ዶክተር ዐቢይ አህመድ

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡በተለያዩ አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች እንዲቆሙ ስለመጠየቅ

ጠቅላይ ሚኒስትር፡- አስቀድመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ የሀገር ግንባታ የነበራትን ታላቅ ሚና ተገንዝበው ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ሰላም ያረጉትን አስተዋጽኦ ሳናመሰግን አናልፍም፡፡

ይሁንና በአሁኑ ወቅት ይህን ደብዳቤ ለእርስዎ ለመጻፍ ያነሳሳን ዐቢይ ጉዳይ በሀገራችን በየጊዜው ድንገት በሚፈጠሩ ሁከቶችና ብጥብጦች ሁሉ ምክንያት ተፈልጎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ካህናቶቿና ተከታዮቿ ምእመናን የአደጋ ሰለባ እንዲሆኑ እየተደረገ መምጣቱ በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢና አፋጣኝ መፍትሔ በመንግሥት ሊሰጠው የሚገባው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

በየትኛውም ዓለም የሚኖሩ የእምነት ተቋማት ለሀገር ግንባታና ዕድገትም ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እንደዚሁ ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ የማይተካ ሚና እንደ ነበራት ግልጽ ነው፡፡ በሥነ ጥበብ፣ በኪነ ሕንፃ፣ በሥነ ሥዕል፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሕግ ቀረጻና ሀገራዊ ክብርና እሴትን በማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና የተጫወተች መንፈሳዊ ተቋም ናት። በረከታቸው ይደርብንና በሕይወት የተለዩን ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በተለያዩ ጽሑፎቻቸውና አባባሎቻቸው እንዳስቀመጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ጽሑፍ ከነፊደሉ፣ ነጻነት ከነክብሩ፣ ዘመን ከነቀመሩ፣ ሀገር ከነድንበሩ፣ አንድነት ከነጥብዓቱ ያስረከበች የኢትዮጵያ ባለውለታ ናት። ቀደም ሲል በክቡርነትዎም አንደበት እንደተነገረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሀገር ባለውለታ ከማለት ይልቅ ራሷን ሀገር አድርጎ መግለጽ የውለታዋን ታላቅነት በተሻለ ሁኔታ ያሳያል። ይህን የምታደርገው ደግሞ የሀገሪቱን ከፍተኛ ቁጥር የያዘ ሕዝብ የምትመራ እንደመሆኗ እንደ ሀገር ስለምታስብና ለሀገር ልማትና እድገት ትኩረት ሰጥታ ስለምትሠራ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም ።

ጠቅላይ ሚኒስትር

ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ያበረከተችው አስተዋጽኦና ውለታ ይህ ሆኖ ሳለ ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ እየተፈጸመባት ያለው ግፍ ከበጎነቷ በተቃራኒ ከመሆኑም በላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ በይዘቱ እየባሰና እየጨመረ በዐይነቱም ለመናገር እስከሚሰቀጥጥ ድረስ ዘግናኝ እየሆነ መጥቷል። ይህ ግፍ የተጀመረው ዛሬ ባይሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያጋጠሙ ያሉ ተደጋጋሚና ቀን ቆጥረው የሚፈጸሙ ጥቃቶች በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተበረታቱባት ይገኛሉ። በተለይም ጽንፍ የረገጠው የዘውግ ፖለቲካ ርእዮተ ዓለምና ኢትዮጵያን በጠላትነት የፈረጁ “የውጭ አካላትን” ሽፋን ያደረገ እንቅስቃሴ ግብ ቤተ ክርስቲያንን የማጥፋትና ለሀገር አንድነትና ነጻነት ያላትን ሚና መቀነስ እንደሆነ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ከሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዘው የመጡ የብዙ አካላት ፍላጎቶችም እንዲህ ዐይነት ቀውሶች እንዲፈጠሩ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም እንረዳለን። በሀገር ውስጥም የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት በሚለው ሃሳብ ላይ ዋልታ ረገጥ የሆነ አመለካከት በሚያራምዱ አካላት መካከል ያለው ውጥረትም ቀላል እንዳልሆነ እንገምታለን።

ይህም ሁሉ ሆኖ መንግሥት ችግሩን ለመፍታትና ምላሽ ለመስጠት ያሳየውን በጎና ቅን ሙከራዎችን ግን ሳንጠቅስ አናልፍም፡፡ ነገር ግን አሁንም ቤተ ክርስቲያን የጥፋት መልእክተኞች የጥቃት ዒላማ ሆና ትገኛለች፡፡ በዚህ ረገድ የሕግ የበላይነት ኖሮ ፍትሕ ማግኘት አለመቻል ከመንግሥትም በቂ ከለላ ሳታገኝ መቅረቷ በኦርቶዶክሳውያን አእምሮ ብሶትና እሮሮ ያስነሳ በመንግሥትም ላይ ትልቅ ጥርጣሬን የሚያጭር እየሆነ መጥቷል። ለዚህም በምሳሌነት ቀደም ያለውን እንኳ ትተን የቅርቡን ብናይ በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ በተነሳው ውዝግብና ከአክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ጥበቃ መነሣት ውዝግብ ጋር ተያይዞ በተቀሰቀሰው ረብሻ በቤተ ክርስቲያን፤ በአገልጋዮችና በምእመናን የተፈጸመውን ጥቃትና የደረሰውን ዕልቂት ማስታወስ ይበቃል፡፡ በአጠቃላይ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በጅግጅጋና አካባቢው ከተፈጸመው ጥቃት እስከ አሁን ቤተ ክርስቲያን ብዙ መከራን አስተናግዳለች። እርስዎ ከመጡ ጀምሮ በተረጋገጠ መረጃ መሠረት በትንሹ 25 አብያተ ክርስቲያን ተቃጥለዋል። ጅግጅጋ፣ ጅማ፣ ሲዳማ፣ ከሚሴ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ባሌና አርሲ በተፈጸሙ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ካህናትና ምእመናን በአሰቃቂ ሁኔታ በድንጋይ ተቀጥቅጠው፣ በእሳት ተቃጥለውና በገጀራ ተቆራርጠው ሕይወታቸውን አጥተዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሕፃናትንና አሮጊቶችን ጨምሮ ብዙ ሴቶች ተደፍረዋል። የብዙ ክርስቲያኖች ቤቶች ተቃጥለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸውና ከሀብት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በተለያዩ የሥነ ልቡና ጫናዎች ውስጥ ወድቀው በፍርሃትና በሥጋት የሚኖሩት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

ቀደም ሲልም የቤተክርስቲያን መቃጠልና ጥቃት ይቁም ብለው የተሰባሰቡና ለክቡርነትዎ ቀርበው ሃሳባቸውን ገልጸው እርስዎም በሰጡት ምላሽ ከክልሎች ጋር በመወያየት ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ብዙ ክልሎችም አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ግን ጉዳዩ ላይ ትኩረት አልሰጠም፤ ፍላጎትም አላሳየም፡፡ አሁን እንደሚታዩት አብዛኞቹ ችግሮች የተፈጸሙትና በመፈጸምም ላይ የሚገኙት በዚሁ ክልል ውስጥ ነው፡፡ ይህን የምንጠቅሰው ስለማያውቁት ሳይሆን እንዲህ ዐይነቶች ጥቃቶች እየተፈጸሙ በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ ሳይወሰድ ሲቀርና የዜጎች የደኅንነት ዋስትና አለመረጋገጥ ምን ማለት እንደሆነ ምንስ ያህል ከባድ እንደሆነ በኋላ የሚያስከትለውም አደጋ ከባድ እንደሆነ ለማሳሰብ ጭምር ነው።

በያዝነው ወርኃ ኅዳር ደግሞ የጥቃት ዒላማ ተረኛ የሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ናቸው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዙ ፍላጎቶች የሚስተናገዱባቸው፣ የሀሳብ ፍጭቶች የሚካሔዱባቸውና፣ ማኅበራዊ መስተጋብሮች የሚፈጸሙባቸው የልሕቀት ማእከላት ናቸው። በአግባቡ ከተያዙ ሀገርን ከድህነት የሚያወጡና ለሀገር ፈውስ የሚሆኑ ሊቃውንት የሚወጡባቸው፣ በአግባቡ ካልተያዙና ለጥፋ መልእክተኞች መሣሪያ ከሆኑ ግን ሀገርን የሚያጠፉ ትምህርትን በአግባቡ ያልተጠቀሙበት የጥፋት ዐርበኞች የሆኑ ትውልዶች የሚፈሩባቸው እንደሚሆኑ የታመነ ነው። ይህን እውነት ከግንዛቤ አስገብተን ስንመለከተው ለሀገር የሚበጅ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ለሕዝብ የሚቆረቆር የተማረ ዜጋ ማፍራት የሚቻለው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተረጋጋ የመማር ማስተማር ከባቢያዊ ሁኔታ መፍጠር ከቻሉ ብቻ ነው። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ አጥልቶ የሚታየው የጥቃት ድባብ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲማሩ ልጆቻቸውን የላኩ ወላጆችንም ሆነ ተማሪዎችን በተረጋጋ መንፈስ እንዲኖሩ የሚፈቅድ አይደለም። በአንዳንድ ቦታ አልፎ አልፎ እየተከሰቱ ያሉ አደጋዎችና ሁከቶች ወላጆችን ለከፍተኛ ሥጋትና ጭንቀት እየዳረጋቸው ነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተፈጸመ ያለው ጥቃትም ሃይማኖትን ማእከል ያደረገ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል። ስለሆነም መንግሥት በአጥፊዎች ላይ ርምጃ አለመውሰድን እንደ “ትዕግሥት” በመቁጠር ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በዝምታ መመልከቱ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ነውና የዜጎችን የመኖር መብትና የደኅንነት ዋስትና ማረጋገጥን መንግሥት በአግባቡ እንዲተገብረው እንጠይቃለን። ሰሞኑን እንደተመለከትነው ጥቃቶችና ግጭቶችን በእንጭጩ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይወጡ መቆጣጠር እየተቻለ ከትኩረት ማነስ ምክንያት ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ በምሥራቅና ምዕራብ ሐራርጌ ምእመናንና አብያተ ክርስቲያናት በሁለት ቀናት ብቻ የደረሰውን ጥፋት ዘርዝረን የማንጨርሰው ሆኖብናል፡፡

በመሆኑም በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች በሚዲያ እንደተገለጸው ከመንግሥት አቅም በላይ ካልሆኑ በአጭር ጊዜ ችግሮቹ እልባት እንዲያገኙ መደረግ አለበት፣ ካልተቻለ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተወሰነ ጊዜ ተዘግተው የማረጋጋት ሥራዎችን ሠርቶ እንደገና ማስጀመር እንደ አማራጭ መፍትሔ መታየት ይገባዋል ብለን እናምናለን። ከዚህም በተጨማሪ ጥቃቶችን እየፈጸሙና እያስፈጸሙ ባሉ አጥፊዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ በግልጽና ሁሉንም ዜጋ በሚያሳምን መልኩ መውሰድ ለዜጎች ደኅንነት ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን። ችግሩ አልፎ አልፎ ከኦርቶዶክሳውያን ውጭ የሚገኙትንም የሚያካትት ቢሆንም አሁን ግልፅ ሆኖ ግን የሚታየው ኦርቶዶክሳውያኑ ላይ እጅግ ያነጣጠረ የሰፋና የከፋም ነው፡፡ አስቸኳይ መፍትሔ ካልተገኘለትም ‘’ኦርቶዶክሳውያኑ በሁሉም አካባቢ የጥቃት ዒላማ ተደርገን እየተቆጠርን ያለነው እኛን ነን’’ በማለት የራሳቸውን ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ከፍተኛ መተላለቅንም ሊያስከትል ይችላል፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ሚዲያዎች አደጋዎችን በትክክል እንደመዘገብ እውነትን ማስተባበልና የተሳሳተ መረጃ ማስተላለፋቸው ደግሞ አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ ሆነ ተብሎ የሚወሰድ ርምጃና በአብዛኛውም ምእመንም ዘንድ መንግሥታዊ ሽፋን ያለው ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጎታል፡፡ በአጠቃላይ የችግሮቹ ሂደት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ጉዳዮች ከመፈጠራቸው በፊት መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እየጠየቅን በጉዳዩ ዙሪያ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ሆኑ ሃይማታዊ ተቋማት ሊሳተፉባቸው በሚገባቸው ኃላፊነቶች ሁሉ የድርሻችን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!