ለዶክተር ዐቢይ አህመድ

የኀዘን መግለጫ

“ብንኖረም ብንሞትም ለእግዚአብሔር ነን”፤ሮሜ ፲፬፥፰

እሁድ መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. ከጠዋቱ ፪፡፵፰ ደቂቃ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ ኬንያ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ የነበረው ET ፫፻፪ የመንገዶኞች አውሮፕላን ከ፮ ደቂቃ በረራ በኋላ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ከምትገኘው ደብረዘይት ወድቆ መከስከሱ ይታወቃል፡፡በመሆኑም ፻፵፱ መንገደኞች ፰ የበረራ አስተናጋጆችን ጨምሮ በድምሩ ፻፶፯ ሰዎች በሙሉ የአደጋው ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ፲፯ ያህሉ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የ፴፫ ሀገራት ዜጎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ በዚህ ድንገተኛ ክስተት ለተጎዱ መላው ወገኖቻችን፤ ኢትዮጵያውያንንና ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ እግዚአብሔር አምላክ ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት ዕቅፍ ያሳርፍልን ፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይሰጥልን ዘንድ እንጸልያለን፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ  ማኅበረ ቅዱሳን

ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ፡፡

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን፡፡

ጥር  17 ቀን  2011 ዓ.ም

እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፡፡ / 1ኛ ጴጥ 4፤7/

በማንኛውም የሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችንና ግድያዎችን ሁሉ እናወግዛለን፡፡  በየቦታው የተከሰቱ ችግሮች እንዲቆሙም በድርጊቱ የሚሳተፉ አካላትን ሁሉ እንማጸናለን፤  እናሳስባለንም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን

የክርስትና ሃይማኖት ማእከላዊ ጉዳዩ ሰው ነው፡፡ አምላክ ሰው ሆነ፣፤ ሰውም አምላክ ሆነ፣ የሚለው የትምህርቱ አስኳል ዋና ነጥብም የሚያመለክተው የነገራችን ሁሉ ማእከል ሰው መሆኑን ነው፡፡ ይህም ለሰው ሲባል አምላክ እንኳ ራሱን ዝቅ አድርጎ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ መገለጡንና በዚሀም ሰውን ከወደቀበት ማንሣቱን፤  ከዚያም በላይ ሰውን በተዋሕዶ ለአምላክነት ክብር ማብቃቱን የሚገልጽ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ  ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ዐለምአቀፋዊ ሆነው በትልቁ የሚከበሩት የአምላካችን ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሣኤና ዕርገት ሁሉ ማእከላዊ ነጥባቸው ሰው ነው፡፡ ሁሉም ነገሮች አምላክ ለሰው ሲባል ያደረጋቸው ናቸውና፡፡

ሌሎች አስተምህሮዎች ሁሉ አሁንም ሰውን ለማስረዳት ሲባል የተለያዩ አርእስት ይሰጣቸው እንጂ ማእከላዊ ነጥባቸው አንድ ነው፤ የሰው ድኅነትና ደኅንነት፡፡ የአንድ ሰው ጽድቁም ኃጢአቱም የሚለካው ለሰው በሚያደርገው ወይም በሰው ላይ በሚያደርገው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህም በምድር ላይ ከሰው በላይ የከበረና ጥንቃቄ ሊደረግለት የሚገባው ምንም ፍጥረት የለም፡፡ በምድር ላይ ጥንቃቄና ዕርምት የሚወሰድበት ነገር ሁሉ የመጨረሻ ዓላማው ሰውን ለመጥቀም ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ከሰው የሚጣላ ከአምላኩም ከአጠቃላይ ከፍጡራንም ሁሉ ጋር የሚጣላ ይሆናል፡፡ በሰው ላይ ያልተገባውን ድርጊት የሚፈጽም ሁሉ በፈጣሪው ላይ የሚያደርግ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፤ ፈጣሪ ሰው መሆንን በተዋሕዶ ገንዘብ አድርጎ ሰው ሆኖ ተገልጧልና በሰው የሚደረግ ሁሉ በእርሱ ላይ የሚደረግ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

የክርስትና ሃይማኖት መምህራንና ተቋማት ዋና ዐላማና ተልእኮም ሊመነጭ የሚችለው ከዚህ መሠረታዊ የሰው ክብርና ዋጋ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም የዓለም ክፍል በማንኛውም ሰው ላይ የሚፈጸሙ መጥፎ ተግባራት ይልቁንም ከሕግ ማሕቀፍ የወጡትንና በሴራና በተንኮል የሚፈጸሙትን እንደ ማኅበር አብዝተን እናወግዛቸዋለን፤ እንጸየፋቸዋለንም፡፡ ይልቁንም በሀገራችን በኢትዮጵያ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣው ንጹሐንን ሰለባ እያደረገ ያለው የተቀነባበረና የተነጣጠረ የሚመስለው ጥቃት በእጅጉ የሚያሳስብ መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

Read more

እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል፣ በሰላም አደረሰን/አደረሳችሁ

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

                                                  በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፡-
ከሁሉ በማስቀደም፣ የዘመናት ባለቤት ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር አምላክ፣ በረከት የምናገኝበትን ፆም በሰላም አስጀምሮ በሰላም በማስፈፀም፣እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል፣ በሰላም አደረሰን/አደረሳችሁ! በማለት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር ተዋቅሮ፣ የቅድስት ቤተክርስቲያንን አገልግሎት ለማገዝ፣ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው ማኀበራችሁ፣ ማኀበረ ቅዱሳን፣ መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

ውድ ምእመናን! የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት፡- የድኀነታችን ተሰፋ ቃል የተፈጸመበት፤ ዓመተ ኩነኔ ተደምስሶ፣ ዓመተ ምሕረት የታወጀበት ዕለት በመሆኑ፤ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን በዓል በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት፣ ደስታና ድምቀት ታከብረዋለች፡፡

እግዚአብሔር ጊዜን ለእኛ የፈጠረ እንጂ፣ለእርሱ ዘመን የማይቆጠርለትና ቦታ የማይወሰንለት አምላክ ሆኖ እያለ፤ እኛን ለማዳን ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍፁም አምላክ፣ ፍፁም ሰው ሆኖ የተወለደበትን ይህን ዕለት በየዓመቱ እየቆጠርን የምናከብረው፡- የቸርነቱን ስራ እያደነቅን፣ በልደቱ ብርሃንነት ከተገኘው በረከት ተካፋይ በመሆን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የበረታን እንሆን ዘንድ ነው፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ፡-ሰብአ ሰገል ልዩ ልዩ ገጸ በረከቶችን ይዘው፣ በቤተልሔም እንደተገኙ ሁሉ፣ እኛም ክርስቲያኖች በአንድ ልብና በጋራ በመሆን፣ በተሰጠን ጸጋ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ልናግዝና ልንጠብቅ ይገባል፡፡እኛ ክርስቲያኖች በዓሉን፡- ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለሰው ልጆች ድኀነትና ፍጹም ሰላም ሲል ወደ ምድር የመጣበትን በማሰብ የምናከብረው ስለሆነ፤ እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር በተሰጠን ሰላም እየተጠቀምንና እርስ በእርሳችን እየተዋደድን፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ብሎም ለሀገራችን ፍሬ ያለዉ ተግባር እንድንፈጽም እግዚአብሔር ይጠብቅብናል፡፡

ውድ ምእመናን! የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን፣ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ትእዛዛቱን አክብረን በቤቱ ውስጥ መኖር የሚጠበቅብን ስለሆን፣ መዳናችን ዘለዓለማዊነት ያለው ይሆን ዘንድ፣ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም የተመሰለችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ስለመሠረተልን፣ በእርሷ መገልገልና ማገልገል፣ የመንፈሳዊ ሕይወታችን ብቸኛዉ መንገድ ስለሆነ፤ በፍጹም ትጋት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ማኀበረ ቅዱሳንም፡-የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጅ በመሆን አገልግሎቷን እየፈፀመ ያለው፣ሁላችንም ያገኘነውን የእግዚአብሔር ልጅነት በማጽናት የሰማያዊው መንግሥት ወራሾች እንሆን ዘንድ ነውና፤ ማኀበሩ፡- ኃይለ እግዚአብሔርን፣ የአባቶችን ጸሎትና ብራኬ አጋዥ በማድረግ እንዲሁም የአባላቱንና የምእመናንን ዐቅምና ድጋፍ በማስተባበር እየፈጸመ ያለው አገልግሎት፣ እግዚአብሔር እንደፈቀደ፣ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የምናፈራበትና በሥነ ምግባር ተኮትኩተው በማደግ ሀገራቸዉን በሥርዓት ማገልገል የሚችሉ ዜጋዎችን ማግኘት የምንችልበት ነው፡፡

በአጠቃላይም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየተፈጸመ ያለው አገልግሎት፡-
 በዘመኑ ከሚፈለገዉ የቅድስት ቤተክርስቲያን ዘመኑን የዋጀ የአገልግሎት ተደራሽነት፣
 መጠናከር ካለበት አሠራር እንዲሁም
 መፈታት ካሉባቸዉ ፈተናዎችና ችግሮች አኳያ ሲታይ፣ በጣም ትንሽና ከሁላችንም ገና ብዙ የሚጠበቅ ነገር ያለ መሆኑን የሚያሳይ ነዉ፡፡

ስለሆነም ኀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ነው፤ ለኀምሣ ሰው ግን ጌጡ ነው! እንደሚባለው፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሆነውን የማኀበሩን አገልግሎት፡ቀርበን በጉልበታችን፣ በጊዜአችንና በገንዘባችን እናግዝ፡፡ እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ እንደ እየአቅማችንና ተሰጥዎአችን በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ዉስጥ በቃለ ዐዋዲዉ መሠረት እየገባን፣ ድጋፍና ተሳትፎ እናድርግ፣ በማለት ማኀበሩ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

በመጨረሻም፡-በቅዱስ ወንጌሉ፣ «በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናችኋለን» ተብሎ እንደተጻፈ፣ በዓሉን ስናከብር፡- እግዚአብሔር ሰላምን በሃገራችን እንዲያጸናልን በመለመን፣ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ እና በፍፁም መንፈሳዊ ሕይወት በመመላለስ፣በረከት የምናገኝበት ይሁንልን በማለት ማኀበሩ ምኞቱን ይገልጻል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በተከሰተው ችግር ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ መግለጫ!

 

                                                               እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል /ሮሜ  1419/

         በሀገራችን በኢትዮጵያ የሚካሔደውን የመንግሥት የአሠራር ለውጥ ተከትሎ ላለፉት ጥቂት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች መከሰታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ በግጭቶችም ከሀብት ውድመት እስከ ክቡሩ የሰው ሕይወት ኅልፈት ድረስ መከሰቱ እና በዚህም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማዘኑና ለመፍትሔውም በሚችለው ሁሉ መረባረቡ የሚታወቅ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ቀናት በሶማሌ ክልል የተከሰተው ግን በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በተለየ ሁኔታ አደጋ ውስጥ መክተቱ ደግሞ የበለጠ አሳዝኖናል፡፡ ይልቁንም ደግሞ ግጭቱ ሆነ ተብሎ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ሰፊ ጥፋት ለመቀስቀስ የታሰበ መምሰሉ በእጅጉ አሳስቦናል፡፡ ሆኖም ክርስቲያኖችም ሆኑ የሌላ እምነት ተከታዮች ነገሩን በጥንቃቄና ኃላፊነት በሚሰማው ሁኔታ እንደሚይዙት እምነታችን ታላቅ ነው፡፡

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና አማኞች ላይ ልዩ ትኩረት አድረገው ግድያ መፈጸማቸው፣ አብያተ ክርስቲያንን ማቃጠላቸው እና የአማኞቹን ሀብት ንብረት መዝረፋቸውና ማቃጠላቸውም ቢሆን ለሟቹቹ የሰማዕትነትን ክብር ከማቀዳጀቱና ለቤተ ክርስቲያንም ጸጋና ኃይል ከማጎናጸፍ ያለፈ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያኖች “በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” /ዮሐ 16፥33 / በሚለው የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል አምነውና ታምነው የሚኖሩ የሰላም ሰዎች ናቸውና፡፡ ሰማዕትነቱም ቢሆን ለሟቾቹ ብቻ ሳይሆን መከራውን፣ ስቃዩንና ጭንቀቱ ሁሉ ለደረሰባቸው ሁሉ ነውና ሥርየተ ኃጢአትንና ጸጋ እግዚአብሔርን ያበዛላቸዋል እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠፋት አይችልም፡፡ እንዲያውም በዘመነ ሰማዕታት እንደሆነው በሌላ አካባቢ ያሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ለሰማዕትነት የሚያበቃ በዚያ ጉዳት የደረሰባቸውንም በመርዳት፤ አብያተ ክርስቲያኑንም የበለጠ አድርጎ በመሥራት የሰማዕትነቱ ተካፋይ የመሆን እድል ይሰጣቸዋል፡፡ በፍትሐ ነገሥታችን አንቀጸ ሰማዕታት ላይ እንደተገለጸውም በዚያ የተጎደቱን ለመርዳት የሚረባረቡ ሁሉ ቁጥራቸው ከሰማዕታት ስለሆነ በመንፈሳዊ ዐይን ለሚያዩት ሁሉ ጥቅም እንጂ ጉዳቱ እምብዛም ነው፡፡

ለክርስቲያኖች እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ጠቀሜታ ቢኖረውም የሰው ሕይወት ክቡር ከመሆኑ የተነሣ ደግሞ በማናቸውም የሰው ልጆች ላይ ያለአግባብ የሚደርሰው ጥፋት በእጅጉ ያሳዝነናል፤ ያሳስበናልም፡፡ ስለዚህም ከመንግሥት ጀምሮ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ ይህን የመሰለ ችግር እየሰፋና እየተበራከተ እንዳይሔድ ቅድመ ጥፋት የጥንቃቄና የሰዎችን ሁሉ የደኅንነት ዋስትና የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ዐይነት ድርጊት የተሳተፉ አካላትንም ለሕግ በማቅረብ ለሰዎች ዋስተናን ለአጥፊዎችም ትምህርትን መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

ጥፋት አድራሾቹ “የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም” /ሮሜ 3፥17-18 / ተብሎ በቅዱሱ ሐዋርያ የተነገረላቸው መሆናቸውን ለመረዳት አይቸግርም፡፡ ስለዚህም እነዚህ አካላት የየትኛውንም ሃይማኖት የማይወክሉና የራሳቸውን ሰላም አጥተው የሌሎቻችንም ለመውሰድ የተነሡ መሆናቸውን ተረድቶ የእነርሱ ጠባይን ላለመውሰድና ለበቀልና ለመሳሰሉት ተጨማሪ አደጋ አምጭ ነገሮች ተጋላጭ እንዳሆን መጠበቅም ክርስቲያናዊ ብቻ ሳይሆን የመልካም ዜግነት ግዴታችን መሆኑንም ለማስታወስ እንወድዳለን፡፡  በዚህ አጋጣሚ ጥፋቱ ከደረሰው በላይ እንዳይሆን ስትከላከሉና የመልካም ዜግነት ግዴታችሁን ስትወጡ ለነበራችሁ ክቡር የሱማሌ ክልል ህዝብ ከፍ ያለ አክብሮታችንን እናቀርብላችሀለን፡፡ አሁንም በየመጠለያውና በየቦታው ያሉ የጉዳት ሰለባዎችን በመደገፍና ከወደቁበት በማንሳት አርአያነታችሁን እንድምታሳዩንእናምናለን፡፡

በሶማሌ ክልልና በሌሎችም ሆናችሁ ይህ አደጋ የደረሰባችሁ ክርስቲያኖችም ነቢዩ ኢሳይያስ “በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ” /ኢሳ 26 ፤ 3/ ሲል በተናገረው ቃለ መጽሐፍ ተማምናችሁ ብትጸኑ ለሰማዕትነት ክብር ከታጩት በቀር እግዚአብሔር እንደሚጠብቃችሁ የታመነ አምላክ ነውና አትረበሹ፡፡ ከዐለም የሆነው ሁሉ ስለመጥፋቱም አትጨነቁ፡፡ “ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?” /ማቴ 6 ፤ 25/ ሲል ያስተማረንን ጌታችንን አስታውሳችሁ እንድትጸኑ በፍጹም ፍቅርና ትሕትና ልናሳታውሳችሁ እንወድዳለን፡፡ እንደታዘዝነውም ለሚያሳድዷችሁና መከራውን ላመጡብን ሁሉ ከልብና ከእውነት እንጸልይላቸው፤ ጌታችንን አብነት አድረገንም በአንድነት አቤቱ  የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብለን በየዕለቱ እንጸልይላቸው፡፡ በየትም ዐለም ያለን ክርስቲያኖች ሁላችንም ከመቼዉም ጊዜ በላይ ስለቤተ ክርስቲያናችን፣ ስለሀገራችንና በስደትና በመከራ ላይ ስላሉት ሁሉ እግዚአብሔር በሃይማኖታቸው መጽናትን፤ በፍቅርም ይቅርታ ማድረግን በልቡናቸው ይጨምር ዘንድ በጥፋት ጎዳናም ያሉት ልቡና አግኝተው ይመለሱ ዘንድ ጊዜ ወስደን ሥራዬ ብለን ልንጸልይ ይገባናል፡፡ ከዚህም በሻገር ከሰማዕትነት ክብር እንካፈልና እኛንም ልንሸከመው ከማንችለው ፈተና እግዚአብሔር ይጠብቀን ዘንድ የተፈናቀሉትን ለማቋቋም፣ የተቸገሩትን ለመርዳት፣ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያንን ለማሳነጽና የሰማዕታቱን ቤተ ሰቦች በዘላቂ ለመርዳት መነሣሣትና ኃላፊነታችንን በአግባቡ በፍጥነት ልንወጣ ይገባናል፡፡

ጉዳት በማድረስ ከምክር እስከ ገቢር የተሳተፋችሁትም በማወቅም ባለማወቅም ከፈጸማችሁት ጥፋት ትመለሱና የእግዚአብሔርንም ይቅርታ ተገኙ ዘንድ “ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም” /መዝ 34፥14/  በሚለው ቃለ መጽሐፍ እንለምናችኋለን፡፡ የማትመለሱ ከሆነ ግን እርሱ የቁጣ ፊቱን ወደ እናንተ ባዞረ ጊዜም ሊያድናችሁ የሚችል ኃይል የለም፡፡ በነቢዩ ዳዊት “እግዚአብሔርን የምትረሱ እናንተ፥ ይህን አስተውሉ አለዚያ ግን ይነጥቃል የሚያድንም የለም” /መዝ 50 ፤ 22/ ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ስለዚህም ይህን አምላካዊ ማስጠንቀቂያ አስባችሁ እንድትመለሱና ሀገራችን የሰላምና የፍቅር ሀገር እንድናደርጋት በእውነት እንማጸናችኋለን። ሁላችንም ልንጠቀም የምንችለው በሰላም፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ብቻ ነውና በታላቁ ሐዋርያ በቅዱስ ጳውሎስ ቃል “እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል በማለት ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን /ሮሜ  14፥19/።

እግዚአብሔር አምላካችን ሀገራችንን ሕዝቦቿን ሁሉ በጽኑ ሰላም ይጠብቅልን፤ አሜን፡፡

 ማኅበረ ቅዱሳን

 

 

 

 

 

 

   የአባቶች አንድነት ላይ የተሰጠ  የደስታ መግለጫ!

       

ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ ከእቶነ እሳት በወጡበት በብሥራተ መልአክ በቅዱስ ገብርኤል የመታሰቢያ ዕለት የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  አባቶች  አንድ ሆነዋል፡፡በዚህም የምእመናን ተስፋ ለምልሟል፡፡የጥል ግድግዳ ፈርሷል፡፡ይህ ታላቅ መንፈሳዊ ተግባር የተፈጸመበት ዕለት ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ የደስታ ዕለት ነው፡፡ይህ ዕለት ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለመዋጋት ጥይቱን የጨረሰበት፤ዝናሩን አራግፎ ባዶ እጁን የቀረበት ነው፡፡ዕለቱ የሰይጣን ጥርሱ የረገፈበትና የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ለዓለም የተገለጠበት በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን የምስራች ቀን ነው፡፡

ለዚህ ዕለት ደርሶ የተገኘውን ዕርቅ አይቶ የማይደሰት ቢኖር ዲያብሎስ ብቻ ነው፡፡ዕርቁ እውን እንዲሆን መለያየት እንዲወገድ፤የተፈጠረው ክፍተት መፍትሔ እንዲያገኝ ያደረገ እግዚአብሔር ይመስገን በማለት በቅን ልቡና የተቀበላችሁ ቅዱሳን ፓትርያርኮቻችን የፈረሰውን አንድነት በዘመነ ፕትርክናቸሁ ለመጠገን ፤የተለያየውን አንድ ለማድረግ፤የሻከረውን ለማለስለስ ያበቃችሁ እግዚአብሔር ይመስገን !

ከቅዱሳን አባቶቻችንና ከቅዱስ ሲኖዶስ የተቀበላችሁትን አደራ ከዳር ለማድረስ አንድ ጊዜ  አሜሪካ ሌላ ጊዜ ኢትዮጵያ በመመላለስ የደከማችሁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና  በየአገሩ የምትገኙ የዕርቀ ሰላም ኮሚቴ አባላት እንኳን የድካማችሁን ፍሬ ለማየትና “ዕርቅ የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (በማቴ፭፥፱) የተባለው ተፈጽሞ ለማየት አበቃችሁ!

ዕርቁ ለቤተ ክርስቲያን፤ ለምእመናን አንድነት እንዲሁም ለሀገር ሰላም የሚኖረውን ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ተመልክተው ለተግባራዊነቱ የሚችሉትን ሁሉ ላደረጉት ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር ለክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ በመጨረሻም ዕርቁ ተግባራዊ እንዲሆን በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን ስትጠይቁ ለኖራችሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፤መምህራን ፤ገዳማውያንና ምእመናን  እንኳን ይህን የአባቶችን የአንድነት ቀን ለማየት አበቃችሁ፤አበቃን በማለት ማኅበረ ቅዱሳን በራሱና በአባላቱ ስም ደስታውን ይገልጻል!

ይህ ደስታ የቤተ ክርስቲያን ታላቅ በዓል በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን በምታደርግልን ጥሪ መሠረት ሁላችንም ምእመናን በአቀባበሉ ሥርዓት በመሳተፍ ፤የድርሻችንን እንድንወጣ ማኅበረ ቅዱሳን ጥሪያውን ያስተላልፋል፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም

 

 ኀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ- የአንተ በሆነ መንፈስ ቅዱስ አንድ መሆንን ስጠን!

በዐለም የክርስትና ታሪክ ውስጥ ምእመናን  ከተፈተኑበት ፈተናዎች አንዱ በአንድ በታወቀ መንበር ላይ ከአንድ በላይ ፓትርያርኮች ወይም ፖፖች መሾም ነው፡፡በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቀድሞ በነበረ ፓትርያርክ ወይም ፖፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ተደርቦ እንደተሾመ የሚነገርለት ቅዱስ አቡሊዲስ ዘሮም ነው፡፡ ቅዱስ አቡሊዲስ (Hippolytus) ተቀናቃኝ ፖፕ የሆነበት መንገድ ከዘመኑ የተነሣ በታሪክ ብዙም ባይገለጽም ተቀናቃኝ ሆኖ የተሾመው ግን ካሊክሰቶስ ቀዳማዊ (Pope Callixtus I) የሮም ፖፕ በነበረበት ዘመን ነበር፡፡ ሆኖም ካሊክስቶስ ሲያልፍ በወንበሩ ከተተካው ከፖፕ ፖንትያን (Pope Pontian) ጋር ታርቆ ችግራቸውን ፈትተዋል፡፡ በመጨረሻም ያረፈው በሰማዕትነት ስለነበረ ተጋድሎው በቅድስና ይታሰባል፡፡ በሮም ካቶሊክ ዘንድ በዓሉ የሚከበርለት ከታረቀው ከፖፕ ፖንትያን ጋር በአንድነት በእነርሱ አቆጣጠር ኦገስት በሚባለው ወራቸው በ13ኛው ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕርቅን አውርዶ ችግርንም ፈትቶ በአንድነት መከበርና መታሰብ የጀመረው ከመጀመሪያው ዐለምአቀፍ ጉባኤ ከጉባኤ ኒቅያ አንድ መቶ ዐመት በፊት ገና ሦስተኛው ክፍለ ዘመን  መጀመሪያ ላይ እንደነበረ ታሪካዊ አስረጅ አለው ማለት ነው፡፡

በርግጥ በፖፕ ላይ ፖፕ እየተሾመ መወዛገብ በሮማ ካቶሊክ ታሪክ ደጋግሞ ያጋጠመ ነገር ነበር፡፡አጥኝዎች እንደሚሉት በሮም ካቶሊክ ታሪክ ይህ ችግር ለ42 ጊዜ ያህል ተከስቷል፡፡ ሆኖም ከፍተኛ ውዝግብ ያስከተለው በ14ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ የተከሰተውና ለ40 ዐመታት የቆየው ታላቅ ውዝግብ ነው፡፡ከ1378 -1417 እንደቆየ የሚነገርለት ይህ ክፍፍል በሮማ ካቶሊክ ታሪክ ትልቁና በታሪክ ተመራማሪዎችም ዘንድ ትልቁ የምዕራቡ ክፍፍል እየተባለ የሚጠራና ከሦስት በላይ ፖፖች እኔ ነኝ ሕጋዊ ፖፕ በማለት የተወዘጋቡበት ነበር፡፡ መነሻውም በግልጽ ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት የፈጠረው እንደነበር ይታወቃል፡፡ቢሆንም ከ1414 – 1418 ኮንስታንስ ላይ በተካሔደ ጉባኤ ችግሩን ፈትተው አንድነታቸውን ለመመለስ ችለዋል፡፡

በምሥራቁም ዐለም ድርጊቱ በተለያዩ ጊዜያት ሲከሰት ኖሯል፡፡ለምሳሌ በቁስጥንጥንያው ንጉሥ ታግዞ በእስክንድርያ መንበር  በቅዱስ አትናቴዎስ ላይ ተተክቶ የነበረው ጊዮርጊስ በእኛ ሊቃውንት ዘንድም በደንብ የሚታወቅ ታሪክ ነው፡፡ ቆይቶ ደግሞ በተለይ ከጉባኤ ኬልቄዶን በኋላ በአንጾኪያ እና በቁስጥንጥንያ መንበሮች ብዙ ውጣ ውረዶች መፈራረቆችና መተካካቶች መሳደዶች በተደጋጋሚ አጋጥመዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ እንኳ በሩስያ፣በሕንድ እና በአርመን ኦርቶዶክሶች ተከስተው የነበሩት መከፋፈሎች ሊዘነጉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ብዙዎቹ ወይም ሁሉም ልዩነቶች ተፈትተዋል፡፡ በግሪክ ኦርቶዶክስ ግን አሁንም ትልቅ ክፍፍል አለ፡፡ ሆኖም የእነርሱ ፖለቲካዊ ጫና የፈጠረው ሳይሆን የትውፊት መለወጥ ነው፡፡ ይኸውም የቀድሞውን ዮልዮሳዊ የዘመን አቆጣጠር ትተው በምዕራባዊ ጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠር መጠቀም ሲጀምሩ ይህንን የተቃወሙት ለብቻቸው ተለይተው ወጥተዋል፤ ስማቸውም ኦልድ ካላንደሪስት ኦርቶዶከስ ቤተ ክርስቲያን (Old Calendarists orthodox Church) የሚል ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ የሚያመለክቱት በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ መለያየትና መከፋፈል በሌሎቹም ላይ ቀደም ብሎ ያጋጠመ እና ሲፈቱት የኖረ ችግር መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም በሮም ለ40 ዐመታት የቆየው ውዝግብ ግን ብዙ ችግር ያስከተለ ከመሆኑም በላይ የተፈታበትም መንገድ ብዙ ትምህርት ሊወሰድበት የሚችል ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ ገና ከሉተር መነሣት በፊት ስለነበረ መላው ምዕራብ አውሮፓ በሮም ካቶሊክ ውስጥ ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ ተወዛጋቢ ፖፖች ደግሞ ትውልዳቸው አንዱ ከፈረንሳይ ሌላኛው ከጣልያን ነበሩ፡፡ ይህም ማለት ተፎከካሪዎቹ ፖፖች በሁለት ሀገርና መንግሥታትም ጭምር ስለሚታገዙ ክፍፍሉ ጠንካራ ነበር፡፡ መንግሥቶቻቸው ደግሞ ሌሎቹን ሀገሮች እየቀሰቀሱ ከፊል የምዕራብ አውሮፓ መንግሥታት አንዱን ሌሎቹ ደግሞ ሌላውን ይደግፉ ስለነበር የጣልቃገብነቱንና ፍላጎት ያለው አካል ብዛትን ስናይ ብዙ ችግሮች እንደነበሩበት ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ለአንዳንዶች ሌሎች ሦስተኛና አራተኛ ፖፖችን እስከመሾም ያደረሳቸውም ከዚህ ከመጀመሪያዎቹ የኃያላን መንግሥታት ፍላጎት የተላቀቀ አዲስ ሲሾም ይፈታል ብለው በማሰብ ነበር፡፡ ሆኖም አልተሳካም፡፡ በመጨረሻ ግን አራት ዐመት በወሰደው ጉባኤያቸው ሁሉንም መንግሥታት፤ ካርዲናሎች፤ ሕዝቡን፤ ደጋፊዎቻቸውንና የመከፋፈል ተጠቃሚዎች የነበሩትን ሁሉ አሳምነውና  አሸንፈው አንድ መሆን  በቁ፡፡ በእውነት ከሆነ እንኳን በቁጥር ከዐሥር በላይ የሆነ ሀገርና መንግሥታትንና ሕዝብ አሸንፈው ለዚህ ከመብቃት በላይ አስደናቂ ነገር የለም፡፡

በእኛ ሀገር የተከሰተውም ምክንያቱ ፖለቲካን ተገን ያደረገ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ፖለቲካን ተገን አድርጎ ቤተ ክርስቲያንን መጉዳት ሲጀመር ይህ የመጀመሪያው አልነበረም፡፡ ከደርግ መምጣት ጋር ተያይዞ ባለ ትልቅ ራእይ በነበሩት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የተፈጸመው ግፍ ቢያንስ መንበሩ ወደ እኛ ከመጣ በኋላ ላለው ታሪካችን የመጀመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ምንም እንኳ በየዋሕነት ለነበሩትና በእንዲህ ያለ ጊዜ ምን መደረግ እንዳለበት ግንዛቤ እንዳልነበራቸው ግምት በምንወስድላቸው አባቶች ላይ ሙሉ በሙሉ ለመፍረድ ቢያስቸግርም ፖለቲካዊ ሒደቱን ተቋቁሞ በሐዋርያዊ መንገድ ችግሩን ለመወጣት የተደረገ ጥረት ግን ጎልቶ አይሰማም፡፡ እንዲያውም የፖለቲከኞችን ተንኮል ካለመገንዘብም ይሁን ከሰብአዊ ድካም በመነጨ በማይታወቅበት መንገድ ባይብራራም ተወቃሽ ተደርገው ሲቀርቡም ይስተዋላል፡፡

የደርግ ዘመን አብቅቶ ኢሕአዴግ ሲገባም ግቡ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ግን በመንበሩ ላይ በነበሩት አባት የወደፊት ሁኔታ ላይ ግን ለየት ያለ ድርጊት ተፈጸመ፡፡ በቀደመው ዘመን በአቡነ ቴዎፍሎስ የነበረውም ድርጊት ተወገዘ፡፡ ሆኖም የቀደመውን ድርጊት አውጋዦቹ ሌላ ተመሳሳይ ድርጊት ላለመፈጸማቸው ዋስትና ከመሆን ይልቅ የሚያወግዙትን ድርጊት አሻሽለው ከመፈጸም አልተመለሱም፡፡ በዚህ ወቅት የነበሩት አባቶችም አሁንም ከሐሜት መትረፍ አልቻሉም፡፡ ሐሜታውም በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉትን የሚያጠቃልል ነው፡፡

ታሪኩን በዚህ መጠን ለማስታወስ ያህል የሞከርነውም የችግሩ ተጠያቂነት በሁሉም ላይ ያረፈ መሆኑን ለመጠቆም ያህል እንጂ በታሪኩ ላይ ለመነታረክ አይደለም፡፡ ይልቁንም በተጠያቂነት ከመጠየቅ አልፈን ታሪካችንን ለሚያድስና ያለፈውን ለትምህርት ብቻ እንድንተወው የሚያደርግ አዲስ ወርቃማ ዕድል በእጃችን መኖሩን አስተውለን ሁላችንም በኅብረተ መንፈስ ቅዱስ አንድ እንድንሆን የምንጸልለውን ጸሎት በተግባር እንድናውለው ለመጠየቅ ያህል ብቻ ነው፡፡

በዚህ መልእክታችንም በቅዳሴያችንና በዘወትር ጸሎታችን የምንጸልያቸውን መነሻ አድርገን ልናደርጋቸው የሚገቡንን በማስታወስ መልእክታችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡

                 ሀበነ እግዚኦ አእይንተ አእምሮ

አባቶቻቸን አርእስተ መናብርቱ፣ በሁሉም በኩል ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳትና ካህናት በሙሉ ቅዳሴ እግዚእን በሚቀድሱበት ጊዜ ሓዳፌ ነፍስ ወይም ነፍስን የሚያጸዳ የሚወለውል ተብሎ በሚጠራው የመጨረሻው ጸሎት ላይ “ኀበነ እግዚኦ አእይንተ አእምሮ ወትረ ኪያከ ይርአያ ወአእዛንነሂ ቃለ ዘባሕቲትከ ይስምዐ” ‘አቤቱ ጆሮዎቻችን የአንተን ቃል ብቻ ይሰሙ ዘንድ ዐይኖቻችንም አንተን ብቻ ያዩ ዘንድ የዕውቀትን የማስተዋልን ዐይኖች ስጠን’ እያሉ ስለራሳቸውም ስለ እኛም ይጸልያሉ፡፡እኛም ልጆቻችሁ ዛሬ ሌላ መልእክት የለንም፡፡ እንደምትጸልዩልን እንደምትለምኑልን ልክ እንደዚያው የሌሎችን ቃል ትታችሁ የጌታችንን ቃል ሰምታችሁ አስታውሳችሁ አንድ ሁኑልን ብቻ ነው የምንለው፡፡የእርሱን ቃል ደግሞ ልትዘነጉት አትችሉም፡፡የጌታችን ቃሉ ደግሞ ትናንት በተፈጠረው በታሪኩ ላይ እንድንነታረክና እንድንከራከር አይፈቅድልንም፡፡ ይልቁንም “ወንድምህን እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት ይቅር በለው” እያለ የትላንቱን እንድንተወው ግዴታ ይጥልብናል እንጂ፡፡ እራሱም ጌታችን አስቀድሞ ሰይጣን ይህን ሊያደርገው ደጋግሞ የሚሞክረው መሆኑን “ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና” (ሉቃ 22 ፥31-32)ሲል እንደገለጸልን ይህ የመለያየት ነገር የሰይጣን ነው፡፡ በመከራ ጊዜ ደግሞ እንደተጻፈው ብዙ ሰው ይፈተናል፡፡ በወቅቱ የድርጊቱ ተሳታፊዎች ባለመሆናችን የምንተቸው ሰዎች ሁሉ በቦታውና በጊዜው ብንኖር ኖሮ ከዚህ የከፋ ልናደርግ እንደምንችል ገምቶ ራስንም በእነርሱ አስገብቶ ይቅር ማለት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ  እነ እገሌ ናቸው ተጠያቂ በሚል መንገድ መተቸት ነገሩን ከማባባስ ያለፈ የሚፈጥረው ፋይዳ የለም፡፡ በርግጥም እንዲህ ያለው ልዩነት ምእመናን በክርስትናቸው የሚበጠሩበት ነው፡፡ ጌታችን ግን በአንጻረ ቅዱስ ጴጥሮስ “እምነትህ እንዳይጠፋ አማለድሁ” ብሎ በሥጋዌው ቤዛ ሆኖ ያቀረበልንን የጸሎት መሥዋዕት ምልጃ ብሎ በመጥራት ነግሮናል፡፡ ይኸውም “ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው”(ዮሐ17፥11) የሚለው ነው። ስለዚህ በቅዳሴያችን  ላይ ጆሮቻችን የአንተን ቃል ብቻ ይሰሙ ዘንድ ካላችሁ አይቀር ቃሉ አንድ ይሁኑ የሚል ስለሆነ አንድ ትሆኑልን ዘንድ በታላቅ ትሕትና እንጠይቃለን፡፡

በርግጥም ልንሰማውና ልንከተለው የሚገባን የእርሱ ቃል ብቻ መሆን አለበት፡፡ በቤተ መቅደስ በቅዳሴ ጊዜ “ባርክ ላዕለ አባግዐ መርኤትከ፤ ወአብዝኀ ለዛቲ አጸደ ወይን እንተ ተከልካ በየማንከ ቅዱስ” እያላችሁ ምእመናንን ለማብዛትና ለመጠበቅ ፈቃዳችሁ ጸሎታችሁ መሆናችሁን ሁልጊዜ ትገልጻላችሁ፡፡”ባርኮ ለዘንቱ ኅብስት … ወሚጦ ለዝንቱ ጽዋዕ … ” እያላችሁ ቅዱስ ምስጢርን እንዲፈጸምላችሁ ትማጸኑታላችሁ፡፡ ያለ እርሱ ሊሆን ሊፈጸም የሚችል አይደለምና፡፡ ታዲያ ለምሥጢራት የምንጠራውን ጌታ ምሥጢራቱን ለሚፈጽሙት አበው አለመግባባት እንዴት ልንዘነጋው እንችላለን? በዚያ ጊዜ ብቻ ይህን አድርግ ብለን ለምነነው ይህን ጉዳይ ግን ብቻችንን ወይም ደግሞ ፖለቲከኞችንና ሌሎች የልዩነት ተጠቃሚዎችን ይዘን እንፈታዋለን ልንልምአንችልም፡፡እንግዲያው ጆሮዎቻችን እንደምንጸልየው የእርሱን ቃል ብቻ የሚሰሙበት፤ዐይኖቻችንም እንደ ምልጃ ጸሎታችን እርሱንም ብቻ ሊያዩበት እና ሌሎች ጊዜያዊ ነገሮችንና ፐሮፓጋንዳዎችን ቸል ሊሉበት የሚገባው እውነተኛው ጊዜ ዛሬ መሆን አለበት፡፡ ለወጡት ሚጠት (መመለስ)፣ለባዘኑት ዕረፍት፣ ለሚጨነቁት መረጋጋት፣ በግጭትና በዕልህም ውስጥ ላሉት ሰላምና አንድነት፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ለምእመናን ኅብረት ይሆን ዘንድ በእውነት ሌሎችንን ተጽእኖዎች ሁሉ ተቋቁመን መገኘት ይገባናል፡፡ ከዚህ ውጭ ከሆንን ግን”በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ”(ሐዋ፳ ፥፳፰) በሚለው ቃለ ሐዋርያ መወቀሳችን የማይቀር ይሆናል።

                 አድኅን እግዚኦ ዛተኒ ሀገረ

  የአባቶች አንድነት ለሀገር አንድነትና ሰላም ያለውም አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ የማይጠረጠር ነው፡፡የጥላቻ፣ የወቀሳና የከሰሳ ፖለቲካ ወደ ኢትዮጵያውያን ልብ ዘልቆ ከገባበት ከላፉት ስድሳ ዓመታት ወዲህ ጥላቻና መለያየት፤መሰዳደብና መወጋገዝ፣ በቀልና ግድያ፣ ተንኮልና ሴራ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ ብሔራዊ መግባባት በተወሰነ ደረጃ በሚቀነቀንበት በአሁኑ ሰዓት እንኳ በሰላም አልባሳት የተደበቁ የበቀል ድምፆች ከአንዳንዶች የሚሰሙ መሆኑን ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ታዲያ እንደዚህ ባለጊዜ ዐለምን በሙሉ ወደ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማቅረብ አደራውን ለተቀበሉ አባቶች ሓላፊነቱ ግልጽ ነው፡፡ ” … ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላመከ ኀበነ ወአጽንዕ ለነ ሰላመከ” ብለን በየቅዳሴያችን እየለመንነው ሰላም አጣን ብንል ሁሉም ይታዘበናል፡፡ ምክንያቱም እኛ ካልገፋናት በስተቀር የእርሱን ሰላም ከእኛ ማንም ሊወስዳት አይችልምና፡፡

ይልቁንም እኛ ፍጹም ሰላም ሆነን ሀገራችንም ከየትኛውም ችግር እንድትወጣ በእውነት መጣር ይኖርብናል፡፡ በዐርብ የሊጦን ጸሎታችን “አድኅን እግዚኦ ዛተኒ ሀገረ ወካልኣተኒ አኅጉረ ወበሐውርተ እለ በሃይማኖተ ዚአከ የኀድሩ” ‘አቤቱ ይህች ሀገር እና አንተን በማመን የሚኖሩ ያሉባቸውን በዐለም ላይ ያሉ ሌሎችን ሀገሮችም ሁሉ አድን’ እያልን የምንማልድ ሰዎች በእኛ ልዩነት ምክንያት ሕዝበ ክርስቲያኑን ለያይተን፣በብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ አስገብተን ፣ በአንድ ቤት ሳይቀር ባልና ሚስት፤ ታላቅና ታናሽ ተለያይተው ጸሎቱ ምልጃው እንዴት ስሙር ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በልዩነቱ ምክንያት ሰብሳቢ አጥተው ባዝነው ከመንጋው እየተለዩ ወደሌሎቹ በረቶች ምንያህል ነፍሳት እንደሔዱ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ እንኳን    ከምእመናን መምህራንና አገልጋይ ከሚባሉት አንኳ ምን ያህሉ በነፍስ ተጨነቁ፤ ስንቶቹስ ባዘኑ፡፡ ስለዚህም ጸሎታችንን በተግባር እንግለጠው፡፡ያ ካልሆነ አቤቱ ሀገራችን አድን ስንለው ልዩነቱንና መለያየቱን እናንተ በተግባር አገዛችሁት እንጂ መች ተጸየፋችሁት የሚያስበለን ይመስላል፡፡ ስለዚህም ስለሀገራችንም፣ ስለሕዝበ ክርስቲያንም አንድነት ስንል አንድነቱን ያለ ቅድመ ሁኔታ በይቅርታ እና በዕርቅ ልንዘጋው ይገባናል፡፡ በዘመናችን የሀገራችን ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት ፖለቲከኞች ለሚሔዱበት የዕርቅና የሰላም ጉዞ አርአያ መሆን እንኳ ባይቻለን ፍኖተ ሣህሉን ለመከተል እንኳ ካልቻልን ጌታችን አይሁድን በዚህ ትውልድ ንግሥተ አዜብ ትፈርድበታለች እንዳለ በእኛም ላይ በመጨረሻው ዘመን የሚያስፈርድብን በእኛው ፖለቲከኞች መሆኑ የማይጠረጠር ነው፡፡ እነርሱ ከእኛ በብዙ መንገድ ተሽለው ተገኝተዋልና፡፡

          በኵሉ ልብ ናስተብቊዖ ለእግዚአብሔር አምላክነ

ይህ ይሆን ይፈጸም ዘንድ ጸሎት እንደሚደርግ የታመነ ነው፡፡ይልቁንም አሁን ደግሞ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት”አመንኩ በዘነበብኩ”‘በተናገርሁት(በጸለይኩት) አመንኩ’ የአመንኩትንም ጸለይኩ፤ መሰከርኩ (መዝ115፥1)እንዳለው የምንጸልየውን የበለጠ አስተውሎ መፈጸም ሳይጠይቅ አይቀርም፡፡ይህን የምናስታውሰው አይደረግም ለማለት ሳይሆን አሁንም በምንቀድሰው ቅዳሴ ዲያቆኑ አስቀድሞ “ያማረ በመንፈስ ቅዱስ የሚፈጸም አንድነትን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር አምላካችን በፍጹም ልብ እንለምነው” ሲል የታወቀውን በአዋጅ እንደሚያነቃን እንደሚያስታውሰው ያለ የልጅነት ማስታወሻ ብቻ ነው፡፡ እናንተም “ኀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ” ‘የአንተ በሆነ መንፈስ ቅዱስ አንድ መሆንን ስጠን’ የምትሉትን በተግባር ማየት የማይመኝ የለም፡፡ይልቁንም በዐርብ ሊጦን ጸሎታችን “ሀበነ ከመ በአሐዱ ልብ ወበአሐዱ አፍ ንሰብሕ ለአብ ወወልድ መንፈስ ቅዱስ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም” ስትሉ እንደምትማልዱት በአንድ ልብ እና በአንድ አፍ በአንድ መቅደስና በአንድ ቅዳሴ አንድ ላይ ሆናችሁ ለፈጣሪ ምስጋና ስታቀርቡ ለማየት አብዝተን የምንመኝና የምንጸልይ እርሱንም “በፍጹም ልብ”ይሁን የምንል መሆናችንን ለሁላችሁም በታላቅ ትሕትና እናቀርባለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 ምንጭ፤ሐመር    መጽሔት    26ኛ ዓመት ቊጥር 2፤ሰኔ2010 ዓ.ም

 

“በሰላም ማሠሪያ፣ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ» (ኤፌ 4፡3)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
“በሰላም ማሠሪያ፣ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ» (ኤፌ 4፡3)
እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፣ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፣ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ፡፡ ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ፡፡ (ሮሜ.12፡16) ተብሎ እንደተጻፈ፡- የቅድስት ቤተክርስቲያን አገልግሎት፣ ምእመናንን ከማጠንከርና ከማብዛት አንፃር፣ ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ መመራት ያለበት በመሆኑ፣ በዘፈቀደ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጐ በመግባባት፣ በፍቅር፣ በስልትና በዕቅድ የሚፈጸም ነው፡፡
«መከሩ ብዙ ሠራተኛው ግን ትንሽ ነው» (ማቴ. 9÷37) ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈው በዘመናችን ብዙ የሰው ኃይልና ዐቅም የሚጠይቁ የቅድስት ቤተክርስቲያን አገልግሎቶች ያሉ ሲሆን፤ ቅድሚያ የሚሰጠውን እየመረጡ ሥምሪት ማድረግ፣ ከቅዱሳን ሐዋርያት የምንማረው ትምህርት ነው፡፡ ለዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያን በየዓመቱ በምታደርጋቸው የቅዱስ ሲኖዶስና የጠቅላይ ቤተ ክህነት አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ከፍተኛ ጉባኤያት፣የትኩረት አቅጣጫዎች ይያዛሉ፡፡ ለእነዚህ አቅጣጫዎች ተፈፃሚነትም፣ በመዋቅሯ ውስጥ ያሉ አካላትና ልጆቿ የሆኑት ምእመናን እርስ በርሳቸው በመናበብ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ይደግፋሉ፡፡
ይህ ሆኖ ሲታይ ግን፡- ያለው ውሱን ዐቅምና ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል፤ ባለቤት እና ድጋፍ ያጣው አገልግሎት ተከታታይ እንዲኖረው፣ ሥርዓት ያልወጣለት አገልግሎት ሥርዓት እንዲወጣለት ይደረጋል እንጂ፣ «ልባሞች የሆን እየመሰለን» አስታዋሽ ያጣውን ሳናስታውስ ከግል ፍላጐት አንፃር በተጀመረ ነገር ላይ፣ እንደ ምድራዊ ሀብትና ሥልጣን ክርክር የምንፈጥርበት አይደለም፡፡
የ2010 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ከሚያዝያ 24-29 ቀን 2010 ዓ.ም ሲካሄድ ቆይቶ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ተልእኮ መሳካት በሚጠቅሙ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተነጋግሮ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳነት ተይዘው ውይይት ከተደረገባቸው ነጥቦች መካከል፡አንዱ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚማሩ ጥቂት የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ የግቢ ጉባኤያት ተሳታፊ ነበርን የሚሉ ተማሪዎች፣ ‹‹ከማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤ መዋቅር ተለይተን ለብቻችን እንማር›› በሚል ያቀረቡት ጥያቄ ይገኝበታል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም ጉዳዩን በጥልቀት ከተወያየበት በኋላ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት በሚጠቅም መልኩ‹‹ጥያቄዎቹ የተነሱባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙባቸው አህጉረ ስብከት ኃላፊነትን ወስደው፣ ጥያቄ ያቀረቡ ተማሪዎችን በሰንበት ት/ቤት ውስጥ ለብቻቸው እንዲማሩ ይደረግ››ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይህ ውሳኔ የማያሻማና ግልጽ ሆኖ ሳለ ቀድሞውኑ ሃይማኖታቸውን በስፋት በመማር በመንፈሳዊነታቸው ከመበልጸግ ይልቅ ማኅበሩን በሐሰት በመክሰስ ጉዳዩን አጀንዳ እንዲሆን ያደረጉት ጥቂት ግለሰቦች የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ በዚህ መልኩ መሆኑ አላስደሰታቸውም፡፡ በመሆኑም ውሳኔውን በማዛባት እና የተለያየ መልክ በመስጠት በተለያዩ ሚዲያዎች የተሳሳተ መረጃ ማናፈስ በመጀመራቸው የውሳኔውን ትክክለኛ ጭብጥ ማብራራት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም መሠረት፡-
1ኛ) ምንም እንኳን ተማሪዎቹ ሁሉንም የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ የግቢ ጉባኤያት አባላትን የማይወክሉ ጥቂቶች ቢሆኑም፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ‹‹አንዲት ነፍስም ብትሆን እንዳትጠፋ›› በሚል የቤተክርስቲያንን መርህ መሠረት በማድረግ፣ ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ መወያየቱን ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን ተቀብሎታል፡፡
2ኛ) ማኅበረ ቅዱሳን በአፋን ኦሮሞም ሆነ በሌሎች አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቋንቋዎች የፈጸመው አገልግሎት በቂ እንዳልሆነ አበክሮ ይረዳል፡፡ በመሆኑም ተማሪዎቹ ‹‹ማኅበሩ በአፋን ኦሮሞ በብቃት አገልግሎት አልሰጠንም›› ሲሉ ያቀረቡት ቅሬታ አገልግሎቱ የበለጠ ሊጠናከርና ሊሰፋ ይገባል በሚለው መልኩ ከታየ አግባብነት ያለው ነው ብሎ መቀበል ይቻላል፡፡ነገር ግን በአንጻሩ የማኅበሩን ማንነት እና ዓላማ በማይወክሉ ክሶች፣ ለምሳሌ ‹‹በቋንቋችን እንዳንማር በደል አድርሶብናል፤ ዐሥራት በኲራት ይሰበስባል፤ በፀጥታ ኃይሎች አማካኝነት ያስፈራራናል ወዘተ›› (ለብፁዓን አበው የቀረበ ክስ) በማለት መወቀሱን አጥብቆ ይቃወማል፡፡ እነዚህንና መሰል አሉባልታዎችን በማስወራት ማኅበሩን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባለት በከሰሱበት ወቅት ማኅበሩም ለቀረቡበት ክሶች ምላሹን እንዲሰጥ ዕድል መሰጠት የነበረበት ቢሆንም፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አባቶቻችን ይህንን ያላደረጉት ማኅበሩ በእነዚህ መሰል ጉዳዮች ውስጥ እጁን እንደማያስገባ ስለሚያውቁ እና በማኅበሩ አሠራርና መርሖች ላይ ያላቸው እምነት ከፍተኛ በመሆኑ፣ ለብቻቸው መማር የፈለጉ ተማሪዎች በሀገረ ስብከት አማካኝነት ይማሩ በማለት ወስነዋል፡፡
3ኛ) የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ በማጣመም ወይንም በተሳሳተ መንገድ ባለማወቅ በመተርጎም በአፈጻጸም ሂደት ውስጥ ችግር እንዳያጋጥም ከዚህ በታች የተገለጹት ነጥቦች በአንክሮ ሊታዮ ይገባቸዋል ብለን እናምናለን፡፡
ሀ) የግንቦቱ ርክበ ካህናት ውሳኔ ‹‹በሲኖዶስ ደረጃ›› ከመሆኑ በቀር ቀድሞውንም ቢሆን በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ተመሳሳይ ውሳኔዎች እና ተሞክሮዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ፡- በጅማ፣ በወለጋ እና በቡሌ ሆራ ከየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በተደረጉ ውይይቶች፣ ቋንቋን መሠረት በማድረግ ‹‹በማኅበረ ቅዱሳን ሥር መሆን አንፈልግም›› ያሉትን በጣም ጥቂት የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ተማሪዎች ‹‹የግድ ማኅበረ ቅዱሳን ሥር ካልሆናችሁ ከቤተ ክርስቲያን ውጡ›› ሊባል እንደማይገባ ግልጽ ስለሆነና የቅድስት ቤተክርስቲያን ጠባይ ባለመሆኑ ለጠያቂዎቹ የተሰጠው ምላሽ ‹‹በአህጉረ ስብከቱ ቀጥተኛ ክትትል ለጊዜው በአጥቢያዎቹ ሥር ሆናችሁ ተማሩ›› የሚል ውሳኔ ነበር፤ ምንም እንኳን አፈጻጸሙ ላይ ግጭቶች ቢስተዋሉም በዚያው አግባብ ለጥቂት ወራት ለማስኬድ ተሞክሯል፡፡ እናም ይህ ውሳኔና የቀደሙ ልምዶች ‹‹የማኅበረ ቅዱሳንን የቤተክርስቲያን አገልግሎት የጎዳ አዲስ ውሳኔ›› ተደርጎ መታየት ስለማይገባ የአህጉረ ስብከት መዋቅራት፣ የግቢ ጉባኤ አገልጋዮችና የማዕከላት አስተባባሪዎች አገልግሎታቸውን አጠናክረውና የጎደለውን ሞልተው ሊቀጥሉበት ይገባል፡፡
ለ) የግንቦቱ ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደግሞ ‹‹ዩኒቨርስቲዎቹ ያሉበት አህጉረ ስብከት ወጣቶቹን ተረክበው፣ መርሐ ግብር አዘጋጅተው፣ መምህራንን መድበው እንዲማሩ እንዲያደርጉ›› የሚል መሠረታዊ ነጥብ አስቀምጧል፡፡ (የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ) ይህም የሚያመለክተው ከዚህ በኋላ ‹‹በማኅበሩ መዋቅር ውስጥ መገልገል አንፈልግም›› ያሉት የተወሰኑ ተማሪዎች ለሚያደርጓቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ከአጥቢያም በላይ ሀገረ ስብከት ቀጥተኛ ኃላፊነት እንዳለበት አጽንዖት የሰጠ ውሳኔ ነው፡፡ አህጉረ ስብከቶቹ ስንቸገርበት የቆየነውን የተማሪዎቹን እንቅስቃሴ በቀጥታ መከታተላቸው ደግሞ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የግቢ ጉባኤ ሐዋርያዊ አገልግሎት መቀላጠፍ ምቹ አጋጣሚን የፈጠረ ከመሆኑም በተጨማሪ ከዚህ በተሻለ ትጋት እንድናገለግል ክፍተቶቻችንን ለመለየት ረድቶናል፡፡ በተጨማሪም ‹‹አህጉረ ስብከቱ ይረከቧቸው፣ መምህራንን መድበው ያስተምሯቸው›› ተባለ እንጂ ‹‹ሌላ ግቢ ጉባኤ ይመስርቱ›› ስላልተባለ ይህ ውሳኔ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትም ሆነ ለማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤ ክርስቲያናዊ አንድነትና የፍቅር አገልግሎት ትልቅ ፋይዳ ያለው ውሳኔ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ሐ) ውሳኔው የፈጠረው መልካም ዕድል ፍሬ እንዳያፈራ ለማድረግ ከዚህ ቀደም ከልምድ እንደታየው መንፈሳዊ ሥነ ምግባራት ከጎደላቸው ጥቂት ወጣቶች በአፈጻጸም ላይ ችግር በመፍጠር አገልግሎቱን ሊያውኩ እንደሚችሉ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች በአጥቢያ ሥር የሚገኙትን የግቢ ጉባኤ ቦታዎች እና ንብረቶች ‹‹ይገባኛል›› ሊሉ ስለሚችሉ፤ አላስፈላጊ ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እስካሁን በነበረው አካሄድ ‹‹በመንፈሳዊ መንገድ ለመፍታት፣ ቅዱስ ሲኖዶስም የመጨረሻውን ውሳኔ እስኪሰጥ›› በሚል ሁሉንም ነገር ለእነዚያ ወጣቶች ተውላቸው እያልን ግቢ ጉባኤያቱን ስንጫን ቆይተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ሁለቱም በየመዋቅሮቻቸው ሥር ሆነው እንዲማሩ ተወስኗልና የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች መብታቸው እየተገፈፈ እንዲቀጥል ዕድል መስጠት እንደማይገባ ማኅበሩ ያምናል፡፡
በመሆኑም በማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት መሳተፍ ‹‹አንፈልግም›› ብለው ከወጡ እና በሀገረ ስብከቱ እንዲማሩ በቅዱስ ሲኖስ ከተወሰነ በኋላ ከግቢ ጉባኤው ጋር የማይስማሙ ከሆነ ግን በየደረጃው ላሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት እንዲሁም ለክልሉ መንግሥትና የጸጥታ አካላት ማሳወቁ ተገቢ ይሆናል፡፡ ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን እና የመንግሥት አካላት አሳውቀን ጉዳዩ ሳይፈታ በቸልታ ከታለፈ በተለያዩ የአስተደዳር ደረጃዎች ለሚገኙ አካላት ሁሉ ከወዲሁ አጥብቆ ማሳሰብ ይገባል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የማኅበረ ቅዱሳን መዋቅራትም ይህንኑ አቋም በየአካባቢያቸው ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት አካላት በአጽንዖት በማሳወቅ አገልግሎቱን ከማይገባ ሥነ ምግባር ከጎደለው ነገር የመጠበቅ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡
መ) ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከላይ የተገለጸው ለብቻችን የሚል የመለየት አጀንዳ ይዘው ለሚገኙ በጣት ለሚቆጠሩ ወጣት ያሉባቸው አህጉረ ስብከት ወረዳ ቤተ ክህነት እና የማኅበሩ ማእከላት ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለባቸውም መዘንጋት የለባቸውም፡- በማኅበሩ የግቢ ጉባኤ መዋቅር ሥር በአፋን ኦሮሞ ለሚማሩት ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ ማስተማር እና መከታተል፤ ከሃይማኖታቸው የበለጠ ሌላ አጀንዳ የሚበልጥባቸውን ወጣቶች አግባብነት ባለው የትምህርት መልእክትና ፍቅር በመስጠት ወደ እውነተኛ ክርስቲያናዊ አመለካከት እንዲመለሱ ማድረግ፣ በቋንቋው የምንሰጠውን አገልግሎት ከበፊቱም ይልቅ አጠናክረን በመቀጠል በተሳሳተ የአሉባልታ መረጃ፣ በክርስትና ትምህርት ባለመብሰል በሚፈጠር የመረጃ ትንታኔና ስሜታዊነት፣ በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ወንድሞችና እኅቶች መካከል የሚዘራውን የጥላቻ ቅስቀሳ ተከትለው ከግቢ ጉባኤ መዋቅር የሚወጡ ተማሪዎችን ለመመለስ አትኩሮ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ማእከላቱ በልዩ ሁኔታ ሊሰጧቸው የሚያስቧቸውን አገልግሎቶች ለማሳካት የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች እና አቅጣጫዎች በተመለከተ ከዋናው ማዕከል የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ጋር በቀጥታ እየተገናኙ፣ ችግሮችንና ጥያቄዎችን በፍጥነት በመወያየት መፍትሔ የመስጠት እና የማሰጠት ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ሠ) እነዚህንና መሰል ተግባራትን ስናከናውን ደግሞ፣ ከየአህጉረ ስብከቶቹ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር መወያየትና መመሪያ እየተቀበሉ መተግበር፣ የቅዱስ ሰኖዶሱን ውሳኔ በተለያየ መንገድ በመተርጎም ወይም ዋጋ ባለመስጠት የራሳቸውን አቅጣጫ የሚከተሉትን ለሚመለከታቸው ሁሉ በፍጥነት ማሳወቅ፤ ከሚመለከታቸው ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አካላትም ጋር ተቀራርቦ መመካከር፣ በአከባቢው ተሰሚነት ካላቸው ኦርቶዶክሳውያን የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ጭምር እየተመካከሩ መሥራት በፍጹም ሊረሳ የማይገባው ነው፡፡ ይህ ሲሆን የግቢ ጉባኤያት ጉዳይ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄዱ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች የማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ሳይሆኑ የሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ አካላት፣ ምእመናንና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት ለሚያስቡ፣ ለሚመኙና ለሚቆሙ ሁሉ ነውና፣ አስተማማኝ እና ቀጣይነት ያለው ክርስቲያናዊ የሆነ፣ ከቡድንና ከስሜት፣ ከድብቅ አጀንዳና ፍላጎቶች የጸዳ እውነተኛ መፍትሔ ያመጣል ብለን እናምናለን፡፡
በአጠቃላይም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ ሆኖ በጐቿን የሚጠብቅ እንዲሆን ስንሻና፣ በእያንዳንዳችን ፍላጐትና ጥበብ ሳይሆን፣ በፍጹም መንፈሳዊነት መሆን ያለበት ስለሆነ፤ የሚፈጸሙ ተግባራት ሁሉ «ሰላምን ማሠሪያ የሚያደርጉ፣ የመንፈስ አንድነትን ለመጠበቅ የሚረዱ እንጂ፣ ተቃራኒ የሆነ ውጤት ለማምጣት ምክንያትና ምቹ ሁኔታ የማይሆኑ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባናል፡፡» ኤፌ. 4÷3 ለዚህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ትእዛዛተ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ ሁኔታ ይፈጸም ዘንድ፣ የተጣመመውን እያቀኑ፣ የጐደለውን እየሞሉ መሄድ ይገባል፡፡ በመሆኑም ሁላችንም እንደ ባለቤት ሆነን በትጋት መከታተል፤ ከቅድስት ቤተክርስቲያን መዋቅር ማለትም ከአህጉረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተ ክህነት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ አባቶች፣ ምእመናን፣ ሰንበት ት/ቤቶች እና ግቢ ጉባኤያት እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚጠበቅ ነውና፤ በሰላም ማሠሪያነት በቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ የመንፈስ አንድነትን ለመጠበቅ የሚያግዙና የሚረዱ ነገሮችን ትኩረት ሰጥተን እንሥራ በማለት ማኅበሩ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!
ምንጭ ፤ሐመር መጽሔት 26ኛ ዓመት ቊጥር ግንቦት 2010ዓ.ም ቁጥር1

የማኅበረ ቅዱሳን ወቅታዊ የአዘክሮ መልእክት

ጥቅምት ፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

‹‹ወንድሜ ሆይ፥ በጎ አድራጊ እንጂ ክፉ አድራጊ አትኹን፤›› (፫ኛ ዮሐ. ቍ. ፲፩)::

በጌታችን ላይ በአይሁድ የተፈጸመውን ዂሉ ለድኅነተ ሰብእ እንደ ተፈጸመ ተቀብለን ሐተታ ላለማብዛት ብንተወው እንኳን መልካም የሚሠሩትን ክፉ ስም እየሰጡ ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል ሥራ መሥራት የተጀመረው በዚያው በሐዋርያት ዘመን እንደ ኾነ ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ ‹‹ከእነርሱ አንዳንዶች በቅናታቸውና በክርክራቸው፥ ሌሎችም በበጎ ፈቃድ ስለ ክርስቶስ ሊሰብኩና ሊያስተምሩ የወደዱ አሉ፡፡ በፍቅር የሚያስተምሩም አሉ፤ ወንጌልን ለማስተማር እንደ ተሾምኹ ያውቃሉና፡፡ በኵራት ስለ ክርስቶስ የሚያስተምሩ ግን፥ ይህን አደርገው በእስራቴ ላይ መከራ ሊጨምሩብኝ መስሏቸው ነው እንጂ በእውነት አይደለም፤ በቅንነትም አይደለም፡፡ ነገር ግን ምን አለ? በየምክንያቱ በእውነትም ቢኾን፥ በሐሰትም ቢኾን ስለ ክርስቶስ ይናገራሉ፤ ሰዉን ዂሉ ወደ እርሱ ይጠራሉ፡፡ በዚህም ደስ ብሎኛል፤ ወደ ፊትም ደስ ይለኛል፤› (ፊልጵ. ፩፥፲፭-፲፰) በማለት የክርስትና ተቃዋሚዎች ቅዱስ ጳውሎስን ለማሳሰርና በእርሱ ላይ ከባድ መከራ ለማምጣት ሲሉ ራሱ የሚሰብከውን ቅዱስ ወንጌል ለመጠቀም መጣራቸውን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ገልጾልናል፡፡ ከመልእክቱ እንደምንረዳው ታላቁ ሐዋርያ በቅንዓትና በክፋትም ቢኾን ‹‹እሰይ! እንኳን ወንጌል ተሰበከ!›› ሲል ለበጎ አድርጎ ይወስደዋል፡፡ ድርጊታቸው ለበጎ ባይኾንም ሰማዕያንን ስለሚያዘጋጅለትና የበለጠ እንዲረዱ ስለሚጋብዝለት እንደ መልካም ዕድል ወስዶታል፤ ኾኖለታልም፡፡

እጅግ የሚያስደንቀው ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንቅፋት ይገጥመው የነበረው ቤተ ክርስቲያንን በሓላፊነት ሊያገለግሉ በተለያየ መዓርግ ከተሾሙት ወገኖች ጭምር መኾኑ ነበር፡፡ ይህም የተከሠተው ልክ እንደ ቀደመው ዂሉ ራሳቸው ሐዋርያት በነበሩበትና ከራሱ ከመድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የሰሙትን የድኅነት ወንጌል በሚመሰክሩበት ዘመን ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ እንደ ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ያሉ ሐዋርያት ይሰሙናል ብለው ለሚያስቧቸው አገልጋዮች የሁለቱንም ዓይነት አገልጋዮች ጠቅሰው በጎውን እንዲመስሉና ክፉውን ግን እንዳይከተሉት ያሳስቡ እንደ ነበረ ለርእስነት ከተጠቀምንበት ኃይለ ቃል ለመረዳት ይቻላል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ይህችን ሦስተኛዪቱን መልእክቱን የላካት ለደቀ መዝሙሩ ለጋይዮስ ሲኾን መልእክቱንና አደራውን የሚሰጠው በዘመኑ የነበሩትን ሁለቱንም ዓይነት አገልጋዮች በንጽጽር ካቀረበለት በኋላ ነበር፡፡ አንድ ምዕራፍ ብቻ ባላት፣ በይዘት አነስተኛ በኾነች፣ በጭብጥና በፍሬ ነገር ግን ከሌሎቹ መልእክታተ ሐዋርያት በማታንሰው በዚህች መልእክቱ ያነጻጸራቸው ሁለቱ አገልጋዮች ደግሞ ዲዮጥራጢስ እና ድሜጥሮስ ነበሩ፡፡

ሐዋርያው በዚህ መልእክቱ ቍጥር ዘጠኝ ላይ እንደ ገለጸው ዲዮጥራጢስ ፍቁረ እግዚእ የተባለ ቅዱስ ዮሐንስ ለቤተ ክርስቲያን የላከውን መልእክት እንኳን የማይቀበል፤ እንዲያገለግሉ የተፈቀደላቸውን አገልጋዮች የሚያንገላታና የሚቀበሏቸውን ሳይቀር ከቤተ ክርስቲያን ለማባረር ጥረት የሚያደርግ ክፉ አገልጋይ ነበረ፡፡ በአንጻሩ ድሜጥሮስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱ የኾኑትን፣ ለዕድገቷና ለጥንካሬዋ የሚላላኩትን ዂሉ የሚቀበል፤ በመልካም የሚያስተናግድና ከበጎዎቹ ጋር ዂሉ አብሮ የሚሠራ፤ የልቡናውን ሳይኾን የቤተ ክርስቲያንን፤ የራሱን ብቻ ሳይኾን የአባቶቹን ድምፅ፣ ምክርና ዐሳብ ተቀብሎ የሚያስተናግድ ቅን አገልጋይ ነበር፡፡ ይህንንም ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ስለ ድሜጥሮስ ዂሉ ይመሰክሩለታል፤ እውነት ራሷም ትመሰክርለታለች፤ እኛም መስክረንለታል፤ ምስክርነታችንም እውነት እንደ ኾነች ታውቃላችሁ፤›› ሲል ይመሰክርታል (ቍ. ፲፪)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ እነዚህን ሁለቱን አገልግዮች ያነጻጸረውም መልእክቱን የሚልክለት ሌላው ረድዕ ቅዱስ ጋይዮስ አብነት ሊያደርገው የሚገባው ዲዮጥራጢስን ሳይኾን ድሜጥሮስን መኾን እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡ ‹‹ወንድሜ ሆይ፥ በጎ አድራጊ እንጂ ክፉ አድራጊ አትኹን፤›› ማለቱም ስለዚህ ነው (ቍ. ፲፩)፡፡

በዘመናችን ያለው የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት የገጠመው ኹኔታም ከዚህ ኹኔታ ጋር በእጅጉ እንደሚመሳሰል ስለምናምን፤ ማኅበሩም ለአባላቱና ለወዳጆቹ ብቻ ሳይኾን በቤተ ክርስቲያን ላሉ አገልጋዮች ዂሉ የሚያቀርበው ወቅታዊ የአዘክሮ መልእክት ይኼው ‹‹ወንድሜ ሆይ፥ በጎ አድራጊ እንጂ ክፉ አድራጊ አትኹን፤›› የሚለው የቅዱስ ዮሐንስን ምክር ነው፡፡ የሐዋርያት ዘመን አገልግሎት በሁለቱ ዓይነት ሰዎች የተያዘ ከነበር የእኛ ዘመን አገልግሎት ከዚያ የተሻለ ነገር እንዴት ሊገጥመው ይችላል? ፍቁረ እግዚእ (ጌታ የሚወደው) የተባለው፤ በክርስቶስ ዕለተ ስቅለት እንኳን ከእግረ መስቀሉ ሳይርቅ ከመከራ መስቀሉ ያልሸሸው፤ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስም ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን እያሰበ ፊቱን ለቅጽበትም ሳይፈታና ፈገግ ሳይል በፍጹም ዂለንተናው ያገለገለው፤ እኔ እስክመጣ ቢኖርስ ብሎ ጌታችን በቅርብ ሞትን እንደማያይ ቃል ኪዳን የገባለት፤ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያምን ‹‹እነኋት እናትህ›› ተብሎ ከእግረ መስቀል የተቀበለው ቅዱስ ዮሐንስ እስኪቸገር ድረስ ቤተ ክርስቲያንን ለፍላጎታቸው ብቻ የሚጠቀሙባት አገልጋዮች በዚያ ዘመን ከነበሩ ‹‹በእኛ ዘመን ለምን እንዲህ ያለ ነገር ኾነ?›› ብለን ልንደነቅበት የማይገባ እንደ ኾነ ለመረዳት የሚያስቸግር አይኾንም፡፡ በዚያው አንጻር ደግሞ እንደ ድሜጥሮስ እውነት ራሷ የምትመሰክርላቸው አገልጋዮች መኖራቸውን መዘንጋት ተገቢ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ዋናውና ለእኛ ለዂላችን የሚያስፈልገው ነገር ‹‹እኛ ልንመስለውና አብነት ልናደርገው የሚገባው የትኛውን ነው?›› የሚለው ሊኾን ይገባል፡፡

የቍጥር መለያየትና የፍሬ ነገሩ መለዋወጥ ካልኾነ በቀር ዛሬም እንደ ጥንቱ ወይም በየዘመናቱ ዂሉ በታሪክ እንደ ተመዘገበው በቤተ ክርስቲያን ሁለቱም ዓይነት አገልጋዮች ይኖራሉ፡፡ ጌታችንም በወንጌል ‹‹ያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በአንድ እርሻ ላይ ይኖራሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛዉንም ይተዋሉ፡፡ ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛዪቱንም ይተዋሉ፡፡ ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ላይ ይተኛሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛዉንም ይተዋሉ፡፡ እንግዲህ ትጉ፤ ጌታችሁ በምን ሰዓት እንደሚመጣ አታውቁምና፤›› (ማቴ. ፳፬፥፵-፵፪) በማለት እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ሁለቱም በእግዚአብሔር ቤት በአንድነት በአንድ የአገልግሎት መድረክ ላይ አንድ ዓይነት አገልግሎት እየፈጸሙ ለመኖራቸውና ለእግዚአብሔር የሚኾነውንና የማይኾነውን የሚለየውም እርሱ ራሱ በረቂቅ ፍርዱ እንደ ኾነ ገልጾልናል፡፡ ስለዚህም በአንዱ የወንጌል እርሻ ላይ እግዚአብሔር የሚወስደውና የሚተወው እንዳለ የሚያውቅ ባለቤቱ ስለ ገለጸልን የተጻፈውን ተረድተን፣ የጌታችንን ቃል ተቀብለን፣ በመኖሩ ከመደነቅ ወጥተን ልናደርገው ስለሚገባን ብቻ ማሰቡ ተገቢ ይኾናል፡፡ ቃሉ ዂላችንንም የሚመለከት የእውነትና የፍርድ ማስጠንቀቂያ ቃል ነውና፡፡

ስለዚህም በመግቢያው አንቀጽ ላይ እንደ ገለጽነው፣ ቅዱስ ጳውሎስን እንደ ገጠመው ዂሉ፣ በአሁኑ ጊዜም ወንጌልን ወይም ነገረ ቤተ ክርስቲያንን ለዓላማና ለጽድቅ የሚላላኩለት አሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ እውነተኞቹን አጥፍቶ ፍላጎትን አንግሦ የራስን አጀንዳ ለማራመድ የሚሯሯጡትም አሉ፡፡ እነዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ገለጸው የንጹሐኑን አግልግሎት ሳይቀር አገልጋዮቹን ለመክሰስና ለመወንጀል በየዘመናቱ ከሚኖሩ የጥፋት አካላት ጋር ወዳጅነትን ለመግዛትና ለመሳሰሉት ይጠቀሙበታል፤ ሕዝብንም ለመቀስቀስና ከራሳቸው ጋር ለማሰለፍ ይሠሩበታል፤ መልካሙን ነገር ለክፉና ለጥፋት እየተረጐሙ ያቀርቡበታል ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስን እንደ ገጠመውም ከቤተ ክርስቲያን ፍላጎት፣ ከሐዋርያት እና ከተላውያነ ሐዋርያት (ከሐዋርያት ተከታዮች) በጎ ምክር ይልቅ የራሳቸውን እና የእኔ የሚሉትን አካል ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ሊጠቀሙበት ይደክማሉ፡፡ ይህ የየዘመኑ ክሥተት እንደ ኾነው ዂሉ የእኛም ዘመን ትንሽና ደካማ አገልግሎት እንኳን ከዚህ ልታመልጥ አልቻለችም፡፡ ምንም እንኳን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ‹‹የእነርሱ ጥፋት፥ የእናንተም ሕይወት ይታወቅ ዘንድ የሚቃወሙን ሰዎች በማናቸውም አያስደንግጧችሁ፡፡ ይህንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቷችኋል፤ ነገር ግን ስለ እርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም፤›› (ፊልጵ. ፩፥፳፰-፳፱) ሲል እንደ ገለጸው የማይቀርና ዂሉም ነገር ልንቀበለው የሚገባ ቢኾንም አንዳንድ ጊዜ ግን ነገሩን ከሃይማኖት አንጻር ከማየት ወጥተን እንዳንገኝ ራስን መመርመሩ በእጅጉ የተገባ ነው፡፡

ምንም እንኳን ግብሩና ስሙ ብዙ የተራራቁ እንደ ኾኑ ጥናቶች ቢያመለክቱም የእኛ ዘመን የመረጃ ዘመን ነው ስለሚባል ኢንተርኔትን ተጠቅሞ በዋና መገናኛ ብዙኃንም ኾነ በየማኅበራዊ ሚዲያው የሚሠራጨውን ዂሉ አምኖና ተቀብሎ መሔድ ሳናውቀውም ቢኾን ወሬ ፈጣሪዎቹንና የጥፋት መልእክት አሠራጮችን ከመምሰል የሚያድን አይደለም፡፡ በማኅበራችን በማኅበረ ቅዱሳን ስም የሚሠራጩ አስመስለው ለሚከስሱና ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ለተንኮልና መከራ ለመጎተት ኾነ ብለው የሚሠሩትን ከመተባበርም፣ ለይቶ ለማየትም አስቸጋሪ ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ ለብዙዎች አያዳግትም፡፡ ማኅበሩ አቋሙን፣ መልእክቶቹንና ለሕዝበ ክርስቲያን ሊደርሱ ይገባቸዋል የሚላቸውን መረጃዎች ዂሉ በራሱ ይፋዊ ሚዲያዎች ወይም ደግሞ ማኅበሩን በሕግ በሚወክሉ አካላት የሚዲያ መግለጫዎች ብቻ የሚገልጽ ቢኾንም አንዳንዶች ግን እነዚህን ዂሉ ሳያጠሩና ሳይመረምሩ በማኅበሩ ስም ለክስ የሚያመቹ አድርገው የሚጽፉ አካላትን መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ሳይቀር እንደሚቀባበሉ፤ የማኅበሩን አገልግሎትና አሠራር ከሚረዱት ምእመናን የሚደርሱት ጥቆማዎች ያመለክታሉ፡፡

ስለዚህም ኾነ ብላችሁና በተንኮልም ባይኾን የማኅበሩ መልእክቶችና አቋሞች መኾናቸውን ከማኅበሩ አካላት ሳትጠይቁና ሳትረዱ፤ ነገሩንም ሳትመረምሩ በችኮላና በስሜት ምን አልባትም ከዚህ በፊት በነበራችሁ የተሳሳተ መረጃና ግምት ምክንያት ለተጻፉና በማኅበራዊ ሚዲያው በሚናፈሱት ዂሉ ማኅበሩን ለምትወቅሱ፣ ለምትተቹና ለምትሰድቡም ዂሉ ወደ ማኅበሩ ቀርባችሁ ኹኔታዎቹን ሳታጣሩና መረጃ ሳትቀበሉ መዘገባችሁን እንድታቆሙ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የሙያ ሥነ ምግባሩ የሚጠይቀውን ያህል እንኳ ሳትጓዙ ለመፈረጅ መቻኮላችሁ የሚያስገርም ኾኖም አግኝተነዋል፤ በሌላው ላይ የማታደርጉትን ማደረጋችሁን በግልጽ ያመለክታልና፡፡ አውቃችሁና ወዳጅ መስላችሁ ለራሳችሁ የተንኮልና የክስ ዓላማ እንዲጠቅማችሁ በማሰብ ይህን በማኅበሩ፣ በአባላቱና በወዳጆቹ ስም ስማቸው በይፋ በማይታወቁ አካላት ስም ይህን የምታደርጉትንም ቢኾን አይጠቅማችሁምና ከዚህ ድርጊታችሁ እንድትታቀቡ እውነትና ፍቅር በኾነው አምላካችን ስም እናሳስባችኋለን፡፡ ባለማወቅ እና ለማኅበሩ አገልግሎት የሚያግዝ እየመሰላችሁ ይህን የምታደርጉ አባላትም ኾነ ደጋፊዎች ካላችሁም እንደሚባሉት ያሉ የስድብና የጥላቻ መልእክቶች ማኅበሩን ሊጠቅሙ ቀርቶ የአገልግሎቱ አደናቃፊዎችንም ሊጎዱ ስለማይችሉ፤ ሊጎዱ እንኳ ቢችሉ በክርስትናችን የተከለከሉና የተወገዙ ስለ ኾኑ ከማድረግ እንድትቆጠቡ ለማሳሰብ፣ በሐዋርያው ቃልም  ‹‹ወንድሜ ሆይ፥ በጎ አድራጊ እንጂ ክፉ አድራጊ አትኹን፤››  ለማለት እንወዳለን፡፡

የማኅበሩ አባላትና ወዳጆቹ፣ እንዲሁም የአገልግሎት አጋሮቹና ተባባሪዎቹ ዂላችሁ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉልንን ምክሮች ከማዘከርና ዂልጊዜም ቢኾን ከክፉው ተጠብቀን መልካም የኾነውን አርአያና አብነት ከማድረግ ልንቆጠብ አይገባንም፡፡ በትንሹ እና ሕይወታችንን በሙሉ ሳይኾን ከትርፋችን የምናገለግላት ቤተ ክርስቲያናችን በምድር ላይ እንዳሉ ሌሎች ተቋማት የዚህ ዓለም አደረጃጀትና አሠራር ብቻ የሚመራት ምድራዊ ተቋም ሳትኾን ረቂቅነትን እና መንፈሳዊነትንም ገንዘብ ያደረገች አካለ ክርስቶስ እንደ መኾኗ መጠን የምንፈጽመው ዂሉ መንፈሳዊነት ከጎደለው፣ ርባና ቢስ መኾኑን ለአፍታም ቢኾን ልንዘነጋው የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ ለድርጊቶቻችን አብነት የምናደርገውም ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረው ብልሆቹን፣  መልካሞቹንና ደጎቹን እንጂ ሞኞቹን፣ ክፉዎቹንና ተንኮለኞቹን ሊኾን አይችልም፡፡ በዚያውም ላይ ከቅዱሳት መጻሕፍት ምክር ልንወጣ አይፈቀድልንም፡፡ ራሱ ጌታችን ‹‹ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ›› አለን እንጂ የተቃዋሚዎቻችን ሰይፍና ጎመድ ልንይዝ አልፈቀደልንም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ወገኖቻችንም ፍሬ ቢሶች እንዳይኾኑ፥ በሚፈለገውም ሥራ ጸንተው እንዲገኙ በጎ ምግባርን ይማሩ፤›› (ቲቶ. ፫፥፲፬) በማለት እንደ ገለጸው ከቤተ ክርስቲያን ወገን የኾናችሁ ዂሉ፣ በውጭ እንዳሉት ወደ ፍሬ ቢስነት ከሚወስድ ማንኛውም መንገድ ልትቆጠቡ ይገባችኋል፡፡

በእርግጥ ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ ‹‹በሕዝቤ መካከል ክፉዎች ሰዎች ተገኝተዋል፤ ሰዎችንም ይዘው ይገድሉ ዘንድ ወጥመድን ይዘረጋሉ፤›› (ኤር. ፭፥፳፮) ሲል እንዳመለከተን፣ በመካከል የተዘሩ አጥማጆችና ባለ ወጥመዶች ሊያሰነካክሉን፣ ስሜታችንን ሊያደፈርሱትና ወደ ወጥመዳቸው ሊያንደርድሩን በተለያየ ዘዴ ይገፉን ይኾናል፡፡ ኾኖም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ‹‹ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፥ ትበዙና ትጨምሩ ዘንድ እንማልዳችኋለን፡፡  የዋሃንም ትኾኑ ዘንድ፥ ሥራችሁንም ታከናውኑ ዘንድ፥ እንዳዘዝናችሁም በእጃችሁ ትሠሩ ዘንድ፥ በውጭ ባሉት ሰዎችም ዘንድ ከማንም አንዳች ሳትሹ በሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናችኋለን፤›› (፩ኛ ተሰ. ፬፥፲-፲፪) ሲል ያዘዘንን ቃል ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ፍጹም ዋጋ እንድታገኙ እንጂ የሠራችሁበትን እንዳታጡ ራሳችሁን ዕወቁ፤›› (፪ኛ ዮሐ. ቍ. ፰) በማለት እንደዚህ ዓይነት ክፉ ተግባር የቀደመ መልካም ተግባራችንን ዋጋ ጨምሮ የሚያጠፋ መኾኑን በማስታወስ ፈጽመን እንዳናደርገው ያስጠነቅቀናል፡፡ ምንም ያህል ፈተና እና መከራ ቢመጣም እኛ ልናደርገው የሚገባን በመልካም ሥራና ልናደርገው የሚገባውን በማደረግ መጽናት ብቻ ይኾናል፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሰዎች በመልካም ምግባር ዂሉ መረዳዳትን እንዲያስቡ ታጸናቸው ዘንድ እወዳለሁ፤ ሰውንም የሚጠቅመው በጎ ነገር ይህ ነው፤›› (ቲቶ ፫፥፰) ሲል ለቲቶ ያሳሰበውና ለዂላችንም የደረሰው፣ ጥቅም የሚገኘው በመንፈሳዊነትና በእውነት ኾኖ በመጽናት ብቻ ስለ ኾነ ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለውን ምክር የማይቀበሉና በራሳቸው ዐሳብ ሔደው ለቤተ ክርስቲያን ጥቅምና ረብ ማስገኘት የሚችሉ አስመስለው የሚናገሩ፤ ዐሳባቸውንም በአንዳንድ ጥቅሶች አስደግፈው በተቆርቋሪነት መንፈስ የሚገዳደሩአችሁ እንኳን ቢኖሩ፣ እንዲህ ያለውንም ፈተና በትዕግሥት እንድትወጡትና አሁንም በጎውን እንድትመርጡ እናሳስባችኋለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹‹እግዚአብሔር ወገኖቹን ያውቃቸዋል፤ የእግዚአብሔርንም ስም የሚጠራ ዂሉ ከክፉ ነገር ይርቃል› የሚለው ይህም ማኅተም ያለበት የእግዚአብሔር መሠረት ጸንቶ ይቆማል፤›› (፪ኛ ጢሞ. ፪፥፲፱) በማለት ለቅዱስ ጢሞቴዎስ ያሳሰበውም በእግዚአብሔር እና በቤተ ክርስቲያን ስም ሰዎች ያልተገባ ድርጊት ውስጥ እንዳይገቡ ለማስጠንቀቅ ነውና፡፡ ሐዋርያው እንደዚህ ያሉትን ሰዎች ከዚህም አለፍ ብሎ ‹‹እግዚአብሔርን እንደሚያውቁት በግልጥ ይናገራሉ፤ በሥራቸው ግን ይክዱታል፤ እነርሱም ርኩሳንና የማይታዘዙ፥ በበጎ ሥራም ዂሉ የተናቁ ናቸው፤›› (ቲቶ ፩፥፲፮) በማለት ድርጊታቸውን ከክህደት ይደምረዋል እንጂ ተቆርቋሪዎች ብሎ አያመሰግናቸውም፡፡ ይህን እውነት ተረድተናል የምንል ደግሞ ‹‹አሁንም ስለዚህ እናንተ እንደምታደርጉ ወንድሞቻችሁን አጽናኑ፡፡ አንዱም አንዱም ወንድሙን ያንጸው (፩ኛ ተሰ. ፭፥፲፩) በተባለው ቃል ተጠቅመን ልንተራረም እንጂ ልንተቻች አይገባንም፡፡ ቢቻል ቢቻል ‹‹ያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ምክንያት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን የታመነ ነበርና፥ ምንም በደል አልተገኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም፤››  (ዳን. ፮፥፬-፭) ተብሎ እንደ ተመሰከረለት እንደ ዳንኤል ሰበብ የለሽ እስከ መኾን መድረስ፤ ካልተቻለ ደግሞ ሊያስፈርድብን ከሚገባ ስሕተትና ጥፋት መቆጠብ ለክርስቲያን ዂሉ የሚገባው ተግባር ነው፡፡

ይህ ዂሉ ግን ክሶችንና ውንጀላዎችን ያስቀራል ማለት እንዳልኾነ የተጠቀሱት ጥቅሶች ለመጻፋቸው ምክንያት ከኾኑት ታሪኮች፣ ይልቁንም ከነቢዩ ዳንኤል ታሪክ የምንረዳው ነው፡፡ ኾኖም ክርስቲያኖች ይህን ዂሉ ሊያደርጉት የሚገባቸው በሌላ በምንም ምክንያት ሳይኾን ‹‹ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ፈተነንና ወንጌሉን ለማስተማር የታመን ስላደረገን እንዲህ እናስተምራለን፤ ሰውን ደስ ለማሰኘት እንደሚሠራም አይደለም፤ ልቡናችንን ለመረመረው ለእግዚአብሔር ነው እንጂ፤›› (፩ኛ ተሰ. ፪፥፬) ተብሎ እንደ ተጻፈው አገልግሎታችን እናገለግልሃለን የምንለውን እግዚአብሔርን ደስ ስለማሰኘት ብቻ ነው፡፡ ማኅበሩም ቢኾን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ልጆቼ በእውነት ሲሔዱ ከመስማት ይልቅ ከዚች የምትበልጥ ደስታ የለችኝም፤›› (፫ኛ ዮሐ. ቍ. ፬) ሲል እንደ ገለጸው አባላቱና ደጋፊዎቹ ብቻ ሳይኾኑ ክርስቲያኖች ዂሉ በእውነት ሲሔዱ ከማየት የተለየ ፍላጎት የለውም፡፡ ስለዚህም ይህ መልእክት የደረሳቸውንም ዂሉ ከታዘዙት በበለጠ እንዲፈጽሙት ይበረቱ ዘንድ ‹‹በመታዘዝህ ታምኜ፥ ካዘዝኹህም ይልቅ እንደምትጨምር ዐውቄ ጻፍኹልህ፤›› (ፊልሞና ፩፥፳፩) የሚለውን ቃለ ሐዋርያ እያስታወስን፤ በቃለ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በድጋሜ ‹‹ወንድሜ፣ ወዳጄ (አባል፣ ደጋፊ፣ ተባባሪ፣ ክርስቲያን ዂሉ) ሆይ፥ በጎ አድራጊ እንጂ ክፉ አድራጊ አትኹን›› በማለት ማኅበረ ቅዱሳን መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር!

ማኅበረ ቅዱሳን