መለሷቸው፡፡ በጣም መሽቶ ስለነበረ ጨለማው ያስፈራ ነበረ፣ ብርዱ ደግሞ በጣም ከባድ ነበረ፡፡ ማደሪያ አጥተው የት እንሂድ እያሉ ሲያስቡ በድንገት አረጋዊ ዮሴፍ “ኑ ተከተሉኝ” ብሎ በመንደሩ ውስጥ ወዳለ አንድ የከብቶች ማደሪያ ቤት ወሰዳቸው፡፡

 

ከከብቶቹ ቤት ሲደርሱ በዚያ አህዮች፣ በሬዎች፣ በጎች፣…. ብዙ እንስሳት ተኝተው አገኙዋቸው፡፡ የበረቱ ሽታ በጣም ያስቸግር ነበረ፡፡ ነገር ግን ማደሪያ ስላልነበረ በዚያ ሊያድሩ ተስማሙ፡፡

 

ወደ በረቱ ሲገቡ እንስሶቹ ከተኙበት ተነሥተው በደስታ እየዘለሉ ተቀበሏቸው፡፡ በዚያም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችው፡፡ ይህም ታላቅ ሕፃን የሁላችንም አምላክ ነው፡፡ ወዲያውኑ የከብቶቹ ቤት በታላቅ ብርሃን ተሞላ፡፡ ቅዱሳን መላእክት ተገለጡ፤ በእመቤታችንም ፊት ሆነው በደስታ ከበሮ እየመቱ፣ እያጨበጨቡ መዘመር ጀመሩ፡፡ መዝሙሩም እንዲህ የሚል ነበር፡-

 

“ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና በሰማያት ይሁን፣ በምድርም ሰላም ለሰውም በጎ ፈቃድ”


ልጆችዬ አሁን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ ነው፡፡ ተዘጋጃችሁ? መልካም፡-

  • የገናን በዓል እንዴት ነው የምታከብሩት? ለሕፃኑ ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት መዝሙር እየዘመርን ነው አላችሁኝ? ጎበዞች! የገናን በዓል ከወላጆቻችሁ ጋር በቤተ ክርስቲያን ተገኝታችሁ እንደ ቅዱሳን መላእክት በደስታ መዝሙር በመዘመር አክብሩት እሺ፡፡

መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ፡፡

የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ /ለሕፃናት/

ኅዳር 7 ቀን 2005 ዓ.ም.

በኪዳነማርያም


አባታችን አብርሃም እግዚአብሔርን በማያውቁ፣ ጣዖት በሚያመልኩ መንደር ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ አባቱ ጣዖት እየቀረጸ የሚሸጥ ነበር፡፡ አንድ ቀን አባቱ ሸጠህ ና! ያለውን ጣዖት ከረሀቡ ያስታግሰው ዘንድ አብላኝ ብሎ ቢጠይቀው አልሰማህ አለው፡፡ የጠየቀውን አልመልስልህ ሲለው ሰባብሮ ጣለው፡፡ ወደ ሰማይ አንጋጦ ጨረቃን ጠየቃት አልመለሰችም፣ ፀሐይን ጠየቀ አልመለሰችም፡፡ ተስፋው ሲሟጠጥ አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ (የፀሐይ አምላክ አናገረኝ) አለ፡፡ እግዚአብሔርም ሰማው ከዘመዶችህ ተለይተህ እኔ ወደ ማሳይህ ስፍራ ውጣ አለው፡፡ አባታችን አብርሃምም እንደታዘዘው በመፈጸሙ እግዚአብሔር ቃልኪዳን ገባለት፡፡ ዘርህን እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለሁ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ አለው፡፡ አብርሃምም ከሣራ ይስሐቅን ወለደ፣ ይስሐቅም ታዛዥ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን አንድያ ልጅህን ሠዋልኝ ባለው ጊዜ አብርሃም ታዘዘ፡፡ ልጁ ይስሐቅም አባቱን ታዘዘ፡፡ አምላክህን ከምታሳዝነው እኔንም ዓይን ዓይኔን እያየህ ከምትራራ በጀርባዬ ሠዋኝ ብሎ አባቱን አበረታው፡፡ እግዚአብሔርም የአብርሃምን እምነት የልጁን ታዛዥነት ዓይቶ በይስሐቅ ፋንታ ነጭ በግ በዕፀ ሳቤቅ አዘጋጅቶ እንዲሠዋ አደረገ፡፡ የበጉም ምሳሌ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

 

ይስሐቅም ለእግዚአብሔር ታማኝ ነበር ካደገ በኋላ ርብቃን አግብቶ መንታ ልጆችን ወለደ፡፡ የልጆቹ ስም ዔሳው እና ያዕቆብ ይባላሉ፡፡ እነዚህ ልጆች ገና በእናታቸው ማኅፀን እያሉ ይገፋፉ ነበር፡፡ ነገር ግን የበኩር (የመጀመሪያ) ልጅ ሆኖ የተወለደው ኤሳው ነበር፡፡ በሀገራቸው ልማድ የበኩር ልጅ መሆን የአባትን በረከት ምርቃት የሚያሰጥ ነበር፡፡ እነዚህ ልጆች ካደጉ በኋላ ዝንባሌአቸው የተለያየ ነበር፡፡ ዔሳው አደን የሚወድ ያዕቆብም በቤት ውስጥ እናቱን የሚላላክ ሆነው አደጉ፡፡ አንድ ቀን ኤሳው ከአደን ሲመለስ ምንም አልቀናውም ነበር፡፡ በጣም ተርቦ ወንድሙ ያዕቆብን ከሠራኸው የምስር ወጥ አብላኝ አለው፡፡ ያዕቆብም ብኩርናህን ስጠኝና ከሠራሁት አበላሀለው ብሎ ነፈገው፡፡ ዔሳውም ብኲርናዬ ረኀቤን ካላስታገሰችልኝ ለችግሬ ካልሆነችኝ ለኔ ምኔ ናት ብሎ አቃለላት፣ በምስር ወጥ ሸጣት፡፡ አባታቸው ይስሐቅ ስላረጀ ምርቃቱን፣ በረከቱን ሊያስተላልፍ የበኩር ልጁ ዔሳውን ጠርቶ እነሆ እኔ አረጀሁ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም፤ ሳልሞት ነፍሴ እንድትባርክህ የምወደውን ምግብ ሠርተህ አብላኝ አለው፡፡ ይህን ሁሉ እናታቸው ርብቃ ተደብቃ ትሰማ ነበር፡፡  አብልጣ የምትወደው ያዕቆብን ነበርና የአባቱ ምርቃት እንዳያመልጠው የሰማችውን ሁሉ ነገረችው፡፡ አባትህ የሚወደውን ምግብ እኔ አዘጋጅልሀለው አለችው፤ አባቱ እርሱ ዔሳው እንዳልሆነ ቢያውቅበት በበረከት ፈንታ መርገም እንዳይደርስበት ያዕቆብ ፈራ፡፡ አባታችሁ በእርጅና ምክንያት ዓይኑ ስለተያዘ አንተንም በመዳበስ እንዳይለይህ እንደወንድምህ ሰውነት ጠጉራም እንድትመስል በበግ ለምድ ሸፍኜ መልካሙን የዔሳው ልብስ አለብስሀለው መርገሙም በእኔ ላይ ይሁን ብላ መከረችው፣  አደፋፈረችው፡፡ ያዕቆብ እናቱ ያዘጋጀችውን ምግብ ይዞ ገባ አባዬ ያልከኝን አዘጋጅቻለሁ፤ ብላ ነፍስህም ትባርከኝ አለው፡፡ አባቱም አንተ ማነህ? ብሎ ጠየቀ፡፡ እኔ የበኩር ልጅህ ዔሳው ነኝ ብሎ ዋሸ፡፡ እንዴት ፈጥነህ አገኘህ? አለው፡፡እርሱም እግዚአብሔር አምላክህ ወደ እኔ ስላቀረበው ነው፤ አለው፡፡

 

እጁንም ዳሰሰና ድምፅህ የያዕቆብን ጠረንህ ደግሞ የዔሳውን ይመስላል ብሎ ልጁ ያዕቆብ ካቀረበለት መአድ ተመግቦ ሲጨርስ የልጁን ጠረን አሸተተ፣ እግዚአብሔር ፈቅዷልና  “እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠል ከምድርም ስብ የእህልንም የወይንንም ብዛት ይስጥኽ፤ አሕዛብ ይገዙልህ ሕዝብም ይስገዱልህ፤ ለወንድሞችህ ጌታ ኹን የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን፡፡” ብሎባረከው፡፡ ዔሳው ከአደን ደክሞ ውሎ ለአባቱ የሚሆን ምግብ አዘጋጅቶ አባዬ ያልከኝን አዘጋጅቻለሁ፤ ብላ ነፍስህም ትባርከኝ ብሎ አገባለት፡፡ አባቱም አንተ ማነህ? አለው፡፡ እኔ የበኩር ልጅህ ዔሳው ነኝ አለ፡፡ አባቱም አሁን በረከቱን የወሰደው ዔሳው አይደለምን? ወይስ ምርቃትህን ታናሽህ ያዕቆብ አታሎ ወሰደብህ? አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ዔሳው በኀይል ጮኸ! መጀመሪያ ብኩርናዬን ቀጥሎ በረከቴን አታሎ ወሰደብኝ እያለ በጣም አዘነ፡፡ አባቱንም እንዲህ ብሎ ጠየቀው በረከትህ አንዲት ብቻ ናት? አባቱ ይሥሐቅም “እንሆ መኖሪያኽ ከምድር ስብ ከላይ ከሚገኝ ከሰማይም ጠል ይሆናል፤ በሰይፍህም ትኖራለህ ለወንድምህም ትገዛለህ፤  ነገር ግን በተቃወምኸው ጊዜ ቀንበሩን ከአንገትህ ትጥላለኽ።” አለው ዔሳውም ለእርሱ የተረፈችውን በረከት ተቀበለ፡፡ በያዕቆብም ቂም ይዞ በልቡ “ለአባቴ የልቅሶ ቀን ቀርቧል፣ ከዚያም በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ!” አለ፡፡  ዔሳው የያዕቆብን ሕይወት ለማጥፋት እንደተነሳሳ እናታቸው ርብቃ በማወቋ ያዕቆብን ካደገበት ከኖረበት ቤት ወደ ካራን ምድር ወደ አጎቱ ላባ እንዲሰደድ መክራ ሸኘችው፡፡

 

በመጽሐፍ ቅዱስ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንደምናነበው ያዕቆብም በእርጅናው ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ልጆቹ አብልጦ ይወደው የነበረውን ዮሴፍን ወንድሞቹ ሸጠውት ሳለ ነገር ግን ክፉ አውሬ በልቶታል ብለው ዋሹት፤ በዚህም ምክንያት ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ፡፡ ነገር ግን ዮሴፍ በተሰደደበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር አብሮት ነበርና ኋላ ላይ ቤተሰቡ በረሀብ ምክንያት ተሰደው ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ ለቤተሰቡ መልካም አድርጓል፡፡

 

ልጆች ከዚህ ሁሉ የምንማረው፡-

  1. ለቤተሰቦቻችን በመታዘዛችን የበለጠ እንደሚወዱን፤

  2. እናትና አባትን ማክበር እንዳለብን፤

  3. የእግዚአብሔርን በረከት ለማግኘት መጣር እንዳለብን፤

  4. የተሰጠንን ብኩርና(ሃይማኖት) ማቃለል መናቅ እንደሌለብን፤

  5. መዋሸት የሚያመጣብን መከራ ሥጋ መከራ ነፍስ እንዳለ፤

  6. እግዚአብሔር የገባውን ቃል ኪዳን እንደማያጥፍ እንደማያስቀርብን፤

  7. እግዚአብሔር የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ ተብሎ እንዲጠራ አላፈረባቸውምና በእነዚህ ደጋግ ቅዱሳን አባቶች ምልጃ መጠቀም እንዳለብን እንማራለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡