በዓለ አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ

እንኳን ለአጋእዝተ ዓለም ሥላሴ በዓል በሰላም አደረሰን!

የኖኅ የትውልድ ነገዶች ከምሥራቅም ተነሥተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፤ በዚያም ተቀመጡ። እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። እግዚአብሔርም አለ። ‹‹ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።›› እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማይቱንም መሥራት ተው። ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ።

እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና፤ ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል። (ዘፍ.፲፩፥፩-፱)

በዚህም መሠረት አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ በኃጢአት የተገነባውን የሰናዖር ግንብ ያፈረሱበት አንድነታቸውንና ሦስትነታቸውን በግልጽ ያሳዩበት ጥር ሰባት ቀን የከበረ በዓል እንደመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡

የሥላሴ ሦስተነታቸው እና አንድነታቸው በስም በአካል በግብር ሦስት መሆኑን እንረዳለን፤ የስም ሦስትነታቸው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ የግብር ሦስትነታቸውስ ደግሞ አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ የመሆኑ ምሥጢር ነው፤ የአካል ሦስትነታቸው ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ ስላላቸው ነው፤ ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው፤ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው፤ የሥላሴ አንድነታቸው በመለኮት፣ በፈቃድ፣ በሥልጣን፣ ወዘተ በመሳሰሉት ነው።

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!