aba zewengel 01

የጀበራ ቅድስት ማርያም ገዳምን ዳግም በማቅናት ላይ የነበሩት አባ ዘወንጌል ዐረፉ

ጥር 22 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

aba zewengel 01በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በደምቢያ ወረዳ በጣና ሐይቅ ውስጥ በ1335 ዓ.ም. ተገድማ የነበረችው የጀበራ ማርያም አንድነት ገዳም ከፈረሰች ከበርካታ ዘመናት በኋላ ዳግም ለማቅናት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ የነበሩት አባ ገብረ ኢየሱስ ወልደ ኢየሱስ /አባ ዘወንጌል/ ጥር 20 ቀን 2007 ዓ.ም. በደረሰባቸው ድንገተኛ አደጋ ማረፋቸውን ከገዳሙ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

 

አባ ዘወንጌል በ1974 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ፋኩልቲ በፊዚክስ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ሊመረቁ ሁለት ወራት ብቻ ሲቀራቸው ይህንን ዓለም ንቀው በምናኔ ለመኖር በመወሰን ወደ ጀበራ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም በማምራት ለ10 ዓመታት ቆይተዋል፡፡

 

በ1984 ዓ.ም. ከጀበራ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ወደ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም በማምራት ለ20 ዓመታት በአገልግሎት ሲተጉ ቆይተዋል፡፡ በ2005 ዓ.ም. “የአባቶቼ ርስት እንዴት ቆይታ ይሆን?” በማለት አባቶችን ለመጎብኘት ወደ ቦታው ሲያቀኑ ቤተ ክርስቲያኗ ፈርሳ፤ ብዙዎቹ መነኮሳት በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በመለየታቸውና ከሞት የተረፉት ደግሞ ተሰደው ሁለት አባቶች ብቻ በእርግና ምክንያት የሚጦራቸው አጥተው በችግር ውስጥ እንዳሉ ይደርሳሉ፡፡

 

በሁኔታው የተደናገጡት አባ ዘወንጌል ከጣና ሐይቅ ማዶ ያሉትን ነዋሪዎች በመቀስቀስ፤ በጎ አድራጊ ምእመናንን በማስተባበር ገዳሟን እንደገና ጥንት ወደነበረችበት ክብሯ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡ ኮሚቴ በማዋቀር ከበጎ አድራጊ ምእመናን በተገኘ ድጋፍ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኗን ለማስገንባት ሲፋጠኑ ድንገት ለግንባታ የተዘጋጀ ድንጋይ ወድቆባቸው ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡

 

በ2005 ዓ.ም. የማኅበረ ቅዱሳን የጋዜጠኞች ቡድን በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ለዘገባ በተንቀሳቀሰበት ወቅት በገዳሙ ተገኝቶ ነበር፡፡ አባ ዘወንጌልም በወቅቱ ወደ ጀበራ ቅድስት ማርያም ገዳም ከመጡ ገና 15ኛ ቀናቸው ስለነበር በገዳሟ ውስጥ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ምንም ዓይነት ልማት አልነበረም፡፡

 

ejebera gdamበ14ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት አባ በረከተ አልፋ በተባሉ አባት ተገድማ እንደ ነበረች የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱ የገለጹት አባ ዘወንጌል፤ ገዳሟ በርካታ መናንያንን ስታስተናግድ የኖረች በመሆኗ በገዳማዊ ሕይወታቸውና በትሩፋታቸው ከልዑል እግዚአብሔር በረከትን ያገኙ አባቶችና እናቶች የኖሩባትና ጸሎት ሲያደርሱ የእጆቻቸው ጣቶች እንደ ፋና ያበሩ ስለነበር የአካባበቢው ነዋሪዎች “እጀበራዎች” እያሉ ይጠሯቸው ስለነበር ገዳሟ “ጀበራ” የሚለውን ስያሜ ማግኘቷን አባ ዘወንጌል በወቅቱ ገልጸውልን ነበር፡፡

 

ገዳሟ በድርቡሽ ወረራ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የጣና ገዳማት መካከል አንዷ ስትሆን ገዳማውያኑም በመሰደዳቸው እስከ 1956 ዓ.ም. ሙሉ ለሙሉ ፈርሳ ቆይታለች፡፡ በ1956 ዓ.ም መምህር ካሳ ፈንታ በተባሉ አባት ዳግም ተመሥርታ ብትቆይም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በማረፋቸው ገዳሟን የሚንከባከብ በመጥፋቱ ገዳማውያኑም ወደ ተለያዩ ገዳማት ተበተኑ፡፡ ተሠርታ የነበረችው መቃኞም በምስጥ ተበልታ ፈረሰች፡፡

 

ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ቤተ ክርስቲኗን የመገንባትና የልማት ሥራዎች በአባ ዘወንጌል አስተባባሪነት እየተሠራ የነበረ ሲሆን፤ በተለይም የቤተ ክርስቲያኗ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ነበር፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ከ15 በላይ መናንያን ተሰባስበውባት በጸሎትና በአገልግሎት በመፋጠን ገዳሟን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡

 

እግዚአብሔር የአባታችንን ነፍስ ከቅዱሳን አበው ነፍስ ጋር ይደምርልን፡፡