ዘወረደ
ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም ካለው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በመነሣት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዚህ ዕለት ምስባክ ‹‹አዳምን ለማዳን ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤ የሰማይን ሥልጣን ያለው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም አላወቁም›› ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ ይህም ድርሰት በቤተ ክርስቲያናችን የጾም መጀመሪያ የሆነው ዕለተ ሰንበት ዋዜማ፣ መግቢያ (መሐትው) ሆኖ ከዋዜማ በፊት ምንጊዜም በየዓመቱ ይቆማል፤ ይዘመራል፤ ይመሰገናል ማለት ነው፡፡