በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከማኅበረ ቅዱሳን ጽሕፈት ቤት የተላለፈ መልእክት

ማኅበረ ቅዱሳን በኢትያጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶሶ በ፲፱፻፷፬ ዓ.ም እውቅና አግኝቶ በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም በጸደቀለት ሕገ ደንብ መሠረት አገልግሎቱን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዐቢይ ተልእኮ የሆነውን የእግዚአብሔርን ወንጌለ መንግሥት በስፋት ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ እንዲዳረስ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል። በየጊዜው ያጋጠሙትን ፈተናዎችን በእግዚአብሔር ቸርነት በከፍተኛ ትጋትና ጽናት ያለፈ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ የሚያውቀው ሀቅ ነው።

ማኅበሩ ካሉት የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ አንዱ የብሮድካስት አገልግሎቱ ሲሆን በ፳፻፲፪ ዓ.ም የተጀመረው ይህ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያሰራጨው የወንጌል አገልግሎት በመላው ምእመን ዘንድ አማራጭ ሚዲያ ከመሆን አልፎ ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው የየዕለት ስንቅ በመሆን በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ እንደ ዐይን ብሌን የሚጠብቁት ሚዲያ ለመሆን በቅቷል።

የብሮድካስት አገልግሎት ልዩ ጥንቃቄ የሚሻ ሥራ ከመሆኑም በተጨማሪ ማኅበራችን አገልግሎቱን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና መንፈሳዊ ቅኝት የሚያከናውን በመሆኑ ሁል ጊዜም ተፈላጊ ጣቢያ መሆኑን ምእመናን ሁሉ የሚመሰክሩት እውነታ ነው።

በዚህ መነሻነት በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው ዐቢይ ኮሜቴ ያዘጋጀውን መግለጫ በማስተላለፋችን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ግንቦት ፲፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ “ጊዜያዊ እገዳ” ማድረጉን ገልጾልናል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለጊዜያዊ እገዳ የሰጠው ምክንያት ማኅበሩ ከተቋቋመለት ዓለማ ውጭ ሆኖ አግኝተነዋል የሚል ነው፡፡ ይህ ግን እንኳን ሊያሳግድ ይቅርና ጥያቄ ሊነሣበት የማይገባ ጉዳይ መሆኑን ማኅበሩ ይረዳል። የእግዱ ሂደትም የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን ያልተከተለና የሚዲያውን አገልግሎት በጸሎት፣ በገንዘብና በእውቀታችሁ በመደገፍ ሊዚህ ያበቃችሁትን ካህናት፣ ምእመናንና አባላትን ያሳዘነ መሆኑን ተረድተናል፡፡

በመሆኑም እግዱ የምእመናን ድምጽ የሚያፍን ብሎም ትምህርተ ወንጌልን የመማር መብታቸውን የሚገድብ መሆኑን በማሳወቅ ለሚመለከተው አካል አቤቱታውን በደብዳቤ አቅርቧል። አቤቱታውም በአግባቡና በሕጉ መሠረት ታይቶ በጎ ምላሽ እንደሚሰጠው ተስፋ እናደርጋለን። እንዲሁም ማኅበራችን ጉዳዩ የሕግ አግባብን ተከትሎ ውሳኔ እስከሚያገኝ አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን መላው ሕዝበ ክርስቲያን እንዲገነዘብልንና ይህንኑ በየጊዜው በይፋ የምናሳውቅ ስለሆነ በታላቅ ትዕግሥት አንዲጠብቅ እንጠይቃለን።

በዚህ አጋጣሚ መላው ሕዝበ ክርስቲያን ስለ ጉዳዩ በተፈጠረባችሁ ቁጭትና ከፍተኛ የቁጣ ስሜት የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስከበር ለምታደርጉት ተነሣሽነት ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ከፍተኛ ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን።

በተጨማሪም ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦቱ ርክበ ካህናት ስብሰባ ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ባደረገው ምልዓተ ጉባኤ ችግር ባለባቸውና አስፈላጊ በሆኑ አህጉረ ስብከቶች ፱ አዳዲስ ኤጴስ ቆጶሳትን በጥናት ለመሾም አስመራጭ ኮሜቴ መሰየሙ ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የምርጫ ሄደቱም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የተከተለ፣ ግልጽነት ያለው፣ ካህናትና ምእመናንን ያሳተፈ እንደሚሆን እንጠብቃለን፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!