• በብፁዕነታቸው መልካም ፈቃድና በሀገረ ስብከቱ ጥረት እርቅ እንደተካሄደ ይታወቃል። የእርቁ ሂደት እንዴት ነው? ከእርቁ በኋላ አለመግባባቶች እንዴት ሊፈጠሩ ቻሉ?
እንግዲህ በኛ በኩል እርቁ አልፈረሰም እንደተጠበቀና እንዳለ ነው፡፡ የዕርቅ ስምምነት የተባለው፤ የተጣላ ኖሮ አንተ ይህን አድርገሀል አንተ ይህን አድርገሀል ተብሎ እርስ በእርሱ የተጣላ ኖሮ አይደለም። ዋናው የቤተ ክርስቲያኒቱ መመሪያና ደንብ አልተከበረም ነው፡፡ ይህንን በሚመለከት በመንግሥት አካላት በኩልም የቤተ ክርስቲያኒቱን ደንብና መመሪያ እንዲያውቁት፥ ግንዛቤ እንዲኖር፥ በታዛቢነትም ተገኘተው ደግሞ የራሳቸውን ሀሳብና አስተያየት እንዲለግሱን አድርገናል። ይህን ከማድረግ አኳያ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ማለትም ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ከሰበካው ጉባኤውና ከልማት ኮሚቴ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ሁሉ የተውጣጡ አካላት ባሉበት፥ ከመንግሥት አካላትም በታዛቢነት አድርገን ባለ ሰባት ነጥብ የያዘ የእርቅ ሰነድ ወይም ውሳኔ የሚባለውን ያዘጋጀነው፡፡
ውሳኔውና የእርቅ ሰነዱ ብዙ ነገሮች ሲኖሩት ሌላው ሁሉ እንዳለ ሆኖ፥ ጠቅለል ባለ መልክ ሁሉም ነገር በቃለ አዋዲው እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና መመሪያ መሠረት እንዲሠራ የሚል ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በእርቅ ሰነዱ ሰባተኛው እና የመጨረሻው ተራ ቁጥር ላይ ሰባክያንና ዘማርያንን የተመለከተ ነው፤ አብዛኛውን ጊዜ ችግር የሚያመጣውና አለመግባባት የሚያስከትለው ጉዳይ እሱ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ይነሳሱና እነ እከሌ መስበክ አለባቸው ይላሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደርና አካሄድ ደግሞ ይህን አይፈልግም፥ ስለዚህ አሁን እገሌ ይስበክ እገሌ አይስበክ ሳይሆን፥ የሚሰብክ ሰው በቤተ ክህነቱ ሕጋዊ እውቅና ኖሮት ይስበክ የሚል ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምሳሌው አይሄድም እንጂ ፈቃድ ሲባል እንደ ንግድ ፈቃድ ወይም እንደ ቀበሌ መታወቂያ አንድ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም። አንድ ጉባኤ፣ ክብረ በዓል ሲኖር ወይም ወደ አንድ ቦታ ላይ ተጉዞ የወንጌል ማስተማር ጉባኤም ካለ፥ ለዚያ ጉባኤ እገሌ የተባለ ሰባኬ ወንጌል ወይም መምህር እንዲያስተምር የሚል ደብደቤ መኖር አለበት ነው፡፡ ያን ደብዳቤ የሚጽፈው ደግሞ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ወይም ደግሞ የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤቱ ሊሆን ይችላል። በዚህ መልኩ ነው ሥራው መሠራት ያለበት፡፡ እነዚህን የመሳሰሉት ውሳኔዎች በእርቅ ሰነዱ ላይ ተካተው ከክልሉ መስተዳድር ጀምሮ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተላልፏል፤ የመንግሥት አካላትም በታዛቢነት በተገኙበት ሕጉን አስረግጠን ነግረን በግልጽ በጉባኤ ተነቧል። በተለይም ሰባክያንን፣ ዘማርያንን፣ ባሕታውያንንና የመሳሰሉትን በሚመለከት ቅድም እንዳልኩት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፊርማ ለመላው አህጉረ ስብከት የተላለፈው መመሪያ በሚገባ ተነብቦ፣ ተገለጾ፣ ታይቶ መመሪያው ተጠብቆ በሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት እንዲሠራ፤ እንዲሁም በተለይ በሀገረ ስብከቱ ክልል ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ወይም ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ያልተፈቀደለት አካል በቤተ ክርስቲያኒቱ አውደ ምሕረት ሲቆም ሀገረ ስብከቱ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ የሚል ሰፍሯል። ስለዚህ የእኛ ትግል የሲኖዶስን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ነው ማለት ነው። በዚያ መሠረት ነው የምንሠራው። የእርቅ ሰነዱ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላም ምንም ዓይነት ጭቅጭቅም ሁከትም አልነበረም።
ከጊዜ በኋላ እንግዲህ አሁንም ሰዎች እነ እገሌ የሚባሉት ሰባክያን ይምጡ፣ ዘማርያን ይምጡ፣ እነ እገሌ ይምጡ ማለት ጀመሩ። ቤተ ክህነቱ ደግሞ በሕጋዊ መንገድ ፈቅዶ የሚልካቸው መምህራንና ሰባኪያን አሉ፡፡ ሰዎችን ይምጡልን ቢሉም ቤተ ክህነቱ ደግሞ እኔ እነዚህን ነው የማሰማራው ብሎ ልኳል፡፡ ሀገረ ስብከቱ እንደ ተዋረድ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚተላለፍለትን መመሪያ የመፈፀምና የማስፈጸም ግዴታ አለበት፡፡ ይሄ ለምን ሆነ? ይሄ አይሆንም ማለት ሕጉም ሥርዓቱም አያስኬድም። በዚህ ምክንያት እንግዲህ እነ እገሌ ካልሰበኩ ወይም እኛ ካልሰበክን በሚል አንዳንድ ሰዎች ተነሥተዋል፡፡ ያው እነዚያ በግል ማለት ነው፡፡ አሁንም ግን የመላው ምእመንና ካህናቱ አመለካከት የውሳኔ ሰነዱ፣ ቃለ ዐዋዲው ይከበር፤ ለሀገረ ስብከቱ አቅርቦ ሲፈቀድለት ይሰማራ ነው፡፡ ይሄንን ሳያቀርቡ ደግሞ እራሳችንን እናሰማራ የሚሉ ክፍሎች ሲነሱ፤ ይሄ አይሆንም፥ ይሄ መደረግ የለበትም በሚል ነው አለመግባባቱ የተፈጠረው፡፡ ከዚህ አንጻር ነው እንጂ እርቅ የፈረሰ ነገር የለም እርቁም ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱን መመሪያ ጠብቀን እንሂድ፤ ሁላችንም ለቤተ ክርስቲያንቱ መመሪያ ተገዥ እንሁን የሚል ውሳኔ ነው እንጂ እገሌና እገሌ ተጣልተው የሚል የግል ጥላቻ በዚህ ላይ የለውም፡፡ የቤተ ክርስቲያንኒቱን መመሪያ ግን በጋራ እናክብር፡፡ መንግሥትም መመሪያውንም ውሳኔውንም አውቆታል፤ ይሄ ውሳኔ ለብፁዕ ቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋሪያዊ ተልእኮ መምሪያ በግልባጭ ደርሷል። በቃ ያንኑ የነበረውን መመሪያና ሕጉን የሚያጸና እንጂ የተለያየ ነገር የለውም። ይሄ ከተባለ በኋላ ግን አሁንም ሰዎች እንደግል ፍላጎታቸው እንዲህ ካልሆነ የሚሉ ሲነሱ አይ ይሄማ ከሕግ ውጪ ነው የሚል ነው ያለው ማለት ነው እንጂ የእርቅ መፍረስ አይደለም።
• ታዲያ ከዚህ ውሳኔ በኋላ አለመግባባቶችና ግጭቶች አልተነሱም ብለው ያስባሉ?
እንግዲህ አንዳንድ ሰባክያን እኛ እንሰብካለን፣ እኛ እንዲህ እናደርጋለን ብለው የሚሉት አብዛኛውን ወሬው የሚወራው በውጪ ነው፡፡ አንዳንዴ ግን ያልተፈቀደላቸው ሰዎች ወይም ያልተመደቡ ሰባክያን ወይም ቤተ ክህነቱ ያላሰማራቸው ዘማርያን ሆኑ ሰባክያን ወደ ዐውደ ምሕረቱ ሲመጡ፥ የለም፤ ይሄ አይደለም፤ ይላል ምእመኑ። ምእመኑ ነው መመሪያውን የሚያስከብረው። ይሄ ሰባኪ አይደለም የተመደበው ይላል። በዚህ ጊዜ የግድ አለመግባባቶች ይመጣሉ።
ሕጉ፣ መመሪያው፣ የሲኖዶሱ ደንብ፣ ቃለ አዋዲውና ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በአግባቡ በሥራ ላይ ይዋል ሲባል፥ የለም እኛ በፈቀድነው መሆን አለበት የሚሉ ክፍሎች ደግሞ ከተነሱ፥ ይኼማ የቤተ ክርስቲያናችን መመሪያዋ አይደለም የሚሉ ክፍሎች ይነሳሉ። በዚህ ጊዜ መቼም የሀሳብ አለመጣጣም አለመግባባት ግድ ይከሰታል። ያን ሲሆን ደግሞ ችግር ሊፈጠር ይችላል። ነገር ግን ያው ዞሮ ዞሮ ችግሮች ሲፈጠሩ በመንፈሳዊነት ሚዛን ይታያል። እንደ ሕግ የሚታየው ደግሞ በሕግ ይታያል። በዚህ ዓይነት ታይቶ እልባት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
• በሀገረ ስብከቱ በኩል የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድን ነው?
እንግዲህ ለወደፊቱ እግዚአብሔር ፈቃዱ ቢሆን ከፍተኛው ሥራ ያለው ከታች ስለሆነ ያለው 13ቱንም የወረዳ ቤተ ክህነቶች በተሻለ መልኩ በተሟላ የሰው ኃይል የማጠናከር፥ ባለፈው ለወረዳ ሊቃነ ካህናት፣ ለርእሰ ከተማው አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሰበካ ጉበኤያት በተቻለ መልኩ ትምህርታዊ ሴሚናር ለመስጠት ተሞክሯል። በቀጣይነት ደግሞ በሂደት ለእያንዳንዱ ወረዳ ቤተክህነት መርሐ ግብር ወጥቶ፥ በወረዳው ሥር ያሉ አብያተ ክርስትያናትን፣ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችን፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትን፣ ሰባክያነ ወንጌልና ካህናትን አሳታፊ ያደረገ፥ የቃለ ዐዋዲውን መመሪያና ሕገ ደንብ በተመለከተ፣ የቃለ ዐዋዲውን ሕግና ደንብ በማይነካ መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱ በልማትና ሁለንተናዊ ሥራዎች ላይ ማከናወን ያለባትና ዘመኑን የተከተለ ዘመናዊ አስተዳደርና የሥራ ሁኔታዎችን በሚመለከት፥ እንደዚሁም ደግሞ የበጀትና የሂሳብ አያያዝ፣ የንብረት ጥበቃና አመዘጋገብን፣ የቅርሶች ምዝገባንና የመሳሰሉትን ሁሉ በየጊዜው ተከታታይ ስብሰባዎችን በማድረግ ሴሚናሮችን መስጠት አስበናል።
በወረዳ ደረጃ የተሰጠው ሴሚናር በአጠቢያው ሥር ላሉ ደግሞ ካልተሰጠ ሥራው ሁለት ዓይነት ስለሚሆን በየወረዳው ሥር ያሉትን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናትን በየወረዳው ርእሰ ከተማ አቅም በፈቀደ መጠን ሴሚናሩ እዚያ ደርሶ ይህንን ሥልጠና መስጠት የመጀመሪያ እቅዳችን ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ደግሞ ያው በሀገረ ስብከቱ ሥር በሚተዳደረው የደ/ታ/ቅ/ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን አጠገብ የካህናት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አለን። በዚህ የካህናት ማሰለጠኛ ትምህርት ቤት ያለንን በጀት በመጠቀም ካህናትን እናሠለጥናለን። የሠለጠኑት ካህናትም ወደ ነበሩበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት እየተመለሱ ምእመናኑን በስብከተ ወንጌልና በመሳሰለው ሁሉ እንዲያገለግሉ የማድረጉን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን።
እንግዲህ ደቡብ ክልል ወደ 56 የሚጠጉ ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈ ክልል ነው። የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተወላጅ የሆኑ እና የየብሔረሰቡን ቋንቋ የሚናገሩ የተወሰኑ ሕፃናትን በማሰባሰብ ለማስተማር ጥረት እያደረግን ነው። ለምሳሌ አሁን 12 ያህል ህፃናት አሉን። ሀገረ ስብከቱ ከኛ ቀደም ብሎ ወደዚሁ ማሠልጠኛ አምጥቶ ትምህርት ቤት ከፍቶ፥ መንፈሳዊውን ትምህርት ማለትም ከፊደል ቆጠራ ጀመሮ እስከ ሥርዓተ ቅዳሴ ሌላም ሌላም የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ትምህርት እያስተማረ አሁን ለዲቁና የሚያበቃ ትመህርት ተምረው የሚገኙና በቅዳሴ አገለግሎት ላይ የሚገኙ አሉ። እነዚህ ልጆች ለጊዜው ቁጥራቸው 12 ቢሆንም ይሄ 12 የሆነው ቁጥር ወደ 24 ወደ 36 ብሎም ወደ 72 እንዲያድግ ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄድበትን መንገድ ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል።
እነዚህ ልጆች ደግሞ ከየብሔረሰቡ የተወጣጡና የየብሔረሰቡን ቋንቋ የሚችሉ እንደ መሆናቸው መጠን ወንጌልን በየቋንቋቸው ለማስተማር ይረዳቸዋል። ኅብረተሰቡም ይቀበላቸዋል። ከመንፈሳዊው ትምህርት ጎን ለጎን ዘመናዊ ትምህርትም እየተማሩ ነው። ይሄን በሚማሩ ጊዜ አንዳንድ በጎ አድራጊዎች ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የሚቻለውን ድጋፍ በማድረግ ቀለባቸውን፣ ልብሳቸውን የትምህርት ቁሳቁስና የመሳሰሉትን ወጪ አድርጎ ዘመናዊውን ትምህርት ያስተምራቸዋል፡፡ ከመንፈሳዊውና አለማዊው ትምህርታቸው በተጨማሪ በቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በዲቁና ያገለግላሉ። ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን፣ እንዲሁ አገለግሎትንም በኪዳንና በመሳሰለው እየተለማመዱትም ይገኛሉ ማለት ነው።
የነዚህ ልጆች ወደዚህ ማሠልጠኛ ገብቶ የማደግና የመማሩ ጉዳይ በብፁዕነታቸው ትኩረት ተሰጥቶበታል። እንግዲህ ይህን ሥልጠና ለማድረግ ቁጥራቸውንም ለመጨመር በጀት ያስፈልጋል፤ ሥራዎች ሁሌም የሚሠሩት በበጀት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን በጀቷ ምእመናን ናቸው፡፡ በዚሁ በሐዋሳ ያሉ አንዳንድ ምእመናን ለልጆቹ የተቻላቸውን ያህል የሚያደርጉ አሉ። ወደፊት ደግሞ ፕሮፖዛል ቀርፀን፣ እቅድ አውጥተን፣ በጎ አድራጊዎችንም በማስተባበር፣ እርዳታ ሰጪ ክፍሎችንም በማፈላለግ ለመንቀሳቀስ አስበናል። ማኅበረ ቅዱሳንም በዚህ በኩል ይረዳናል የሚል ተስፋ አለን። እንዲሁም ማሠልጠኛው ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ የልማት ሥራዎችን በፕሮጀክት ቀርፀን ለመሥራት አስበናል። እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን የምናከናውነው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እስከ ገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን ያለው በቃለ አዋዲው ድንጋጌ የሠፈረው የሥራ እንቅስቃሴ እንዳለና እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡ ያኛው እንዳለና እንደ ተጠበቀ ሆኖ ሌላው እቅዳችን ደግሞ በተለይ በቤተ ክርስትያኒቱ ተተኪ ትውልድ የመፍጠርና የመተካት፥ የዛሬው ትውልድ የነገይቱ የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ እንዲሆን የማስቻል፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሉት በጥንካሬና በስፋት ቀጣይነት እንዲኖረው የማድረግ፥ ለነገይቱ ቤተ ክርስቲያን በትምህርት ሰዎችን የማዘጋጀት እና ተተኪዎችን የማፍራቱን ጉዳይ ከምንግዜውም የበለጠ አቅም በፈቀደ መጠን አጠንክረን ለመሥራት ነው፡፡
• በመጨረሻ የሚያስተላለፋት መልእክት ካለ?
እንግዲህ በሲዳማ አማሮና ቡርጂ ልዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ለሚገኙ ለመላው ካህናትና ምእመናን በሀገረ ስብከታችን ጽ/ቤት ስም የማስተላልፈው መልእክት፤ አሁንም የቤተ ክርስትያኒቱን ሁለንተናዊ መንፈሳዊ፣ የልማት እና የሥራ እንቅስቃሴ ተባብረን ሁሉንም ለማከናወን እንድንችል መላው ምእመናን እና ካህናት የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ እና መመሪያ፥ የቃለ አዋዲውን ድንጋጌ እና ደንብ ጠብቀን ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት በተዋረድ በምታስተላለፍልን መሠረት ሕጓን ጠብቀን አክብረን ተባብረን እንድናገለግልና እንድናስገለግል ነው። ወደ ፊት ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፥ ሰንበት ትምህርት ቤቶች እንዲጠናከሩና ቤተ ክርስቲያናችን በልማት ልትጠናከር ያስፈልጋል።
ምእመናን ደግሞ በዕውቀታቸው በገንዘባቸውና በጉልበታቸው አብያተ ክርስቲያናትን በማስፋፋት፣ በማሳነጽና በማሠራት እንዲተጉ አሳስባለሁ። ሀገረ ስብከቱም ጠቅላላ ሥራውን የሚያከናውነው ከካህናትና ምእመናን ጋር ነውና፥ ካህናቱም ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፥ መንፈሳዊ አገለግሎትን አጠናክሮ በመቀጠልና ልማትም በቤተ ክርስቲያን እንዲስፋፋ በማድረግ ሊተጉ ይገባል። ምእመናኑ እውነት በመንገር ማሳሰብ ብቻ ነው የሚፈለጉት። በእውነት ይሄ ቀረ የማይባል ከፍተኛ ሥራ የሚሠሩ በርካታ ምእመናን አሉ። በእውነት ከተነገረና ካሳሰቡአቸው፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ለቤተ ክርስቲያናቸው ወደኋላ የሚሉበት አንድም ነገር የለም። ስለዚህ ከኛ የሚጠበቀው መንገርና ማስረዳት ብቻ ነው። እኛም የሚቻለንን ያህል እግዚአብሔር እንደፈቀደ ለማስረዳት ለመንገር እንሞክራለን። አሁንም እየነገርን እያሳሰብን ነው፤ ምዕመናኑም እየሰሙን ነው፡፡ ስለዚህ መላው ምእመናንና ካህናት ተባብረን ስብከተ ወንጌሉንም እንድናስፋፋ አብያተ ክርስቲያናቱንም በልማት እንድናጠናክር እላለሁ። የሁሉም ምእመናንና ካህናት ከሀገረ ስብከቱ ጋር መተባበር አስፈላጊ ስለሆነ እስከ አሁን ያለውን ቀና ትብብራቸውን አጠናክረው አንዲቀጥሉ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ ቤት ስም መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
• በእውነት ጊዜዎን ሰውተው ለሰጡን ቃለመጠይቅ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡
እንግዲህ ከመጣን አጭር ጊዜ ቢሆንም ከሞላ ጎደል ያለውንና እንዲሁም ለወደፊት ያለውንና ለመሥራት የታቀዱትን እኔ የሚቻለኝን ያህል ብያለሁ፤ ብፁዕ አባታችን አቡነ ገብርኤል ደግሞ በአባትነታቸው በሀገረ ስብከቱ ያለውን ሁኔታ አስፍተው አምልተው ከኔ የበለጠ አድርገው፥ እኔ ምናልባት ያተረፍኩትም ያጎደልኩትም ካለ የበለጠ ብፁዕነታቸው አርመው አስተካክለው አስፍተው በጥሩ ቋንቋ በጥሩ ሁኔታ ለትውልዱ በሚመች መልኩ ይገለፁታል። እኔም በሀገረ ስብከቱ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ፥ እግዚአብሔር ይስጥልኝ።