ፀሐይና የአጥቢያ ኮከብ የተባለ ታላቅና ክቡር የሆነ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የምስክርነት ፍጻሜ የሆነበት ቀን ሚያዚያ ፳፫ የከበረ ነው፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ አባት ቀጰዶቅያ አገር ይኖር የነበረ አንስጣስዮስ የተባለ መስፍን ነው፡፡ እናቱም ቴዎብስታ የተባለች ፍልስጥዔማዊ ነበረች፤ የዚህ ቅዱስ አባትም የሞተው በልጅነቱ ስለዚህም ሌላ ደግ ክርስቲያናዊ መስፍን ወስዶ አሳደገው፡፡ መስፍኑም በጦር ኃይል አሰለጠነው፡፡ ሃያ ዓመትም በሞላው ጊዜ መስፍኑ የ፲፭ ዓመት ልጁን ሊያጋባውና ሀብቱን ሊያወርሰው ድግስ ደገስ፤ ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዚህ አልመረጠውምና የመስፍኑን ነፍስ ወሰደ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ኀዘኑን ከጨርሰ በኋላ ወደ ቤሩት ሀገር ሄደ፡፡ በዚያም ደራጎንን ያመልኩና ሴት ልጆቻቸውን ይገብሩለት ነበር፤ ሰማዕቱም ደራጎኑን በኃይለ መስቀል ድል ነሥቶት ገድሎታል፤ ሕዝቡንም ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሷቸዋል፡፡