ቃና ዘገሊላ

ጥር፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

በቃና ዘገሊላ ወይም በገሊላዋ ቃና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመውን ተአምር በማሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዓል ታከብራለች፡፡ ይህም በጥምቀት በዓል ማግስት በጥር ፲፪ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና በተደረገ ሰርግ ላይ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ተገኝቶ ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ ‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ድንግል ማርያምም በዚያ ነበረች›› እንዳለ እመቤታችን ለሠርገኞቹ ዘመድ ነበረችና ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሠርጉ ላይ ተገኝታ ነበር፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ጋር በሠርጉ ተገኝተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን የሠርጉ ሥነ ሥርዓት እየተከናወነ ባለበት ጊዜ ድንገት የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ አሳላፊዎቹም በጭንቀት ግራ በገባቸው ጊዜ የጭንቅ አማላጅ አዛኝ እናታችን ድንግል ማርያም ጭንቀታቸውን ተረድታ ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወር ብላ ‹‹የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም›› አለችው፡፡

እርሱም መልሶ ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› አላት፡፡ እመቤታችንም ለአሳላፊዎቹ ‹‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› አለቻቸው፡፡ ጌታም በቦታው የነበሩ ስድስት የድንጋይ ጋኖች ውኃ ሞልተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ ሲያመጡለትም ውኃውንም ወደ ወይን ለውጦ ለአሳዳሪው እንዲሠጡት አዘዘ፡፡ አሳዳሪውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፡፡ ከወዴት እንደመጣ ስላላወቀ ሙሽራውን ‹‹ሰው ሁሉ መልካሙን የወይን ጠጅ አስቀድሞ ያመጣል፤ ከጠገቡ በኋላም ተርታውን ያመጣል፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆየህ›› አለው፡፡ (ዮሐ.፪፥፩-፲፩)

ይህንን ድንቅ ተአምርም በማሰብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ የተፈጸመው የካቲት ፳፫ ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የካቲቱን በዓል ወደ ጥር ፲፪ አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማከናወን ነው፡፡

ከበዓሉ ረድኤት ያሳትፈን፤ አሜን!