health

ለአብነት ተማሪዎች በጤና አጠባበቅ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ተሰጠ

ሚያዚያ 14 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

healthበማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ከጎንደር ማእከል ጋር በመተባበር በጎንደር ውስጥ ከሚገኙ አብነት ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ ተማሪዎች በግልና በአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ላይ ያተኮረና አንድ ቀን የወሰደ ስልጠና በደብረ ኀይል ወደብረ ጥበብ በዓት ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ  ሚያዚያ 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ተሰጠ፡፡

“ጤና ሀብት ነው” በሚል መሪ ቃል የተሰጠውን ሥልጠና በማስመልከት በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የአብነት ትምህርት ቤቶች ክትትል ክፍል ምክትል ኃላፊና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ሊቀ ዲያቆን መሐሪ መዘምር የሥልጠናውን ዓላማ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ “በአብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግሮች ይታያሉ፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ 25 ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት በመቅረጽ የጤና አጠባበቅ ትምህርት ለአብነት ትምህርት ተማሪዎች ለመስጠት አቅደን ወደ ትግበራ በመሸጋገር ላይ እንገኛለን፡፡ ጎንደር ከተማ ውስጥ እስከ 2000 ተማሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ስለሚገመት ለሁሉም ሥልጠና ለመስጠት ስለሚያዳግት ከየአብነት ትምህርት ቤቱ ለተውጣጡ 200 ተማሪዎች ሥልጠናውን እየሰጠን እንገኛለን፡፡ ተማሪዎቹም በአብነት ትምህርት ቤቶቻቸው ውስጥ ለሚገኙ ጓደኞቻቸው የአቻ ለአቻ ሥልጠና እንዲሰጡ እናደርጋለን፡፡” ብለዋል፡፡

በጎንደር ማኅበረ ቅዱሳን ማእከል የአብነት ትምህርት ቤቶቹን የጤና አጠባበቅ ሁኔታ የሚከታተልና የሚቆጣጠር ኮሚቴ እንደሚዋቀር የተገለጸ ሲሆን የግልና የአካባቢ ንጽህና ለመጠበቅ የሚረዱ ቁሳቁሶች እደላና አጠቃሙን ለማሳየት በየአብነት ትምህርት ቤቶቹ የሙከራ ሥራ እንደሚሠራ ሊቀ ዲያቆን መሐሪ መዘምር ገልጸዋል፡፡

ከመንበረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ገዳም የቅኔ ጉባኤ ቤት ተማሪ የሆኑት መሪ ጌታ ዮሴፍ ታረቀኝ ስለ ሥልጠናው ጠቀሜታ ሲገልጹ “አብሮ ስላደገብን ቀሸሽ ብለን ስለምንታይ ለተለያዩ በሽታዎች ስንጋለጥ ኖረናል፡፡ ንጽሕናችንን መጠበቅ የሚጠቅመው ራሳችንን ስለሆነ ማኅበረ ቅዱሳን እየሰጠን ያለውን ስልጠና ወስጄ ለተማሪዎች በቅኔ ነገራ ወቅትም ሆነ አመቺ በሆነ ስዓት ለማስተማር ተዘጋጅቻለሁ” ብለዋል፡፡

ስልጠናው የግልና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ፤ የውኃ አያያዝና አጠቃቀም፤ የምግብ አያዝና አጠቃቀም፤ የበሽታ መንስኤዎች፤ የበሽታ መተላለፊያ መንገዶች፤ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል፤ ወባ፤ የግርሻ በሽታ፤ . . . የሚሉ ርዕሶችን ያካተተ ሲሆን ለሃያ አምስት ሺህ ተማሪዎች በአራት ዓመታት ውስጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተገልጧል፡፡