‹‹ልቤም በማዳንህ ደስ ይለዋል›› (መዝ.፲፪፥፭)

መምህር አብርሃም በዕውቀቱ

ሚያዚያ ፲፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በሰው ዘንድ የነበረውን መርገም በማጥፋት የሁሉም ፈጣሪ አምላካችን እግዚአብሔር ሞትን ድል አድርጎ ዓለምን አዳነ።  ትንሣኤ ሙታን በተባለው የሙታን መነሣትም ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው በመነሣት የዘለዓለማዊ ሕይወት መገኛ ጥበብ ወይም የድኅነት መንገድ ሆነልን፡፡

ሙታን በመጨረሻው ቀን ዳግመኛ በማይሞት ሥጋ ሕያዋን የሚሆኑበት አምላካዊ ጥበብ የሙታን መነሣት በሰው ልጅ አእምሮ ሊደርስበትና ሊታወቅ የማይችል ረቂቅ ስለሆነ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ምሥጢር ተስፋ የምናደርገው ሲሆን ክርስቶስ ዳግመኛ ከመጣ በኋላ ለሚኖረው ዘላለማዊ ሕይወት መጀመሪያ ነው፡፡ ትንሣኤ ሙታን በአዳምና በልጆቹ ላይ የተፈረደው የሞት ፍርድ ለመጨረሻ ጊዜ የሚጠፋበት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊትም ‹‹ልቤም በማዳንህ ደስ ይለዋል›› በማለት እንደተናገረው በኋላኛው ዘመን በትንሣኤው ሙታን መንግሥተ ሰማያትን እንደምንወርስ ተስፋ በማድረግ በአምላካችን ማዳን ሐሴት እናደርጋለን፡፡ (መዝ.፲፪፥፭)

በሐዋርያት እግር የተተኩና የእነርሱንም አሠረ ፍኖት የተከተሉ ሃይማኖታቸው የቀና ቅዱሳን አባቶች መናፍቃንን ባወገዙባቸውና ርትዕት ሃይማኖትን ባጸኑባቸው ጉባዔያት ሌሎቹን አንቀጾች ‹‹እናምናለን›› በማለት ካስቀመጡ በኋላ ‹‹የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን፤ የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ›› ብለው ደንግገዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ሌሎቹ አንቀጾች ‹‹እምነት›› ላይ ሲያተኩሩ ይህ ግን ‹‹ተስፋ›› መሆኑን ነው፡፡ ይህ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስንና የሐዋርያትን አስተምህሮ መሠረት ያደረገው የቤተ ክርስቲያናችን ጸሎተ ሃይማኖት (የሃይማኖት ጸሎት) የመጨረሻው አንቀጽ ነው፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹ልጁንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው። እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ» እንዳለው ትንሣኤ ሙታን የእምነታችን አንዱ መሠረት ነው፡፡ (ዮሐ.፮፥፵)

ከትንሣኤ በኋላ የሚኖረውም ዘለዓለማዊ ሕይወት ታላቅ ተስፋችን ስለሆነ ቅዱሳን አበው ‹‹የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ አሜን›› በማለት የሃይማኖት ድንጋጌውን ፈጽመውታል፡፡ ስለዚህ የዘለዓለም ሕይወት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ «ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን» በማለት ሲናገር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም «እኛ አገራችን በሰማይ ነውና። በዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርቶስን እንጠብቃለን። እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደ ሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል» ብሎ ዘላለማዊ ተስፋችንን አጽንቶልናል፡፡ (፪ጴጥ.፫፥፲፫፣ፊል.፫፥፳-፳፩) ባለራእዩ ዮሐንስም «አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርንም አየሁ፤ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና። ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ» በማለት ተስፋ መንግሥተ ሰማያት አዲሲቱ ኢየሩሳሌም መሆኗን ተራግሯል፡፡(ራእ.፳፩፥፩-፪)

ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ስለትንሣኤው ብዙ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱና ለሕዝቡ እንዲሁም ለፈሪሳዊያን ጭምር አስተምሯቸዋል፡፡ ‹‹እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል›› በማለት ስለትንሣኤው ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ፤በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀመዛሙርቱ በግልጥ ነግሯቸዋል፡፡ (ማቴ.፳፥፲፰-፲፱፣፲፮፥፳፩)

በገሊላም ሲመላለሱ «ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፤ ይገድሉትማል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል» ብሏቸዋል (ማቴ.፲፯፥፳)፡፡ «ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና፤ ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ» በማለት አስቀድሞ ተናግሮታል፡፡ (ዮሐ.፲፥፲፯) ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅም “በሦስተኛውም ቀን ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሐዳት›› ያለው በገዛ ሥልጣኑ መነሣቱን ሲገልጽ ነው፡፡ የትንሣኤው በኩርና የሰውን ልጅም የሚያስነሣ እርሱ መሆኑን ሲናገርም ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም» በማለት አረጋግጦልናል፡፡ (ዮሐ.፲፩፥፳፭-፳፮)

ትንሣኤ ሙታን አስቀድሞ ነቢያት ያስተማሩት ተስፋ ነው፡፡ ነቢዩ ዳንኤል ‹‹በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነሣሉ፤ እኩሌቶቹ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እኩሌቶቹ ወደ እፍረትና ጉስቁልና›› በማለት የሙታን ትንሣኤ መኖሩን ተናግሯል፡፡ (ዳን.፲፪፥፪) ነቢዩ ኢሳይያስም ‹‹ሙታን ሕያዋን ይሆናሉ፤ ሬሳዎችም ይነሣሉ፤ በምድርም የምትኖሩ ሆይ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ፤ ዘምሩም›› ብሎ በመጨረሻ ያንቀላፉት ሁሉ እንደሚነሡ በትንቢቱ አስተምሯል፡፡ (ኢሳ.፳፮፥፲፱) በተጨማሪም ነቢዩ ሕዝቅኤል ‹‹ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ። ጅማትም እሰጣችኋለሁ፤ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ፤ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ፤ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ›› በማለት ሙታን እንደሚነሡ አብራርቶ ተናግሯል፡፡ (ሕዝ.፴፯፥፩-፲) ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም እንዲሁ ‹‹ብዙ መከራና ጭንቀት አሳይተኸኛልና ተመልሰህ ሕያውም አደረከኝ፤ ከምድር ጥልቅም እንደገና አወጣኝ››  በማለት ስለ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ዘምሯል፡፡(መዝ.፸፥፳)

በሐዲስ ኪዳንም እንዲሁ ስለትንሣኤ ሙታን ጌታችን በወንጌል ሐዋርያትም በመልእክቶቻቸውና በስብከታቸው አጽንተው አስተምረዋል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ›› በማለት ሙታን ለክብርና ለአሳር እንደሚነሡ አስተምሯል፡፡ (ዮሐ.፭፥፳፰-፳፱) ስለነገረ ምጽአቱ በተናገረበት ክፍልም ‹‹የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል›› ብሎ ስለሙታን መነሣትና ስለመጨረሻው ፍርድ ነግሮናል፡፡ (ማቴ. ፳፭፥፴፩-፴፪) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን›› በማለት የሰው ልጅ በማይበሰብስ ሥጋ እንደሚነሣ በመልእክቱ ጽፎታል፡፡(፩ቆሮ.፲፭፥፶፪)

በዕለተ ምጽአት (ዳግም ምጽአት) የሚነሡት ጻድቃን የሚወርሱት መንግሥተ ሰማያትን ሲሆን ሲነሡ ብርሃን ለብሰው ብርሃን ተጎናጽፈው እንደ ፀሐይ እያበሩ ወንዶች የ፴ ዓመት ጎልማሳ ሴቶች የ፲፭ ዓመት ቆንጆ ሆነው ለዘለዓለም በደስታ በሕይወት ለመኖር የሚነሡት ትንሣኤ ነው፡፡ (ራእ.፳፩፥፩-፭፣፪መቃ.፲፫፥፰-፲፬) የ፴ ዓመትና የ፲፭ ዓመት መባሉ አዳምና ሄዋን ሲፈጠሩ የ፴ ዓመትና የ፲፭ ዓመት ሆነው ተፈጠሩ ብለው ሊቃውንት ከሚያስተምሩት ጋር በተመሳሳይ መልኩ ለሰው በሚገባ ቋንቋ ሙሉ ሰው መሆናቸውን ለማስገንዘብ እንጂ ከትንሣኤ በኋላ የሚቆጠር ዕድሜ ኖሮ አይደለም፡፡ ዕድሜ የሚቆጠረው በፀሐይ፣ በጨረቃ፣ በከዋክብት ነውና፡፡ ከዳግም ምጽአት በኋላ እነዚህ ሁሉ ፍጥረታት ስለሚያልፉ በማይቆጠር ዕድሜ እንኖራለን፡፡