የማቴዎስ ወንጌል

ምዕራፍ 13

ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም.

1. ስለ ዘሪው ምሳሌ
2. ስለ ሰናፍጭ ቅንጣት ምሳሌ
3. ስለ እርሾ ምሳሌ
4. ስለ እንክርዳድ ምሳሌ
5. ስለ ተሰወረው መዝገብ ምሳሌ
6. ስለ ዕንቁ ምሳሌ
7. ስለ መረብ ምሳሌ እና
8. ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አደገባት መንደር ወደ ናዝሬት ስለመሄዱ፡፡

1. የዘሪውም ምሳሌ
በዚህ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው በዘሪው ምሳሌ ውስጥ የምንመለከተው፡- በመንገድ ዳር፣ በጭንጫ መሬት ላይ፣ በእሾህ መካከል እና በመልካም መሬት ላይ ስለወደቁት የዘር ዓይነቶች ነው፡ እዚህ ላይ ዘሪ የተባለው እግዚአብሔር ሲሆን ዘሩ ደግሞ ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡

በመንገድ ዳር የወደቀውን ዘር ወፎች መጥተው በልተውታል፡፡ ይህም ቃሉን ሰምተው ለማያስተውሉ የልበ ዝንግጉዓን ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡ ወፎች የተባሉትም አጋንንት ናቸው፡፡ “ወፎች መጥተው በሉት፤” ማለትም አጋንንት መጥተው አሳቷቸው ማለት ነው፡፡ የበሉት ደስ እንዲያሰኝ አጋንነትም በማሳታቸው ደስተኞች ናቸው፡፡ ለማሳት ፈጣኖች በመሆናቸውም በወፍ ተመስለዋል፡፡

በጭንጫ /በድንጋያማ/ መሬት ላይ የወደቀው ዘር ለጊዜው በቅሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፡- ሥርም ስላልነበረው ደረቀ፡፡ ይህም ቃሉን ለጊዜው በደስታ ተቀብለው መከራ እና ስደት በሚመጣ ጊዜ ግን የሚሰናከሉ ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ስፋሐ – አእምሮ ማለትም ጥልቅ ዕውቀት ስለሌላቸው ፈጥነው ሃይማኖታቸውን ይክዳሉ፡፡

በእሾህ መካከል የወደቀው ዘር ደግሞ በቅሎ ፍሬ እንዳያፈራ እሾሁ አንቆ ይዞታል፡፡ ይህም እንደ ቃል እንዳይኖሩ በዚህ ዓለም ሃሣብና ባለጸግነት የሚያዙ እና የሚታለሉ ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቃሉን ተምረውና አውቀው ሥራ እንሠራለን በሚሉበት ጊዜ በአምስት ነገሮች ይያዛሉ፡፡ እነዚህም፡-

1. ብዕል ሰፋጢት /አታላይ ገንዘብ/
2. ሐልዮ መንበርት /ስለ ቦታ ማሰብ/
3. ትካዘ ዓለም /የዚህ ዓለም ሃሣብ/
4. ፍቅረ ብእሲት /የሴት ፍቅር/
5. ፍቅረ ውሉድ /የልጆች ፍቅር/ ናቸው

በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር ግን አንዱም ሠላሳ፣ አንዱም ስድሳ፣ አንዱም መቶ ፍሬ አፈራ፡፡ ይህም ቃሉን ሰምተው ለሚያስተውሉ በተግባርም ለሚገልጡት ሰዎች የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቃሉን ሰምተው ሥራውን በሦስት ወገን ይሠሩታል፡፡ በሦስት ወገን የተባለው 1ኛ በወጣኒነት፣ 2ኛ. በማዕከላዊነት፣ 3ኛ. በፈጹምነት ነው፡፡ ክብሩንም በዚያው ይወርሱታል፡፡ በዚህም መሠረት በወጣኒነት ሠላሳ፣ በማዕከላዊነት ስድሳ በፍጹምነት ደግሞ መቶ ፍሬ ያፈራሉ፡፡ ፍሬ የተባለው በሃይማኖት የሚፈጸም ምግባር ነው፡፡

ከሰማዕታት እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ እነ ቅዲስ ቂርቆስ፣ ከመነኰሳት እነ አባ እንጦንስ መቃርስን፣ እነ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ከሰብአ ዓለም እነ ኢዩብ፣ እነ አብርሃም ባለ መቶ ናቸው፡፡

2. የሰናፍጭ ቅንጣት ምሳሌነት
የሰናፍጭ ዘር ስትዘራ መጠኗ ከዘር ሁሉ ያንሳል፤ በአደገች ጊዜ ግን ከአታክልቶች ትበልጣለች፤ የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች፡፡ ምሳሌነቷም ለመንግሥተ ሰማያት መሆኑ ተገልጧል፡፡ እዚህ ላይ መንግሥተ ሰማያት የተባለች ወንጌል ናት፡፡ ምክንያቱም በሕገ ወንጌል ጸንቶ የኖረ መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳልና፡፡ በዚህም መሠረት ሰናፍጭ ለወንጌል ምሳሌ የሆነችበት ምክንያት ከዚህ እንደሚከተለው ነው፡፡

– ሰናፍጭ ፍጽምት ናት፣ ነቅ የለባትም፤ ወንጌልም ነቅዓ ኑፋቄ የሌለባት ፍጽምት ናት፡፡
– ሰናፍጭ ላይዋ ቀይ ውስጧ ነጭ ነው፤ ወንጌልም በላይ ደማችሁን አፍስሱ ትላለች በውስጥ ግን ሕገ ተስፋ ናት፡፡ ይህም ተስፋ መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡
– ሰናፍጭ ጣዕሟ ምሬቷን ያስረሳል፤ ወንጌልም ተስፋዋ መከራን ያስረሳል፡፡
– ሰናፍጭ ቁስለ ሥጋን ታደርጋለች፣ ወንጌልም ቁስለ ነፍስ ታደርቃለች፡፡
– ሰናፍጭ ደም ትበትናለች፤ ወንጌልም አጋንንትን፣ መናፍቃንን ትበትናለች፡፡
– ሰናፍጭ ከምትደቆስበት ተሐዋስያን አይቀርቡም፤ ወንጌልም በእውነት ከምትነገርበት አጋንንት መናፍቃን አይቀርቡም፡፡
– ሰናፍጭ ስትደቆስም ስትበላም ታስለቅሳለች፤ ወንጌልም ሲማሯትም፣ ሲያስትምሯትም ታሳዝናለች፡፡
– ሰናፍጭ ከበታቿ ያሉትን አታክልት ታመነምናለች፤ ወንጌልም የመናፍቃንን ጉባኤ ታጠፋለች፡፡
– ሰናፍጭ አንድ ጊዜ የዘሯት እንደሆነ ባመት ባመት ዝሩኝ አትልም፤ ተያይዞ ስትበቅል ትኖራለች፡፡ ወንጌልም አንድ ጊዜ ተዘርታ ማለትም በመቶ ሃያው ቤተሰብ ተጀምራ እስከ ምጽአት ድረስ ስትነገር ትኖራለች፡፡
– ሰናፍጭ የሰማይ ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ እንድትሆን፣ ወንጌልም ሕዝብም አሕዛብም ተሰብስበው መጥተው እስኪያምኑባት ድረስ ደግ ሕግ ትሆናለች፡፡

3. የእርሾ ምሳሌነት
መንግሥተ ሰማያት ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት በሸሸገችው ዱቄት ተመስላለች፡፡ ይህም እንደሚከተለው ይተረጐማል፡፡

1ኛ. – እርሾ የጌታ ምሳሌ
– ብእሲት የጥበቡ ምሳሌ
– ሦስቱ መስፈሪያ የሥጋ፣ የነፍስ እና የደመ ነፍስ ምሳሌ ናቸው፡፡
– አዋሕዳ ሸሸገችው የሚለው ደግሞ በተዋሕዶ ሥጋን የባሕርይ አምላክ የማድረጉ ምሳሌ ነው፡፡

2ኛ. – እርሾ የወንጌል ምሳሌ
– ብእሲት የመምህራን ምሳሌ
– ሦስቱ መሥፈሪያ- የሦስቱ ስም የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ናቸው፡፡
– አዋሕዳ ሸሸገችው የሚለው ደግሞ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዲስ የተጠመቁ ሁሉ በጥምቀት የመክበራቸው ምሳሌ ነው፡፡

3ኛ. – እርሾ የጸጋ ምሳሌ
– ብእሲት – የቡርክት ነፍስ ምሳሌ
– ሦስቱ መስፈሪያ ጌታ በመቃብር የቆየባቸው የሦስቱ መዓልትና የሦስቱ ሌሊት ምሳሌ ናቸው፡፡
– አዋሕዳ ሸሸገችው የሚለው ደግሞ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ አንድ ወገን ሆኖ ለመነሣቱ ምሳሌ ነው፡፡

4ኛ. – እርሾ የጌታ ምሳሌ
– ብእሲት የዮሴፍ የኒቆዲሞስ
– ሦስቱ መስፈሪያ ጌታ በመቃብር የቆየባቸው የሦስቱ መዓልትና የሦስቱ ሌሊት ምሳሌ ናቸው፡፡
– አዋሕዳ ሸሸገችው የሚለው ደግሞ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ አንድ ወገን ሆኖ ለመነሣቱ ምሳሌ ነው፡፡

ይቆየን

ምንጭ፡-ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 5ኛ ዓመት ቁጥር 2 ኅዳር 1990 ዓ.ም.