‹‹ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ!›› (ሉቃ.፪፥፲፭)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ታኅሣሥ ፳፮፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን! ትምህርት እንዴት ነው? አሁንማ ፈተና ደርሷል አይደል ልጆች? ስለዚህ ጨዋታ ሳያታልላችሁ በትኩረት በማጥናት፣ ያልተረዳችሁትን በመጠየቅ፣ የግማሽ ዓመት ፈተናውን በጥሩ ውጠየት ለማለፍ ማቀድ አለባችሁ! በሰንበት ቤተ ክርስቲያን ሄዳችሁ መንፈሳዊ ትምህርት በመማር አስተዋይና ቅን ታዛዥ ልጆች ልትሆኑም ይገባል፤ ጾመ ነቢያትን አቅማችሁ በፈቀደ ስትጾሙ እንደ ነበረ ተስፋችን እሙን ነው፤ ታዲያ በቀደሙት ትምህርታችን ስለ ጾመ ነቢያትና ስለ ነቢያት አባቶቻችን ስንማማር ነበር፤ አሁን ደግሞ የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓል እናከብራለን፤ ታዲያ ልጆች! ስለ ታላቁ ዐበይት የልደት በዓል በዛሬው ትምህርታችን ‹‹ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ›› በሚል ርእስ አዘጋጅተንላችኋል! መልካም ንባብ!

‹‹ወደ ቤተልሔም እንሂድ›› ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ይህንን ደስ የሚል ቃል የተናገሩት በቤተ ልሔም አካባቢ የነበሩ እረኞች ናቸው፤ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ‹‹የምሥራች ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት ክርስቶስ ተወልዷል›› ብሎ አበሠራቸው፤ ከዚያም እረኞቹ ይህን ለማየት ‹‹ወደ ቤተልሔም እንሂድ›› ተባብለው ሄዱ፤ ጌታችን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ልሔም ተወልዶ አገኙት፤ ደስም አላቸው፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፡፡ (ሉቃ.፪፥፲፭)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቤተ ልሔም ከተማ ጌታችን ከመወለዱ በፊት በነቢዩ ሚክያስ ጌታችን እንደሚወለድባት ትንቢት ተነግሮላት ነበር፤ ‹‹ …አንቺ ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታነሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ፣ በእስራኤልም ላይ ገዢ የሚሆን ይወጣልናል›› በማለት እንደ ተነበየው ንጉሥ ክርስቶስ ተወለደባት፤ (ሚክ.፭፥፪) ዕድለኞች የሆኑ እረኞች ልደቱን ተመለከቱ!

ልጆች! ጌታችን በመወለዱ የሰው ልጆች ሁሉ ከጠላታችን ሰይጣን ባርነት ነጻ ወጥተናል፤ የቤተ ልሔም እረኞች የእግዚአብሔር መልአክ የምሥራች በነገራቸው ጊዜ ወደ ቤተ ልሔም ሄዱ፤ ከዚያም የተነገራቸው ነገር እውነት እንደሆነ ተመለከቱ፡፡

ዛሬም እኛ ቤተ ልሔም ወደ ሆነች እመቤታችን ካለችበት፣ ጌታችን ካለበት፣ ቅዱሳን መላእክት ከሚገኙበት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንሂድ! ቤተ ልሔም ስንሄድ ብዙ ነገር እናገኛለን፤ እረኞች ወደ ቤተ ልሔም በመሄዳቸው የጌታችንን ልደት ተመለከቱ፤ ከቅዱሳን መላእክት ጋር አብረው ዘመሩ፤ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ምሥጢር ተገለጠላቸው፤ ከሁሉም ሰዎች ቀድመው የጌታችንን ልደት አዩ!

ልጆች ቤተ ልሔም ወደ ሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስንመጣ፣ ስንማር፣ ስንጸልይ ማስተዋል ይሰጠናል፤ ዕውቀት ጥበብ ይገለጥልናል፤ አስተዋዮች፣ ታዛዥና ጎበዝ ልጆች እንሆናለን፡፡ ታዛዥ መሆን የተሰጠን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ለታላቅ ክብር ያበቃል፤ አያችሁ! በሰዎች እሳቤ ብዙ ጊዜ እረኛ መሆን ታናሽነት ተደርጎ ይቆጠር ነበር፤ እውነተኛ ጠባቂያን ጌታችን በተወለደ ጊዜ ግን ልደቱን ገለጠላቸው፤ እኛም ታዛዥ እንሁን!

እንግዲህ ልጆች! በዓሉን ስናከብር ከወላጆቻችን ጋር ቤተ ልሔም ከሆነች ቅዱሳን መላእክት፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር እንዲሁም በኅሊናችን እነ ቅዱስ ዮሴፍ ከሚገኙባት በመሄድ መሆን አለበት፡፡ ለእኛ ያደረገልንን ውለታ እያስታወስን በዝማሬ እንዲሁም አባቶች የሚሰጡንን ምክር በመስማት በዓሉን ልናከብር ያስፈልጋል፡፡ እኛም ለሰዎች መልካም በማድረግ፣ አብዝተን ለአገራቸችን ሰላም ለሕዝባችን ፍቅር እየጸለይን እናሳልፍ!

አምላካችን እግዚአብሔር በረከቱን ያድለን! ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!