በዓለ ጰራቅሊጦስ፣ ጾመ ሐዋርያትና ጾመ ድኅነት

ሰኔ ፲፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች ሰኔ ፲፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በዓለ ጰራቅሊጦስ በሚል ርእስ አቅርበነው የነበረውን ጽሑፍ ለንባብ እንዲያመች በዓለ ጰራቅሊጦስ፣ የጰራቅሊጦስ መዝሙርና ምንባባት፣ እንደዚሁም ጾመ ሐዋርያትና ጾመ ድኅነት በሚሉ ሦስት ንዑሳን አርእስት ከፋፍለን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

፩.በዓለ ጰራቅሊጦስ

*ጰራቅሊጦስ* የሚለው ቃል ከሦስቱ አካላት አንዱ ለኾነው ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መጠሪያ ስሙ ሲኾን፣ ትርጕሙም በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ናዛዚ (የሚናዝዝ)፣ መጽንዒ (የሚያጸና)፣ መስተፍሥሒ (የሚያስደስት) ማለት ነው፡፡ በዓለ ጰራቅሊጦስ በሌላ ቃል በዓለ ጰንጠቆስጤ በመባልም ይታወቃል፡፡ ይኸውም በግሪክ ቋንቋ በዓለ ኀምሳ፣ የፋሲካ ኀምሳኛ ዕለት፣ በዓለ ሠዊት (የእሸት፣ የመከር በዓል) ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፱፻፮ እና ፱፻፯/፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ፲፪ቱ ደቀ መዛሙርት፣ ፸፪ቱ አርድእት፣ ፭፻ው ባልንጀሮችና ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት በኢሩሳሌም ከተማ በአንድነት ኾነው ለጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ በሚያርግበት ጊዜም *እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፤* /ሉቃ. ፳፬፥፵፱/ ሲል ለሐዋርያቱ በገባላቸው ቃል መሠረት ባረገ በ፲ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፡፡

በሐዋርያት ሥራ እንደ ተጻፈው በበዓለ ጰራቅሊጦስ ማለዳ ኹሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው ሳሉ እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ድንገት ከሰማይ መጣና የነበሩበትን ቤት ሞላው፡፡ ከዚያም እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎች በኹሉም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ኹላቸውም መንፈስ ቅዱስን ከተሞሉ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ባደላቸው መጠን በየአገሩ ቋንቋዎች ኹሉ መናገር ጀመሩ /ሐዋ.፪፥፩-፬/፡፡ ጌታችን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት ይህ ዐቢይ በዓል ጰራቅሊጦስ ይባላል፡፡

ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ ከ፶ኛው፤ ከዐረገ ከ፲ኛው ቀን ጀምሮ እስከሚቀጥለው እሑድ ድረስ ያለው ወቅትም ዘመነ ጰራቅሊጦስ ተብሎ የሚጠራ ሲኾን፣ ይህ በዓል ካህናተ ኦሪት ዐሥራቱን፣ በኵራቱን፣ ቀዳምያቱን ይቀበሉበት ነበርና በብሉይ ኪዳን በዓለ ሠዊት ይባል ነበር፡፡ በበዓለ ጰራቅሊጦስም ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለውበታልና በበዓለ ሠዊት ምትክ በዓለ ጰራቅሊጦስ ገብቶበታል፡፡

የበዓለ ትንሣኤ መነሻው የአይሁድ የፋሲካ በዓል ማለትም በግብፅ እስራኤል ከሞት የዳኑበት የመታሰቢያ በዓል እንደ ኾነው ኹሉ፣ ለበዓለ ጰራቅሊጦስም መነሻው ይኸው የአይሁድ የፋሲካ በዓል ነው፡፡ የአይሁድ ፋሲካ ከተከበረ ከሰባት ሳምንታት በኋላ በ፶ኛው ቀን የሩቆቹ ከከተሙበት ወጥተው፣ የቅርቦቹ ከተሰባሰቡበት ተገናኝተው ለበዓሉ ፍጻሜ የሚኾነውን በዓለ ሠዊት ያከብሩ ነበር፡፡

ከግብፅ እስከ ከነዓን ምድር የደረሰው የእንስሳት መሥዋዕት ሲጠናቀቅ በ፶ኛው ቀን ይሰባሰብ የነበረው የአይሁድ ጉባኤም መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ዕለት ጀምሮ ተበትኗል፡፡ መሥዋዕተ ኦሪቱ በአማናዊው መሥዋዕት በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም እንደ ተለወጠ ኹሉ ጉባኤ አይሁድም በኢየሩሳሌም ከተማ በተሰበሰቡ በቅዱሳን ሐዋርያት ጉባኤ ተለውጧል (ተቀይሯል)፡፡ ይህችውም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ *ከኹሉ በላይ በምትኾን፣ ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን፤* እንዳሉ ሠለስቱ ምእት /ጸሎተ ሃይማኖት/፡፡

ሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወርዶ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትና ጸጋን አድሏቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላም በአእምሮ ጎልምሰዋል፤ ጥቡዓን (ቈራጦች)፣ ጽኑዓን ኾነዋል፤ ለስብከተ ወንጌል የሚፋጠኑበትንና ለሰማዕትነት የሚዘጋጁበትን ልቡና ታድለዋል፡፡ ቀድሞ ይናገሩት ከነበሩት ከዕብራይስጥ ቋንቋ በተጨማሪ ፸፩ ቋንቋዎች ተገልጸውላቸው ምሥጢራትን መተርጐም ጀምረዋል፡፡ ሐዋርያት በየገአሩ ቋንቋ ሲናገሩ የሰሙ ከአይሁድ ወገን አንዳንዶቹም ሐዋርያትን *ጉሽ ጠጅ ጠጥተው ሰክረው የኾነ ያልኾነውን ይቀባጥራሉ* ይሏቸው ነበር፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ዐሳባቸውን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ *ሰክረዋል የምትሉ እናንተ እንደምትጠራጠሩት አይደለም፡፡ ጊዜው ማለዳ፣ ሰዓቱም ገና ሦስት ሰዓት ነውና፡፡ ዳሩ ግን በነቢዩ ኢዩኤል ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ /ኢዩ.፪፥፳፰/ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ይህንን ድንቅ ተአምር ያደረገው እናንተ የሰቀላችሁት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤* በማለት ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት፣ ምሳሌ የመሰሉለት አምላክ ወልደ አምላክ መኾኑን፣ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን፣ ማረጉንና ዳግም በክብር በምስጋና መጥቶ በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈረድ መኾኑን እንደሚመሰክሩ በአይሁድ ፊት አሰምቶ ተናገረ፡፡

በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት የተማረኩ አሕዛብም *ምን እናድርግ* ብለው በጠየቁት ጊዜ ከክፋታቸው ተመልሰው፣ ንስሐ ገብተው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ ነገራቸው፡፡ በዚያችም ሰዓት ሦስት ሺህ ሕዝብ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል /ሐዋ.፪፥፩-፵፩/፡፡ ይህም ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ ያደረባቸው የማሳመን ጸጋና ተአምራትን የማድረግ ኃይላቸው እንደ በዛላቸው ያመላክታል፡፡

ይህ ዕለት ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የተሰጠበትና ብዙ ሺሕ ምእመናን የተገኙበት ዕለት በመኾኑ ሊቃውንት የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን በማለት ይጠሩታል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት *በዚህች ቀን በሦስት ሰዓት ኢየሱስ ክርስቶስ ጰራቅሊጦስን ልኮልናልና በላያችን ኃይልን ሞላ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን እንዳለው በአዲስ ቋንቋ ተናገርን፤* በማለት በዕለቱ ያዩትንና የተደረገላቸውን፣ እንደዚሁም ስለ በዓሉ ታላቅነት ከመሰከሩ በኋላ ይህንን በዓል ማክበር እንደሚገባ አዝዘዋል፤ በአንጻሩ በዚህ ወቅት (በበዓለ ኀምሳ) መጾምና ማዘን ተገቢ አለመኾኑንም ተናግረዋል /ዲድስቅልያ ፴፥፴፰-፴፱፤ ፴፩፥፷፱-፸/፡፡