ከመስከረም 26 እስከ ሕዳር 6 ቀን ያለው ጊዜ ዘመነ ጽጌ ይባላል፡፡ በዚህ ዘመን ውስጥ አምስት ወይም ስድስት እሑዶች ይውላሉ፡፡
ዮሐ. 3-29
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በልደቱ ጌታን በ6 ወር እንደሚቀድመው ሁሉ በይሁዳ አካባቢዎች እየተዘዋወረ «መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» አያለ ማስተማር የጀመረውም ጌታችን ማስተማር ከመጀመሩ 6 ወር ያህል ቀድሞ ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በእግዚአብሔር መንፈስ የተሞላና ትምህርቱ የሰዎችን ልብ የሚነካ ስለነበር፣ አለባበሱም አስደናቂ ስለነበር እንዲሁም እርሱ እስኪመጣ ድረስ አይሁድ ለ300 ዓመታት ያህል ከእግዚአብሔር የተላከ ነቢይ አይተው ስለማያውቁ በርካታ ሰዎች ትምህርቱን ተቀብለውትና ተከትለውት ነበር፡፡ እርሱም ስለ ኃጢአታቸው እየወቀሰ፣ ንሰሐ እንዲገቡ እያስተማረና ማድረግና መተው የሚገባቸውን እየነገረ የንስሐ ጥምቀት ያጠምቃቸው ነበር፡፡
በዚህም ጊዜ አይሁድ ቅዱስ ዮሐንስን «ይመጣል የተባልከው መሲህ አንተ ነህን?» እያሉ ይጠይቁት ነበር፣ እርሱ ግን «እኔ መሲህ አይደለሁም፤ እኔ የእርሱን መንገድ ለመጥረግ ከፊቱ የተላክሁ መንገደኛ ነኝ፤ እርሱ ግን ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እኔ የማጠምቃችሁ በውኃ ነው፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፡፡ እርሱን ለመቀበል በንስሓ ልቡናችሁንና ሰውነታችሁን አዘጋጁ» እያለ ያስተምራቸው ነበር፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በዚህ መልኩ ለ6 ወራት ያህል ከአገለገለ በኋላ ጌታ ወደ እርሱ ዘንድ መጣ፤ ተጠመቀም፡፡
ቅዱስ ዮሐንስም «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ ከእኔ በፊት የነበረው፣ ነገር ግን ከእኔ በኋላ የሚመጣው ያልኳችሁ እርሱ ነው፡፡» ብሎ ለደቀ መዛሙርቱና አብረውት ለነበሩት አስተማራቸው፤ ብዙዎችም ጌታችንን ተከተሉ፡፡
ከዚህ በኋላ ጌታችን በገሊላ «ጊዜው ደርሷል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ» እያለ ማስተማር ጀመረ /ማር.1-15/፡፡ ብዙዎችም ተከተሉት፡፡ ደቀ መዛሙርቱንም ይዞ ወደ ይሁዳ ሄደ፡፡ በይሁዳም የጌታችን ደቀመዛሙርት እንደ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሓ ጥምቀት ማጥመቅ ጀመሩ፡፡ /ዮሐ.3-22፤ 4-2/ ብዙ ሰዎችም የጌታችን ደቀመዛሙርት ሆኑ፡፡
«በዚህን ጊዜ ዮሐንስ በሳሌም አቅራቢያ ሪምን በተባለ ሥፍራ ብዙ ውኃ ሳለ ያጠምቅ ነበር፣ ሰዎችም ለመጠመቅ ይመጡ ነበር፡፡ . . . » ወደ ዮሐንስም መጥተው «ረቢ /መምህር/ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው፣ ስለ እርሱም የመሰከርህለት ሰው እነሆ ያጠምቃል፤ ሰውም ሁሉ ወደ እርሱ እየሐሄደ ነው» አሉት፡፡ /ዮሐ.3-23- 27/፡፡
ጠያቂዎቹ ነገሮችን በሥጋዊ ዓይን ይመለከቱ ስለነበር በሁለቱ /በቅዱስ ዮሐንስና በጌታችን/ መካከል ውድድርና ፉክክር ያለ መስሏቸው ነበር፡፡ ንግግራቸው «የአንተ ነገር አበቃለት፣ ሰው ሁሉ ወደዚያ አንተ ወደ መሰከርህለት እየሔሄ ነው፡፡» የሚል መንፈስ ነበረው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ «ከሰማይ ካልተሰጠው በቀር ማንም አንዳች ነገርን ገንዘብ ማድረግ አይችልም፡፡ እኔ ክርስቶስ /ይመጣል ተብሎ ትንቢት የተነገረለት አዳኝ መሲህ/ አይደለሁም ብዬ እንደተናገርሁ እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ /ታውቃላችሁ/፡፡» በማለት የሆነው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ዓላማና ፈቃድ እንደሆነ፣ እነርሱም ያሰቡት ነገር ከንቱ መሆኑን፣ እንዲሁም እርሱ ዓላማው ሰዎችን ወደ እውነተኛው መድኃኒት ማቅረብ እና መምራት እንጂ ሰዎችን በዙሪያው መሰብሰብ እንዳልሆነ ነገራቸው፡፡ በመቀጠልም የሰዎች ወደ ጌታችን መሄድ እነርሱ እንዳሰቡት እርሱን የሚያሳዝነው ሳይሆን የበለጠ የሚያስደስተው መሆኑን እንዲህ ሲል ገለጠላቸው፡፡
«ሙሽራ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ድምፁን ለመስማት አጠገቡ የሚቆሙ ሚዜ ግን የሙሽራውን ድምፅ ሲሰማ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ያ ደስታ የእኔ ነው፡፡ እርሱም አሁን ተፈጽሟል፡፡ እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ላንስ ይገባል፡፡»/ዮሐ 3. /
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በሙሽራ በሙሽሪት እና በሚዜ መስሎ የተናገረው የክርስቶስን፣ የቤተክርስቲያንን እና እንደ ራሱ ያሉ አገልጋዮችን ነገር ነው፡፡ በክርስቶስ እና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት በሙሽራ እና በሙሽሪት /በባል እና በሚስት/ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር የሚያመሳስሉት በርካታ ነገሮች አሉ፡፡
– ሙሽሪትን /ሚስቱን/ የሚመርጣት፣ የሚያጫት ሙሽራው /ባል/ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንንም የመረጣትና ሙሽራው እንድትሆን ያደረጋት ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡
– ባል ሚስቱን መጠበቅ፣ መንከባከብ ራሱን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ መውደድ ይጠበቅበታል፤ ክርስቶስም ስለ ቤተክርስቲያን ይህንን አድርጓል፡፡ ሚስት ራሷን ለባሏ ራሷን ማስገዛት አለባት፡፡ ቤተክርስቲያንም ለክርስቶስ እንዲሁ ማድረግ አለባት፡፡
– ሙሽሪት በሰርጓ ቀን ራሷን አስውባ ትቀርባለች፤ ክርስቶስም ቤተክርስቲያንን ወደ ራሱ ያቀረባት ሙሽራው ያደረጋት በሥጋውና በደሙ አንጽቶ፤ ነውሯን አስወግዶና አስውቦ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔርን እና የሰው ልጆችን ግንኙነት በሙሽራና በሙሽሪት /በባልና በሚስት/ እየመሰሉ በብሉይ ኪዳንም በሐዲስ ኪዳንም ብዙዎች አስተምረዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን ከነበሩት መካከል በፍቅር ግጥም መልክ የተጻፈው መኅልየ መኅልይ ዘሰሎሞን፣ ትንቢተ ሕዝቅኤል /ምዕራፍ 16/፣ ትንቢተ ሆሴዕ /ምዕ.1/ ተጠቃሸ ናቸው፡፡
በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ቅዱስ ጳዉሎስ በሁለተኛው የቆሮንቶስ መልእክቱ «እናንተ እንደ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁ» /11-2/ ብሎ ጽፏል፡፡ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱም እንዲህ ይላል፤
«ሚስቶች ሆይ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነው ሁሉ ባልም የሚስቱ ራስ ነው፡፡ ባሎች ሆይ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ በቃሉ አማካኝነት በማንፃት እንድትቀደስ. . . አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተክርስቲያን አድርጎ ሊያቀርባት ነው. . . ይህ ምስጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይኽንን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተክርስቲያን እናገራለሁ፡፡» /5-22-32/፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ነባቤ መለኮትም በራእይ መጽሐፉ ሰማያዊት ቤተክርስቲያን የሆነች አዲሲቷን ኢየሩሳሌምን የበጉ ሙሽራ ይላታል፡፡
«ቅድሰቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ» /21-1-9/፡፡
በዚህ ትምህርት ይህን በሙሽራ እና በሙሽሪት መካከል ባለው የፍቅር ግንኙነት የተመሰለውን የክርስቶስ /የእግዚአብሔር/ እና የቤተክርስቲያን /የእኛን/ ግንኙነት በሁለት ከፍለን እንመለከታለን
1. እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ምን ይመለከታል
2. እኛስ በእግዚአብሔር ውስጥ ምን እንመለከታለን
1. እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ምን ይመለከታል? እርሱ እንደወደደን የሚያደርግ ምን አለ?
በሕዝቅኤል የትንቢት መጽሐፍ ስለዚህ ጉዳይ የተጻፈው እንዲህ ይላል፤
«ኢየሩሳሌም /እስራኤል/ ሆይ….. በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቆረጠም፤ ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፤ በጨውም አልተወለወልሽም፤ በጨረቅም አልተጠቀለልሽም፤ በጭንም አልታቀፍሽም፡፡ በተወለድሽበት ቀን ከሰውነትሽ ጉስቁልና የተነሣ በሜዳ ላይ ተጣልሽ እንጂ ከዚህ አንዳች ይደረግልሽ ዘንድ ዓይን አልራራልሽም፤ ማንም አላዘነልሽም፡፡
«በአንቺም ዘንድ ባለፍሁ ጊዜ በደምሽም ተለውሰሽ ባየሁሽ ጊዜ ‘ከደምሽ ዳኝ አልሁ’. . . አንቺም አደግሽ፤ ታላቅም ሆንሽ፤ በእጅጉም አጌጥሽ፤ ከከተማ ወደ ከተማ ገባሽ፤ ጡቶችሽም አጎጠጎጡ፤ ጠጉርሽም አደገ፤ . . . በውኃም አጠብሁሽ፣ ከደምሽም አጠራሁሽ. . . ዘይትም ቀባሁሽ፣ ወርቀዘቦም አለበስሁሽ፣. . . በጌጥም አስጌጥሁሽ. . . እጅግም ውብ ሆንሽ፤ ለመንግሥትም የተዘጋጀሸ አደረግሁሽ . . .» /16.4-14/፡፡
እግዚአብሔር የሚያየን ትንሽ ፣በኀጢአት የቆሸሸች ¬፣ የማታምርና የተመልካችን ዓይን የማትስብ ጎስቋላ ነፍስ ሆነን ነው፡፡
ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ሲየየን እርሱ የማያየው ዛሬ የሆንነውን ብቻ ሳይሆን ወደፊት ልንሆን የሚችለውን ነው፡፡ ኃጢአቶቻችን፣ ቆሻሻችንን አለማማራችንን አይወድም፡፡ ነገር ግን እነዚህን በንስሓ ብናስወግዳቸው የሚኖረን ውበት ያውቃል፡፡ይህም ይስበዋል፡፡
ስለዚህም ጠፍተን ሳለን ካለንበት ከወደቅንበት መጥቶ ከነቆሻሻችን ይወስደናል፡፡ አስተምሮ፣ ለውጦ፣ የተሻልን ያደርገናል፤ አጥቦ ያነጻናል፤ወዳጆቹ ሙሽሮቹ ያደርገናል፡፡
ሰዎች አብረዋቸው እንዲሆኑ የሚፈልጉት በራሳቸው ደረጃ ያሉ ሰዎችን ነው፡፡ በሌሎችም ሰዎች ዘንድ እንዲሆን የሚጠበቀው ይኸው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይኽን ድንበር ሲያልፉና ከእነርሱ በጣም ዝቅ ካሉ ሰዎች ጋር ተወዳጅተው ማየት ብዙዎቻችንን ያስደንቃል፡፡ እስቲ የእኛን ኃጢአትና የእግዚአብሔርን ቅድስና እናስበውና በመካከላችን ያለውን ልዩነት ደግሞ እናስተውለው፡፡ የእርሱ ከእኛ ጋር መወዳጀት እንዴት አስደናቂ ነው!
እንግዲህ እግዚአብሔር እኛን የሚወደን እንዲህ ሆነን እየተመለከተን መሆኑን ሁል ጊዜ ማሰብ ይገባናል፤ በእውነት በእርሱ እንድንወደድ የሚያደርግ ምንም መልካም ነገር የለንም፡፡ ስለዚህ ለጸሎት በፊቱ ስንቆም፣ ወደ ቤተክርስቲያንም ስንገባ ከልባችን በፍርሃት ሰግደን ይቅርታውን መጠየቅ አለብን፡፡ «ይኽ የእግዚአብሔር ቤት ነው፣ የቅዱሳን፣ የመላእክቱም ማደሪያ ነው፤ እንዴት እዚህ ልገኝ እችላለሁ?» ልንል ይገባናል፡፡ አስቀድመን እንዳልነው የሚወደው ኃጢአታችንን ሳይሆን ይህንን ስናስወግድ የሚኖረንን ውበት መሆኑን ተረድተን ውለታውን እያሰብን በተሰጠን ጊዜ ለንጽህና ለቅድስና ልንተጋ ይገባል፡፡ስብሐት ለክርስቶስ ዘአፍቀረነ፡፡
2. እኛ በእርሱ ውስጥ ምን እናያለን? በእርሱ እንድንሳብ የሚያደርገን ምን ነገር አለ?
ከላይ እንዳየነው እግዚአብሔር እኛን የወደደን እንዲሁ ነው፡፡ የሰው ልጆች ግን ለመውደድ ምክንያት (ድጋፍ) ያስፈልገናልና እርሱን ለመውደድ የሚያበቁ ነገሮችን እርሱ ራሱ አዘጋጅቶልናል፡፡
ይቅርታው
ከላይ እንደተመለከትነው አምላካችንን ስናስብ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ሊያነጻን መውደዱን እናስባለን፡፡ ይቅር የተባለ ሰው ደግሞ ይቅር ያለውን አብዝቶ ይወዳል፤
እኛ እንደ ጠፋው ልጅ ትተነው ሄደን በጣም ርቀን ያለንን ሁሉ አጥተን ተመልሰን ስንመጣ እርሱ ቆሞ ሲጠብቀን እናገኘዋለን፤ በመምጣታችን ደስ ይለዋል እንጂ በመቆየታችን፣ እርሱን በመካዳችን አይቆጣንም፡፡ ስለዚህ እንደ ማርያም እንተ እፍረት በፍቅር በእግሩ ላይ ሽቱ እንድናፈስ፣ እንድንጠርገው እንገደዳለን፡፡
ሰማያዊ ድኅነት
በዕለተ አርብ ከጌታችን ጎን ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ ጌታችን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚወሰደው መሆኑን ተረዳ፡፡ ስለዚህም «በመንግሥትህ አስበኝ» ሲል ተማፀነ፡፡ «ከአንተ ጋር ውሰደኝ» እንደማለት ያለ ነው፡፡
ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚገኝበት ብቸኛ መንገድ ነው፡፡ እርሱም ይህንን ሊሰጠን ፈቅዷል፡፡ ይህም እንድንወደው በፍቅሩ እንድንወድቅ ያደርገናል፡፡
ምድራዊ ድኅነት
በችግር ውስጥ የነበረና በእግዚአብሔር ችግሩ የተቀረፈለት ሰው እግዚአብሔርን ይወዳል፡፡ እግዚአብሔር በየቀኑ በተለያዩ መንገዶች ያድነናል፤ በጸሎተ ቅዳሴ ላይ ካህኑ እንዲህ እያለ ይጸልያል፡፡ «ለእኛ በጎ ነገርን ያደረገ ይቅር ባይና መሐሪ እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፣ ከመከራ ሰውሮናልና፣ ጠብቆናልና፣ ረድቶናልና፣ ወደ እርሱም ተቀብሎናልና፣ አጽንቶ ጠብቆናልና. . . እስከዚህም ሰዓት አድርሶናልና»
የፍቅር ዝንባሌ
ሰዎች በባሕርያችን መውደድንና መወደድን የመፈለግ ከፍተኛ ዝንባሌ አለን፡፡ ይህ ፍቅርም ዘለዓለማዊ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ «ለዘለዓለም እወድሃለሁ፤ እወድሻለሁ» የሚለው አባባልም ከዚሁ የመነጨ ነው፡፡
እግዚአብሔር ይኽንን ዝንባሌ በውስጣችን ያስቀመጠው እርሱን እንወድበት ዘንድ ነው፡፡ በዚህ ምድር ያሉትን የቤተሰብ፣ የወንድም፣ የጓደኛ እና ጾታዊ ፍቅሮችንም ያዘጋጀው ከእርሱ ጋር ወደሚኖረን ፍፁምና ሰማያዊ ፍቅር የሚያደርሱ መለማመጃዎች፣ ቅምሻዎች. . . እንዲሆኑ ነው፡፡ፍጻሜያቸው ግን ከእርሱ ጋር የሚኖረን ዘለዓለማዊ ፍቅር ነው፡፡
ስለዚህ ይህ እርሱ ራሱ በውስጣችን ያስቀመጠው ዝንባሌ እርሱን ወደ መውደድ ያመራናል፤ እርሱ ምን ያህል እንደወደደን ስናስብም እኛም ለእርሱ ያለን ፍቅር ይጨምራል፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔር እኛን ያለዋጋ ወዶናል፤ እርሱን እንወደው ዘንድ እነዚህን ሁሉ ነገሮች አዘጋጅቶ ቆሞ ይጠብቀናል፤ ደጃችንንም ያንኴኴል፤ ስለዚህም ጊዜያችን ሳያልፍ፤ እርሱም ከእኛ ፈቀቅ ሳይል ጥሪውን ልንሰማ፤ የልባችንን በር ከፍተን በፍቅር ልናስተናግደው ይገባናል፤ ቅዱስ ዳዊት አንድም ስለ ንጽሕት ነፍስ አንድም ንጽሕት ስለሆነች ስለ እመቤታችን በዘመረው መዝሙር ነፍሳችንን እንዲህ ይላታል፤ ”ልጄ ሆይ አድምጪ አስተውዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ ሕዝብሽንና የአባትሽን ቤት እርሽ፡፡ንጉሥ በውበትሽ ተማርኴልና፡፡” /መዝ 46-10-11/