ታኅሣሥ 8 ቀን 2005 ዓ.ም.
ሪፓርታዥ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማሳካት የገማት ድርሻ በሚል መሪ ቃል ማኅበረ ቅዱሳን ባዘጋጀው ዐውደ ጥናት ላይ ለመገኘት ከ65 ገዳማት የመጡ አበምኔቶችና እመምኔቶች ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጠዋት በማኅበሩ ሕንጻ ላይ ስለ ማኅበሩ ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል በተዘጋጀው መርሐ ግብር ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ከስዓት በኋላ በዐውደ ጥናቱ ላይ ለመገኘት በተዘጋጀላቸው መኪና ከማኅበሩ ዋና ጽሕፈት ቤት ወደ ኢትዮጵያ ስብሰባ ማእከል አዳራሽ ያመሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ስብሰባ ማእከል እንደደረሱ በማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን በዝማሬ በመታጀብ ወደ አዳራሹ ገብተዋል፡፡ በአዳራሹ ውስጥ የተገኙ ምእመናን በእልልታና ዝማሬ አቀባበል በማድረግ ገዳማውያን አባቶችም እጅ እየነሱና ምእመናን እየባረኩ ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ በማምራት ቦታቸውን ያዙ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበር ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን እንደተገኙም ዐውደ ጥናቱ ተከፍቷል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክታቸውን ለማስተላለፍ መድረኩን የተረከቡ ሲሆን በመልእክታቸውም ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ጥንታዊ ገዳማት ላይ እየደረሰ ያለውን ልዩ ልዩ ችግሮች ለመታደግና የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ያሉባቸውን ሁኔታ ለማጥናትና አግባብ ያለው መፈትሔ ለመስጠት መርሐ ግብር ነድፎ ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ከ100 በላይ ፕሮጀክቶች የተተገበሩና በመተግበር ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ስብሰቢው በ145 አብነት ትምህርት ቤቶች ለ136 መምህንና ለ988 የአብነት ተማሪዎች ቋሚ ወርኀዊ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ለገዳማት አበምኔቶችና እመምኔቶች ጥሪ የተደረገበትንም ምክንያት ሲገልጹ “ገዳማት ራሳቸውን እንዲችሉ በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል፤ ገዳማት ከገዳማት ጋር ያላቸውን ትሥሥር ለማጠናከርና ወሳኝ አቅጣጫዎችን ለማስያዝ ከገዳማት አባቶች ጋር መመካከርና መወያያት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማኅበሩ ጥሪ አድርጓል” ብለዋል፡፡
ገዳማውያን አባቶችም ጥሪውን ተቀብለው አስቸጋሪውን ጉዞ ሁሉ ተቋቁመው በመገኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በቀጣይነት የቀረበው በቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዮም ለሁለንታናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት የገዳማት ድርሻ በሚል ርእሰ ጉዳይ ላይ በመመርኮዝ “የገዳማት መጠናከር ለቤተ ክርስቲያን እድገት ያለው ሚና ምንድን ነው?” በሚል ጥናታቸውን አቅርበዋል፡፡ በጥናታቸውም ከዳሰሷቸው መካከል
-
ገዳማት የቤተ ክርስቲያናችን ሥውር ጓዳዎችና የምስጢር መዝገቦች ናቸው፡፡
-
ገዳማት የመማጸኛ ከተሞች ናቸው፡፡
-
ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የተገኙባቸው ምንጮች ናቸው
-
የተግባራዊ ክርስትና ሞዴሎች ናቸው
-
ገዳማውያን ለእግዚአብሔር የሚቀርቡ አሥራት በኩራት ናቸው፡፡
-
ገዳማት የብዝሃ ሕይወት መገኛና መጠበቂያ ናቸው፡፡
-
ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መሠረት ናቸው
-
የማኅበራዊ ደኅንነት አገልግሎት መሥጫ ሥፍራዎች ናቸው፡፡
በማለት ሰፊ ትንታኔ በመስጠት ገዳማት ለቤተ ክርስቲያን እድገት አስፈላጊ መሆናቸውውን አብራርተዋል፡፡
በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ በኢትዮጽያ ገዳማት ላይ ያደረጉትን ጥናት አቅርበዋል፡፡ በጥናታቸውም ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ገዳማት ያላቸው ሚናና እነዚህንም የሥልጣኔ ምንጮቻችንን ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ ትኩረት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጥንታዊ ገዳማት ውስጥ ከ1500 በላይ ዘመናት ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍት መኖራቸውና በምሳሌነትም በአባ ገሪማ ገዳም የሚገኘውን የብራና ወንጌልን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ ሥዕላትና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ ቤተ ክርስቲያናትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ሳይፈርሱ በቅርስነት መያዝ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
በጥናታቸው ማጠቃለያም “እነዚህ ቅርሶች የእኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ የሁላችንም የኢትዮጵያውን /ሃይማኖታችን ምንም ቢሆን/፤ የመላው ጥቁር ሕዝቦች እንዲሁም የሰው ልጆችና የዓለማችን ቅርሶች ናቸው፡፡ ጥቁር ሕዝቦች እጅግ የረዘመ የሥእልና የኪነ ጥበብ ቅርስ የላቸውም የሥእልና የኪነ ጥበብ ቅርስ ያለው ሕዝብ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ እነዚህን ቅርሶች ያቆየችልን ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት” ብለዋል፡፡
ጥናቱ እንደተጠናቀቀ ማኅበረ ቅዱሳን በገዳማት ውስጥ እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት መካከል ለምሳሌነት የቀረቡ ገዳማትን በመጥቀስ የባሌ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም፣ የአቃቂ ደብረ ገነት አባ ሳሙኤል ቤተ ደናግል ገዳም፣ የምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አበምኔቶችና እመምኔት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ያከናወኑትን ሥራ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም በትግራይ ክልል የሚገኙትን ገዳማት በመከታተል ከፍተኛ አገልግሎት እያበረከተች የምትገኘው ጸጋ ኪሮስ ግርማይ ሪፖርት አቅርባለች፡፡
የባሌ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም መጋቢ አባ ክንፈ ገብርኤል “ማኅበረ ቅዱሳን ወደ ገዳማችን በመምጣትና ችግራችንን በማየት ባጠናው ጥናት መሠረት የከብት እርባታ ለመጀመር የሚያስችለን ፕሮጀክት በመንደፍ 2 የወተት ላሞችን ሰጥቶን ሥራችንን ጀመርን፡፡ ዛሬ 24 ደርሰውልናል፡፡ 27 ደግሞ ሸጠን ተጠቅመናል፡፡ 18 ሞተውብናል፡፡ ተጨማሪ ሥራዎችንም በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ ውጤታማም ሆነናል” ብለዋል፡፡
ከአቃቂ ደብረ ገነት አባ ሳሙኤል ቤተ ደናግል የገዳሙ እመ ምኔት እማሆይ መብዐ ጽዮን ማኅበሩ ስላደረገላቸው ድጋፍ ሲገልጹ “አንድ የልብስ ስፌት መኪና፤4 ጣቃ ጨርቅ እንዲሁም 2 ላሞችን ሰጥቶን ሥራችንን የጀመርን ሲሆን ዛሬ 10 የወተት ላሞች አድርሰናል” ብለዋል፡፡ በተጓዳኝም 10 ሕጻናትንም እያሳደጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ከገዳማት ጋር ባደረገው የተቀራረበ ሥራ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍተኛ አፈጻጸም ላሳዩ ገዳማት የዋንጫ ሽልማት ማበርከቱ አንዱ የመርሐ ግብሩ አካል ነበር፡፡ ለሽልማት የበቁትም የባሌ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም፣ የአቃቂ ደብረ ገነት አባ ሳሙኤል ቤተ ደናግል ገዳምና የደቡብ ጎንደር ገዳመ ኢየሱስ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል፡፡
በዐውደ ጥናቱ ላይ ከቀረቡት መርሐ ግብሮች መካከል የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እና የአባ በጸሎተ ሚካኤል ገድል ምረቃ ሲሆን ከምረቃው በፊት በገድሉ ዙሪያ አጭር ትንታኔ በማኅበረ ቅዱሳን የኤሌክትሮኒክስና ሚዲያ የቴሌቪዥን ክፍል አስተባባሪ በዲያቆን ሄኖክ ኀይሌ ተሰጥቷል፡፡
የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገድል ለመተርጎም ከሦስት ዓመታት በላይ መውሰዱንና ገድሉን ሦስት ተርጓሚያን እንደተሳተፉበት፤ በ350፣000 ብር ለመታታመም እንደበቃ ተጠቅሷል፡፡በመጽሐፉ የሚገኘው ገቢም ሙሉ ለሙሉ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ሁለገብ ሕንፃ ግንባታ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ለገዳሙ ሁለገብ ሕንፃ ማሠሪያ ደራሲት ፀሐይ መላኩ “የንስሐ ሸንጎ” የተሰኘውን መጽሐፋቸው አበርክተዋል፡፡
ሁለቱንም መጻሕፍት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበር በመመረቅና በመባረክ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለማርያም ተረክበዋል፡፡ ደራሲት ጸሐይ መላኩ “እመምኔት” የተሰኘው መጽሐፋቸው ለማኅበሩ ሕንፃ ግንባታ እንዲውል ከዚህ ቀደም ማበርከታቸው ይታወሳል፡፡
በዐውደ ጥናቱ ላይ ከተገኙት ተጋባዥ እንግዶች መካከል የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለ አደራ ከንቲባ የነበሩት አቶ ብርሃነ ደሬሳ ሲሆኑ በዚህ መርሐ ግብር ላይ በመገኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
“ማኅበረ ቅዱሳን የሚመሰገንና ብዙ ቁም ነገር እየሠራ ያለ ማኅበረ ነው፡፡ አንድ ምክር ልለግሳችሁ፡፡ “ለነፍሳችሁ ብቻ ሳይሆን ለሰላምም መሥራት አለባችሁ፡፡ ሰላም ስትኖር ትረሳለች ሳትኖር ግን ታንገበግባለች፡፡ ማኅበሩ ለዚህ መቆም አለበት፡፡” ብለዋል፡፡
ገዳማትን አስመልክቶም ቅዱስ መጽሐፍ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ይላል፡፡ የተዘረጉ የኢትዮጵያውያን እጆች የታጠፈበት ጊዜ ነበር እርሱም ደርግ እግዚአብሔር የለም ብሎ ቤተ ክርስቲያን ለመዝጋት በተነሣበት በ17ቱ ዓመት የቤተ ክርስቲያን የመከራ ወራት /ዘመን/ ነበር፡፡ በዚህን ጊዜም ቢሆን ያልታጠፉ ወደ እግዚአብሔር የተዘረጉ እጆች ነበሩ፡፡ እነዚህ እጆች የመነኮሳትና የመነኮሳይያት እጆች ናቸው፤ ለዚህ ያበቃን የገዳማውያኑ ጸሎት ነው፡፡ ስለዚህ መረዳት አለባቸው” ብለዋል፡፡ ለዚህም አገልግሎት ይረዳ ዘንድ 20 ሺህ ብር ለመሥጠት ቃል ገብተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት ከተገኙት መካከል በኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ፔፕሲ ኮላ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ደርቤ ሥነ ጊዮርጊስ ማኅበሩ ለገዳማት ለሚያከናውነው አገልግሎት 10 ሺህ ብር ለመሥጠት ቃል የገቡ ሲሆን “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አጥታ አይደለም እንደዚህ የሚያስተባብርላት፣ ፕሮጀክት ቀርጾ አቅርቦ የሚፈጽም አካል ብቻ ነበር የጠፋው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ማኅበረ ቅዱሳንን አስነሥቷል፡፡ የሚሠራውን ሥራ በተግባር ያየሁት በመሆኑ አብሬ እየሠራሁ ድጋፌን እቀጥላለሁ” ብለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይም በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳን በመስጠት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በሰጡት ቃለ ምዕዳንም “አባቶቻችን የገደሟቸውን ገዳማት ለእግረኞችም ሆነ ለፈረሰኞች አይመቹም፡፡ ከዛሬ 4ዐ ዓመት በፊት ከዋልድባ ተነሥተን የኢትዮጵያ ገዳማትን ሁኔታ ለማየት ተንቀሳቅሰን ነበር፡፡ ነገር ግን አልቻልንም፡፡ ዛሬ ባለቤት ያገኘ ይመስላል፡፡ ልጆቻችን እየወጡ እየወረዱ የተዘጉትን ገዳማት በማስከፈት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን ልጆቻችን ስለሰጠን እናመሰግነዋለን፡፡ ….የጉርምስና ጊዜ ለመንፈሳዊ ሥራ አይመችም፡፡ ይህንን ለመሥራት ከእግዚአብሔር መመረጥ፤ መታደል ያስፈልጋል፡፡ ልጆቻችን ከኑሮ ጋር እየታገሉ ጊዜያቸውን ለማኅበራችን እንስጥ በማለት ለቤተ ክርስቲያን መሥዋእት እየሆኑ ነው፡፡ እኔም ከማኅበሩ ጎን በመቆም እታዘዛለሁ፡፡ ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል የአማካሪ ቦርድ ሰብሪሳቢ በሰጡት ቃለ ምእዳንም “ማኅበሩ ከገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን አንሥቶ የቤተ ክርስቲያናችን አእምሮና ልቡና እስከ ሆነው ገዳም ድረስ በመዝለቅ ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ገዳማት የምስጢር፣ የዜማ፤ የመጻሕፍት፤ የሊቃውንት፣ የካህናት መገኛ ናቸው፡፡ ልጆቻችን የሚሠሩት ሥራ እስከዚያ ዘልቋል፡፡ እግዚአብሔር ያስተማረው ሰው የእግዚብሔርን ሥራ ይሠራል፡፡ የእግዚአብሔርን ንብረት ይጠብቃል፡፡ ልጆቻችን ከእግዚአብሔር የተማሩት እየሠሩበት ነው፡፡ ከጎናቸው እንቁም፡፡ እኛም ከማኅበሩ ጎን ቆመን እንሠራለን፣ እንላላካለን፣ እንልካለንም፡፡” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበርና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለምዕዳንና ቡራኬ “ያሰባችሁት ሁሉ መልካም ነገር ነውና ያሰባችሁትን ሁሉ እንድትሠሩ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፡፡ ማኅበሩን ያስፋልን ማኅበሩን ከስም አወጣጥ ጀምሮ እኛ የሰጠነው በመሆኑ አብረን እንሠራለን ብለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የገዳማት አበምኔቶችና እመምኔተች ካህናት የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡