‹‹ልጅነቴ!››

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ጥር ፲፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን! የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀቱን በዓል እንዴት አሳለፋችሁ? መቼም ሁላችንም ሐሳባችንን የመግለጡ ዕድል ቢሰጠን በዓሉ እንዴት እንደ ነበርና በበዓሉ ደስታ ምን እንደ ተሰማን እንገልጽ ነበር፡፡ እናንተ ደግሞ ደስ በሚል ሁኔታ አሳልፋችሁታል ብለን እናስባለን፡፡

በሰንበት ትምህርት ቤት አባል የሆንን መዝሙር በመዘመር እንዲሁም ከወላጆቻችን ጋር፣ አንዳንዶቻችን ደግሞ ዲያቆናት የሆንን ልብሰ ተክኖውን ለብሰን፣ ታቦታቱን አጅበን፣ ወደ ጥምቀተ ባሕር፣ ከዚያም በነጋታው ደግሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሸኝ፣ አቤት ደስ ሲል! በጣም ያምር ነበር አይደል? የጥምቀቱ በዓል የሰው ልጆች የዕዳ ደብዳቤ የተደመሰሰበት፣ ልጅነት ያገኘንበት በዓል ነውና ደስ ብሎን በደስታ ሆነን ይህን ላደረገልን ፈጣሪ ምስጋና እናቀርብ ዘንድ ይገባል!

መቼም ደግሞ የማንዘነጋው አንድ ነገር አለ፤ በዘመናዊ ትምህርታችን የመንፈቀ ዓመት የመመዘኛ ፈተና ወቅት ነውና ቸል ሳንል በርትተን በማጥናት ፈተናውን በአግባቡ እንሥራ! መልካም! ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ዛሬ ልንነግራችሁ የፈለግነው ስለ ‹‹ልጅነት›› ነው፡፡

ልጅነቴ! ብለን ስንናገር ወይም ደግሞ ስናስብ ብዙ ሊታወሱን የሚችሉ ነገሮች አሉ፤ በሕፃንነታችን ወላጆቻችን ወይም መምህሮቻችን በቤታችን ወይም በትምህርት ቤት ‹‹ልጅነቴ›› ብለን እንድንዘምር ወይም እንድንጫወት አድርገውን ይሆናል፡፡ ‹‹ልጅነቴ፣ ልጅነቴ፣ ማርና ወተቴ›› ብለን ያልዘመርን እንኖራለን ማለት ዘበት ነው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ የልጅነት ጊዜ የሰው ልጆች እስከ እርጅና ባለው ቆይታ (ኑሮ) አንዱ ክፍል እንደሆነ ታስተምረናለች፤ ደስ የሚልና የሚጣፍጥ፣ ዳግመኛ በተመለሰ ተብሎ የሚናፈቅ ግን ደግሞ የማይመለስ የሕይወት መሠረት የሚጣልበት ጊዜ ነው፤ ለወጣትነት ለጉልምስና እንዲሁም ለሽምግልና ጊዜ የሚሆነውን ሕይወት ለመወሰን ምቹ ጊዜ ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደው ስለ ልጅነት ጊዜ መልካም አጋጣሚ አነሣን እንጂ ልጅነቴ በሚል ዐቢይ ርእስ ልንነግራችሁ የወደድነው በተወለድን ወንዶች በ፵ (ዐርባ) ቀናችን ሴቶች ደግሞ በ፹ (ሰማንያ) ቀናችን ከቅድስት ሥላሴ በጥምቀት የምንወለደውን ልጅነት ነው! በሕፃን እሳቤያችን ማስታወስ አንችልም እንጂ ዕድሉን አግኝተን የማስታወስ አልያም የመመልከት አጋጣሚው ቢኖረን ከሥላሴ ልጅነት ያገኘንባት ያች ደግ ዕለት፣ ቀን፣ ወርና ዓመት ምንኛ በሕይወታችን ካሉ ቀናት ሁሉ የተባረከች መሰላችሁ!

ልጆች! ይህች ‹‹ልጅነቴ›› የምንላት ቀን እኮ ከሁሉ የከበረች ናት፤ በእናቶቻችን እቅፍ ሆነን፣ አዲስ ልብስ ተገዝቶልን ቤተ ሰብ ሁሉ ተሰብስቦ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ አባቶች ካህናት እና ዲያቆናት በማይ (በጸበሉ) ላይ ጸሎት አድርሰውበት፣ ከዚያም ያ ውኃ በጸሎቱ ኃይል መንፈሰ እግዚአብሔር አድሮበት፣ ከውኃነት ወደ ማየ ገቦ ተለውጦ (ማየ ገቦ ማለት ልጆች ጌታችን በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ ለንጊኖስ የተባለ ጭፍራ ጎኑን በጦር ሲወጋው ከጎኑ የፈሰሰልን ነው) እኛም ተጠምቀንበት ልጅነትን ያገኘንባት ድንቅ ዕለት ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ካህኑ ስም አውጥተውልን (የክርስትና ስም) አንገታችን ላይ ክርስቲያን የመሰኘታችንን ልዩ ምልክት ክር አስረውልን አቤት ‹‹ልጅነቴ›› እንዴት ደስ ይላል!! ቤተ ሰብ እና ጎረቤት እኛ ልጅነት ከቅድስት ሥላሴ በማግኘታችን ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ አያችሁ የልጅነት ጊዜ እንዴት ደስ እንደሚል?

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለ መምህር እንዲህ ብሎ አስተምሮት ነበር፤ ‹‹እውነት እውነት እልሃለው ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም›› (ዮሐ.፫፥፭) ልጆች! እንግዲህ በዚህ አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት ነው በሕፃንነታችን ተጠምቀን የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆነው ታዲያ ይህ ልጅነት ደስ አይልምን!?

ለዚህም እኮ ነው ሁል ጊዜ ‹‹ውድ የእግዚአብሔር ልጆች›› እያልን የምንጠራችሁ! እንግዲህ ይህ ልጅነት የሚሰጠው ደግሞ በእግዚአብሔር ላመኑ ብቻ ነው! የልጅነታችን ጊዜ መልካም ነው፤ ክፋት የሌለበት፣ ለሰው መልካም እንጂ ክፉን የማንመኝበትና ጥሩ ጊዜ ነው፤ ሰው ደግሞ ከክፉ ሥራ ከራቀ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይሆናል፤ የሚሠራው ይከናወንለታል፤ መንገዱ ይቀናል፤ የፈለገውን በጎ ነገር ያገኛል፤ ቢማር ትምህርት ይገባዋል፤ ማስተዋል ይሰጠዋል፤ ቢሠራ ይባረክታል፤ ቢናገር ይደመጣል፤ ከክፉ ነገር ይጠበቃል፤ የሚያስፈራው ነገር የለም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነውና፤ በእግዚአብሔር ያምን የነበረ ልበ ቅኑ የይቅርታ ሰው ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔር ልጆቹን ከክፉ እንደሚጠብቅ በመዝሙሩ እንዲህ በማለት ይመሰክርልናል፤ ‹‹በእኔ ተማምኗልና አስጥለዋለው፤ ስሜንም አውቋልና፤ እጋርደዋለው ይጠራኛል፤ እመልስለትማለው፤ በመከራው ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለው›› (መዝ.፺፥፲፬)፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ልጅነት መልካም ነው ! ልጅነታችን የዋህ ልብና ንጽሕና አብሮን እንዲኖር የሚያደርግ ነው፤ ከቅድስት ሥላሴ በጥመቀት ስንወለድ ልበ ንጹሐን እንሆናለን፤ ይህ የልብ ንጽሕና ደግሞ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዲሆን ያደርገናል፤ ታዲያ ልጆች ‹‹ልጅነቴ ማርና ወተቴ›› እያለ ሰው ሁሉ የሚመኘው እኮ ይህን ደግ ጊዜ ነው፤ እናንተ ይህን መልካም ነገር ጠብቆ የመኖር ብዙ ዕድል አላችሁ፤ ምክንያቱም ክፋትን፣ ቂም በቀልን አታውቁምና! ለሰዎች መልካምን እንጂ ክፋትን አትመኙምና!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በጥምቀት ባገኛችሁት ልጅነት ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርን አግኝታችኋል፤ ይህንን ጠብቃችሁ ቅን፣ ታዛዥና አስተዋይ ልጆች በመሆን ማደግ አለባችሁ፤ በኋላ ስታድጉ ይህን ዳግመኛ የማይመጣን የልጅነት ጊዜ ከመመኘት ይዞ ማቆየት ይበጃልና፤ ጌታችን እኮ በአንድ ወቅት ቅዱሳን ሐዋርያትን ምን አላቸው መሰላችሁ? ‹‹እውነት እላችኋለው ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም፡፡›› (ማቴ.፲፰፥፫)

ዳግመኛ ሕፃን እንዲሆኑ ሳይሆን ልባችሁ ንጹሕ ካልሆነ፣ ከክፉ ሥራ ካልራቃችሁ የዋሃን ካልሆናችሁ ማለቱ እኮ ነው፤ ልጅነት ምን ያህል መታደል ነው! ‹‹ልጅነቴ›› ከቅድስት ሥላሴ በጥምቀት ተወልጄ፣ ልቤ ክፋት ሳይጻፍበት እንደ ንጹሕ ሰሌዳ ሆኖ የነበረበት ጊዜ ‹‹ልጅነቴ›› እንዴት ደስ ይል ነበር!!!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እስኪ ክርስትና የተነሣችሁበትን ዕለት ወላጆቻችሁ በምን ያህል ደስታ እንዳሳለፉት፣ በዚያን ወቅት ቤተ ሰብ ምን ያህል እንደተደሰተ፣ ለእናንተ ምን ምኞት እንደተመኙላችሁ፣ ምን ብሎ እንደመረቃችሁ፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነበረው ሥርዓተ ጥምቀት ምን ይመስል እንደ ነበር ጠይቁና ያችን ድንቅ ዕለት በልዩ ማስታወሻችሁ ከትቧት (ጻፏት)! ለዛሬ አበቃን! መልካም ጊዜ ይሁንላችሁ!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!