ሆሣዕና (ለሕፃናት)

በቤካ ፋንታ

መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢየሩሳሌም በምትገኝ በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ ነው የምኖረው፡፡ ከተወለድኩ አምስት ዓመት ሞልቶኛል፡፡ በዕለተ ሰንበት በቤት ውስጥ እየተጫወትሁ፣ እናቴም በጓዳ ሥራ እየሠራች ሳለን በድንገት የብዙ ሰዎች የዕልልታ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ ሰማን፡፡ እናቴም በፍጥነት ከጓዳ ሮጣ ወጥታ ‹‹ልጄ! ልጄ! ነይ እንሒድ!›› ብላ አዝላኝ እየሮጠች ከቤት ወጣች፡፡ በኹኔታው ተገርሜአለሁ፡፡

በሰፈር ውስጥ ያሉ ጓደኞቼ ዅሉ በእናቶቻቸው ጀርባና በአባቶቻቸው ትከሻ ላይ ኾነው ከወላጆቻቸው ጋር በደስታ ዕልል ይላሉ፡፡ የሕፃናቶቹን ብዛት ሳይ ይበልጥ ተደሰትሁ፡፡ የሚያለቅስ አንድም ልጅ የለም፡፡ ‹‹ዛሬ የሕፃናት የደስታ እና የዝማሬ ቀን ነው›› ብሎ ልቤ በደስታ ፈነደቀ፡፡ ወላጆቻችን ዅሉ የዘንባባ ዝንጣፊ እየቈረጡ ያዙ፤ ለእኛም ሰጡን፡፡ ከዚያ ዕልል እያልን በደስታ ወደ ቤተ መቅደስ ሮጥን፡፡

በመንገድ ላይ በጣም ብዙ ሕዝብ አየሁ፤ እነርሱም ዘንባባ ይዘው ደስ ብሏቸው እንደኛ ወደ ቤተ መቅደስ ይሮጣሉ፡፡ በመካከላቸው አንድ ትልቅ አህያ አየሁኝ፣ ከአህያይቱም ጋር ውርንጫዋ (ልጇ) አለች፡፡ የሚያማምር ልብስ በአህያዎቹ ጀርባ ላይ ተነጥፏል፡፡ በውርንጫዋም ላይ የዅላችን ፈጣሪ፣ ንጉሣችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀምጦ ስመለከት በደስታ ዘለልሁኝ፡፡

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መኾን በጣም ያስደስታል፡፡ ምክንያቱም እርሱ እኛ ሕፃናትን እቅፍ አድርጎ ስሞን በጉልበቱ ላይ ቁጭ አድርጎ ያስተምረናል፣ ይመክረናል፡፡ በዙሪያውም ላሉት ሰዎች ‹‹እንደነዚህ ሕፃናት ንጹሓንኑ፤ ኃጢአት አትሥሩ፤›› እያለ ይመክራቸዋል፡፡

ከዚያ ዕልል እያለ የሚያመሰግነው ሕዝብ፣ እንደዚሁም በእናትና በአባቶቻችን እቅፍ ውስጥ ያለን ሕፃናት በአንድነት ኾነን ጮክ ብለን የዘንባባውን ቅጠል እያውለበለብን መዝሙር መዘመር ጀመርን፡፡ መዝሙሩም እንዲህ የሚል ነው፤ ‹‹ሆሣዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፡፡ ሆሣዕና በአርያም፤ ሆሣዕና በአርያም፤ ሆሣዕና በአርያም፡፡›› የመዝሙሩ ድምፅ በኢየሩሳሌም ከተማ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተሰማ፡፡ በጣም ደስ ያለኝ ደግሞ የእኛ የሕፃናቱ ድምፅ ከትልልቆቹ በልጦ መሰማቱ ነው፡፡

ጌታችንን በአህያዋ ላይ ተቀምጦ ባየሁት ጊዜ ትዝ ያለኝን አባዬ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ ያስተማረኝን ታሪክ ልንገራችሁ፤ ታሪኩም፡- ‹‹አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፣ እጅግ ደስ ይበልሽ! አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፣ ዕልል በዪ! እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም በአህያ፣ በአህያይቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፤›› የሚል ነው (ትንቢተ ዘካርያስ ፱፥፱)፡፡

የዝማሬውን ድምፅ ሲሰሙ አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወዱት በከተማው ውስጥ ያሉ ጨካኝ ሰዎች ወደ እኛ መጡ፡፡ ሰዎቹም ሕዝቡ ዅሉ ደስ ብሏቸው እየዘመሩ፣ ዕልል እያሉ፣ የዘንባባውን ቅጠል እያውለበለቡ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እያመሰገኑ ወደ ቤተ መቅደስ ሲሔዱ በተመለከቱ ጊዜ ተናደው ሕዝቡን ‹‹ዝም በሉ!›› ብለው ተቈጧቸው፡፡ ሕዝቡም ፈርትው ዝም አሉ፡፡

እኔና ጓደኞቼ ግን በእናታችን ጀርባ ላይ ካሉት ሕፃናት ጋር አብረን ኾነን ጮክ ብለን ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› የሚለውን መዝሙር ሳናቋርጥ እንዘምር ነበር፡፡ የገረመኝ ደግሞ ከእኔ የሚያንሱ ሕፃናትም መዝሙሩን ጮክ ብለው ሲዘምሩት መስማቴ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ሆይ መናገር የማንችለውን እኛን እንድንዘምርልህ ስለፈቀድህልን ተመስገን!›› ብዬ አምላኬን አመስግኜ መዝሙሩን መዘመር ቀጠልሁኝ፤ ‹‹ሆሣዕና፣ ሆሣዕና፣ ሆሣዕና በአርያም …፡፡››

በኋላ ግን እነዚያ ጨካኞቹ ሰዎች ስላስፈራሯቸው ወላጆቻችን ዝም አስባሉን፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአህያዋ ውርንጫ (በትንሿ አህያ) ላይ ቁጭ ብሎ ለጨካኞቹ ሰዎች ‹‹ከሕፃናት ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራሴ አዘጋጅቻለሁ፡፡ የእነርሱንም አፍ ይዛችሁ ዝም ብታስብሏቸው በዙሪያዬ ያሉት ድንጋዮች ያመሰግኑኛል፤›› አላቸው፡፡

ከዚያም ጌታችን፡- ‹‹የፈጠርኋችሁ ድንጋዮች ሆይ! ሕፃናት እንደ ዘመሩ እናንተም በመዝሙር አመስግኑኝ፤›› በማለት በታላቅ ድምፅ ሲናገር ግዙፍ ድንጋዮች ከመሬት ወደ ላይ እየተነሡ ‹‹ሆሣዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና እናቀርባለን …›› እያሉ በሚያስደስት ድምፅ እየመዘመሩ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ጨካኞቹ ሰዎች አፍረውና ፈርትው ተመለሱ፡፡

እኛ ሕፃናት፣ ወላጆቻችንና በዙሪያችን የነበሩ ድንጋዮችም አምላካችንን ከበን በዕልልታ እየዘመርን፤ ለአህያዎቹ መርገጫ ልብሳችንንና የዘንባባውን ዝንጣፊ እያነጠፍን ወደ ቤተ መቅደስ ገባን፡፡ በዚያም ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደስ የሚል ትምህርት አስተማረን፡፡

በመጨረሻም ‹‹ሆሣዕና›› ብለን ምስጋና ላቀረብነውና በቤተ መቅደስ ተገኝተን ቃሉን ለምንሰማው ሕፃናት ጌታችን እንዲህ ብሎ መከረን፤ ‹‹ልጆቼ በመዝሙራችሁ ተደስቻለሁ፡፡ ዅል ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጣችሁ ዘምሩልኝ፡፡አንደበታችሁ በመዝሙር አግዚአብሔርን አመስግኑበት እንጂ ዘፈን እንዳትዘፍኑበት፡፡ ዘፈንጢአት ነው፡፡››

ትምህርቱን ተከታትለን ከእናቴ ጋር ደስ እያለን ወደ ቤታችን ተመለስን፡፡ ታዲያ ዅል ጊዜ ይህችን የሆሣዕናን በዓል በውስጤ አስባታለሁ፤ መዝሙሩን መዘመር በጣም ያስደስተኛል፡፡ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻ የመከረኝንም ምክር ጠብቄ ዘፈን የሚባል በአፌ ሳልዘፍን በመዝሙር እግዚአብሔርን እያመሰገንሁ አደጌአለሁ፡፡

ልጆችዬ! ዛሬ የምታነቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፩ ከቍጥር ፩ እስከ ፲፮ እና የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፩ ከቍጥር ፩ እስከ ፲፯ ያለው ትምህርት ነው፡፡

‹‹ሆሣዕና በአርያም›› ብለን እንድናመሰግነው የፈቀደልን፤ ኃይሉን ጥበቡን የሰጠን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡