ሆሣዕና

መምህር አብርሃም በዕውቀቱ

ሚያዚያ ፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ሆሼዕናህ ከሚለው በዕብራይስጥ ቃል የተገኘው ሆሣዕና ትርጉሙ እባክህ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል በዘመነ ብሉይ በቀደምት ነቢያት ዘንድ የተለመደ ቃል ነው፡፡ ‹‹አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፡፡›› (መዝ.፻፲፯፥፳፭-፳፮) የሆሣዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕፃናት ‹‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም›› በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡ በዓሉም ሆሣዕና የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዕለቱ ከተዘመረው መዝሙር ነው፡፡ (ዮሐ.፲፪፥፲፫)

በሌላ አነጋገር ይህ ዕለት ‹‹የጸበርት እሑድ ሆሣዕና›› ይባላል፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫ ሆኖ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ይኸውም ሣራ የወላድነት ዕድሜዋን ጨርሳ ልማደ እንስት ከተቋረጠባት በኋላ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ የጎበኟትን አምላክ አመስግነዋል፡፡ እስራኤል ከአስከፊው የግብፃውያን አገዛዝ ተላቀው ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ሲሻገሩ የተሰማቸውን እጥፍ ድርብ ደስታ በገለጡ ጊዜ እንዲሁም ዮዲት የተባለች ንግሥተ እስራኤል ሆሎፎርኒስ የተባለ አላዊ ንጉሥን ድል ባደረገች ጊዜ ቤተ እስራኤል እንደ ሰንደቅ ዓለማ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ዐደባባይ ወጥተው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በዘመነ ሐዲስም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ከዲያብሎስ ቁራኝነትና ከሲኦል ባርነት ነጻ ለማውጣት ወደ ዙፋን መስቀሉ በተጓዘ ጊዜ ሕፃናት እና አእሩግ ነጻ የሚወጡበት ቀን መድረሱን እነርሱ ሳያውቁ እግዚአብሔር ባወቀ ዘንባባ በመያዝ ዘምረዋል፡፡ (ሉቃ.፳፪፥፲፰) እስራኤል ዘንባባ በመያዝ እንዳመሰገኑት እኛም አስራኤል ዘነፍስ ዕለቱን ዘንባባ /ጸበርት/ በግንባራችን በማሰር በዓሉን በየዓመቱ እያስታወስን እናከብራለን፡፡ በዚህ ዕለት ዘንባባ እየተባረከ ለሕዝቡ ይታደላል፡፡

ሕፃናትና አእሩግ ‹‹ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል›› እያሉ ዘምረዋል፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲሆን በሌላ በኩል የነበረው አቀባበል ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ‹‹ሥርዓተ ኦሪትን፣ ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከተላለን›› ይሉ የነበሩ ጸሐፍት ፈሪሳውያን መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት፡፡ ጌታችንም መልሶ ‹‹እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ›› ሲል መልሶላቸዋል፡፡ ቅናት አቅላቸውን ያሳታቸው ፈሪሳውያንም የዋህ የሆነው ሕዝብ ምስጋና ወደ ጥላቻ እንዲለወጥ አድርገዋል፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው በዕለተ ሆሣዕና እሑድ ዘንባባ ይዘው የዘመሩለትን ጌታ በዕለተ ዓርብ ‹‹ይሰቀል ዘንድ ይገባል›› ማለታቸው ነው፡፡ (ማቴ.፳፩፥፱፣ሉቃ.፲፱፥፵)

ነገር ግን በዕለተ ሆሣዕና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ንጉሥነቱን አሥመስክሯል፡፡ በዚህም በነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡ ‹‹እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡›› (ዘካ.፱፥፱፣ማቴ.፳፩፥፬፣ማር.፲፩፥፩-፲፣ሉቃ.፲፱፥፳፰-፵፣ዮሐ.፲፪፥፲፭) ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲሆንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታም ‹‹እውነተኛ ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ›› ሲለን በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ሕይወታችን ተጉዟል፡፡

መላእክት በዕለተ ልደቱ ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል፤ በምድር ሰላም ለሰው ሁሉ ይሁን›› እያሉ የዘመሩለት የሰላም ባለቤት ነው፡፡ (ሉቃ.፪፥፲፫) በመዋዕለ ትምህርቱም ‹‹ሰላሜን እሰጣችኋለሁ›› ብሎ እንዳስተማረ ያን ሰላም የሚሰጥበትን ዕለት መቅረቡን ለማመልከት ነው፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፳፯) በሌላ በኩልም በአህያ ጀርባ መቀመጡ ኅቡዕ ምሥጢር አለው፡፡ በአህያ ጀርባ የተቀመጠ ሰው ሌላውን አሳድዶ አይዝም፤ እርሱም ሮጦ አያመልጥም፡፡ በዚህም ጌታችን በእምነት ለሚፈልጉት የሚገኝ ቅርብ ሲሆን በእምነት ለማይፈልጉት ግን የማይገኝ መሆኑን አስተምሯል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ፀሐይ ዕድሜያችን ሳትጠልቅ በእምነት እንፈልገው፡፡ የአህያን ጀርባ ያልናቀ ጌታችን ትሑት ሰብእና እና የተሰበረ ልቡና ወዳለው ሰው ዘወትር ይጓዛል፤ የተዋረደውንና የተሰበረውን ልብ አይንቅም፡፡ (ኢሳ.፷፮፥፪፣ መዝ.፶፥፲፯)

ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ ሰው የሆነ ጌታችን ከማሰሪያዋ በተፈታች አህያ እንደተቀመጠ ሁሉ ከኃጢአት እስራት በተፈታ ሕይወት ዛሬም ያድራል፤ የኅሊና ሰላምን ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ንስሓ ገብተን ጌታችንን ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› እያልን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ በዓሉ ከምንም በላይ የሚጠቅመን ለእኛ ነውና ።

ስለዚህ ይህን በዓል ስናከብር ሰላምንና ፍቅርን የእርሱን የክብር አመጣጥ እያሰብን ልንተገብረው ይገባል። ለጌታ የማያስፈልግ ፍጥረት የለም፤ ይልቁንም የክብር ዘውድ አድርጎ በመልኩ የፈጠረው ሰው ያስፈልገዋል። ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጠረ ማንም የለም። እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ዓላማና ዕቅድ የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን እግዚአብሔር የሚከብርበትን ሥራ ልንሠራ ይገባል። አህያ በሰው ሰውኛ ሲታይ የንቀትና የውርደት ሲመስል ይችላል። የአህያን ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ስንመለከት ግን በለዓም በሥጋዊ ገንዘብ መንፈሳዊ ዓይኑ ታውሮ እግዚአብሔር ያልረገማቸውን እስራኤላውያንን ሊራገም ሲሄድ ሕዝቡን እንዳይራገም ለመንገር ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው መልአክ በሚሄድበት መንገድ ላይ ቆሞ ሳለ ከበለዓም ይልቅ ያየችው የበለዓም አህያ ነበረች። አህያይቱም መልአኩን አክብራ መንገዱን እንደለቀቀችለት ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። (ዘኅ.፳፪፥፳፫)

በትንቢተ ኢሳያስ ‹‹ሰማይ ስሚ ምድርም አድምጪ፤ በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እሥራኤል ግን አላወቀም›› እንደተባለው ጌታ በተወለደ ጊዜ ትንቢቱን ምሳሌውን የሚያውቁ እሥራኤላውያን ባላወቁ ባለተቀበሉ ሰዓት በዚያ በብርድ ወራት እናቱ የምታለብሰው ልብስ አጥታ ቅጠል አልብሳው በነበረ ጊዜ ለጌታ ሙቀት የገበሩለት እረኞቻቸውን ተከትለው የመጡ ከበቶች ላሞችና አህዮች ናቸው። አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ‹‹ወአስተማወቅዎ አድግ ወላህም›› እንዳለው ነው። (ኢሳ.፩፥፫)

በሆሣዕና ዕለት ከሌሎች እንስሳት ይልቅ ጌታን በከብር የተሸከመችው አህያ ናት። አህያይቱም ከዚያ በፊት ያላየችውና ያልተደረገላት ክብር ተደርጉላታል። አህያ ከዚህ በፊት ለእኛ እህል ተሸክማ ስትሄድ ‹‹ሂጂ›› እያልን በዱላ እንደበድባት ነበር። ነገር ግን በሆሣዕና ዕለት እንኳን በዱላ ልትደበደብ ቀርቶ ሰዎች በእርሷ ላይ ለተቀመጠው ጌታ ሲሉ ልብሳቸውን ሁሉ እያነጠፉላት በንጣፍ ላይ ተራምዳለች።

ስለዚህ ክርስቶስ በአህያይቱ ላይ እንዲቀመጥባት ልብስም እንደ ተጎዘጎዘላት እኛም ጌታ በጸጋውና በረድኤቱ እንዲያድርብን ልባችንን ከኃጢአትና ከተንኮል አንጽተን ፍቅርንና ትሕትና ልንጎዘጎዝ ይገባል። ጌታ በእኛ ላይ በጸጋው ሲያድር በእርሱና በቅዱሳኑ ዘንድ ያለን ክብርና ጸጋ ታላቅ ነው። በነገር ሁሉ መከናወን ይሆንልናል። ክርስቶስን በመሸከሟ የአህያይቱ ታሪክ እንደተለወጠ ሁሉ በክርስቶስ ማደሪያነታችን ያለፈው መጥፎ ታሪካችን ይለወጣል። እንግዲህ በዕለተ ሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ሕዝቡ ሁሉ በደስታ በዝማሬ እንደ ንጉሥ እንደተቀበሉት እኛም ሐሴትን አድርገን ››ሆሣዕና እምርት እንተ አቡነ ዳዊት…›› በማለት እናመሰግናለን።

ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!