ስሞት እጸልይላችኋለሁ

በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ

“ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ!”2ኛ ጴጥ.1÷13-15

ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም በመጣበት ወቅት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መሥርቶአል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያቱን “እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ መልሶ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ “አንተ ዓለት ነህ በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፤ የሲኦልም ደጆች ሊያናውጿት አይችሉም፡፡” በማለት ቤተ ክርስቲያንን በሐዋርያት መሠረት ላይ መሠረተ/ማቴ.16÷16-18/፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በአምሳ አምስት ዓመቱ ወደ ሐዋርያት የተጠራ፣ በሁሉም ስፍራ በሐዋርያት ስም ዝርዝርም፣ መልስ በመስጠትም፣ በመካድም፣ ንስሓ በመግባትም ፈጣን እንደነበር ቅድመ ትንሣኤ ክርስቶስ የተጻፈው ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ከትንሣኤ በኋላ ሦስት ጊዜ ክዶት መጸጸቱን የተመለከተለት ጌታ አንዳች የሚቆጠቁጥ የወቀሳ ቃል ሳይኖረው በጭቃ ላይ የወደቀ ዕንቁን ወልውለው ወደ ቦታው አንደሚያስቀምጡት ወደ ክብር ስፍራው መለሰው፡፡ አልፎ ተርፎም ለምሕረቱ ወሰን የሌለው አምላክ ይህን ሐዋርያ “ ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ” ብሎ ምእመናንን ከሕፃናት እስከ አረጋውያን አደራ ሰጠው /ዮሐ.21÷15-17/፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በተቀበለበት ዕለት በአንድ ቀን ሦስት ሺህ ነፍሳትን በትምህርቱ ማርኮ “ምን እናድርግ?” በማሰኘት ጠብቅ አሰማራ የተባለውን መንጋ ወደ በረቱ ማስገባት ጀመረ፡፡ /ሐዋ.2÷31/ በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ምእመናንን በአፍም በመጽሐፍም ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ በኋላም ጠብቃቸውና አሠማራቸው የተባለውን ግልገሎች፣ ጠቦቶችና በጎች ሲጠብቅና ሲያሠማራ ከተኩላ ታግሎ ነፍሱን ሰጠ፡፡ የእረኝነት ሥራውን ሊፈጽም ቁልቁል ተሰቅሎ “የእረኞች አለቃ” /1ኛጴጥ.5÷4/ ብሎ በመልእክቱ የጠራውን የጌታውን ፈቃድ ፈጸመ፡፡

ይህ ሐዋርያ በመልእክታቱ ምእመናንን ሲገሥጽና ሲመክር ሲያስተምር የኖረ ሲሆን በሁለተኛይቱ መልእክቱ ላይ ግን ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነ ኃይለ ቃልን ጽፏል፡፡ “ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁ በእናንተም ዘንድ ባለ እውነት ብትጸኑ ስለ እነዚህ ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም፡፡ ሁል ጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና፡፡ ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ” /2ኛጴጥ. 1÷13-15/

ብታውቁም፤ ብተጸኑም ማሳሰቤን ቸል አልልም!

ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክታቱ ስለ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትና ስለ ሰው ልጅ ብሎ ስለተቀበለው መከራ፣ ክርስቲያኖች ሊኖራቸው ስለሚገባ መንፈሳዊ አኗኗር፣ አለባበስ፣ ስለ ጋብቻና ቤተሰባዊ ጉዳዮች፣ በምእመናን ላይ ስለሚመጡ መከራዎችና የዲያብሎስ ውጊያዎች፣ ድል ሲያደርጉም ስለሚያገኙት ጸጋና ዋጋ፣ ስለሚደርሱበት መዓርግ በአጠቃላይ በቀላሉ ተዘርዝሮ የማያልቅ ሰፊ ትምህርትን በመልእክቱ አስተምሯል፡፡ ይሁንና ሐዋርያው አውቀውታል፣ ጸንተዋል ብሎ ማሳሰቡን አላቆመም፡፡ ሰው ከመንገድ የሚስተው በእውቀት ጉድለት ብቻ አይደለም፡፡ እያወቁ መሳት፣ ጸናሁ ሲሉም መጥፋት አለ፡፡ ስለዚህም “አሳስባችሁ ዘንድ ቸል አልልም፡፡” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መንጋውን ጠብቅና አሰማራ የተባውን አደራ የማይረሳ፣ በጥበቃ ተሰላችቶ ቸል የማይል፣ ትናንት የበሉት የጠጡት ይበቃቸዋል የማይል በመሆኑ ያውቁታል ብሎ ከመናገር ሳይቆጠብ “ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም፡፡” አለ፡፡

በዚህ ማደሪያ ሳለሁ!

ሥጋ የነፍስ ማደሪያ ናት፤ አዳሪዋ ነፍስ ከማደሪያዋ ሥጋ ስተለይ ሰው ያን ጊዜ ሞተ ይባላል፡፡ “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ ነው” እንዲል /ያዕ.2÷26/ ጻድቁ ኢዮብም “ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ÷ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ፡፡” ኢዮ.19÷26/ ያለው ሥጋ ጊዜያዊ ማደሪያ መሆኑን ሲያስረዳና ራሱን ከነፍስ አንጻር አድርጎ በሞት ሥጋውን ጥሎ እንደሚሄድ ሲናገር ነበር፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ “በዚህ ማደሪያዬ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ ይገባኛል፡፡” ሲል በሥጋዬ ሳለሁ፣ ነፍሴ ሳትወሰድ ማለቱ ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን ቀሪ ዕድሜውን በችኮላ የሚጠቀመው ለሌላ ሥጋዊ ተርታ ጉዳዮች ሳይሆን ምእመናን ያስተማረውን ትምህርት እንዳይገድፍና አንዳይጠፉበት በማሳሰብ ማንቃት ነው፡፡

ጌታዬ እንዳመለከተኝ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁ!

“በእግዚአብሔር ፊት የቅዱሳኑ ሞት የከበረ” ስለሆነ ሞት ለቅዱሳን ድንገተኛና ያልተጠበቀ አይሆንባቸውም፡፡ እርግጥ ነው ሰው ሁሉ ሟች እንደ ሆኑና የሞትን አይቀሬነት በመጥቀስ ሁሉም ሰው እንደሚሞት ያውቃል ሊባል ይችላል፡፡ ቅዱሳን ግን የሚሞቱ መሆናቸውን የሚያውቁት ሞት አይቀርም ብለው ሳይሆን የሚሞቱበትን ጊዜና ሁኔታ ለመረጣቸው ለባሪያዎቹ የሚያደርገውን የማይሠውር እግዚአብሔር ገልጣላቸው ነው፡፡ የሚከተሉት የሊቀ ነቢያት ሙሴንና የቅዱስ ጳውሎስን ንግግሮች እንመልከት፡-

“እኔ ግን በዚህች ምድር እሞታለሁ ዮርዳኖስንም አልሻገርም” /ዘዳ.4÷22/

“በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና የምሄድበትም ጊዜ ደርሷል” /2ኛጢሞ.4÷6/

እነዚህ ታላላቅ ቅዱሳን የሚሞቱ መሆናቸቸውን ብቻ ሳይሆን የሚሞቱበትን ቦታ ጊዜ አስቀድመው መናገራቸው ከእግዚአብሔር ስለተነገራቸው ነው፡፡ የቅዱሳን አባቶቻችንን እና የቅዱሳት እናቶቻችንን ገድላት ስንመረምር ቅዱሳን ዕለተ እረፍታቸው ቀድሞ በእግዚአብሔር እንደሚነገራቸው እንረዳለን፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ሰው እንደመሆኑ “መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ” ብሎ ጌታ ለሁሉ ካመለከተው ጥሪ በተጨማሪ ከቅዱሳን አንዱ እንደመሆኑ ከመሞቱ በፊት እንደሚሞት ያውቅ ነበር፡፡ ጌታችን ከዕርገቱ በፊትና ከዕርገቱ በኋላ ሁለት ጊዜ ተገልጦ ስለሞቱ ነግሮታል፡፡

ከዕርገቱ በፊት ከላይ የጠቀስነውን የእረኝነት አደራ ከሰጠው በኋላ “እውነት እውነት እልሃለሁ አንተ ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል፡፡” ብሎታል፡፡ ወንጌልን ጽፎ በብዙ ቦታዎች የጻፈውን ሲተረጉምና ሲያትት የምናገኘው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ትርጓሜን ሳንሻ ንባቡ ላይ “በምን ዓይነት ሞት  እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ፡፡” ብሎ የጌታን ንግግር ትርጓሜ አስከትሎ ጽፎልናል፡፡

በእርግጥም ቅዱስ ጴጥሮስ በሸመገለ ጊዜ እጆቹን በተዘቀዘቀ መስቀል ላይ ዘርግቶ ቁልቁል መሰቀል ትንቢተ ክርስቶስን ፈጽሟል፡፡

ጌታችን ከዐረገ በኋላ ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሲያስተምር “ልበ ንጹሖች ብጹዓን ናቸው፡፡” ብሎ ባስተማረው ትምህርት ሚስቶቻችንን አሸፈተብን ያሉ ሰዎች ተነሡበት፡፡ በዚህን ወቅት ሴቶቹ ተማክረው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲሸሽ ነገሩት ከከተማይቱ ወጥቶ ሊሄድ ሲል ጌታችን ተገልጦ ታየው “ጌታ ሆይ ወዴት ትሄደለህ” ቢለው “ዳግም በሮም ልሰቀል” በማለት ነገረው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ልቡ ተነክቶ ወደ ሮም ተመለሰና የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ፡፡ “ጌታችን እንዳመለከተኝ” ያለው ይህን ነበር፡፡

ከመውጣቴም በኋላ አንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ!

ከላይ የተመለከትናቸው ሃሳቦች ቅዱስ ጴጥሮስ ጊዜ ሞቱ እንደቀረበ አውቆ መናገሩን እና ምእመናን የተማሩትን በማሳሰብ ሲያነቃቸው እንደነበር የሚያስረዱ ናቸው፡፡ እስካሁን የተመለከትናቸው የሚያወሱት ይህ ሐዋርያት በሕይወት ሳለ ስለሚያደርጋቸው ነገር ነበር፡፡ በመጨረሻው ዐረፍተ ነገር ግን “ከመውጣቴ በኋላ የሚል ሐረግ እናገኛለን፡፡ “ከመውጣቴ በኋላ” ሲል ምን ማለቱ ነው?

ቀደም ባሉት ዐረፍተ ነገሮች እንደሚሞትና ይህንንም ጌታችን እንዳመለከተው ተናግሮ ነበር፡፡ ስለዚህ መውጣቴ ያለው ሞቱን እንደ ሆነ እሙን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ሞት መውጣት ተብሎ ሲነገር የቅዱስ ጴጥሮስ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ በታቦር ተራራ ከሙሴና ኤልያስ ጋር ስለመነጋገሩ በተጻፈበት ስፍራ “በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር” ይላል፡፡ በኢየሩሳሌም የተፈጸመው መውጣቱ ደግሞ ሞቱ ነው፡፡ /ሉቃ.9÷31/ ስለዚህ ቅዱስ ጴጥሮስ ባስተማርኳችሁ እንድትጸኑ “ከሞትኩም በኋላ እተጋለሁ!” እያለ ነው፡፡ “ከሞትኩ በኋላ” የሚለውን እናቆየውና “እተጋለሁ!” የሚለውን ቃል በጥቂቱ እናብራራው፡፡

ትጋት ምንድርን ነው? ትጋት አንድ ነገር ያለማቋረጥ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፣ ያለመታከት ማድረግ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “ታካች ሰው ምንም አደን አያድንም፤ የሰው የከበረ ሀብቱ ትጋት ነው” በማለት ትጋት የታካችነት ተቃራኒ መሆኑንና ጥቅሙን ተናግሯል /ምሳ.12÷27/፡፡ ጌታችን በምሴተ ሐሙስ ቅዱሳን ሐዋርያቱን “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳን ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” ብሎ ገሥጿቸው ነበር /ማቴ.26÷30/፡፡ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ግን ሐዋርያት ትጉሐን ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደ መሰከረላቸው “ወደዚህም ወደ ተሰፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው” /ሐዋ.26÷7/ በዚህ ሁሉ ትጋት አለመታከት፣ አንድን ነገር ሌሊትና ቀን ማድረግ መሆኑን ተረዳን፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ “ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ” ሲል የሚተጋው በምንድርን ነው? እየዞረ በማስተማር ይሆን? ይህማ ቢሆን ከመሄዴ በፊት  ላሳስባችሁ ባላለን ነበር፡፡ ደግሞም ማስተማሩን በሚገባ ፈጽሞ በሰማዕትነት አርፏል፡፡ ታዲያ ከሞተ ወዲያ የሚተጋው ምን በማድረግ ነው? የትስ ነው የሚተጋው? መቼስ በመቃብር ያለሥጋው ሊተጋ አይችልም፡፡ “የሞቱትስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን? በመቃብርስ ውስጥ ቸርነትህን ይናገራሉን?” ብሏል ቅዱስ ዳዊት /መዝ.87÷15/ ራሱ ቅዱስ ጴጥሮስም “ከማደሪያዬ እለያለሁ፡፡ ብሎ ከሞተ ወዲያ እኔ የሚላት ነፍሱን እንደሆነ አስረድቶናል፡፡ ታዲያ በነፍሱ በሰማይ ምን እያደረገ ይሆን የሚተጋው? መቼስ በሰማይ እርሻ ቁፋሮ፣ ጽሕፈት፣ ድጒሰት የለም፡፡ ሐዋርያው በምን ይሆን የሚተጋው? በጸሎት ነዋ!

ስለዚህ ቅዱስ ጴጥሮስ “እንደተማራችሁት መኖርን እንዳትዘነጉ በየጊዜው /አንድ ጊዜ ብናስብ አንድ ጊዜ መዘንጋት አለና/ ትችሉ ዘንድ ከሞትኩም በኋላ ያለማቋረጥ ያለመሰልቸት ስለ እናንተ በመጸለይ እተጋለሁ! ማስተማርና መልእክትን ጽፎ መተው ብቻ ሳይሆን በተማራችሁት መገኘት እንድትችሉ በአጸደ ነፍስም ብሆን እለምናለሁ፣ እማልዳለሁ! እያለ ነው፡፡

በቅዱስ ጴጥሮስ ዓለትነት የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ስለእርሷ የተጻፋላት፣ በደሙ የዋጃት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሷ ነው፡፡ እርሱ በሁሉ የሞላ ሲሆን “ሁሉን በሁሉ ለሚሞላ ለእርሱ ሙላቱ የሆነች” አካሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት /ኤፌ.1÷22/፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ስትሆን ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራሷ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የሰውነት አካል ክፍሎች ነን፡፡ “እንግዲህ እናንተ የክርስቶስ አካሉ ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁ የአካሉ ክፍሎች ናችሁ፡፡” ተብለናል /1ኛቆሮ.12÷27/፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሕይወትን የሚሰጡ ጥምቀትን፣ ንስሐን፣ ቊርባንን የመሳሰሉ ምስጢራትን በመፈጸም ራሳችን ከሆነው ከመድኃኔዓለም ጋር አንድ እንሆናለን፡፡

ክርስቲያኖች ሲሞቱ ከዚህ ኅብረት ይነጠላሉ ማለት አይደለም፡፡ ራሷ ክርስቶስ በሰማይም በምድርም ስላለ ቤተ ክርስቲያንም በምድርም በሰማይም አለች፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ነፍሱ ከሥጋው ስትለይ ወደ ሰማያዊቱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል፡፡ የሰማይዋ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ድል በነሱ ቅዱሳን የተሞላች ፍጹም መንፈሳዊ የሆነ ሥርዓት ያለባት፣ ሥጋዊ ደማዊ አሳብ የማይሰለጥንባት ናት፡፡ ከእኛ ተለይተው ወደዚያ ኅብረት የተደመሩ ወገኖቻችን በላይ ያሉ የክርስቶስ አካላት ናቸው፡፡ ከእኛ በምድር ካለነው የክርስቶስ አካላት ጋር አንድነታቸው አይቋረጥም፡፡ የክርስቶስ አካል አይከፈልማ! ስለዚህ በሰማይ ካሉት ድል የነሡ ቅዱሳን ጋር እኛ ደካሞቹ በጸሎት እንገናኛለን፡፡

“ዐይን እጅን አልፈልግሽም ልትላት አትችልም፤ ደካሞች የሚመስሉህ የአካል ክፍሎች ይልቁንም የሚያስፈልጉህ ናቸው፡፡ ተብሎ እንደተነገረ እኛ ኃጢአተኞቹ የቤተ ክርስቲያን የአካል ክፍሎች ብንሆንም ቅዱሳኑ ስለ እኛ ይጸልያሉ /1ቆሮ.12÷21/፡፡ ምክንያቱም ደካማ ብንሆንም ለቅዱሳን እናስፈልጋቸዋለን፡፡ ቅዱሳን ኃጥአንን ካልወደዱ ቅድስናቸውን ያጣሉ፡፡ እኛን ካልወደዱ “እኔ ክርስቶስን እንደመሰልሁ እናንተም እኔን ምሰሉ” “አሁን እኔ ሕያው ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፡፡” ብለው ለመናገር እንደምን ይችላሉ? /ገላ.2÷20/  

እኛ በሥጋ ድሆች የሆኑ ነዳያንን በመመጽወት እንደምንከብር ቅዱሳንም በነፍስ ድሆች የሆንን እኛን በአማላጅነት ጸሎታቸው እየመጸወቱ ይከብራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ለድሀ ግን የሚራራ ምስጉን ነው፡፡” ይላልና በምግባር ድሆች ለሆንን ለእኛ መራራት የቅዱሳን ግብር ነው፡፡ “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል” ተብሎ እንደተነገረላቸው ቅዱሳን ክቡር ሆነን ሳለን ለማናውቅ እንደሚጠፉ እንስሶች ለመሰልን ለእኛ ለኃጢአተኞች ይራራሉ፤ ይማልዱማል /ምሳ.12÷10፣ 14÷21/፡፡

ቅዱሳን በሕይወተ ሥጋ እያሉ መከራን ታግሠው ስለ ሌሎች በደል ይለምናሉ፡፡ ሳይበድሉ ራሳቸውን በኃጢአትኛው ቦታ አርገው፣ ከደካሞች ጋር እንደ ደካማ ሆነው ይማልዳሉ፡፡ ታዲያ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለይታ “ሲሄዱና ከክርስቶስ ጋር ሲኖሩ” /ፊል.1÷23/ ምንኛ ይለምኑ ይሆን?

በምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሕይወተ ሥጋ ለሌሉና ወደ ሰማዩ ኅብረት ለሄዱ ምእመናን ጸሎተ ፍትሐትን፣ መታሰቢያን በማድረግ፤ ለዚያ የሚያበቃ ቅድስና ያላቸውን ደግሞ በዓላቸውን በማክበር ታስባቸዋለች /2ጢሞ.1÷17-18/፡፡ በሰማይ ያሉት ቅዱሳን ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው ስለ እኛ ይተጋሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን መከራና የምእመናንን ስቃይም በዝምታ አይመለከቱም፡፡ በዙፋኑ ፊት ቆመው “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ስለ ደማችንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” እያሉ ያማልዳሉ፡፡ /ራእ.6÷10/ የቅዱስ ጴጥሮስ በረከቱ አይለየን! አሜን፡፡

/ምንጭ፡ ሐመር  ሐምሌ 2002 ዓ.ም./