የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፰

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፰ ቀን ፳፻፲ .

ለ. ምንኵስና

ምንኵስና፣ ‹መንኰሰ – ሞተ› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲኾን ትርጓሜውም ሥጋዊ ስሜትን መግደልን (ማሸነፍን) ያመላክታል፡፡ ይኸውም ሥጋዊ ስሜትን በመግታት ራስን የመንፈስ ደሃ ማድረግን፤ ምድራዊ ደስታን በመናቅ ለሰማያዊው መንግሥት መዘጋጀትን የሚያጠይቅ ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ብልና ዝገት በሚያጠፉት፣ ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፡፡ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤” በማለት ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ሰማያዊ ዋጋ እንደሚያስገኝ ተናግሯል (ማቴ. ፮፥፲፱-፳)፡፡ ምንኵስና፣ ጌታችን የሰጠውን ይህን ተስፋ መሠረት በማድረግ አባቶችና እናቶች በብሕትውና (በብቸኝነት) የሚኖሩበት ሕይወት ሲኾን፣ ይኸውም ምድራዊውን ተድላና ደስታ የሚያስተው፤ ከሥጋ ጥቅም ይልቅ ለነፍስ የሚያደላ የቅድስና ኑሮ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ምንኵስና፣ ቍምስናንና ጵጵስናን የመሰሉ የክህነት መዓርጋትን ለመቀበል አንደኛው መሥፈርት ነው፡፡ ስለዚህም አንድ ዲያቆን በሕግ ተወስኖ (ሚስት አግብቶ) መኖር ካልፈለገና በቍምስና ወይም በኤጲስ ቆጶስነት ከፍ ሲልም በጵጵስና የማገልገል ዓላማ ካለው ቅስና ከመቀበሉ አስቀድሞ መመንኰስ ግድ ይለዋል፡፡ ሚስት ማግባትን ከመረጠ ግን ከቅስና መዓርግ ባለፈ ለኤጲስ ቆጶስነትም ለጵጵስናም ሊበቃ አይችልም፡፡ ኾኖም ምንኵስና፣ ለደናግል ብቻ ሳይኾን ለመዓስባንም ማለትም ትዳር መሥርተው ለኖሩ ምእመናንም ይፈቀዳል፡፡ የተቻላቸው ከሴት ጋር ሳይተዋወቁ (ትዳር ሳይመሠርቱ) በድንግልናቸው እንደ ጸኑ ይመነኵሳሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ጋብቻ መሥርተው ከቆዩ በኋላ በሞት ወይም በሌላ ምክንያት ከትዳር አጋራቸዉ ጋር ቢለያዩ መመንኰስ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ይህ የሚኾነው ፈቃደ ሥጋቸዉን (የፍትወት ስሜታቸዉን) ለማሸነፍ ከቻሉ ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛ የማግባት ፍላጎቱ ያላቸው ወገኖች ግን እንዲመነኵሱ አይገደዱም፡፡

ወደ መነሻ ርእሳችን ስንመለስ ፍቺ ከሚፈቀድባቸው መንገዶች አንደኛው ምንኵስና ነው፡፡ ይኸውም በፍትሐ ነገሥት እንደ ተገለጸው ባልና ሚስት “አይበላስ የለም፤ አይጠገብ ይባስ” ብለው በፈቃዳቸው ለመመንኰስ ሲወስኑ ነው፡፡ ውሳኔው ግን የሥጋ ስሜትንና የቤተሰብ ኹኔታን ባገናዘበ መልኩ መኾን አለበት፡፡ ምክንያቱም አንዳቸው ለመመንኰስ ፈልገው አንዳቸው ፈቃደኛ ካልኾኑ ወይም ልጆችን የሚረከብና የሚያሳድግ ሰው ከሌለ ቤተሰብን በትኖ መመንኰስ ተገቢ አይደለምና፡፡ ሁለቱም ጥንዶች ፈቃደ ሥጋ ጠፍቶላቸው ከኾነ፣ ልጆቻቸዉን የሚያሳድግላቸውም ከተገኘ (ወልደው ከኾነ) ተመካክረው መመንኰስና መለያየት ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ጋብቻ ይፈርሳል (ፍቺ ይፈቀዳል)፡፡ ከዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባን ቁም ነገር ከመነኰሱ በኋላ ወደ ጋብቻ መመለስ በፍጹም አይፈቀድም፡፡ ስለዚህም ያላገባንም ኾነ ያገባን ሰዎች በስሜታዊነት ተነሣሥተን ፈቃደ ሥጋችንን በትክክል ሳናዳምጥ መመንኰስ የለብንም፡፡ የምንኵስና ሕይወት ከገቡ የማይወጡበት የመላእክት ሥርዓት ነውና፡፡

ሐ. ሞት

መፋታት የሚፈቀድበት ሌላኛውና ዋነኛው መንገድ ሞት ነው፡፡ ሞት ለሰው ልጅ የማይቀር ጥሪ ነውና ባልና ሚስት ተስማምተው እየኖሩ ሳሉ ከሁለት አንዳቸው በሞት ሊለዩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለተኛ ጋብቻ (ፍቺ) ይፈቀዳል፡፡ በሕይወት የቀረው ወገን ለብቻው መኖር ከተቻለው ራሱን ጠብቆ ቢኖር መልካም ነው። ፍትወትን መጠበቅ ካልተቻለ ግን ለሁለተኛ ወይሜ ለሦስተኛ ጊዜ ማግባት ይፈቀዳል፡፡ የትዳር አጋር በሞት ከተለየ በኋላ በሕይወት ያለው ወገን ከጋብቻ ሕግ ነጻ ነውና፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚኾነን የሚከተለው የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ነው፤ “ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በሕግ ታስራለችና፤ ባልዋ ቢሞት ግን ስለ ባል ከኾነው ሕግ ተፈታለች፡፡ ስለዚህ ባልዋ በሕይወት ሳለ ለሌላ ወንድ ብትኾን አመንዝራ ትባላለች፤ ባልዋ ቢሞት ግን ከሕጉ አርነት ወጥታለችና ለሌላ ወንድ ብትኾን አመንዝራ አይደለችም … ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይኹን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት” (ሮሜ. ፯፥፪፤ ፩ኛ ቆሮ. ፯፥፲፩-፴፱)፡፡

መ. ሌሎች መንገዶች

ከዝሙት፣ ከምንኵስና እና ከሞት በተጨማሪ በተፈጥሮ ወይም በድንገተኛ ምክንያት የመራቢያ አካላትን ጤንነት የሚያውክ ደዌ ወይም ሌላ ችግር ከተከሠተ ፍቺ እንደሚፈቀድ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል፡፡ ለምሳሌ የአባለ ዘርዕ መሰለብ ካጋጠመ፣ ሩካቤ ሥጋ መፈጸም ካልተቻለ ማለት የመራቢያ አካላት ለሩካቤ ሥጋ ብቁ ካልኾኑ ለአንደኛው ደኅነትና ደስታ ብሎም ሰላማዊ ሕይወት ሲባል መፋታት ይቻላል፡፡ ከዚሁ ዂሉ ጋርም አንዱ በሌላው ሕይወት ላይ ለሞት የሚያበቃ በደል ወይም ድብደባ በየጊዜው የሚፈጽም ከኾነ፤ ከዚህ ክፉ ልማድም በምክር ካልተመለሰ፤ እንደዚሁም አንደኛው ወገን ሃይማኖቱን ከለወጠና አልመለስም ካለ መፋታት ይፈቀዳል፡፡ ከዚህም ሌላ አንደኛው ወገን ባልታወቀ ምክንያት ከአገር ቢጠፋና ባይመለስ አንደኛው አካል ለአምስት ዓመታት ከጠበቀ በኋላ ሌላ ማግባት ይችላል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የዕድሜ ልክ ወይም የብዙ ዓመታት እስራት ቢፈረድበትና አንደኛው ወገን መታገሥ ካልቻለ ከንስሐ አባት ጋር ተመካክሮ ፍቺ መፈጸምና ሌላ ማግባት ይቻላል፡፡ እንደዚሁም አንደኛው አካል ወደ ውትድርና ሔዶ መሞቱ በምስክር ከተረጋገጠ፣ ከሞተ ከአንድ ዓመት በኋላ ያልሞተው ወገን ሌላ ትዳር መመሥረት ይችላል፡፡ ከላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች መፋታትና ሁለተኛ ጋብቻን መመሥረት ቢቻልም ከመለያየት በፊት ችግሮችን በውይይት ለማስተካከልና ለመስማማት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባን መዘንጋት የለብንም፡፡ ምክንያቱም ‹‹መፋታት ይፈቀዳል›› በሚል ሰበብ በሚረባውም በማይረባውም ጉዳይ ጋብቻን ማፍረስ ተገቢ አይደለምና፡፡

ግጭት፣ ሐሜት፣ አሉባልታ፣ ጭቅጭቅ፣ ቅናት፣ ሱስና የመሳሰሉ ጎጂ ልማዶች ጋብቻን ከሚፈታተኑ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ልማዶች የትዳር ሕይወትን አሰልቺ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ለፍቺ የሚያበቁ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም በሁለቱ ጥንዶች መካከል ውስጣዊ መናበብ ካለ ለችግሮቹ መፍትሔ ማምጣት ይቻላልና፡፡ ለዚህም መፍትሔው ከጸሎት ቀጥሎ የችግሩን መንሥኤ በትክክል መረዳትና መውጫ መንገዱን መፈለግ ነው፡፡ በመሠረቱ በጋብቻ ሕይወት የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን እንደ መልካም አጋጣሚ መውሰድ እንችላለን፡፡ እንዴት ከተባለ የትዳራችንን መሥመር ለማስተካከል በምናደርገው ጥረት ውስጥ ልዩ የፍቅር ጕዞ ልንጀምር ስለምንችል፡፡ ለምሳሌ ከጥንዶች አንዱ እያመሸ የሚገባ፣ በሱስ የተጠመደ፣ የሚጨቃጨቅ፣ የሚሳደብ፣ ወዘተ ከኾነ ከመቈጣትና ከማጥላላት ይልቅ ከዚህ ልማድ እንዲወጣ ልዩ ክብካቤ ማድረግ ውጤቱ ጥሩ ይኾናል፡፡ ይህም ትዳሩን ይበልጥ እንዲወድና ራሱን እንዲያይ ሊያግዘው ይችላል፡፡ ፍቅር፣ የጠብ ዂሉ መድኀኒት ናትና፡፡

በአጠቃላይ የመጀመሪያ ጋብቻን ማፍረስና ሁለተኛ ወይም ከዚያ በላይ ማግባት ባይፈቀድም ሃይማኖትን የሚያስክድ፣ ሩካቤ ሥጋን የሚከለክልና ለሕይወት የሚያሠጋ ይኸውም ሊቀረፍ የማይችል ችግርና ጭንቅ ከመጣ መፋታት ተፈቅዷል፡፡ ፍቺ የሚፈቀድባቸው መንገዶችም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፳፬፣ ከቍጥር ፱፻፵-፱፻፶፰ ተዘርዝረዋል፡፡ በዚህ መሠረት ጋብቻ እንደ አስፈላጊነቱና እንደ ኹኔታው እስከ ሦስት ጊዜ ድረስ ሊፈቀድ ይችላል፡፡ ከዚያ በላይ ግን እንደ ርኵሰት ይቈጠራል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን የመሰለ ችግር ካልመጣ በቀር ቀላ (ቀላች)፤ ጠቈረ (ጠቈረች) ከሣ (ከሣች)፤ አጠረ (አጠረች)፤ ቀጠነ (ቀጠነች)፤ ደኸየ (ደኸየች) ብሎ ትዳርን ማፍረስ ተገቢ አለመኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምራሉ፡፡ ሕመም ቢያጋጥም ማስታመም፣ ድህነት ቢመጣ አብሮ ማሸነፍ፣ ፈተና ቢበዛ በጋራ ድል ማድረግ እንጂ ትዳርን በየሰበቡ ማፍረስ ክርስቲያናዊ ምግባር አይደለምና፡፡

ይቆየን