አሻራ አዲስ መንፈሳዊ ተውኔት

አዲስ መንፈሳዊ ተውኔት ይመረቃል

በይበልጣል ሙላት

ሰኔ 6፣2003ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማዕከል የትምህርትና ኪነጥበባት ክፍል የተዘጋጀውና “አሻራ” የሚል ስያሜ የያዘው ተውኔት ይመረቃል፡፡

ተውኔቱ እሑድ ሰኔ 12 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 በማኅበረ ቅዱሳን ህንፃ እንደሚመረቅ የተገለጸ ሲሆን ከዚያ በኋላ ለምዕመናን ክፍት ይሆናል ተብሏል፡፡

  አሻራ አዲስ መንፈሳዊ ተውኔት
የተውኔቱ አስተባባሪ አቶ አበራ ምታው ስብከተ ወንጌል በተለያየ ዘዴና መልክ እንደሚተላለፍ ገልጸው የሰዎችን ቀልብ ስቦ በመያዘ በቀላሉና በማይረሳ መልኩ ለማስተማርና ሃይማኖታዊ መነቃቃትንም ለመፍጠር እንደሚጠቅም አስገንዝበዋል፡፡

ተውኔቱ ሕዝበ ክርስቲያኑ ቅርሱን እንዴት? ከማን? እና መቼ? መጠበቅ እንዳለበት እንዲሁም እስከምን ድረስ መስዋዕትነት መክፈል እንዳለበት የሚያስገነዝብ ሲሆን ስለ ሃይማኖት ጽናትና ስለመንፈሳዊ ጥበብም እንደሚያስተምር አያይዘው ዓላማውን ገልጸዋል፡፡

በተውኔቱ 12 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ለማዘጋጀትም ከአንድ ዓመት ጊዜ በላይ ፈጅቷል፡፡ በዝግጅት ወቅት የተለያዩ ችግሮችን እንዳለፉ የገለጹት አቶ አበራ በተለይ የመለማመጃ ቦታ አለመመቸት፣ የበጀት በጊዜው አለመድረስና የተዋንያኑ የሥራ መደራረብ ችግር እንደፈጠረባቸው አልሸሸጉም፡፡

ይህ ተውኔት ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ መንገድ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት እንደሚቻል ለማስገንዘብ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣና ደራስያን ተዋንያንና ሌሎች የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከዚህ ዘርፍ በመሳተፍ ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ያበረታታል ሲሉ አቶ አበራ ያሳስባሉ፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው ምዕመናን እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡