እምቤተ ክህነት ወመንግሥት ዘኀረይዋ ይእቲኬ ማርያም ድንግል

           በዲ/ን ታደለ ሲሳይ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትኩረት አድርጋ የምታከብራቸው በርካታ የቅዱሳን በዓላት አሉ፡፡ የእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በዓላትም በቤተ ክርስቲያኗ ሰፊ ቦታ ተሰጥተው የሚከበሩ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህልም በየዓመቱ ግንቦት አንድ ቀን የሚከበረውን የቅድስት ድንግል ማርያምን የልደት በዓል መመልከት ይቻላል፡፡ ለሃይማኖታችን መሠረት፣ ለክርስትናችን ዋስትና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ስንቅ የሆኑት ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስረዱን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግንቦት 1 ቀን በ15 ዓ.ዓ  ቅድመ ልደተ ክርስቶስ መወለዷን እንረዳለን፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የእመቤታችን ልደት መስከረም 10 በማለት ያከብራሉ፡፡ ይህንንም የተኣምረ ማርያም መቅድም «ወቦ እለ ይቤሉ አመ ዐሡሩ ለመስከረም ልደታ፤ መስከረም 10 ቀን ልደቷ ነው የሚሉ አሉ» ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግን በዐዋጅ ግንቦት 1 ቀን ታከብረዋለች፡፡ ወላጆችዋም ኢያቄምና ሐና ይባላሉ፡፡ አባትዋ ኢያቄም ከቤተ ይሁዳ (ከይሁዳ ነገድ) ሲሆን፣ እናትዋ ሐና ከቤተ ሌዊ (ከነገደ ሌዊ) ናት፡፡ የተወለደችበት ሀገርም ናዝሬት ይባላል፡፡

       የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግን በዐዋጅ ግንቦት 1 ቀን ታከብረዋለች፡፡ ወላጆችዋም ኢያቄምና ሐና ይባላሉ፡፡ አባትዋ ኢያቄም ከቤተ ይሁዳ (ከይሁዳ ነገድ) ሲሆን፣ እናትዋ ሐና ከቤተ ሌዊ (ከነገደ ሌዊ) ናት፡፡ የተወለደችበት ሀገርም ናዝሬት ይባላል፡፡የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዘር ሐረግ ነገደ ይሁዳና ነገደ ሌዊ መሆኑን በተለያዩ ቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ እናገኘዋለን፡፡ ለአብነት ያህልም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ «ትወጽእ በትር እምሥርዎ እሴይ ወየዐርግ ጽጌ ይእቲ በትር አምሳለ ማርያም ቅድስት ይእቲ ወጽጌ ዘይወጽእ እምኔሃ አምሳሉ ለወልድ……..” በትር ከእሤይ ሥር ትወጣለች አበባም ከእርስዋ ይወጣል፤ በትር የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት» በማለት እመቤታችን ከዳዊት ዘር መሆንዋን ይገልጻል፡፡ ይህንንንም ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ « አንቲ ውእቱ ዘመድ ዘእምሥርወ ዳዊት፤ ከዳዊት ዘር የተገኘሽ ዘመድ አንቺ ነሽ» ሲል ያጠነክረዋል፡፡ «በሩካቤ ዘበሕግ እለ ወለድዋ እምቤተ ክህነት ወመንግሥት ዘኀረይዋ ይእቲኬ ማርም ድንግል፤ በሕጋዊ ሩካቤ የወለዱአት ከቤተ ክህነት እና ከቤተ መንግሥት የመረጡአት ድንግል ማርም ናት» በማለት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ከቤተ መንግሥትና ከቤተ ክህነት መመረጧን ይገልጻል፡፡ (ድጓ ዘነሐሴ)
ወደ ጥንተ ነገራችን ስንመለስ፣ ኢያቄምና ሐና በመጀመሪያ ልጅ መውለድ ተስኖአቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ልጆች ባሏቸው ሰዎች ሁሉ መንፈሳዊ ቅንዓት ያድርባቸው ነበር፡፡ በመዝሙረ ዳዊት «ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው» (መዝ. 126÷3) ተብሎ ስለተጻፈ ልጅን መመኘት መንፈሳዊ ፍላጎት ነውና ኢያቄምና ሐናም አጥብቀው ይሹ ነበር፡፡ የኢያቄምና የሐና ልጅ ማጣት ግን እጅና እግራቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ አላደረጋቸውም፡፡ ይልቁንም «አንኳኩ ይከፈትላችኋል» እንደተባለው እግዚአብሔር አምላክ በቸርነቱ በልጅ ይጎበኛቸው ዘንድ አጥብቀው ይጸልዩ ነበር እንጂ፡፡ (አንዳንድ ሰዎች በትዳር ሕይወታቸው ልጅ መውለድ በተሳናቸው ጊዜ እንደ ሐናና ኢያቄም በጸሎት ከመትጋት ይልቅ መከነች መከነ ብዬ ላልክድሽ ላልክድህ ተባብለው የገነቡትን ትዳር ወደማፍረስ መሄዳቸው የሐናንና የኢያቄምን መንፈሳዊ የትዳር ተሞክሮ አለመቅሰም ነው፡፡) ጸሎታቸውም የሚጦረን፣ የሚንከባከበን፣ ርስታችንን የሚወርስልን ልጅ ስጠን ሳይሆን፣ ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያስደስት፣ ለቤተ እግዚአብሔር የሚገባ፣ አንተን የሚስደስት ልጅ ስጠን የሚል ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በልጅ ቢጎበኛቸው ልጃቸውን ለእግዚአብሔር እንደሚሰጡ ተሳሉ፡፡
ከዚህም በኋላ የለመኑትን የማይነሳ፣ የነገሩትን የማይረሳው ልዑል እግዚአብሔር የሐናን ማኅጸን በጽንስ ጎበኘው፡፡ ይህም የሆነው ነሐሴ ሰባት ቀን ነው፡፡ ከዚያም ግንቦት አንድ ቀን፣ እሙ ለፀሐየ ጽድቅ፣ መድኃኒታ ለሔዋን፣ የኖኅ ቃልኪዳን፣ የአዳም ተስፋ፣ ላዘኑ መጽናኛቸው፣ ለተሰደዱ ተስፋቸው፣ ለተራቡ ምግባቸው፣ ለታረዙ ልብሳቸው፣ ንጽሕት በድንግልና ሥጋ ወሕሊና የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች፡፡ጽንሰቷም ሆነ ልደቷ ርኩሰት የሌለበት፣ በቅድስና የተመላ፣ በሕግ የጸና ነው፡፡ «ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በጢአት ፍትወት (በዝሙት በርኩሰት) የተፀነስሽ አይደለሽም፤ በሕግ፣ በሩካቤ፣ በሥርዓት ከሐናና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጅ» እንዳለ (አባ ሕርያቆስ፤ ቅዳሴ ማርያም

         የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ ለጊዜው ደስታው ለኢያቄምና ሐና ቢሆንም በመጨረሻ ግን ለዓለም ነው፡፡ እመቤታችን በመጀመሪያ ለኢያቄምና ሐና ብትሰጥም ፍጻሜው ግን የዓለም ስጦታ ናት፡፡ ምክንያቱም የድኅነታችን ዘውድ ናትና፡፡ (ቅዳሴ ማርያም)
አዳምና ሔዋን ትእዛዘ እግዚአብሔርን ተላልፈው የሞት ሞት በተፈረደባቸው ጊዜ እግዚአብሔር ተስፋ የሰጣቸው ከልጅ ልጃቸው ተወልዶ እንደሚያድናቸው ነው፡፡ ይህም በብሉይ ኪዳን በትንቢት ሲነገር ነበር፡፡ በትንቢተ ኢሳይያስ ላይ በትር ከእሴይ ግንድ ይወጣል ተብሎ የተነገረው ትንቢትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዓለምን መድኅን ለመውለድ እንደምትወለድ የሚገልጽ ነበር፡፡ (ኢሳ. 11÷1) ከላይ እንደተገለጸው የአዳም የልጅ ልጅ የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ይህንን ቃል ኪዳን ሲሰጣቸው አዳምና ሔዋን በተስፋ መኖር ጀምረዋል፡፡ በኋላም ግንቦት አንድ ቀን እመቤታችን ስትወለድ የአዳም የድኅነት ቀን መድረሱ ታውቋል፡፡ ለዚህም ነው አባ ሕርቆስ «አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት፤ ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ» (ቅዳሴ ማርያም) ያለው፡፡ ከገነት ተባሮ በረከቱን ሲገፈፍ የተሰጠው ቃል በእርሷ መወለድ እንደሚድን ነበርና፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ሲለው፣ ለድኅነቱ ምክንያት የሆነች የልጅ ልጁን መወለድ ተስፋ ያደርግ ነበርና፣ ምክንያተ ድኂን ቅድስት ድንግል ማርያም መወለዷ ለአዳምና ለልጆቹ ትልቅ ክብርና የብርሃን ተስፋ ነው፡፡
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ ለአዳም መዳን ምክንያት እንደሆነ ሁሉ ለሰው ልጆች፣ እንዲሁም በኃጢአት ለተወሰደው ዓለም ሁሉ ከኃጢአቱ ነጽቶ በሥራው ገነት መንግሥተ ሰማያትን ይወርስ ዘንድ የሚችልበት መንገድ የተጠረገበት ነው፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ ቀዳማዊ አዳምና ቀዳሚት ሔዋን በሠሩት ጥፋት የመጣው ሞት የተሻረው በዳግሚት ሔዋን (በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም) መወለድና ዳግማዊ አዳምን (መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን) በመውለድ ነውና፡፡ ሔዋን ያመጣችው መርገም በእመቤታችን ቀርቷል፤ አዳም ያመጣው ሞት በክርስቶስ ድል ተደርጓልና፡፡የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት በድቅድቅ ጨለማ የነበረው ዓለም ብርሃንን ያየበት ነው፡፡ ዓለም ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ያህል በዲያብሎስ ቁራኝነት፣ በኃጢአት ሞት ጨለማነት፣ ተይዞ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህን ጨለማ ለማስወገድም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ኆኅተ ምሥራቅ ሆና፣ በእርሷም ፀሓየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ወጥቶ ለዓለም ሁሉ ብርሃን ሆኖአል፡፡ «ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኩሉ ሰብእ ለእለ ይነብሩ ውስተ ዓለም፤ በዓለም ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን እርሱ ነው» እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም በሰኞ ውዳሴ ማርያም፡፡
እኛም ብርሃንን ወልዳልናለችና እሙ ለብርሃን፣ የዓለም ፀሓይ ከእርሷ ተገኝቷልናልና ኆኅተ ምሥራቅ፣ ለመዳናችን ምክንያት ናትና ምክንያተ ድኂን፣ የአዳም ተስፋው ናትና ተስፋሁ ለአዳም እያልን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት እናከብራለን፡፡የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው ዲያብሎስ ክብረ ድንግል ማርያምን ደብቆ ለማስቀረት ደፋ ቀና ቢልም፣ እኛ ግን ብርሃንን አይተንባታልና ልደቷን እንደ አባቶቻችን በማኅሌት፣ በቅዳሴና በሌሎች አገልግሎቶች እያከበርን «ዮም ፍስሓ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ልደት አማካኝነት ዛሬ በዓለም ሁሉ ደስታ ሆኗል» እያልን እንዘምራለን፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በረከትና ረድኤት ይክፈለን አሜን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር