የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርትን አስመረቀ

 ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

sewa sewe brhan 3በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመደበኛና በማታ መርሐ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ 212 ደቀመዛሙርትን በዲፕሎማ አስመረቀ፡፡

ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተካሔደው የምረቃ መርሐ ግብር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዲፕሎማና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ደቀመዛሙርት የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት ቃለ ምእዳን “ቤተ ክርስቲያን ከአጽናፈ ዓለም አሰባስባ፤ አስተምራ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ልታሰማራችሁ በዝግጅት ላይ ቆይታችኋል፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ሐብት በመሆኑ ያገኛችሁትን እውቀት ለወገኖቻችሁ እንድታካፍሉና ቤተ ክርስቲያን የጣለችባችሁን ሓላፊነት እንድትወጡ አደራ እላለሁ” ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ፤ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ፤ የሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ደቀመዛሙርቱ መንፈሳዊ ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተው ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል የሚዘጋጁበት ወቅት እንደሆነ አስታውሰው፤ በአባቶች ቡራኬ ለመመረቅ በመብቃታቸው እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኮሌጁ ዲን መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሃና ባቀረቡት ሪፖርት በመማር ማስተማሩ ሂደት ያጋጠሟቸውን ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት መምህራን ሲለቁ በቦታቸው ቶሎ ተተኪ ያለመመደብ፤ የሚመሩ ደብዳቤዎች ባልታወቀ ሁኔታ መጥፋት፤ ኮሌጁ ለሚጽፋቸው ደብዳቤዎች ምላሽ ያለማግኘት፤ የሥራ ጣልቃ ገብነት ጎልተው ከሚታዩት ችግሮች ውስጥ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

ኮሌጁ ምሁራንን እያፈራ የሚገኝ ቢሆንም ዘመኑን ባልተከተለ አሠራር እየተጓዘ ከአባቶች እንደተረከብነው ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ እንችላለን ወይ? በሚል ጥያቄ ውስጥ እንደሚገኙም መጋቤ ጥበብ ምናሴ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኮሌጁ በየዓመቱ የሚቀበላቸው ደቀመዛሙርት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱም እንደማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

sewa sewe brhan 2ከተመራቂ ደቀ መዛሙርቱ መካከል አባ ኪሮስ ወልደ አብ የትምህርት ቆይታቸውን አስመልክቶ የተሰማቸው ስሜት ሲገለጡ “ትምህርት ጀመርኩ እንጂ አልጨረስኩትም፤ የበለጠ እንድማር አነሳሥቶኛልና እቀጥልበታለሁ፡፡ በኮሌጁ ቆይታዬም በእቅድ መመራት በመቻሌ በጥሩ ሁኔታ ተምሬ በማዕረግ ለመመረቅ ችያለሁ” ብለዋል፡፡

 

ተመራቂ ደቀመዛሙርት ያወጡትን የጋራ መግለጫ በተወካያቸው አማካይነት ያቀረቡ ሲሆን፤ በኮሌጁ ውስጥ አንዳንድ መልካም ሥራዎች ቢኖሩም በኮሌጁ ቆይታቸው በስፋት ይታያሉ ያሏቸውን ችግሮች ዳስሰዋል፡፡ የትምህርት አሠጣጡ ዘመኑን የዋጀsewa sewe brhan 1 ያለመሆን፤ ለመምህራን በቂ ደሞዝ ያለመከፈል፤ ከሌሎች መሰል የቤተ ክርስቲያኒቱ ኮሌጆች ጋር የልምድ ልውውጥ ያለማድረግ፤ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኙ መጻሕፍት በቂ ያለመሆናቸው፤ የመደበኛ ተማሪዎች ቁጥር መቀነስ እንደ ችግር ከጠቀሷቸው ውስጥ ይገኙበታል፡፡

ደቀመዛሙርቱ እንደመፍትሔ ካቀረቧቸው ውስጥ፤ የትምህርት አሰጣጡ በሚመጥን መልኩ ቢቀረጽ፤ ተቋማዊ አቅሙን ወደ ዩኒቨርስቲነት ቢያሳድግ፤ በከፍተኛ ውጤት ለሚመረቁ ደቀመዛሙርት የነጻ ትምህርት እድል ቢመቻች የሚሉት ሐሳቦች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ከ212 ተመራቂ ደቀ መዛሙርት መካከል 12ቱ በመደበኛነት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንድ በብሉያት፤ አንድ በሐዲሳት ትርጓሜ የተመረቁ ናቸው፡፡ 200 ደቀመዛሙርት ደግሞ በማታው የትምህርት መርሐ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የኮሌጁ መምህራንና የተመራቂ ደቀመዛሙርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡

 

የሚዛን ተፈሪ ማዕከል 14ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ

 

ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.

በሚዛን ተፈሪ ማዕከል ሚዲያ ክፍል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የሚዛን ተፊሪ ማዕከል ከሰኔ 13 እስከ 15 2006 ዓ.ም 14ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ በአቡነ ተክለ ሃይማኖትና ቅዱስ ኡራኤል የእናቶች አንድነት ገዳም የስብከተ ወንጌል አዳራሽ አካሄደ፡፡

ሦስት ቀናት በፈጀው ጉባኤ የማእከሉ 2006 ዓ.ም ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በማዕከሉ ሰብሳቢ በአቶ መስፍን ደጉ የቀረበ ሲሆን፤ በእቅድ አፈጻጸሙ በተገቢው ሁኔታ የተከናወኑትን፤ ያጋጠሙ ችግሮች ፤ የተወሰዱ የመፍትሄ ሃሳቦች እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ችግሮች ከአባላት የአገልግሎት ዝለት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ክፍሎች ያቀዷቸውን እቅዶች አባላት የማስፈጸም አቅማቸዉ ያልተመጣጠነ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በቀረበው ሪፖርት መሠረት የተሻለ የእቅድ አፈጻጸም እንዲሁም ዝቅተኛ የዕቅድ አፈጻጸም ያሳዩ ክፍሎችም ተለይተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ለ2007 ዓ.ም. ክፍሎች ራሳቸውን በማጠናከር ያቀዷቸውን እቅዶች ተግባራዊ በማድረግ ጠንክረው እንዲሰሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የ2007 ዓ.ም ዕቅድ በማዕከሉ የዕቅድ ዝግጅትና ከትትል ክፍል ቀርቦም በውይይት በማዳበር ማስተካከያ ተደርጎበት ጸድቋል፡፡

ከማእከሉ አባላት በተጨማሪም ከሀገረ ስብከት፣ ከወረዳ ቤተ ክህነት፣ ከዋናው ማዕከል፣ ከምዕራብ ማዕከላት ማስተባበርያ፣ ከወረዳ ማዕከላት፣ ከግቢ ጉባኤያትና ከግንኙነት ጣብያዎች ተወክለው የመጡ እንግዶች በጉባኤው ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

 

በንባብ ባሕል ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ

ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የንባብ ባሕልን ለማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል አዘጋጅነት ሰኔ 28 ቀን 2006 ዓ.ም ከ8፡00-11፡00 ሰዓት በማኅበሩ ሕንፃ ላይ እንደሚቀርቡ ማእከሉ አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን የሚቀርቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ሁለት ሲሆኑ፤ “ትርጉም ያለው የንባብ ባሕል”፤ እንዲሁም “የንባብ ባሕልን ለማሳደግ የተለያዩ አካላት ሚና” በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያረጉ የጥናትና ምርምር ማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰይፈ አበበ ገልጸዋል፡፡

ትርጉም ያለው ንባብ ምንድን ነው? የንባብ ባሕልን ያሳደጉ አገራት ልምድ ምን ይመስላል? የንባብ ልምድ በሀገራችን እና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምን እንደሚመስሉ በጥናቶቹ ይዳሰሳሉ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል በየዓመቱ በሀገራችን የንባብ ባሕልን ለማበረታታት ከሚያዘጋጀው የመርሐ ግብር አካል አንዱ ሲሆን፤ ጥናቶቹም የንባብ ባሕላችን ምን ላይ እንደሚገኝ የሚዳስሱና የሚያነብ ትውልድን ለመፍጠር ምን መደረግ እንዳለበት የሚያመላክቱ መሆናቸውን አቶ ሰይፈ ጠቁመዋል፡፡

ይህ የንባብ ጉባኤ ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በመርሐ ግብሩ በንባብ ባሕል ላይ የሚሠሩ አካላት፣ ምሁራን፤ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት፤ እንዲሁም ምእመናን ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

 

የማቴዎስ ወንጌል

ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም.

ምዕራፍ ሁለት 

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የምንረዳውና የምንገነዘበው ጌታ በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን እንደተወለደ እንረዳለን፡፡ ቤተልሔም ማለት ቤተ ኅብስት ማለት ነው፡፡ ስምዋም የተሰየመው ካሌብ ኤፍራታ የተባለች ሚስት አግብቶ ወንድ ልጅ ከኳ በወለደ ጊዜ እንጀራ እገባ እገባ ብሎት ስለነበር የልጁን ስም ልሔም /ኅብስት/ አለው፡፡ በልሔም ቤተልሔም ተብላለች፡፡

የጥበብ ሰዎች ከሩቅ ምሥራቅ መጥተው የበረከት ሳጥናቸውን ከፍተው ለጌታ ገጸ በረከት አበርክተውለታል፡፡

  • ወርቅ-ለመንግሥቱ

  • ዕጣን ለክህነቱ

  • ከርቤ- ለመራራ ሞቱ፡፡ ምሳሌ ናቸው፡፡

ሰብዓ ሰገል ከሄዱ በኋላ ጌታ ሄሮድስ ሊገድለው ስለሚፈልገው አስቀድሞ በነብያት በተነገረው መሠረት ወደ ግብፅ ተሰደደ ሆሴ.11፡1፡፡

ንጉሡ ሄሮድስም ጌታን ያገኘ መስሎት 144ሺ የቤተልሔም ሕፃናትን አስፈጅቷል፡፡ ከሔሮድስ ሞት በኋላ ጌታ ከስደት ተመለሰ የስደት ዘመኑ 3 ዓመት ከመንፈቅ ነበር፡፡ ራዕይ 12፡7፡፡

እድገቱንም በነቢያት አስቀድሞ እንደተነገረው በናዝሬት ከተማ አደረገ፡፡ ናዝሬት የወንበዴዎች የቀማኞች የተናቁ ሰዎች ከተማ ነበረች፡፡ ጌታም ወደ ተዋረድነው ወደ እኛ መጥቶ ከውርደት ሊያድነን መሆኑን ሊያስገነዝበን በናዝሬት ኖረ፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 3ኛ ዓመት ቁጥር 1 ታኅሥሥ 1988 ዓ.ም.

ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ የድረ – ገጽ አገልግሎት ሊጀምር ነው

ሰኔ 13 ቀን 2006 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል የኦሮምኛ ድረ ገጽ አገልግሎት በቅርቡ እንደሚጀምር የዋና ክፍሉ ሓላፊ ዲያቆን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ገለጹ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፤ ቀኖና እና ትውፊት የጠበቁ ትምህርቶችን በኦሮምኛ ቋንቋ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ዘዴዎች ለምእመናን ለማሰራጨት እቅድ ከያዘ መቆየቱን የገለጹት ዲያቆን ዶ/ር መርሻ፤ የድረ ገጽ አገልግሎቱ ቅድሚያ ተሰጥቶት ለምእመናን ተደራሽ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት “በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የኦሮምኛ ድረ ገጽ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር ሲሆን፤ ወደፊት የኅትመትና የብሮድካስት ዝግጅቶችን ለምእመናን ለማዳረስ ማኅበሩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ ያደርጋል” ብለዋል፡፡

የኦሮምኛ ዝግጅት ንዑስ ክፍል አስተባባሪ ዲ/ን መዝገቡ ከፍያለው ለኦሮምኛ ድረ ገጽ መከፈት ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ሲገልጹ “በኦሮሚያ ክልል ምእመናን ስለ እምነታቸው በቋንቋቸው መማር አለመቻላቸው፤ በቋንቋው የተዘጋጁ ሃይማኖታዊ የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ውጤቶች አለመኖር እና ምእመናን በሌሎች የእምነት ተቋማት መወሰዳቸው ነው” በማለት ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት እና ያሉትን ምእመናን ለማጽናት፤ የጠፉትንም ለመመለስ እንዲቻል ከዐውደ ምሕረት ስብከት በተጨማሪ በመገናኛ ብዙኀን ዘዴዎች ወደ ምእመናን ለመድረስ አዲስ የተዘጋጀው ማኅበራዊ ድረ ገጹ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡

በድረ ገጹም ትምህርተ ሃይማኖት፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ነገረ ቅዱሳን፤ ስብከት፤ ለጥያቄዎች ምላሽ /ከምእመናን ለሚጠየቁ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት/፤ መዝሙር እና ኪነጥበብ ወዘተ. . . የተካተቱበት ሥራዎች እንደሚቀርቡ ዲ/ መዝገቡ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የድረ ገጹ አድራሻ፡- www.eotcmk.org/afaanoromo

በተያያዘ ዜና ከዚህ ቀደም ተቋርጦ የነበረው የእንግሊዝኛ ድረ ገጽ በቅርቡ የሚጀምር ሲሆን፤ የድረ ገጹ አድራሻ፡- www.eotcmk.org/site-en መጎብኘት ይቻላል፡

 

 

ለማእከላት ሓላፊዎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተሰጠ

 

ሰኔ 12 ቀን 2006 ዓ.ም.

በሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት

ማኅበረ ቅዱሳን ለማእከላት፤ ለማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሓላፊዎችና አስተባባሪዎች ከሰኔ 10- 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ሁለት ቀናት የቆየ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጠ፡፡

በሥልጠናው ከሀገር ውስጥና ከውጪ የተውጣጡ የ25 ማእከላት ጸሐፊዎች፤ የማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሓላፊዎች፤ የግቢ ጉባኤያት አስተባባሪዎችና መምህራን መካፈላቸውን የማኅበረ ቅዱሳን የሰው ሀብት ሥራ አመራርና ጠቅላላ አገልግሎት ክፍል ሓላፊ አቶ ዳንኤል ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት የቆየው ሥልጠና የግንኙነት ክህሎትን ማዳበር፤ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም እና የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎትን ያካተተ ሲሆን፤ ሠልጣኞች የተሻለ አገልግሎት ለማበርከት እንደሚረዳቸው አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
ሠልጣኞቹ በበኩላቸው ለሁለት ቀናት የተሰጣቸው ሥልጠና በአገልግሎት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን የሚሞላ ከመሆኑም ባሻገር፤ ከአባቶችና ከምእመናን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዛቸው ጠቁመዋል፡፡

ከሥልጠናው ጋር በተያያዘም የልምድ ልውውጥና ውይይት ተደርጓል፡፡

ሥልጠናውን በማኅበረ ቅዱሳን የሰው ሀብት ሥራ አመራርና ጠቅላላ አገልግሎት፤ የሀገር ውስጥ ማእከላትና የግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ዋና ክፍል አዘጋጅተውታል፡፡

 

ለማእከላት ሓላፊዎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተሰጠ

 

ሰኔ 12 ቀን 2006 ዓ.ም.

በሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት

ማኅበረ ቅዱሳን ለማእከላት፤ ለማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሓላፊዎችና አስተባባሪዎች ከሰኔ 10- 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ሁለት ቀናት የቆየ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጠ፡፡

በሥልጠናው ከሀገር ውስጥና ከውጪ የተውጣጡ የ25 ማእከላት ጸሐፊዎች፤ የማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሓላፊዎች፤ የግቢ ጉባኤያት አስተባባሪዎችና መምህራን መካፈላቸውን የማኅበረ ቅዱሳን የሰው ሀብት ሥራ አመራርና ጠቅላላ አገልግሎት ክፍል ሓላፊ አቶ ዳንኤል ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት የቆየው ሥልጠና የግንኙነት ክህሎትን ማዳበር፤ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም እና የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎትን ያካተተ ሲሆን፤ ሠልጣኞች የተሻለ አገልግሎት ለማበርከት እንደሚረዳቸው አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞቹ በበኩላቸው ለሁለት ቀናት የተሰጣቸው ሥልጠና በአገልግሎት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን የሚሞላ ከመሆኑም ባሻገር፤ ከአባቶችና ከምእመናን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዛቸው ጠቁመዋል፡፡

ከሥልጠናው ጋር በተያያዘም የልምድ ልውውጥና ውይይት ተደርጓል፡፡

ሥልጠናውን በማኅበረ ቅዱሳን የሰው ሀብት ሥራ አመራርና ጠቅላላ አገልግሎት፤ የሀገር ውስጥ ማእከላትና የግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ዋና ክፍል አዘጋጅተውታል፡፡    

   

 

 

ጉባኤ ቃና

Gubae Kana

የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ለመታደግ ጥሪ ቀረበ

 ሰኔ 10 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

debre libanoseየደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም ያጋጠሙትን በርካታ ችግሮች ለመታደግ ዘላቂ መፍትሔ መሻት እንደሚገባ ሰኔ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተካሔደ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ጥሪ ቀረበ፡፡

debre libanose 2006 2ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገዳሙ ያለበትን ችግር አስመልክቶ ሲገልጹ “የደብረ ሊባኖስ ገዳም የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ገዳምና ሀብት ነው፡፡ ገዳምነቱን ሊሸረሽሩ የሚችሉ በርካታ ችግሮች አጋጥመውታል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና የአባቶች የጸሎት ቦታ ተጠብቆ እንዲቆይ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ስለሆነ ምእመናን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል፡፡

የገዳሙ አስተዳዳሪ ፀባቴ አባ ወልደ ማርያም አድማሱ የጉዳዩ አሳሳቢነትና ሊወሰድ ስለሚገባው አፋጣኝ መፍትሔ ሲያብራሩ “ገዳሙ ጊዜ የማይሰጥ፤ የቤተ ክርስቲያኑን ሕልውና የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮች ከፊት ለፊት ተደቅነውበታል፡፡ ከተራራማው አካባቢ ወደ ታች በሚወርደው ጎርፍ መሬቱ እየተንሸራተተና እየተሰነጠቀ ነው፡፡ የገዳማውያኑና የምእመናን ቦታዎች ያለመለየት፤ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ፤ የገዳሙ ወደ ከተማነት እየተቀየረ መምጣት፤ የአካባቢያዊ ንጽሕና መጓደልና ሌሎችም ችግሮች አሉብን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡፡

ገዳሙ ገዳማዊ ሕይወቱን ጠብቆ እንዲዘልቅ በማኅበረ ቅዱሳን ባለሙያዎች ጥናት ተካሒዶ፤ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ የሚናገሩት ፀባቴ አባ ወልደ ማርያም፤ በተዘጋጀው ፕሮጀክት መሠረት የመጸዳጃ ቤትና የጎርፍ መከለያdebra libanose 2006 1 ግንባታ በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡ ምእመናን ይህንን በመረዳት የታቀዱት ፕሮጀክቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው እንዲተገበሩም የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም ሊተገበሩ የታቀዱት 11 ፕሮጀክቶች መሆናቸውን በመጥቀስ ለጉባኤው በዝርዝር ያቀረቡት ኢንጂነር ዮናስ ምናሉ እስካሁን ድረስ ኣፋጣኝ እርምጃ ባለመወሰዱም በጎርፍ ዐራቱ ተግባር ቤቶች፤ የመናንያኑ መኖሪያዎች፤ እንዲሁም ድልድዩ ጉዳት እንደደረሰባቸውና፤ የቤተ ክርስቲያኑንም መሠረት እየቦረቦረው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የአድባራት አስተዳዳሪዎች ተገኝተው የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፤ ምእመናን የድጋፍ ማድረጊያ ቅጽ እንዲሞሉ ተደርጓል፤ ጨረታም ተካሒዷል፡፡ ይህ ጉባኤ የመጀመሪያ መሆኑንና በቀጣይነት የሚካሄዱ የገቢ ማሰባሰቢያና ሌሎች ዝግጅቶች እንደሚኖሩም ተጠቅሷል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላትና የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ፤ እንዲሁም በገጣሚያን ግጥም ቀርቧል፡፡

 

 

የደብረ ሊባኖስ ገዳም የልማት ፕሮጀክት ትግበራ በመፋጠን ላይ ይገኛል

 

ሰኔ 5 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

  •  ሰኔ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ ይካሔዳል፡፡

Debre libanos Monastary.በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም በ2004 ዓ.ም. በገዳሙና በማኅበረ ቅዱሳን ባለሙያዎች ተጠንቶ የቀረበው የገዳሙ ሁለንተናዊ የልማት ፕሮጀክት ተግባራዊ በመሆን ላይ እንደሚገኝ የገዳሙ የልማት ኮሚቴ ገለጸ፡፡

የጥናት ቡድኑ በገዳሙ የሚታዩትን ዋና ዋና ችግሮች በመለየትና ጥናት በማካሔድ፤ የፕሮጀክት ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር ለመሸጋገር በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በጥናቱ ተለይተው የተያዙትን ችግሮች ለመቅረፍ በሦስት ዙር የተከፈሉ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ዙር የብዝኀ ሕይወት ጥበቃ፤ የአፈርና የውኃ ጥበቃ፤ የመነኮሳት መኖሪያ ግንባታ፤ የመጸዳጃ ቤትና የአካባቢ ጽዳት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡ በሁለተኛው ዙር የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ (የተማሪዎች መኖሪያና መመገቢያ፤ የመምህራን መኖሪያ፤ ቤተ መጻሕፍትና የምርምር ማእከል) የያዘ ነው፡፡ በሦስተኛ ዙር የጤና ጣቢያ፤ የሁለገብ ሕንፃ፤ የዘመናዊ ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ የሚደረጉበት መሆኑ የፕሮጀክት ሰነዱ ያመለክታል፡፡

የጎርፍና የመሬት መንሸራተት፤ የቀብር ቦታና የቀብር ሐውልት መስፋፋት፤ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና የአውቶቡስ መናኸሪያ መስፋፋት በጥናቱ የተካተቱና እንደችግር የታዩ በመሆናቸው በፕሮጀክቱ ተካተዋል፡፡ የመጀመሪያው ዙር ትግበራም በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ የመጸዳጃና የገላ መታጠቢያ ቤቶች ግንባታቸው 60% መድረሱን የገዳሙ የልማት ኮሚቴ አስታውቋል፡፡ በሦስት ዙር የሚጠናቀቀው የልማት ፕሮጀክት ከሁለት ዓመት በፊት በተጠናው ጥናት መሠረት 65,925,976 ብር (ስልሳ አምስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃያ አምስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ስድስት ብር) ይፈጃል ተብሎ ይገመታል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የገዳሙንና የምእመናን መንደር፤ የአባቶችና የእናቶች መኖሪያ ይለያሉ፤ መናንያን ለጸሎትና ለአገልግሎት የሚመች በዓት ይኖራቸዋል፡፡ ሱባኤ ለመያዝ በሚመጡ ምእመናንና በገዳሙ አባቶች መካከል ያለው ግንኙነት ሥርዓቱን የጠበቀ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በጥናቱ የተካተቱትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል የልማት ኮሚቴው የተለያየ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በመንደፍና በማዘጋጀት ፕሮጅክቱን በታቀደለት ሁኔታ ለማጠናቀቅ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት ሰኔ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡30 በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል፡፡ ምእመናን በሥፍራው ተገኝተው ድጋፍ እንዲያደርጉ የገዳሙ ፀባቴ አባ ወልደ ማርያም አድማሱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም ከ2500 በላይ የአብነት ተማሪዎችና ከ800 በላይ ማኅበረ መነኮሳት እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡